>
5:26 pm - Thursday September 17, 9226

"ላሊበላን ከውድመት እንታደግ!!"  (ታደለ ጥበቡ)

“ላሊበላን ከውድመት እንታደግ!!”
ታደለ ጥበቡ
ቅዱስ ላሊበላ በ 1101 አ.ም ታህሳስ 29 ቀን ከ እናቱ ከኬርዮርና ከአባቱ ዛንስዮም ላሰታ ቡግና ወረዳ ሮሃ ወይንም አዳፋ ከተባለች ቦታ ከፍልፍል ቤተ መቅደስ ውስጥ ተወለደ።
 ቅ/ላሊበላ ሲወለድ በንቦች ተከቦ እንደነበረና እናቱም በክስተቱ በጣም እንደተገረመች ይነገራል። ህጻኑን «ላሊበላ»  ንቦች ከበውት በማየቷ ለወደፊቱ የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት ለመሆኑ ምልክት ይሆናል ብላ ተንበየውም ነበር።«ከእናቱ ወተት በፊት ማር አቀመሱት ምን አይነት ተአምር ነው» በማለት ስሙን ላልይበላ እንዳለችው ታሪክ ይነግረናል። ላል በአገውኛ ማር/ንብ ማለት ነው።  ላሊበላ በትክክለኛ አጻጻ ላል-ይበላል ሲሆን ቃሉ በጥንቱ አገውኛ ‹‹ ማር ይበላል ማለት ነው›› «ንቦች ሳይቀር ንጉስነቱን እውቅና ሰጡ» ማለትም ነው።
ስድስት አመት ሲሞላው ቤተ-መንግስት አባ ዳንእል የተባሉ መምህር ተቀጥረውለት ከፊደል እስከ ዳዊት አጠናቆ ከዚያም የተማረውን የጽሁፍ ጥበብ በቤተ ጎሎጎታ ደብረ ሲና በሚገኘው ከኪዳነ ምህረት መንበር ታቦት ዙሪያ ላይ እራሱ የተጻፋቸው የሚለይበት ጽሁፎች ይገኛሉ፡፡ በኋላም በእየሩሳሌም በነበረው አስራ ሶስት አመት ቆይታው ተምሯል። ላነፃቸው አብያተ ቤተክርስትያን መሰረት የሆኑት የመፅሐፍ ቅዱስ እውቀቱ እና እየሩሳሌም ለአስራ ሶስት አመታት በኖረበት ጊዜ የተማራቸውና የቀሰማቸው የቤተ ክህነት እውቀቶቹ እንደሆነ ይነገራል።
 ቅዱስ  ላሊበላ 12 አመት ሲሞላው አባቱ ዘንሳዮም 40 አመት ነግሶ በተወለደ በ 76 አመቱ ከዚህ አለም በሞት ተለየው። ወድያው ብዙም ሳይቆይ እናቱ ኬርዮርና በሞት ተለየች፡፡ ቅዱስ ላሊበላ በእናቱ ና አባቱ ህልፈተ ህይወት በደረሰበት ሀዘን የተነሳ ሁሉን ነገር ለመርሳት ና የትምህርት ፍላጎት ለማሟላት ጉዞውን ወደ ጎጃም በማድረግ አለም ስላሴ ከተባለው ደብር ከመምህር ኬፋ ሃዲሳቱን አጠናቆ በመመረቅ ወደ ሀገሩ ተመልሷል።
ዓፄ ገብረ መስቀል ላሊበላ ንጉሠ ነገሥት ዘኢትዮጵያ ግዛት ከ1181-1221 እ.ኤ.አ.የገዙ ሲሆን ከሳቸው  በፊት የነገሰው ቅዱስ ሐርቤ ሲሆኑ ተከታይ  ንጉስ ዓፄ ነዓኩቶ ላሊበላ ይባላሉ። ባለቤታቸው መስቀል ክብረ ሲባሉ  ልጃቸው ይትባረክ ይባላል።ሥርወ-መንግሥታቸው ደግሞ ዛግዌ አባት ጃን ስዩም ይባላል።
በዛጉዬ ዘመነ መንግስት ከ920 እስከ 1237 ዓ.ም 11 ነገሥታት ነግሰዋል።መቀመጫቸውም ላስታ ነበር። ከ 11ዱ ውስጥ ቅዱስ የሚባል ስም የተሰጣቸው ፅላት ተቀርጾ ከክህነት ጋር ንግስን አጣምረው  የያዙ 4ት ሲሆኑ እነሱም፦
      ቅ/ይምረሀክርስቶስ
     ቅ/ገ/ማርያም
     ቅ/ላሊበላ
     ቅ/ነአኩቶለብ ናቸው።
ከትውፊት አንጻር የወደፊቱ ከአጎቱ ታታዲም እና ከራሱ ወንድም ንጉስ ሐርቤ ጋር ባለመስማማቱ ለስደት ተዳረገ።ጉዞውን እየሩሳሌም አደረገ። ለተከታታይ 13 አመታትም ቆይታ በኋላ ወደ ባለቤቱ ተመልሶ ከ ውንድሙ ከቅዱስ ገብረ ማሪያም ጋር እርቅ በማውረድ ቅዱስ ገብረ ማሪያም ንግስናውን ለከቅዱስ  ላሊበላ በተወለደ በ57 አመቱ በማስረከብ ኑሮውን በገዳም አደረገ፡፡
ቅዱስ ላሊበላ ስልጣን ላይ ከወጣ በኋላ ሕንጻዎችን ለመገንባት አሰበ።ላሊበላ በአይነ ህሊናው እየሩሳሌምን እንደተመለከተና አዲስ እየሩሳሌምን በኢትዮጵያ ለመገንባት ፍላጎት እንዳደረበት በታሪክ ይጠቀሳል። ስለሆነም ለዚህ ተግባር አሁን ላሊበላ የሚባለውን ድንቅ የአለት ፍልፍል ከተማ ለማሰራት ተሰማራ። ከላሊበላ አቅድ አንጻር ይህ አዲሱ ከተማ ኢየሩሳሌምን መምሰል ስላለበት ብዙ ቦታዎቹ ከዚህ አቅድ አንጻር ተሰይመዋል። ለምሳሌ በአካባቢው የሚፈሰው ወንዝ ዮርዳኖስ ወንዝ በመባል ይታወቃል። አዲሱ ከተማ ሮሃ፣ ከ12ኛው እስከ 13ኛው ክፍለ ዘመን የኢትዮጵያ ዋና ከተማ በመሆን አገልግሏል።
ከዚያም በጊዜው ከነበሩት አባቶች በተለይ ቀይት ከምትባል ባለአባት የጠየቀውን 40 ጊደር ለመግዛት በሚያስችለው ወርቅ ቦታውን ገዝቶ በከርሰ ምድር ውስጥ ያሉትን ሕንጻዎቸ ሊያወጣ ተዘጋጅ፡፡
በኢትዮጵያ ትውፊት መሰረት እነዚህ አብያተ-ክርስቲያናት በንጉሥ ላሊበላ ዘመን በቅዱሳን መላዕክት እንደተሰሩ የሚታመን ሲሆን
ንጉስ ላሊበላ ከመሬት ውስጥ ፈልፍሎ ከሰራቸው 10 ቤተክርስትያኖች በፊት ማነጽ የጀመረው አሸተ ማርያምን ነበር።ቅዱስ ላሊበላ የሚገነባባቸውን መሳሪያዎች ለ10 አመታት አዘጋጅቶ ማለትም በ1157 አ.ም ነግሶ በ1166 አ.ም ሕንጻውን ገንብቶ ጨረሰ፡፡
የላሊበላ ቤተክርትያናት በሁለት የተከፈሉ ናቸው።
 
1ኛ በምድራዊ እየሩሳሌም የተሰየሙት
 
         ቤተ መድኃኔአለም
         ቤተ ማርያም
         ቤተ መስቀል
         ቤተ ደናግል
         ቤተ ሚካኤል
         ቤተ ጊዮርጊስ
 
2ኛ በሰማያዊ እየሩሳሌም የተሰየሙት
         ቤተ ገብርኤል
         ቤተ መርቆሬዎስ
         ቤተ አማኑኤል
         ቤተ ሊባኖስ
        ቤተ ጊዮርጊስ
አለም የሚደነቅበት ሲመለከቱት ስራዊ አስገራሚና ማራኪ የሆነው የጊዮርጊስ ቤተክርስትያን የቅ/ላሊበላ የመጨረሻ ስራው ነው። ይህ ቤተመቅደስ በመስቀል ቅርፅ ከላይ አስከታች የተሰራ ነው። መግብያው በሸለቆ መልክ የተሰራ ሲሆን አስገራሚነቱ የውሃ ፍሳሽ መውረጃው አሰራርና ቴክኒኩ ነው። ይህ የጊዮርጊስ ቤተክርስትያን የተሰራው በኖህ መርከብ አምሳያ መሆኑ ያንን የሚያመላቱ ስራዎች ተሰርተውበታል።
የውጭው ክፍል
በእግዚአብሔር ትእዛዝ ኖህ መርከብ ሰርቶ ከያንዳንዱ ፍጡር ይዞ ከመጥለቅለቅ የቆየበትን ታሪክ የሚያሳይ ህንፃ ነው። የታችኛው የቤተክርስትያኑ ክፍል 9 ዝግ መስኮቶች ያሉት ሲሆን የላይኛው የቤተክርስትያኑ ክፍል ደግሞ ለብርሃን ማስገብያ የሚሆኑ 12 ክፍት መስኮቶች አሉት።
ከቤተክርስትያኑ መግቢያ ፊትለፊት በስተግራ በኩል የሚታየው የቄጤማ ሳር ተክል የኖህ መልክተኛ እርግብ የውሃውን መጉደል ለማብሰር ቀንጥባ ያመጣችውን ሳር የሚያመላክት ነው። በመቀጠል ከቤተክርስትያኑ ጀርባ በስተግራ የሚታየው ጉብታ ቦታ የኖህ መርከብ መሬትን የነካችበትን የአራራ ተራራ የሚያመላክት ነው።
ቅዱስ ላሊበላ ከ 40 አመታት የንግስና ዘመን በኋላ በተወለደ በ 97 አመቱ ሰኔ12 ቀን ከዚህ አለም በሞት ተለየ፡፡
  አሁን ላይ የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት ጉዳት እየተባባሰ ነው።በላሊበላ ውቅር አቢያተ ክርሲቲያናት ላይ  የተከሰተው ሰው ሠራሽና የተፈጥሮ ጉዳት ተባብሶ ቀጥሏል፡፡
በ1930 ዓ.ም የተደረገው ጥገና በቅርሱ ተፈጥሯዊ ገፅታ ላይ ጠባሳውን ጥሎ ከማለፉም ባሻገር ቅርሱን ለበለጠ ጉዳት ዳርጐታል፡፡ በ1960ዎቹ የተደረገው ጥገናም ቅርሱን ቦርቡሮ ለከፋ ጉዳት መዳረጉን የአዲስ አበባ የኒቨርሲቲ የሳይንስና ቴክኖሎጂ እንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ኢሳያስ ገብረዮሐንስ በጥናት አረጋግጠዋል፡፡
ዶ/ር ኢሳያስ በጥናታዊ ፅሁፋቸው እንዳስረዱት ከ10 ዓመት በፊት ከፀሐይና ከዝናብ ይከላከላል ተብሎ የተሠራው መጠለያም ቅርሱን የማፍረስ አደጋ ደቅኖበታል፡፡
የመጠለያዎቹ ምሰሶዎች የቆሙት ያለጥናትና ከታሰበው ዲዛይን ውጭ በመሆኑ በነፋስ ወደ ላይ ተነስተው መልሰው ቅርሶቹ ላይ የመውደቅና ወደታች ተደርምሰው አደጋ የማድረስ ሥጋት ፈጥረዋል፡፡ በተለይ የቤተ ማርያም መጠለያ ምሰሶ በቤተ ጐልጐታ ቤተ መቅደሶች ላይ፤ የቤተ አማኑኤል መጠለያ  ደግሞ ወደ ቤተ መርቆሪዮስ በሚወስደው የዋሻ ውስጥ መንገድ ላይ የመውደቅ አደጋ ከተጋረጠባቸው ተርታ እንደሚመደቡ  የዶ/ር ኢሳያስ የጥናት ውጤት ያስረዳል፡፡
የቅዱስ ላሊበላ ደብር ጽ/ቤት ሠራተኞችም ሆኑ የላሊበላ ከተማ ነዋሪዎች ሥለ ቅርሱ ጉዳት ጉዳይ፣ “እንቅልፍ አጥተናል” በማለት ነው ስጋታቸውን የሚገልፁት፡፡
ውስብስብ ችግር ውስጥ የሚገኙትን የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርሲቲያናት ለመታደግ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ሊነሳሳ እንደሚገባው ለማስገንዘብ እወዳለሁ።
       በተጨማሪ ልታዩት የሚገባ ማጣቀሻ
(ፈረንሳይኛ) J. Perruchon. Vie de Lalibala, roi d’éthiopie: texte éthiopien et traduction française. Paris 1892. (Online version in Gallica website at the “Bibliothèque National Française”)
4.Taddesse Tamrat, Church and State in Ethiopia (Oxford: Clarendon Press, 1972), p. 56n.
5.Getachew Mekonnen Hasen, Wollo, Yager Dibab (Addis Ababa: Nigd Matemiya Bet, 1992), p. 22.
6. Taddesse Tamrat, p. 61.
7.Richard K.P. Pankhurst in his The Ethiopian Royal Chronicles (Addis Ababa: Oxford University Press), 1967
Filed in: Amharic