>
5:29 pm - Friday October 11, 6318

«እኔን እጎዳለሁ ብለህ  መሃል ሰፋሪውን አድማ አስተማርክ» (አቻምየለህ ታምሩ)

«እኔን እጎዳለሁ ብለህ  መሃል ሰፋሪውን አድማ አስተማርክ»
አቻምየለህ ታምሩ
ብላታ መርስዔ ኀዘን ወልደ ቂርቆስ በዘመን ታሪክ ትዝታቸው በርካታ ዘመን ተሻጋሪ ወጎችን  አስተምረውናል። ብላታ ካስተማሩን ዘመን ተሻጋሪ ወጎች መካከል ዛሬ ቤተ መንግሥት አካባቢ የተከሰተውን የወታደሮች አድማና ትቶት የሚያልፈውን ጠባሳ ከእቴጌ ጣይቱ የመጨረሻ ዘመን ጋር አያይዘው  በማውሳት ለትውልድ ያስቀሩት ታሪክ  አንዱ ነው።
ከዛሬ 108 ዓመታት በፊት በዳግማዊ ምኒልክ አልጋ ወራሽ በልጅ እያሱ ሞግዚትና እንደራሴ በራስ ቢትወደድ ተሰማ ናደውና በእቴጌ ጣይቱ መካከል የጦፈ የስልጣን  ፍክክር ተከስቶ ነበር። ራስ ተሰማ ከጦር ሚንስትሩ ከፊታውራሪ ሀብተ ጊዮርጊስ ዲነግዴ ጋር በመመካከር እቴጌ ጣይቱ የመንግሥት ሥልጣን ጨብጠው ሹም ሽር እያደረጉ የሚፈጽሙትን ተግባር ለማስቀረት ተስማሙ። ሆኖም አስቀድሞ ወገንን ማብዛትና ኃይልን ማደርጀት እንደሚያስፈልግ ስለተረዱ እንደራሴው አጋሮቻቸው ለሆኑት መኳንንት ጉዳዩን እያስጠኑ ይደራጁ ጀመር።
ራስ ቢትወደድ ተሰማ ናደው መኳንንቶችን  በስውር እያደራጁ  በእቴጌ ላይ ማስነሳታቸው  በመሰማቱ በሁለቱ መካከል የነበረው  የሥልጣን ትግል እየጸና መሄድ ጀመረ። መሃል ሰፋሪ የሚባለው የመንግሥት ጦርም  በእቴጌ ጣይቱ ላይ አድማ መቋጠር ያዘ። መሃል ሰፋሪ ማለት በቤተ መንግሥቱ በልዩ ልዩ የሥራ ክፍል ላይ የሚገኙት ሻለቆችና ሻምበሎች፤ በነርሱም ስር ያሉት ሹማምንትና ጭፍሮች  ናቸው። ከዚህ በተጨማሪ መሃል ሰፋሪ የተባለው ስም በየዳር አገር የሚገኘውን የመንግሥት ጦር ሁሉ የሚጨምር ነው። የአድማው አለማ ባጭሩ «እቴጌ በመንግሥት ሥራ ላይ አይግቡብን፤ እንደራሴው ማለትም ራስ ቢትወደድ ተሰማ ናደው ብቻ ያስተዳድሩን» የሚል ነበር። በዚህ ጊዜ የአድማው አፈጉባኤ ሆነው የተነሱት  የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመን  የመጨረሻው የውጭ ጉዳይ የነበሩት የደጃዝማች ዘውዴ ገብረ ሥላሴ አባት የአድዋው ደጃዝማች ገብረ ሥላሴ ባርያ ጋብርና  የዳግማዊ ምኒልክ የፍትሕ ሚንስትር የነበሩት የአፈ ንጉሥ ነሲቡ መስቀሎ ቦርጃ ልጅ የአብቹው ደጃዝማች ደምሰው ነሲቡ ነበሩ። ይሁን እንጂ በውስጠ መንገድ የአድማው መሪ እንደራሴው ራስ ቢትወደድ ተሰማ ናደው ነበሩ።
እቴጌ ጣይቱም በበኩላቸው  እየተካሄደባቸው የነበረውን  አድማ  ለማሳወቅ  በስውር አዲስ አበባ ከነበሩ ሌጋሲዮኖች ጋር  ደብዳቤ መጻጻፍ ጀመሩ።  የእቴጌ ደብዳቤ   መጻጻፍ  በመታወቁ የመሃል ሰፋሪው  አድማ ወደ ቁጣ ተለወጠ። ከዚህ በኋላ እቴጌ ጣይቱ የነገሩን መበላሸት ስለተመለከቱና ሥልጣን ለመልቀቅ ስለወሰኑ ራስ ቢትወደድ ተሰማንና የአድማው አፈ ጉባኤ የሆኑትን ሰዎች ወደ ቤተ መንግሥት አስጠሯቸው። እነርሱ ከፊታቸው ሲቀርቡላቸው ከልብ እያዘኑና እያለቀሱ የወቀሳ ናዳ አወረዱባቸው። ይልቁንም ራስ ቢትወደድ ተሰማ ናደውን ብዙ ነገር ተናግረው ከወቀሷቸው በኋላ ስማቸውን በነጠላ ጠርተው «ተሰማ እኔን እጎዳለሁ ብለህ ለመሃል ሰፋሪው  አድማ አስተማርከው፤ በኢትዮጵያ ላይ እሾህ ተከልክባት፤ ወደፊት አንተም ታገኘዋለህ» አሏቸው ይባላል።
የእቴጌ  «እኔን እጎዳለሁ ብለህ  ለመሃል ሰፋሪ  አድማ አስተማርክ»  የሚለው ምክር ዘመን ተሻጋሪ ነው። በዛሬው እለት በቤተ መንግሥት ዙሪያ የዚህ ዘመን መሃል ሰፋሪዎች አድማ መትተው እንደነበር ሰምተናል። ታሪክ ሁልጊዜ አሻራ ወይንም ጠባሳ ይተዋል። ዐቢህ አሕመድ  ከአድማው በኋላ በቴሌቭዥን ቀርቦ  ምንም እንዳልተፈጠረ አድርጎ በመናገር ከወታደሮቹ ጋር ፑሽ አፕ እየሰራ ፎቶ መነሳቱ ባይከፋም  የአድመኞቹ  ወታደሮች  ድርጊት ግን ለሌላው ወታደር አድማ  ወይንም አመጽ
ማስተማሩ የማይታበይ ሃቅ ነው።
ደርግ የተወለደው የኮንጎ ዘማቾች  የነበሩ ወታደሮች ሊሰጠን ይገባል ያሉትን የአገልግሎት  ክፍያ አስመልክቶ ከንጉሠ ነገሥቱ ውጭ ማንንም አናነጋግርም ብለው ቤተ መንግስት አስገድደው መግባት በመቻላቸውና ይህንን የተመለከቱ ሻለቆችና የበታች መኮንኖችም ተመሳሳይ እርምጃ ብናደርግ ወደ ሥልጣን እንመጣለን ብለው በተነሱ  አጥናፉዎች ነው።  የዛሬዎቹም አድመኛ ወታደሮች ቤተ መንግሥት የገቡት ከጠቅላይ ሚንስትሩ ውጭ ማንንም አናናግርም ብለው ነው። ከጠቅላይ ምኒስትሩ በታች አለን የሚሉትን  እሮሮ የሚሰማ ሰው  ታጥቶ ነው?
ዐቢይ  አሕመድ  የተፈጠረውን የአድመኛ ወታደሮች ተግባር ለሕዝብ ግንኙነት ፍጆታ  ሲል ቀላል አድርጎ ሊያቀርበው ቢሞክርም  ድንጊቱ ግን ባለፉት ስድስት ወራት ውስጥ  ከተፈጥሩ ከባድ  የፖለቲካ ክስተቶች መካከል  ቀዳሚው ነው። ስለሆነም ዳፋው ግን በቀላሉ ሊታይ የሚችል አይደለም።
ዐቢይ አሕመድ የዛሬውን አድማ ልክ እንደያኔው  ራስ ቢትወደድ ተሰማ ናደው አቅሎ  ቢመለከተውም  ዐቢይ  ራሱ በተደጋጋሚ ጊዜ እንደ ሞዴል  ስሙን የሚጠራውና ራስ  ቢትወደድ  ተሰማ ናደውም  በእንደራሴነት ያገለገሉት የነበረው  ልጅ እያሱ  ግን የተወገደው  ራስ ቢትወደ ተሰማ ናደው  ጉዳቱን ባለማየት እቴጌ ጣይቱን ለማስወገድ አድማ ያስተማሯቸው መሃል ሰፋሪዎች መሆናቸው መዘንጋት የለበትም። ስለሆነም  ለወታደሮቹ አድማ ያስተማሩት  የዛሬዎቹ ተሰማ ናደዎች ድርጊታቸው  ወደፊት ፍሬ አፍርቶ ብዙ ችግር ከመለቀሙ  በፊት የዛሬውን አድማ በጀርባ ሆነው የጠነሰሱት ተሰማ ናደዎች፤  አድማውን  ያደረጉት በተዋረድ ያሉ አመራሮች እና ወታደሮች የሚገባቸውም ቅጣት፣  ተግሳፅና  እርምት  መስጠት እንጂ  ከአድመኞቹ ጋር አብሮ ፑሽአፕ መስራት መፍትሔ ሊሆን አይችልም።
ባጭሩ የዛሬው ወታደሮች አድማ  ለምንም አላማ ይደረግ ለምን  እቴጌ እንዳሉት  የዛሬዎቹን መሃል ሰፋዎሪች ማለትም   በቤተ መንግሥቱ በልዩ ልዩ የሥራ ክፍል ላይ የሚገኙት ሻለቆችና ሻምበሎች፤ በነርሱም ስር ያሉት ሹማምንትና ጭፍሮች እንዲሁም መላውን መለዮ ለባሽ  ቤተ መንግሥት ቅጥር ግቢ ብቻ ሳይሆን ጠቅላይ ሚንስትሩ ጽሕፈት ቤት ድረስ ከነሙሉ ትጥቅ ሰተት ብሎ  መግባት የሚያስችል አድማ ማድረግ እንደሚቻል  ወታደሩን አስተምሮ አልፏል።
ገጣሚውም የዛሬ ድርጊት የነገን ተግባር ቁልፍ እንደያዘ  እንዲህ ሲል ቋጥሯል፤
ዘመን  ሲቀያየር የዛሬው ተሽሮ የነገው  ፊት ለፊት፣
ይመስለናል እንጂ ሁሉም ነገር ኅልፊት፣
ተመልሶ መጭ ነው ያለፈው ወደፊት፤
ትናንት ይመስለናል በሽኝት ተጉዟል፣
ግን መልሶ መጭ ነው የነገን ቁልፍ ይዟል።
የዛሬውን  ባለቀይ ኮፍያ ወታደሮች አድማም በታሪካችን  ውስጥ ካሳለፍናቸው  ጠባሳ ትተው ያለፉ  ወቅቶች  አኳያ ካልታየና  አድመኞቹና ከጀርባቸው ባለው አካል ላይ የማያዳግም እርምጃ  ሳይወሰድ  በሕዝብ ግንኙነት ስራ ብቻ ሊታለፍ ከተሞከረ  በቀ.ኃ.ሥ.  ዘመነ መንግሥት በ1966 ዓ.ም.  ተከስቶ   በቂ ትምህርት ሳይወሰድበት  የታለፈው የኮንጎ ዘማች ወታደሮች እንስቅስቃሴ  ያስከተለው የወታደር እብጠት ፍሬ  አፍርቶ በቅርቡ መስከረም 2 ቀን 1967 ዓ.ም ሲደገም ማየታችን አይቀሬ ነው።
Filed in: Amharic