>

'....ይህ አሰራር የፕሬስ ነጻነትን የሚጋፋ ስለሆነ ሊታረም ይገባዋል።'' (አበበ ገላው)

”ይህ አሰራር የፕሬስ ነጻነትን የሚጋፋ ስለሆነ ሊታረም ይገባዋል።”

አበበ ገላው

 

ሰሞኑን በተለያዩ የሚድያ ተቋማት ላይ አሉታዊ የሆኑ ዘመቻዎች መጧጧፋቸው የፕሬስ ነጻነትን የሚፈታተን ክስተት ነው። የሚድያ ተቋማት የሚሰሩት ሁሉ ፍጹም ነው ብሎ ማለት ባይቻልም የተለያዩ ቡድኖች፣ የዘርና ያመለካከት ጎራዎችን ስሜት ለማርካት ፈጽሞ መንቀሳቀስ አይጠበቅባቸውም። ይህ ማለት ግን ተቋማቱ ለሚሰሩት ስራ ሃላፊነት እና ተጠያቂነት የለባቸውም ማለት አይደለም። ሲሳሳቱ መታረም ይገባቸዋል። ሃላፊነት የጎደለው ስራ ሲሰሩ ሊገሰጹ ይገባቸዋል።

ይሁንና የእርምት ጥያቄውም ይሁን ተግሳጹ ገደብ ያስፈልገዋል። ምክንያቱም ነጻና ገለልተኛ የሚድያ ተቋማትን መገንባትና ማሳደግ የሚቻለው የባለሙያው ነጻነት ሲረጋገጥ ብቻ ነው። ዛቻ፣ ስድብ፣ የጠላትነት ፍረጃ፣ እና ሌሎች የግለሰብና የተቋማትን ነጻነት የሚጋፉ ዘመቻዎች ከጥቅማቸው ጉዳታቸው ያመዝናል። በመሆኑም አሉታዊ ዘመቻዎችና ፍረጃዎችን ወደ ጎን ትቶ ወደ መነጋገርና መደማመጥ መሸጋገር የሚድያ ተቋማትን የበለጠ ለማጠናከር እገዛ ያደርጋል። 


ዛሬ ከሰፊ የፌስቡክ ዘመቻ በሁዋላ የብሮድካስት ባለስልጣን ቤቴልሄም ታፈሰንና LTVን ማስጠንቀቁንና ከአብን ሊቀመንበር ከዶ/ር ደሳለኝ ጫኔ ጋር ጋዜጠኛዋ ያደረገቸውን ቃለ መልልስ “አድሏዊ” በመሆኑ ከዩቲዩብ ላይ እንዲወርድ ማድረጉን ሰማን። ይህም ባለስልጣኑ ከተሰጠው ውስን ሃላፊነት አንጻር አጠያያቂ የሆነ እርምጃ ነው።


በእርግጥ ጥያቄ የተነሳበት ቃለ ምልልስ የተሻለ ሊሆን ይችል ነበር። ጋዜጠኛዋ እንግዳዋን ጠይቃ መልሱን ማስጨረስና ከስሜታዊ ሙግት ወጣ ባለ መንገድ ብታስተናግድና እንግዳውም ለጥያቄዎቹ የሚመጥኑ መልሶች ለመስጠት በቂ ዝግጅት አርጎ ቀርቦ ቢሆን ኖሮ ለሁሉም የተሻለ ይሆን ነበር። ይሁንና ባለስልጣኑ የሚድያ ውጤቶችን ገምጋሚ እና ኢዲተር መሆኑ ወደፊት ብዙም የሚያራምደው ይሆናል ብዬ አላምንም።
አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ የእርምትና የማስተካከያ እርምጃ መውሰድ የሚገባው ጣቢያው እንጂ ባለስልጣኑ አይደለም። ይህ አሰራር የፕሬስ ነጻነትን የሚጋፋ ስለሆነ ሊታረም ይገባዋል።

Filed in: Amharic