>

ትችት እንደ ርችት! (ሞሀመድ ኤ እድሪስ)

ትችት እንደ ርችት!
ሞሀመድ ኤ እድሪስ
የፖለቲካ ሜዳ በሀሳብ ከተለየህ ብቻ ሳይሆን ከጠላትህ ጋር የምትሰራበት፣ ትችትን ብቻ ሳይሆን ስድብን የምትሸከምበት፣ ከፍተኛ የራስ መተማመን የሚጠይቅ ነው፡፡ እዚህ ቦታ ለመገኘት የሚመጥን ሰብዕና እኛ ጋር የለም!!” 
እናቴን ልዘይር ሰፈር ገብቼ ስመለስ ሁለት ጓደኞቼ ቁመው ሲያወጉ ተመለከትኩና ሰላምታ አቅርቤ ተቀላቀልኳቸው፡፡ እያወሩ የነበሩት ሰለ ሙስሊሙ የፖለቲካ ተሳትፎ ነበር፡፡ አንዱ ጓደኛዬ የሙስሊሙ የፖለቲካ ተሳትፎ አናሳነት ገፊ ምክኒያት ያላቸውን ነጥቦች ዘረዘረ፡፡  የዘረዘራቸው ነጥቦች ግን ውጫዊ ተግዳሮቶችን ብቻ ነበር፡፡ ሁለተኛው ያነሳው ነጥብ ግን ማረከኝ፡፡ በራሴ ቋንቋ ሰነ ፅሁፋዊ ለዛውን ጠብቄ እንደሚከተለው ላቅርበው፡-
  “ፖለቲካ የራሱ የሆነ የጨዋታ ህግ ያለው ሲሆን የመጫወቻ ሜዳውም የተለየ ሰብዕና ይጠይቃል፡፡ አብዘሀኛው ሙስሊም ደግሞ አሸወይና የሚወድ ዋቴ(አርቴፊሻል ማንነት ያለው) ነው፡፡ ባልሰራው መወደስ የሚፈልግ፣ ሀቢቢ ሀቢቢ እየተባባለ የሚሸዋወድ፣ ትችት እንደ ርችት ጩሀት የሚያሰደነግጠው፣ ከሚመሰለውና በሀሳብ ከሚሰማማው ብቻ ጋር የሚሰባሰብ፣ ተምሮ ዶክትሬት እንኳ ይዞ ከመስጂድ አጀንዳ ከፍ ያለ ቦታ ላይ የማታገኘው፣ ሀሳብን የሚፈራ፣ በራሱ የማይተማመን ነው፡፡ የፖለቲካ ሜዳ በሀሳብ ከተለየህ ብቻ ሳይሆን ከጠላትህ ጋር የምትሰራበት፣ ትችትን ብቻ ሳይሆን ስድብን የምትሸከምበት፣ ከፍተኛ የራስ መተማመን የሚጠይቅ ነው፡፡ እዚህ ቦታ ለመገኘት የሚመጥን ሰብዕና እኛ ጋር የለም፡፡”
ከዚህ የጓደኛዬ ሀሳብ የምስማማበትም ብዙ ነጥብ አለ፡፡ ከዚህ ቀደም የፖለቲካ ተሳትፎዎችን ከፖለቲካዊ ባህልና ምህዳር አንፃር ነበር ለመረዳት ሰሞክር የነበረው፡፡ ሰለ ፖለቲካዊ ብልህነትም የተወሰነ ባነብም ሰለ ፖለቲካዊ ሰብዕና የተደራጀ ንባብ የለኝም፡፡ የልጁ ሀሳብ በዚህ ረገድ ማንበብ እንደሚገባኝ የቤት ሰራ የሰጠኝ ቢሆንም የራሴን ዙሪያና ተሞክሮ (በዙሪያ ያለን ብቻ መሰረት አድርጎ የሙስሊሙ ማለት ተገቢ ባይሆንም) መሰረት አድርጌ የሙስሊሙ ሰብዕናን ለፖለቲካዊ ተሳትፎ ምን ያህል ምቹ ነው የሚለውን ማሰላሰሌን ቀጠልኩ፡፡
**ትችትና የእውቀት ምርት**
ከተወሰነ ጊዜ በፊት መሰረቱን እንግሊዝ ባደረገ አለም አቀፍ መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት ባዘጋጀው “ቢዝነስ ሊደርሺፕ” ሰልጠና ላይ ተሳትፌ ነበር፡፡ በስልጠናው ከ23 ሀገራት የተውጣጡ 44 ተሳታፊዎች የነበሩ ሲሆን ብዙሀኑ አውሮፓውያን ናቸው፡፡ ከአፍሪካ 4 ተሳታፊዎች ብቻ ነበርን፡፡ ሰልጠናው ቀድሞ በተያዘ ርዕስና በተሰጠ ጥናት ላይ ተመርኩዞ ውይይትና ሙግት ላይ የተገነባ ነበር፡፡ በስልጠናው አውሮፓውያን ተሳታፊዎች(በብዛት እንግሊዛውያን) ተሳታፊዎች ሀሳባቸውን የሚያቀርቡበት መንገድ እጅግ ቀልቤን ሳበው፡፡ አንዱን የአንዱን ሀሳብ ሲተች እጅግ ጠንካራ ቃላት ይጠቀማሉ፡፡ እንግሊዛውያን አሰልጣኞቹም ትችታቸው እጅግ ጠንካራ ነው፡፡ ለሀሳብ አቅራቢዎች በሚሰጡት ምላሽ “rubbish” “non sense” “illogical” “lame” “shallow” የሚል ጠንካራ የትችት ቃላት የተለመዱ ናቸው፡፡ ያደኩበት ሰፈር ለትችት የማይደነግጥ፣ ለስድብ የማይበረግግ፣ ማንንም እንደአመጣጡ መመለስ የሚያስችል ሰብዕና እንዳዳብር አድርጎኛል የሚል ስሜት ይሰማኝ ነበር፡፡ ይህ ስሜቴ ግን የተሳሳተ መሆኑን የገባኝ በዚህ ስልጠና ወቅት ነበር፡፡ ምንም እንኳ ቢዝነስ የትምህርት ዘርፌ ቢሆንም በውይይቶቹ ላይ ግን ተሳትፎዬ እጅግ ውስን ነበር፡፡ ጠንካራ ትችቶቹ በራስ መተማመኔን ያጎደሉት ይመስለኛል፡፡ ከሰልጠናው በላይ የአውሮፓውያኑ የትችት ጥንካሬ፣ ባህልና የራስ መተማመን ትኩረቴን ስቦት ይህ ሰብዕናቸው በእውቀት ማምረት ሂደት የዋለላቸውን ውለታና በስልጣኔያቸው ውስጥ ያለውን ድርሻ እንዲሁም በተቋማዊ ብልህነት ውስጥ የሚጫወተውን ሚና ማሰላሰሉን መረጥኩ፡፡
በአካዳሚያ ውስጥ ያለፈ የሚረዳው ተጨባጭ ትችትና ወቀሳ የአካዳሚያዊ ህይወት አንዱ አካል ነው፡፡ ሴሚናሮች፣ ወርክሾፖች፣ ፓናል ዲስከሽኞች፣ ጥናትና ምርምሮች የሚደምቁትና ፍሬያማ የሚሆኑት፤ ከእውቀት ውስጥ አዳዲስ እውቀቶች የሚወለዱት በትችትና ወቀሳ ገፊነት በሚነሱ የሀሳብ ፅንሶች ነው፡፡
ትችትና ወቀሳ በዲሞክራሲያዊ ሰርዐት ግንባታ ያለውን ሚና ለተረዳ በዲሞክራሲያዊ ሰርዐት ግንባታ ውስጥ ጉልህ ሚና የሚኖራቸው ሰብዕናዎችን መለየት አይከብደውም፡፡ ጠንካራ የዲሞክራሲያዊ ሰርዐት የዳበረባቸው ሀገራት በፖርላማቸው፣ በሚዲያ፣ በፕረሰ ኮንፍረንሰ፣ በሰላማዊ ሰልፎች፣ ጠንካራና ጥልቅ ትችትና ወቀሳዎች ይዘንባሉ፡፡ ይህ ዝናብ የዳበረውን ዲሞክራሲ የሚያርስና የሚያለመልም በረከት ይሆናል፡፡ ወቀሳና ትችት የሚፈራ ሌሎችን ለመተቸትና ለመወቀስ ድፍረቱ አይኖረውም፡፡ ይህ ሰብዕና ደግሞ የአምባገነንነት አረም ተሰማምቶት ፍሬ የሚያፈራበት ምቹ ሜዳ ነው፡፡
በተለያዩ አጋጣሚዎች በተሳተፍኩባቸው የሙስሊም ጀመዐዎች ውስጥ ትችት እንደር ርችት አሰደንጋጭ መሆኑን ተመልክቻለው፡፡ ትልልቅ አጀንዳዎች ሳይቀሩ ትችትን የሚያሰተናግድ ቁመና ስላልገነባን ሳይታሹ የሚቀሩበት አጋጣሚ በርካታ ነው፡፡ በርካታ ሰራዎችን ጀምረን ማቆም ባህላችን እሰኪመስል ድረስ የምንበታተንበት አንዱ ምክኒያት ተቋማዊ ብልህነትን አለማዳበራችን ነው፡፡ ተቋማዊ ብልህነት የሚገነባት አንዱ ማዕቀፍ ለትችት፣ለቅሬታና ለወቀሳ በርን ክፍት በማድረግ ነው፡፡ ትችትና ወቀሳን መፍራት ከራስ ጋር ተመሳሳይ አመለካከትና አቋም ካለው፣ ከማይወቅሰንና ከማይተቸን ጋር ብቻ እንድንሰራና እንድንሰበሰብ ያሰገድደናል፡፡ ይህ ደግሞ ተቋማዉ ጥንካሬ በመሸርሸር ስራችንን የደቦ ያደርገዋል፡፡
 **ማህበረሰባዊ ትችት (social critics)**
ማህበረሰብ ከሚያስፈልጋቸው አካላት አንዱ የማህበረሰብ ሳይንቲስት ነው፡፡ የማህበረሰብ ሳይቲስት ለማህበረሰቡ ከሚያበረክታቸው አስተዋፅዖዎች አንዱ በማህበረሰቡ ውስጥ ያሉ ችግሮችን ነቅሶ በማውጣት፣ በመተቸትና በመወቀስ የሚመለከታቸው አካላት ማሰተካከያ እንዲያደርጉ መግፋትና መሞገት ነው፡፡ ማህበረሰባዊ ተቺዎች የማህበረሰቡ መሰታወቶች ናቸው፡፡ ጉድፉን ነቅሰው በማሳየት ራሱን እንዲያፀዳ ይገፋታል፡፡ ማህራዊ እድገት ሊመጣና ሊረጋገጥ የሚችለውም በዚህ ሂደት ውስጥ ማለት ሲቻል ነው፡፡ እንዳለመታደል ሆኖ  በሙስሊሙ ሰብስብ (ንቁ በሆነው) ማህረሰባዊ ትችት አቅራቢዎች እንደ ዋልጌ ይቆጠራሉ፡፡ በሙስሊሙ ማህረሰብ አንኳር አጀንዳ ዙሪያ ባሉ ልዩነቶች ጠንካራ ሀሳብ የሚያቀርብ የሰው ክብር የሚደፍር ተብሎ ይከሰሳል፡፡ ማህበራዊ ክብራችንን ባጣንበት ተጨባጭ ማህበራዊ ክብር ማጣታችን ሳያሳስበው  ክብሬ ተደፈረ የሚልን ራስ ወዳድ  እንጂ ሌላ ምን ሊባል ይቻላል? የሙስሊሙ ማህበራዊ ክብር ተደፈረ ብለው የሚጮሁ ጥቂቶች ናቸው፡፡ ሀሳቡ ሰለተተቸበት ብቻ ክብሬ ተደፈረ ብሎ የሚያኮርፈው፣ የበቀለ አለንጋ የሚመዘው፣ አግላይ እርምጃዎችን የሚወስደው ግን ሁልቆ መሳፍርት ነው፡፡ ምህዋሩ የራስ ክብር፣ የራስ ሀሳብ፣ የራስ ማንነት በሆነበት ተጨባጭ ማህበራዊ እድገት የማይታሰብ ነው፡፡ በዚህ  ትችትና ወቀሳ ጠል መሰተጋብራችን የምንገነባው ስስ ሰብዕናም በሀገር መሪነት ደረጃ ንቁ ተሳታፊ ሊያደርገን ይቀርና ትዳራችንን እንኳ የሚያፀና አይደለም፡፡ በግልፅ መነጋገር፣ መወቃቀስ፣ መተቻቸት ተፈርቶ በመጠባበቅና በመሸመጋገል ላይ የተመሰረተ መሰተጋብር ጥቂት ንፋስ ሲመጣ የሚናድ ይሆናል፡፡
በማህበራዊ ሚዲያ አብዘሀኛው ሙስሊም ተረትና ታሪክን ከማውራት ያለፈ በማህበረሰባዊ ትችት ውስጥ ሲሳተፍ የማይታየው ማህበረሰባዊ ትችት የሚያሰከትለውን መገለል በመፍራትና በተዛባ የዋልጌነት ትርጓሜ ነው ማለት ግነት ላይሆን ይችላል፡፡ አብዘሀኛው ሙስሊም ፀሀፊ እንደ አይስክሬም ነጋዴ ሁሉንም ለማሰደሰት የሚታትር፣ እንደ ፓስተር ምናባዊ ሰበካ የሚያበዛ፣ እንደ ዳንኤል ክብረት ተረት የሚወድ፣ እንደ አባባ ተስፋዬ በምክር ጀምሮ በምክር የሚጨርስ፣ እንደ ቺር ሊደርስ ጭብጨባና ፉጨት የሚያዘወትር፣ እንደ የመዋዕለ ህፃናት አሰተማሪ አነቃቂ ንግግር (motivational speech) የሚያበዛት ምክንያት ምን ይሆን? እነዚህ ዘርፎች አያስፈልጉም እያልኩ አይደለም፡፡ በችግር ለተከበበ ማህበረሰብ መሰል ተግባራት በማህበራዊ እድገቱ ላይ የሚኖራቸው ሚና ግን አናሳ ነው፡፡
Filed in: Amharic