[ሰሎሞን ዳውድ (ኤም.ኤ) ጎንደር ዩኒቨርሲቲ]
ክፍል አንድ
መግቢያ
ኢትዮጵያ ዘመን ተሻግረው በመጭው ዘመን ስለሚሆኑ እና ስለሚፈፀሙ ሁነቶች መናገር ብሎም ማስተማር የሚችሉ በርካታ ሊቃውንት የነበሯት/ ያሏት ሃገር ነች፡፡ ከነዚህም ውስጥ በርካታ ትንቢቶችን ማለትም ከዘመነ አጼ (ሃይለ ስላሴ)፣ እስከ ዘመነ ደርግ (መንግስቱ ሃይለማርያም) እንዲሁም በዘመነ ወያኔ (መለስና ሽፍቶቹ) ስለተከወኑ ወይም በመፈፀም ላይ ስላሉ ኩነቶች በቃል ግጥማቸው በርካታ ንግርቶችን ያስቀመጡት ወረሼህ (የወረሂመኖው ሸህ ሁሴን ጅብሪል) አንዱና ዋነኛው ናቸው፡፡ የዚህ ፅሁፍ ዓላማ በዋነኝነት የዘመነ ወያኔ ሶሲዎ-ፖለቲካዊ ሁነቶችን የሚያሳዩ ግጥሞችን ከአቶ ቦጋለ ተፈሪ መፅሃፍ በመምረጥ ከወቅቱ ነባራዊ ሁኔታ ጋር የማያያዝና አገባባዊ ፍቾችን በመስጠት ማህበራዊ ንቃትና ውይይት በማህበረሰቡ መካከል መፍጠር ነው፡፡ ይህ ፅሁፍ ካካተታቸው ዋና ዋና ይዘቶች መካከል የዘመነኞቹ የሃገሪቱ ነገስታት ወይም ገዥዎች የበትረ መንግስት አጨባበጥ መሰሪ አካሄድ፣ የከፋፍለህ ግዛ ስርዓታቸው፣ ጥንተ መሰረታዊ ሃገር አፍራሽ ተልዕኳቸውና የማስፈፀም ትጋታቸው፤ ያሰፈኑት የጎሳ ፖለቲካ (አንዱ በዳይ ሌላው ተበዳይ) የሆነበት ስርዓት እና ገዥዎቹ (ስርዓቱ) በህዝብ ላይ ያሰፈነው በደል ናቸው፡፡
በዚህም መሰረት ይህ ፅሁፍ በአምስት (05) ንዑስ ርእሶች የተከፋፈለ ነው፡፡ እነሱም ጥንተ አመጣጣቸውና ውጤቱን የሚመለከቱ ግጥሞች፣ የትግሬ ሕዝብ ውክልናን የሚመለከቱ ግጥሞች፣ የመሬት ይዞታውና ተያያዥ ነገሮችን የሚመለከቱ ግጥሞች፣ የካድሬና ኮሚቴ ሥርዓት የሚመለከቱ ግጥሞች እና የቀደሙትን ነገስታት ከዘመኑ አስተዳደር ጋር የሚነፃፅሩ ግጥሞች በሚል ተከፋፍለውና በቅደም ተከተል ተሰናድተው ቀርበዋል፡፡
- ጥንተ አመጣጣቸውና ውጤቱ የሚመለከቱ ግጥሞች
በትንቢት አዘል ግጥሞቻቸው የሚታወቁት ሼህ ሁሴን ጅብሪል የዘውድ ንጉስ መች እንደሚያበቃለትና ተከታዮቹ አገረ ገዥዎች በምን መንገድ ወደ መንግስትነት እንደሚበቁ ጠቁመዋል፡ ይኸውም፤ በምርጫ እንደሚነገስ ያውም በቀላጤ ወይም በበላይ በትዛዝ ብቻ እንደሚሆን የተነበዩት ሼህ፤ ምርጫ ተብየውን ኩነት ተከትሎ ደግሞ ፍጥረተ አዳም ብዙ የልቅሶ ቀናትን እንዲገፋ እንደሚያደርገውም ታይቷቸው ኖሮ እንዲህ ሲሉ ይነግሩናል፤
ግባ በቀላጤ ውጣ በቀላጤ፤
ከተፈሪ ወዲያ አይባልም አጤ፡፡
ተቴወድሮስ አንስቶ ተፈሪ ድረስ፤
ዘመኑ ያበቃል፤ የዘውድ ንጉስ፤
ንጉስ አለ ብለህ አትወሳወስ፤
በምርጫ ታልሆነ የለም የሚነግስ፤
ግን ሕልቁን አየሁት ብዙ ቀን ቲያለቅስ፡፡
እኒህ ትንቢት አዋቂ ሸህ ታዲያ ስለዚህ ዘመን መሪዎች ወደ ወንበር /ስልጣን/ አመጣጥ እና የህዝቡ ድጋፍ እንዴት ለእድገት እንዳበቃቸው ነገር ግን እነርሱ ያንን ረስተው ህዝቡን ሊወጉ እንደተነሱ እንዲህ በማለት ይገልፁታል፡፡
እደግ እደግ ብለን ያሳደግነው ቀጋ፤
ይላል ጎንበስ ቀና እኛኑ ሊወጋ፡፡
ከዚያም በማስቀጠልም እኒሁ ገዥዎቻችን፤ በስልጣን ዘመናቸው መጀመሪያ ካሰፈኑት አገዛዝ /አስተዳደር/ መካከል አንዱ ሀገርን በክልል መሸንሸን መሆኑ እና በአንድ ገበያ ይገበያዩ የነበሩ ህዝቦችና የገበያ ቦታዎችን ሳይቀር እንደሚለያዩ ብሎም የይለፍ ወረቀት አልያም ጎሳ፣ ቀበሌና መንደር የተፃፈበት የመታወቂያ ወረቀት ያልያዘ ግለሰብ ማለፍ የሚከለከልበት ስርዓት እንደሚሰፍን ሲያመለክቱ እንዲህ አሉ፤
ያን ግዜ ይበጃል ክልል የሚሉት፤
እንዳይገናኙ ተንታና ሆርማት፤
ታልያዘ በስተቀር አንዳች ወረቀት፡፡
ይኸንኑ የክልል ስርዓት ገደብ ያጣ ግፍ ለማሳየት ብሎም የመሬት ቅሚያው በመንግስት ተከልሎ ከተሰጠው ከሌላው ክልል ነዋሪ ጋር በማነፃፀር በኛ (በአማራው) በኩል ከልክ ወይም ከተፈጥሮ ድንበር ያለፈ እንደሆነ ለማሳየት የሞከሩበት ትንቢታዊ ግጥም ደግሞ እንዲህ የሚል ነው፤ ይህ ግጥም በተጨማሪም የድንበር ማስፋትና መንጠቅ ስራውንም ገልጦ በአንድ በኩል ደግሞ ከልክ (ድንበር) ያለፈ መሆኑን ከዚያም ባለፈ የሃገርን ድንበር ለባዕዳን ብሎም ለጎረቤት ሃገራት እና አጎራባች ክልሎች አሳልፎ እየተሰጠበት ያለውን ሁናቴ በሚያሳይ መልኩ እንዲህ ተቀኝተውለት ነበር፤
የሰው ሁሉ ሁዳድ የሰው ሁሉ መሬት ሁሉም አለው ኩል ኩል፤
ተድንበር አለፈ ምነው በኛ በኩል፤
ትንቢተኛው ሼህ አስከትለውም አኒሁ መሪዎች የሀበሻን ሀገር ከክልል በጠበበ በወረዳ ወይም በቀበሌ እንደሚሸነሽኗት ያስቀመጡ ሲሆን የግጥም ስንኞቹም እንዲህ ይነበባሉ፤
እኔም ተናገርጉኝ አላህ ያውቃል መሌ፤
እስንት ከፈሏት ያበሻን ቀበሌ፡፡
በመጀመሪያው የግጥም መስመር እንደተጠቀሰው ትንቢት ተናጋሪው ሸህ ከሃያ አመት በላይ ሃገሪቱ ሲያዙ ሲናዙ የነበሩትን የአቶ መለስ ዜናዊ ስም በቁልምጫ እየጠቀሱ ነውን? ያሰኛል ከዚያ ባሻገር ግን መሌ ብለው የሚጠቅሱት ድርጊቱን በውሃ ሙላት ወይም በየቦታው እየሞላ በሚፈስ ውሃ ሲመስሉት ነው፡፡ ይህንን እና ሌሎች መሰል ድርጊቶቹ በማህበረሰቡ ዘንድ ተቀባይነት የሌላቸው እንደሆኑና ቀድሞውንም የተፈሩና ቀስ በቀስ ተግባራዊ የሆኑ ነገሮች ለመሆናቸው በሚከተለው የግጥም ስንኝ ይገልፁታል፡፡
ተጎድጓዳ ስፍራ ይበቅላል ደደሆ፤
የፈራነው ነገር መጣ ድሆ ድሆ፡፡
ቀስ በቀስ በህዝቡ ዘንድ ተቀባይነትን እያገኙ ሲሄዱ ነገራቸው የጎተተቱትን ወያኔዎች ሼህ ሁሴን ጸባያቸውን በደንብ ያውቋቸዋልና አመጣጣቸው እንዴት እንደነበር ሲገልፁ በግድግዳ ላይ ተባይ በትኋን የሚመስሏቸው ሲሆን አወጣጣቸው ግን ከዚያ በተለየ እንደ አንበጣ እንደሆነ በግጥማቸው እንዲህ ሲሉ ይገልፃሉ ፤
ቲገቡ እነደ ትኋን ቲወጡ እንዳንበጣ ነው የሚሆኑት፤
መጋዘን ይበጃል ብረት ማስቀመጫ ጥይት ለሚሉት፤
የትምህርት ደረጃ ሲጠየቅ አስር ሲደመር አንድ፣ ሁለት፣ … እየተባለ በሚገርበት በዚህ ዘመን ጉዳዩን ያስተዋለ አሽሟጣጭ የእገሌ አባባሉ የትምህርት ደረጃ ምን ያህል ነው ቢሉት “ቲወልቭ ፕላስ ምላስ” እንዳለው፤ ያለምንም (ያለ በቂ) ትምህርት ምሁሩን፣ ልሂቁን፣ አዋቂውን ሁሉ ከሃገር አሰደዱት፣ ስማቸውንና የንቀት ምሳሌያቸው ወደር ያልነበረው ሆነው ሳሉ አሁን ግን ከእነሱ የተሻለ የሚባለውን ሁሉ እንደ ጎርፍ በቀደዱለት የሚፈስ፣ በተናገሩት የሚናገር፣ ያሉትን ብቻ የሚፈፅም እንዲሆን አደረጉት ሲሉ ትንቢተኛው ሼህ ሁሴን ጅብሪል እንዲህ ብለው ነበር፤
ስማችን ወያኔ ስድባችን ቅማላም፤
የደርግን ወታደር ነዳነው እንደላም፡፡
ምላሳቸው ምላጭ፤ ልብሳቸው እድፍ፤
ትልልቁን ሁሉ ነዱት እንደጎርፍ፡፡
ወደ ስልጣን ከመጡም በኋላ፤ የተሻለ ነገርን ጠብቆ ሳለ የባሰ ሲመጣበት “ትተምትምን ሰድጄ፤ ትጎርድምን አመጣሁ” እንዲል የጎንደር ስነቃል እኒህ ዘመነኛ ሃገረ ገዥዎች፤ ታዲያ ለህዝቡ ከቀደሞዎቹ የከፉ፣ የባሱ እንደሚሆኑበት በትንቢት አርቆ ማሳያ መነፅራቸው የተመለከቱት ሼህ እንዲህ ብለው ነበር፤
ያምናን ቀን አማሁት ላፌ ለከት የለው፤
የዘንድው መጣ እጅ እግር የሌለው፤
ቀን ይወጣ ብየ ብጠብቅ ባስጠብቅ፤
እንኳን ቀን ሊወጣ ጨለማ ነው ጥቅጥቅ፡፡
በተጨማሪም እኒሁ ክፋትን የተላበሱ ገዥዎች ከሚያመጡብን መዓት ወይም መከራ ፈጣሪ ይጠብቀን ዘንድ የተመኙበትና በልተው የማይጠግቡ አጋሰሶች፣ ይህም ሲባል አንድም ሆዳቸው በልቶ የማይጠረቃ፤ አልያም ጉቦ የሚያግበሰብሱ እንደሆኑ ሀገርን ለማቅናት ይባትሉ ከነበሩት ከአፄ ሃይለ ስላሴ ጋር በማነፃፀር ኮሳሳዎች እንደሆኑ በሚከተሉት ስንኞች እንዲህ ይገልጧቸዋል፤
ጠጉራቸው ሆጭራራ ጫማቸው ነጠላ፤
አላህ ይጠብቀን፤ ከሚያመጡት በላ፡፡
በልተው አይጠጡ ጅስማቸው ቀጭን ነው፤
ተፈሪ ያልወፈረው አሳሩ በዝቶ ነው፤
ከዚህም ባሻገር እኒሁ ወያኔዎች አመጣጣቸው ከወደ አስመራ መሆኑና እነርሱ ብረት ካነሱ ማጣፊያው እንደሚያጥር፣ ህዝቡም በአጼ ሃይለስላሴ ምትክ ንጉስ ሳይተካ አስፈራተው እንደሚነግሱ ይኸውም ለዝርፊያ እንዲመቻቸው መደላድል ሲያዘጋጁ እንደሆነና መዳረሻቸውም በሃገሪቱ ላይ ፋይዳ ቢስ ደም መፋሰስ እንደሚያሰፍን በሚከተሉት ግጥሞች ይጠቁማሉ፤
ያስመራ ወያኔ ተያዘ ጠመንጃ፤
የኋላ የኋላ ሐቲማውን እንጃ፤
ምን አስለፈለፈኝ ሊገኝ ፈረጃ፡፡
ሸዋ መርዙን ገዛ መሪውን ታይተካ
ወያኔ አስፈራርቶ ንጉስ እንዳይተካ
መዝረፍ እንዲመቸው ቦታና ፈረንካ
እንዴት ሰው ባገሩ ደም ለውሶ ያቡካ
ጥይት እህል ሆኖ ሐሻ ላይቦካ፡፡
በተጨማሪም አጼ ሃይለስላሴም በተያዙ ግዜ ለሃገሪቱ ሰዎች የሚቸግራቸው መሆኑን፤ የሚበላ እንደሚጠፋ ብሎም በዚሁ ጭንቅ ወቅት ኢትዮጵያ ከሁለት ኤርትራ (አስመራ) እና ሸዋ (አዲስ አበባ) ተብለው እንደሚከፋፈሉ ፍፃሜያቸው የማያምር መሆኑ እና የወያኔ መነሳት አስመራ ላይ እሳት እንደሚያስነሳ ከዚህ በታች የቀረቡትን ስኞች ቋጥረው ነበር፤
ተፈሪ መኮነን የተያዘ እንደሆን፤
እንግዲህ ሃበሻ ምን ይበጀው ይሆን?
እህል ያልገዛ ሰው ወት ይገባ ይሆን?
አስመራና ሸዋ ይሆናል እንዳይሆን፤
ወያኔ ተነስቶ አስመራ እሳት ቲሆን፡፡
በታህሳስ ወር የሚጀመረው ጦርነት ለበርካታ ሰዎች እልቂት እንደሚዳርግ ነገር ግን መጨረሻው መገንጠልና መለያየት እንደሆነ እና ለመገንጠላቸውም ተባባሪ የሆነና ህዝቡን በአየርና በየብስ ትራንስፖርት አስወጥቶ የሚልክ ስውር እጅ እንዳለ የገለፁባቸው ስንኞች ደግሞ ከዚህ በታች ቀርበዋል፡፡
ያስመራ ጦርነት ትሳስ ቲጀመር፤
ብዙ ሰው ይጎዳል፤ ነገሩ ታያምር፤
ወዲያው ሰደዳቸው በሰማይ በምድር፤
ወያኔ ይሞታል አያገኝም ነስር፡፡
ጦርነቱም በርካታ የሃገሬውን ሰዎች የሚያሳትፍና የሚጨርስ መሆኑን የቦታዎቹን ስሞች እየጠቀሱ በርካታ ፍጥረት እንደሚያልቅ እንዲህ በማለት ገልፀውታል፡፡
ያን ግዜ ይበዛል፤ ጦርና ዱለት፤
ደላንታ ያዋጋል፤ ቦረና መሬት፤
አላሻም ይዋጋል፤ ኤርትራ ለሚሉት፤
በሸዋ በደሴ በትግሬ በጎንደር የሚያልቀው ፍጥረት፡፡
በጦርነቱ መጨረሻም ስለሚሆነው የቦታና መሬት መወሰድ ያንን ተከትሎም ስለሚመጣው መዓት፣ ያልታሰበ ጦርነት እንዲሁም የህዝብ ለህዝብ ዕልቂት ብሎም የአዲስ አበባን ጥይት ተታኩሶ ጠላት ማፍራትም ሼህ ሁሴን ጅብሪል እንዲህ ያትቱታል፤
ቦታና መሬቱ ከተወሰደበት ይወርዳል መዓት፤
ያልታሰበ እልቂት፤ የእርስ በርስ ጦርነት፤
በተለይ አስመራ ትሆናለች እልቂት፤
ሸዋ ጠላት ገዛ ጥይት ደጉሶበት፡፡
ትንቢተኛው ሼህ አስከትለውም ይህንኑ በሁለቱ የአንድ አገር ቦታዎች ላይ ፍጅት ያወጀውንና ተግባራዊ ያደረገውን አካል ሲያስጠነቅቁት እንዲህ ይሉታል፤ ሁለቱን ህዝብ እንዳፋጀሃቸው ማምለጫ የለህም፤ አንተም ዱቄት ትሆናለህ ይሉታል፤ እስኪ ስንኞቹን እንመልከት፤
ሸዋ አስመራን ፈጅተህ አቃጥነህ በሳት፤
ማምለጫ አታገኝም ታትሆን ዱቄት፡፡
ትንቢት ተናጋሪው ሼህ ትግሬና አስመራ እንደሚገጥሙና ሸሙናየ ወይም ሆታ እንደሚያበዙ፤ በግጥሞቻቸው ቀጥሎ ያለውን ሃሳብ አስፍረዋል፤ ነገር ግን በዚያ ወቅት አንድ በእባብ የተመሰለ አካል ከተፍ እንደሚልባቸው፤ የሸዋም ሰው ትግሬ ትግሬ ሲያይ መጅ (የደደረ እጅ) ጀርባውን እንደሚመታው አጉል ዋይታንም እንደሚበዛ ከዚህ በታች በቀረቡት ስንኞች ይገልፃሉ፡፡
አስመራና ትግሬ ትትል ሸገዳይ፤
እባብ ከተፍ ይላል መምጫው ታይታይ፤
ሸዋ የዛን ግዜ ይላል ዋይ ዋይ፤
ጀርባውን መጅ መታው ወደ ትግሬ ቲያይ፡፡
በመጨረሻም የሁለቱን ቦታዎች መለያየትና መገንጠል ሲገልፁ ከሃገር ላይ ሆኖ ሀገር እንደሚናፍቅ፤ ይህም ሁኔታ እንደ ቀበሮ ጉድጓድ መግባትን እንደሚያስመኝ እንዲህ ሲሉ ገልፀውት ነበር፡፡ (ክፍል ሁለት ነገ ይቀጥላል)
ጸሃፊውን ለማግኘት solomon123@yahoo.com