>

ሃዘንሽ ቅጥ አጣ' ሆነ የኛ ነገር (ያሬድ ሀይለማርያም) 

ሃዘንሽ ቅጥ አጣ’ ሆነ የኛ ነገር
ያሬድ ሀይለማርያም 
ከአንድ ሃዘን ወደ ሌላ፤ ላለፉት ጥቂት ወራት ክልላትን እያዳረሰ ያለውና ጎሳ ላይ ያነጣጠረው ግጭት ከቡራዩ ሃዘን ሳናገግም በዚህ ሳምንት ደግሞ ዳግም ወደ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ዞረ። በክልሉ ይኖሩ የነበሩ የኦሮሞ፣ አማራ እና የሌሎች ብሔር ተወላጆች ላይ ሌላ አስከፊ ጥቃት መፈጸሙን መርዶ ሰማን። ሰዎች ተገድለዋል፤ ቁጥራቸው በአሥር ሺዎች የሆነ ሰዎችም ተፈናቅለዋል። ለዚህም ጥቃት የተለያዩ ኃይሎች እንደ ምክንያት እየተጠቀሱ ነው። ከእንዲህ ያለው አስነዋሪ እና እጅግ ኋላ ቀር ከሆነ የጎጠኝነት ስሜት እንዴት ይሆን የምንላቀቀው? መቼ? በጎጥ ጥላቻ ላይ ምህለቁን የጣለው ዘር ተኮር ፖለቲካችንስ መቼ ይሆን የሚጸዳው?
ከእንዲህ ያለው ቅርቃር ለመውጣት እንደ ሰው ማሰብ ብቻ ይበቃን ነበር፤ ከዚያም ሲያልፍ የአንድ አገር ልጆች በመሆናችን ብቻ ልንተዛዘን፣ ልንደጋገፍ እና አብረን ልንኖር በቻልን ነበር። ይህ ሁሉ ቢቀር በየጎሳ አጥራችንም ውስጥ ተከልለን ግን በመከባበር መኖር ብንችል እሱም ትልቅ እድል ነበር። ይህም ቢያቅተን ግጭቱ ሀሃሳብ እና በቃላት ብቻ ቢወሰን ጥሩ ነበር። እነዚህን ሁሉ ማድረግ አቅቶንም እንኳ በዛቻ፣ በማስፈራሪያ እና በመጠነኛ አካላዊ ግጭትም ጉዳያችን ትኩረት እንዲያገኝ ያህል ተጋጭተን ብናቆም ደህና ነበር። በየክልሉ እየታየ ያለው አስነዋሪ እና ከሰው ልጅ የማይጠበቁ ድርጊቶች ያለንበትን አፋፍ ነው የሚያሳየው። በእነዚህ ሁለት ሳምንታት እንኳ በቡራዩ እና በቤኒሻንጉል ጉምዝ የታዩት የጥቃት አይነቶች የግጭቱን ባህሪይ እና ደረጃ ማሳያዎች ናቸው። ይህ ጉዳይ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል። አደጋ በደረሰ ቁጥር መጯጯሁ ብቻ በቂ አይደለም። በየክልሉ ማህበረሰቡን ለግጭት የሚዳርጉት ችግሮች ባፋጣኝ ተጠንተው መፍትሔ ሊበጅለት ይገባል።
Filed in: Amharic