>
5:12 pm - Friday August 19, 2022

የኢትዮጵያ ሞዴል፣ ባንዲራና ውክልናው (ሞሀመድ እድሪስ)

የኢትዮጵያ ሞዴል፣ ባንዲራና ውክልናው
ሞሀመድ እድሪስ
ስለ ኢትዮጵያ ሀገር ግንባታ እና ዘመናዊነት ጉዞ በታሰበ ቁጥር የሚገርመው ጉዳይ በዚያን ግዜ ተጀምሮ አሁን ላይ አልቆ ህዝቦች የሚስማሙበት እና ተጠቃሚ የሆኑበት ትሩፋት አለመኖሩ ነው፡፡ ቀድመን ጀምረነው ይህ የኢትዮጵያ ሞዴል (መንገድ) ነው የምንለው ነገር አናሳ መሆኑ ከጥንታዊነታችን ጋር ሲነፃፀር በቀድሞዋ ኢትዮጵያ እውን ኢትዮጵያውያን ነበሩን ያስብላል፡፡
ብዝሀነትን ለማስተናገድ ጥረት ያደረገው ኢያሱ ሚካኤል (ልጅ ኢያሱ) መቶ አመት ቢሞላውም ያንን አስቀጥሎ ሁሉም ኢትዮጵያዊነት እንዲሰማውና ኢትዮጵያም የሁሉም እንደሆነች ሙሉ እውቅና የሚያገኝበት ዘመን እስካሁን አለመምጣቱ አሁንም ይህ ጉዳይ የሚያንቃቸውን እዚህም አዛም ማየቱ ማስረጃ ነው፡፡ የኢትዮጵያ የዘመናዊነት አንዱ ታሪክ በኢንዱስተሪው ሴክተር እንደመጀመሩ (የባቡር ዝርጋታውን የመሰለ) ሀገራችን የጠንካራ ኢኮኖሚ ባለቤት በሆነች ነበር፡፡ ይሄም አልተሳካም:: በሀገር ምስረታ እና በዘመናዊነት ሂደት በህዝቦች መካከል ግጭት እና የባህል መጨፍለቅ እንዲሁም በከተሞች ምስረታ ሂደት ከቦታ መፈናቀል እና መቀላቀል የሚጠበቁ ናቸው፡፡ በምኒልክ ዘመን የሆነው ይሄ ነው ብለን ልንቀበለው እንችል ነበር፡፡ ነገር ግን በዘመናዊነት አካሄድ ቀጣዩ ደረጃ ግን እነዚህን ችግሮች የሚቀርፉ ስልጣኔ የወለዳቸው የትምህርት፣ መገናኛ ዘዴዎችን (መፅሀፍት፣ ጋዜጣ… በመጠቀም የርስ በርስ ትስስን ማጠናከር፣ ሀገር በማስፋፋት የተበተኑትን መሰብሰብ፣ ያኮረፉትን ማቅረብ እና ሀገር ምስረታው እና ዘመናዊነቱ ለጋራ ሀገር እንደሆነ ማሳየት ነው፡፡ በብዙ ሀገሮች የተካሄደውም ይሄው ነው፡፡ በኢትዮጵያ የነበረው እውነታ ግን በሀገር ምስረታ ሂደት የተፈናቀሉ፣ ባህላቸው የተጨፈለቁ ከሌላውጋር በግድ የተቀላቀሉቱ “ከስልጣኔው” ትሩፋትም እንዳይቋደሱ ተደረጉ፡፡ ትምህርቱ የተወሰነ ማህበረሰብ ልዩ መብት ሆኖ በመቀጠሉ የባህል መበላለጥ እና ሀገርን እና ስልጣኔን የኔ ብሎ የማይወስድ ማህበረሰብ ፈጠርን፡፡ ትልቅ ባህል እና ትንሽ ባህል ተፈጠረ፡፡ ኦፊሴላዊ ባህል እና የአንድ ውስን መደብ ባህል የሚል ተፈጠረ፡፡
በሀይለስላሴ እንደነበረው ደግሞ ግዛቶችን በአካባቢ ሹማምንቶች ውክልና የማስተዳደር ሂደት በገዢው እና በተገዢው መካከል የሚኖረውን ግንኙነት ለማስተካከል ቁልፍ ሚና በተጫወተ ነበር፡፡ ይሄ ደግሞ መዋቅሮች፣ ሰራተኞች እና ህግ ወጥቶለት ህዝቦች በመሪ በጎ ፍቃድ ብቻ የሚመሩ መሆናቸውን የሚያመላክቱ ነገሮች እየቀነሱ መጥተው በህግ የመተዳደርን ባህል ያዳብር ነበር፡፡ የኢትዮጵያ ሞዴል ግን ህገመንግስቱም ከንጉሱ የተበረከተ ስጦታ አድርጎት ይዘቱንም ኢትዮጵያ እና ህዝቦቿን የማይወክል አደረገው፡፡ ከዚያ ተነስተን የምናሻሽለው ሳይሆን አዲስ የምንጀምረው የህግ ማውጣት እና የመሪ ተመሪ ግንኙነት መርቀቅ ግድ ሆነብን፡፡
የባንዲራ ታሪካችንም ተጀምረው ካላለቁ ፕሮጀክቶች አንዱ እንጂ ፍፃሜ ያገኘና ጥያቄ በማያስነሳ ደረጃ የደረሰ አይደለም፡፡ ባሳለፍነው አንድ መቶ አመት ውስጥ አራት መንግስታት ስምንት አይነት ባንዲራዎችን ጥቅም ላይ አውለዋል፡፡ በአፄ ምኒልክ እና በአፄ ሀይለስላሴ ዘመነ መንግስት መንግስታዊ ሀይማኖት ክርስትና በመሆኑ ያንን የሚወክል አርማ ማስቀመጣቸው ለመንግስታቱም ሆነ በወቅቱ የተሸለ ውክልና እና ተጠቃሚ ለነበረው የህብረተሰብ ክፍል አርማው እነርሱን የመወከል አቅም ነበረው ማለት ይቻላል፡፡ ደርግ ብቻ በስልጣን ዘመኑ ሶስት አይነት አርማዎችን በባንዲራው ላይ አስፍሯል፡፡  አርማዎቹ በአመዛኙ ደርግ በየወቅቱ የተከተላቸውን ርዕዮተ አለም እና ፖሊሲዎቹን ታሳቢ ያደረጉ ስለነበሩ አርማዎቹ ከህዝብ ጋር ይሄ ነው የሚባል ግንኙነት የላቸውም፡፡ ኢህአዴግ ወደስልጣን ሲመጣ እስከሽግግር መንግስቱ መቋቋም ምንም አርማ ያልነበረውን ባንዲራ ሲጠቀም ከሽግግር መንግስቱ በኋላ ግን አሁን ላይ በህገመንግስቱ የፀደቀው ባንዲራ ጥቅም ላይ ዋለ፡፡ በአዲሱ ባንዲራ ላይ የሰፈረው አርማ የተሰጠው ትርጓሜ ውሃ ያነሳል ወይ የሚለውን ለመመለስ ከታች ትንሽ ለማለት ልሞክር፡፡
ንጉሳዊ አገዛዝ ለሰሞናዊ ስርወመንግስት የተሸለ ስለነበር እና በወቅቱ በርካታ ሀገራት በዚያ ሲስተም ይተዳደሩ ስለነበር ለኢትዮጵያም እንደመንገድ ተወስዷል፡፡ የአውሮፓ ሀገራት የፖለቲካ እድገትም የሚያሳየው ከፊውዳል ስርአት ከተላቀቁ በኋላ ንጉሳዊ አገዛዝ እጣፈንታቸው እንደነበር ሁሉ ኢትዮጵያም የተለየ እጣ አልነበራትም፡፡ ኢህአዴግ ወደስልጣን በመጣበት ግዜ ግን በርካታ ሀገራት የግለሰብ መብትን ያስቀደመ የፖለቲካ ርዕዮተ አለም የሚከተሉበት ወቅት ነበር፡፡ ኢህአዴግ ከዚህ ግለሰብ ተኮር እሳቤ በተለየ ብሄር ተኮር ፖለቲካን ሲከተል ህወሀት ከአናሳ ብሄር በመወለዱ አማራጭ ማጣት ብቻ ነው ብሎ ማሰብ ከእውነታውጋ ለመጋፈጥ ድፍረት ማጣት ነው፡፡ በሀገራችን የፖለቲካ ተሳትፎ እያደገ በመጣባቸው ግዚያት ሁሉ የብሄር ጥያቄ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ቁልፍ ማጠንጠኛ ነው፡፡ በዚህ ላይ የሚገነባ የፖለቲካ ስርዓት ከማህበረሰቡ የፖለቲካ ባህል እና የእድገት ደረጃጋ በቀጥታ የሚመጣጠን ነው፡፡ ሽሙዔል ኖህ የተባሉ ምሁር እንደሚያስቀምጡት ለውጥ ከሚመጣባቸው መንገዶች አንዱ በማህበረሰብ ውስጥ ያሉ ማህበራዊ ካፒታል ላይ በመመሰረት ሊሆን እንደሚችል ነው፡፡ በተቃራኒም አዲስ እና ሁሉን ሊስብ ሚችል ሲምቦል (አስተሳሰብ) በማፍለቅ ማንም በብቸኝነት የኔ ነው የማይለው የፖለቲካ ሽግግር ማድረግ ይቻላል፡፡ ኢህአዴግ በህዝቡ ውስጥ ባሉ ጥያቄዎች ላይ የተንተራሰ የለውጥ ሂደትን መረጠ፡፡ ይህን ሂደት የኢህአዴግ ሴራ እና ሸፍጥ በሚል ማስቀመጥ ሙሉ ምስል የሚሰጥ አይደለም፡፡ ኢህአዴግ እና ፌዴራሊዝምን አንድ አድርገው የሚስሉ ወገኖች አንድም ለኢህአዴግ ያላቸው ጥላቻ ስለፌዴራሊዝም ምንም መስማት እንዳይፈልጉ አድርጓቸዋል፡፡ ወይንም ፌዴራሊዝምን በአግባቡ አልተረዱትም፡፡
የኢህአዴግ ደጋፊዎች ፌዴራሊዝምን እርሱ አቡክቶ እንደጋገረው እንደሚኮፈሱበት ሁሉ ተቀናቃኞቹ ደግሞ የአለማችን አንድ ሶስተኛ ሀገራት የሚተዳደሩበትን የፌዴራል ስርዓት ኢህአዴግ ስለመረጠው ብቻ አይን እና ጆሯቸውን ዘግተው ስለመልካም ጎኖቹ እና ትሩፋቶቹ ሳይቀር አንሰማም አናይም እያሉ ነው፡፡ ፌዴራሊዝም አንድ አማራጭ ለመሆኑ በአሁኑ ወቅት ከክልል እስከ ቀበሌ ድረስ ለእልፍ አዕላፍ ወጣቶች የፖለቲካ ተሳትፎ እና አቅም ግንባታ ምቹ መድረክ ሆኗል፡፡ ከክልል እስከ ቀበሌ የራስን ክልል በማስተዳደር መርህ መሰረት የነቃ ተሳትፎ ያለውና ብቁ አቅም ያለው ወጣት ደግሞ በነገዋ ኢትዮጵያ በሚኖር የፖለቲካ ሂደት መብቱን ሳያስነካ እርሱ ያለውን መብት ሌሎች የማግኘት መብት እንዳላቸው በማመን ላይ የተመሰረት የጋራ ጉዞ ለማድረግ የተመቸ ሀይል ይሆናል፡፡ ይህ አማራጭ መንገድ ባልነበረባቸው እና በማይኖርበት ሁኔታ በፖለቲካው እና ሀገርን የማስተዳደር ጉዳዮች ደጅ ሊጠኑ የሚችሉ በርካቶች ግንባር ቀደም ተሰላፊ ሆነው ይገኛሉ፡፡ እነዚህን አዕላፍ ወጣቶች ኢህአዴግ ለዘመኑ የማይመጥን ሲሆንባቸው እየታገሉት ይገኛሉ፡፡ በተመሳሳይ መልኩም እነሱን ታሳቢ ያላደረገ ቀጣይ የኢትዮጵያ ግንባታ ፍሬ አያፈራም፡፡ አሁን እየተፈጠሩ ያሉ የአጋርነት ምልክቶች በጋራ ጠላት ዙሪያ የሚደረግ ተራ መሰባሰብ በሚል አሳንሶ ማየት አይቻልም፡፡ ህልውናቸው የተሳሰሩ ህዝቦች እጅ ለእጅ ተያይዘው የጋራ አንድ ሀገር ለመመስረት ስምምነት ላይ የደረሱበትም ደረጃ አይደለም፡፡ አጋርነቱ ሊገለፅ የሚችልበት የተሸለ አቀራረብ አንዱ ለብቻው ቀድሞ ወይንም ሌላውን ደፍቆ መሄድ የማይችልበትና ሁሉም ለራሴ በሚል በገነባው ማንነት ዙሪያ የተፈጠረ አቅምን እውቅና በመስጠት እና ከመጠላለፍ ይልቅ በመከባበር የተፈጠረ አጋርነት ሆኖ ይገኛል፡፡
ከላይ ያነሳኋቸው ነጥቦች የብሄሮች እኩልነትን እንዲወክል የተቀመጠው አርማ በሴራ የመጣ ሳይሆን መሬት ላይ ያለውን የህዝቦችን ጥያቄ ታሳቢ ያደረገ ነው የሚለውን ሀሳቤን ያስረዳል፡፡ ይህን የህዝቦች ጥያቄ ኢህአዴግ manipulate አድርጎታል  ለማለት የተቀመጠውን ማስረጃ  እውቅና መንፈግ አግባብ አይሆንም፡፡ ይህ አርማ ገብስ፣ አካፋ፣ ዶማ፣ ሊሆን ይችላል፡፡ ምንም አርማ ሳይኖረው ሊቀጥልም ይችላል፡፡ ብዝሀነት በተነሳ ቁጥር ቅር የሚላቸው አካላት ያለምንም ማብራሪያ እና የሌላውን የህብረተሰብ ክፍል ስሜት ታሳቢ ካለማድረግ ዛሬም አርማ መራጭ እና ወሳኝ ለመሆን ሲሞክሩ ማየት ግን ላለንበት ወቅት የማይመጥን ነው፡፡ ተጀምረው ባላለቁ የሀገር ግንባታ ፕሮጀክቶቻችን ላይ ከዚህ በኋላ የሚኖረው እርምጃችን መናበብ እና መደማመጥ ሲኖረው ይበልጥ ያማረ እና ፈጣን ለውጥ እናመጣለን፡፡ ይህ ካልሆነ የሰሞኑ መልካም መግባባት እና አጋርነት ነገ ካላለቁ ፕሮጀክቶቻችን ሁነው ዳግም ሀ ብለን መጀመራችን አይቀርም፡፡
Filed in: Amharic