>

ጠላፊው ጠርናፊው ደ.ም.ኢ.ት ወደ ሀገርቤት ገባ!! (ጌታቸው ሽፈራው)

ጠላፊው ጠርናፊው ደ.ም.ኢ.ት ወደ ሀገርቤት ገባ!!
ጌታቸው ሽፈራው
ደምህት የሚባለው ቡድን ወደ ሐገሩ ተመለሰ ተብሏል። የሚያሳዝነው ወደ ሐገር ቤት ሲመለሱ የመኪና አደጋ አጋጥሟቸዋል። ያሳዝናል!
የትግራይ ተቃዋሚ የሚባለው ደምህት አባላት አብዛኛዎቹ ታፍነው የተወሰዱ መሆናቸው የሚያውቅ ስንት ሰው ነው?
ሞላ አስግዶም ከድቶ ከመጣ በኋላ ከሞላ ጋር የተመለሱ የድርጅቱ አባላት የተወሰኑት ወደ ትግራይ ሲመለሱ ቀሪዎቹ “እንጠራችኋለን” ተብለው ወደአማራ እና ወደ ኦሮሚያ ክልል ሄደዋል። መጀመርያ እንደሚያቋቁሟቸው የሞላ አስግዶምን ስልክ ሰጥተው ያሰናበቷቸው ሲሆን ምንም ያደረጉላቸው እገዛ አልነበረም። አንድ የድሬዳዋ ልጅ ደግሞ ጎዳና ላይ ወድቆ ነበር። በ2008 ዓም በአንድ ሰው በኩል አፈላልጌ አግኝቸው “ሊቀመንበሩን ስልክ አያነሳልንም” ብሎኛል። አንድ የሰማያዊ ፓርቲ አባል ሲያግዘው እንደነበር አስታውሳለሁ።
አብዛኛዎቹ የደምህት ተዋጊዎች ለቀን ስራ ወደሁመራ እና ሱዳን በሄዱበት፣ እንዲሁም ወደ ስደት ሲሄዱ የተጠለፉ የአማራ እና የኦሮሞ ልጆች ናቸው። የደምህት ሰዎች ሀፍረት የላቸውም፣ ኤርትራ ውስጥ የሚገኙ የሌሎች ድርጅቶች ተዋጊዎችንም ይጠልፋሉ።
ደምህት ሰፊ የቃሪያና የቲማቲም እርሻ ነበረው። በጠረፉ ጤፍም ማላመድ ችሏል። የተጠለፉት የሌሎች ድርጅት አባላት በታጣቂ እያስጠበቀ የቀን ስራ ያሰራቸው ነበር። የመረራቸው የአማራ ወጣቶች ወደ አዲኃን እንምጣ ሲሉ “ቀን ጠብቁ” እያላቸው ደምህት ጋር ቆይተዋል። ይህ የሆነው የተጠለፉትም ቢሆን ወደሌላ ድርጅት እንዛወራለን ቢሉ በድርጅቶቹ  መካከል ችግር ስለሚፈጥርና ሻዕቢያም መሰል አሰራር ስለማይፈቅድላቸው ነው።
አንድ የግንቦት 7 አባል አስመራ ለህክምና ሄዶ ወደ ካምፕ ሲመለስ በመኪናቸው ተሳፍሮ  ከካምፑ ሲደርስ “ልውረድ” ሲላቸው አምብይ ብለውት፣ ከመኪና ዘሎ ወርዶ እንዳመለጣቸው አጫውቶኛል።  ኤርትራ ከነበሩት ቡድኖች መካከል የደምህትን ያህል ጠላፊ ቡድን አልነበረም።  ከአማራና ኦሮሞ ወጣቶች በተጨማሪ ማዕደን የሚቆፍሩ የትግራይ ወጣቶችም  የጠለፋ ሰለባ ነበሩ። የወልቃይት አማራዎችም በተመሳሳይ። ሙሽሮቹም አንድ ቀን ይናገሩ ይሆናል።
Filed in: Amharic