>

ግጭት ስንት ቀን ይፈጃል…??  (አሰፋ ሀይሉ)

ግጭት ስንት ቀን ይፈጃል…?? 
አሰፋ ሀይሉ
ስለ ግጭቶች — ዓይነታቸው ፣ መንሥዔያቸው ፣ መፍትሄያቸው ! ! ! 
— MEDIATING CONFLICTS OF NEED, CREED, AND GREED
     (- Ira William Zartman)
ሰሞኑን በሃገራችን ግጭቶች በርክተዋል፡፡ በተለይ ደግሞ ብሔር-ተኮር የሆኑ አካባቢያዊ እንቅስቃሴዎችና ግጭቶች ወሬዎች ከዚህም ከዚያም ይሰማሉ፡፡ አሣዛኝ ዜናዎችም ይደመጣሉ፡፡ ይህ ሁሉ ግጭቶች – በተለይም ብሔርን-ተንተርሰው የሚነሱ – ግጭቶች አሳሳቢ ደረጃ ላይ እየሄዱ ለመምጣታቸው… ከሰው ህይወት መቀጠፍ.. ከዜጋ መሞት.. ከወገን መፈናቀል በላይ.. ከዚህ የበለጠ ማስረጃ አያሻውም፡፡ እና… ይህን ሁሉ ‹‹አላይም! አልሰማም! አልናገርም!›› ብሎ እንደዳር ተመልካች ቆሞ ማየት እንደ ዜጋ አያስችልም፡፡ ባህላችንም አይደለም፡፡ እና… ትንሽም ብትሆን… ‹‹ያለውን የሰጠ ንፉግ አይባልም›› ነውና.. እስቲ አንድ ሁለት ነገሮችን ጣል እናድርግ፡፡ እስቲ በቅድሚያ… ሰሞኑን የሶማሌና-ኦሮሞን ብሔረሰቦች መነሻ በማድረግ የተነሡ የታጠቁ ሰዎች/ቡድኖች ያደረሱትን ጥፋት፣ ግጭትና እልቂት አስመልክቶ… የቮይስ ኦፍ አሜሪካ የድረገጽ ዘጋቢ… አንዲትን በአካባቢው የተሰማሩ ተመራማሪና የልማት ፕሮጀክት አስተባባሪ ስትጠይቅ ስለአጠቃላይ የሃገራችን ሁኔታ ከሰጧት ምላሽ ብንጀምርስ??? — መልካም፡፡ እንዲህ ነበር ያሉት ምሁሩ፡-
‹‹የአስቸኳይ ጊዜ  አዋጁ በእርግጥ ተቃውሞዎችንና ከዚያ ጋር ተያይዘው የሚቀሰቀሱ የአመፅ ተግባራትን አስቁሟል፡፡ ነገር ግን በዚያው ልክም በሃገሪቱ — በተለይ ተቃውሞዎችን ባስተናገዱ አካባቢዎች — መሣሪያ በታጠቁ ሰዎች የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች እየተበራከቱ መጥተዋል… በኢትዮጵያ እየታየ ያለው ብሔር-ተኮር የታጠቁ አንጃዎች መበራከት ሲታይ… እ.ኤ.አ. ከ1997 {ከ1990} ዓ.ም. ወዲህ ከፍተኛውን መጠን አሣይቷል… በእርግጥም በተለይ … በቀደምት ጊዜያት ከተወሰዱ መረጃዎች አንፃር ሲታይ.. ነገሩ በጣም.. በጣም ከፍተኛ ሆኖ ተገኝቷል፡፡››
— ዶ/ር ማርጎዝ ፒኖድ፤ በአፍሪካ በመሣሪያ የታገዙ ግጭቶች ተመራማሪ (የአርምድ ኮንፍሊክት ሎኬሽን ኤንድ ኢቬንት ዴታ ፕሮጀክት አስተባባሪ)፤ ለቪኦኤ አፍሪካ የድረገጽ በኢትዮጵያ ኦሮሞ-ሶማሊ ግጭቶችን አስመልክቶ ለቪኦኤ አፍሪካ የድረገጽ የዜና ማሰራጫ ከሰጡት ቃለምልልስ፡፡
በእርግጥ የሃገራችን ሁኔታና እያመራንበት ያለነው መዳረሻ ያሳስባል፡፡ ግጭት… በተለይም አስቀያሚ ዓይነት ግጭት ደጋግሞ ሰለባው እያደረገን ነው፡፡ እና ‹‹ግጭት››ን ለማስቀረት ስንነሳ… በቅድሚያ እና በመሰረታዊነት… ጥቂት ስለ ‹‹ግጭት›› ማሰብ.. መነጋገርና መወያየት የግድ ሊለን ደርሧል፡፡ እና እስቲ ካመጣው አይቀር በሰዎች ዘንድ ‹‹ግጭት›› ምንድነው?? በግለሰብስ?? እኔ ግጭትን እንዴት ነው የማየው? ሌላውስ? ብሎ መጠየቅ፣ መጠያየቅ ሳይበጀን አይቀርም መሠል፡፡
በነገራችን ላይ ብዙዎቻችን ግጭትን እንደ ትልቅ መቅሰፍት ስንቆጥር እንታያለን፡፡ ነገር ግን ብዙዎች ከሚያስቡት በተቃራኒው.. ግጭት አውሬያዊ አይደለም፡፡ ግጭት ሰብዓዊም ነው፡፡ ማለቴ ‹‹ሰዋዊ›› — በእኛ በሰዎች ማህበራዊ ግንኙነት ሊፈጠር የሚችል ብልጭታ ነው..፡፡ እና መጋጨት ሰዋዊ ነው፡፡ ማህበራዊ ኑሮ እስካለ ድረስም.. አንድ ሰው ከሌላው ሰው ጋር መገናኘቱ እስካልቀረ ድረስም… ከሰው ልጅ ጋር የሚኖር ነው — ግጭት፡፡ ጥንትም ዛሬም ወደፊትም፡፡ አባቶቻችን ሲናገሩ ‹‹እግር እንኳ እርስ በርሱ ይጋጫል›› ይላሉ፡፡ ይህ ከኑሮ የተቀሰመ ጥበብ ነው፡፡ እውነትም ነው፡፡ ፖዘቲቭና ኔጌቲቭ ሲጋጩም አይደል የማናቸውም ኃይል ምንጭ የሚሆኑት? ኤሌክትሪክ የሚፈጥሩት? እና ግጭት ተፈጥሯዊ ነው፡፡
ግን ግጭት ከግጭትነቱ አልፎ ወደሌላ የጉዳት ደረጃ እንዳይሸጋገር መከላከል ያሻል፡፡ ገና ብልጭ እንዳለ፤ ምልክቱ እንደታየ፤ ማስቆም፣ ማምከን፣ ማጥፋት ያስፈልጋል፡፡ አሊያ.. የግጭትን ብልጭታ… ካልተጠነቀቁት.. ተረባርበው ካላስቆሙት.. ሰደድ እሳት ይሆንና ሃገር ምድሩን ያጠፋል፤ ነፍስ ያጠፋል፣ ነፍጥ ያማዝዛል፣ ቁስል ይፈጥራል፣ ቁርሾ ያረግዛል፣ በቀልን ይወልዳል፣ ደም ያፋስሳል፡፡ እና ግጭት ይኖራል፡፡ ይከሰታል፡፡ ግጭት ግን ለፍሬ ሳይበቃ.. ማስቆም ያባት ነው፡፡ የግጭት ብልጭታዎች ቀስ በቀስ ሲቀጣጠሉ ዝም ብሎ ማየት — ያው ማባባስ ነው፡፡ ግጭትን ባጭሩ መግታት እየተቻለ ኋላ ተፋፍሞ ከተቀጣጠለ በኋላ አጠፋዋለሁ ብሎ የማሰቡ ከንቱ የዋህነት ደግሞ — ያ ደግሞ ሌላ ጉዳይ ነው፡፡ ‹‹ትንሿ ምላጭ፤ አገር ትላጭ›› ነው እሣት፡፡ እሣት ሲያቀጣጥል እያዩ ቆይ ካቃጠለ በኋላ አጠፋዋለሁ ማለት የዋህነትም ብቻ ሳይሆን አድካሚ ልፋት ነው፡፡
በግጭቶች አፈታት ላይ ዕድሜያቸውን ሙሉ ያሳለፉት… እጅግ በጣም በርካታ የዕድሜ ልክ የክብር ሽልማቶችን ያገኙት.. የቀድሞው የአሜሪካ ስቴት ዲፓርትመንት የግጭቶች አፈታትና ድርድሮች ጉዳዮች ከፍተኛ አማካሪ ፕሮፌሰር አይራ ዊሊያም ዛርትማን ግጭትን በአጭሩ ማስቆምን እና ግጭት ከተባባሰ በኋላ ማስቆምን እያነፃፀሩ ሲናገሩ እንዲህ ይላሉ፡-
‹‹ማንኛውንም ግጭት — አስቸጋሪ ፈተናዎች ቢኖሩትም — ገና በመነሻው ላይ እያለ መፍታት ይቻላል፡፡ ግጭቱ እየተከሰተ ሣለ ግን ባብዛኛው ሰሚ ጆሮዎች አይገኙም፡፡ ግጭቱ ካለፈ በኋላ ለመፍታት መሞከር ግን ብዙ ዕዳ፣ ብዙ ቁስል፣ ብዙ ችግር አለው፡፡››
— ዶ/ር ፕሮፌሰር አይራ ዊሊያም ዛርትማን፤ የጆን ሆፕኪንስ ፕሮፌሰር ኤሜሪተስ፤ የዓለማቀፉ የሰላምና የሠላምና ደህንነት ተቋም መሥራችና ዳይሬክተር፤ ‹‹ሚዲዬቲንግ ኮንፍሊክትስ ኦፍ ኒድ፣ ግሪድ፣ ኤንድ ክሪድ›› ከተሰኘ መጽሐፋቸው የተወሰደ፡፡
እና ‹‹ሣይቃጠል በቅጠል›› የሚል የአበው በጥበብ የተቃኘ ቃል እያለን… ከተቃጠለ በኋላ ለማጥፋት የምንዳክር አሳዛኝ ሕዝቦች ሆነናል፡፡ ትልቁ የዘመናትን ኪሳራ… ከቀደመው ስህተታችን አለመማራችን ሆኖብናል፡፡ አንዱ ጋር የተከሰተው ግጭት ሌላው ጋር ሲደገም እንጂ.. ሌላው ጋር እንዳይመጣ ስንከላከለው አንታይም፡፡ እና ችግራችን ‹‹ተያይዘን ዘፍ›› ዓይነት ነው፡፡ እዛው ላይ ደጋግመን እየዳከርን ተያይዘን ዘፍ!!!
በመሠረቱ እኮ የምንኖረው አብረን ነው፡፡ ስንኖር ግን ከጋራው እኛነታችን ጥላ ሥር… የየራሳችን ማንነትና ሰብዕና አለን፡፡ የየራሳችን ጎጆ፤ ገጆዋን የሚከልል የግቢም አጥር አለ፡፡ ጠበበ እንጂ የግቢ አጥር ራሱ እኮ ድንበር ነው፡፡ ድንበርተኞች ደግሞ ጎረቤታሞች፡፡ ጉርብትና የማህበራዊ ኑሮ አይነተኛውና ዋናው ገጽታ ነው፡፡ መለያየቱ.. መካለሉ.. መጎራበቱ.. አብሮ ባንድ ቀዬና ከተማ መኖሩ.. የግድ የግጭት መንሥዔ አይሆንም፡፡ አብሮ መኖርም፣ መጎራበትም እንዳለ ሁሉ ደግሞ… መጋጨትም ቢኖር.. ቅድም እንዳልነው… ያም ራሱ ብርቃችን አይደለም፡፡ ለምን?? ሰው ከሰው ጋር ሲኖር ከሚከሰቱ ነገሮች አንዱ ግጭት ነዋ!!! አሊያማ… ወንድማማቾቹ አቤልና ቃየል ሳይጣሉ ይኖሩ ነበር፡፡ እና ምን ለማለት ነው?? አብረን በመኖር ውስጥ… ሰላምም ግጭትም ለዘመናት አብረውን ኖረዋል፡፡ አብረውን ናቸው፡፡ ወደፊትም ይኖራሉ፡፡ ልክ አብሮ በሰላም መኖር እንዳለ ሁሉ፤ አብረን እየኖርን መጋጨትም ደግሞ አለ፡፡
ችግሩ የሚያለያይ ነገር መኖሩ… ወይም ለግጭት መንሥዔ የሚሆን ነገር መፈጠሩ አይለም፡፡ ያ ብርቅ አይደለም ብለናል፡፡ ነገር ግን ግጭቶችን እና የግጭት መንሥዔዎችን ፖለቲካዊ ቀለም ለመቀባት… ፖለቲካዊ ለዛ ለመስጠት… ፖለቲካዊ ለማድረግ መሞከር… ለድንበር ፖለቲካዊ ትርጉም መስጠት… የፖለቲካ ቅሬታን… የብሔር ልዩነትን… አጥርን.. ድንበርን.. ሁሉንም ነገር ፖለቲካዊ ቀለም… ሁሉንም ነገር ‹‹ብሔር-ነክ›› ትርጉምና ቀለም እየሰጡ ማራባት… ይህ… ይህ ነው ት ል ቁ   ች ግ ር — ነው የሚሉን እንግዲህ አንቱ የተሰኙ ምሁራን ጭምር፡፡
እስቲ ድንበርን ለአስተዳደርነቱ እንጂ ለፖለቲካ ፋይዳ አናውለው፣.. ብሔርን ለሰላምና ለሕዝቡ ጥቅም እንጂ ለፖለቲካ ማቀጣጠያነት አናውለው… የሚሉትን የኛኑ ፕሮፌሰር ፈቃዱ አዱኛ ከፊል ሃሳብና መፍትሄ… ከትልቅ አክብሮት ጋር… እንስማ፡-
‹‹ፓለቲከኞችን ጣልቃ ሳናስገባ… የአካባቢውን ሕዝቦች፣ ሽማግሌዎቹን፣ የኃይማኖት መሪዎቹን እና የመሣሠሉትን አንድ ላይ እናምጣቸው…፡፡ እነዚህ ሰዎች ግጭቱን እንዴት መፍታት እንደሚቻል መናገር ይችላሉ፤ ለግጭት መንሥዔ የሆነውን ነገር (ወይም ድንበር) ይናገራሉ፤… እና በቃ… የማናቸውም ድንበር ፖለቲካዊ ተደርጎ እንዳይታይ ማድረግ ሲቻል… ተጎራባቾቹ ሰዎች በመልካም ግንኙነት አብረው መኖር አይሣናቸውም፡፡ ሰዎቹ እኮ ግጭት እንዲኖር አይፈልጉም… በግጭቱ ዋነኛ ተጠቂዎቹ መልሰው ራሳቸው ናቸዋ፡፡… ስለዚህ ድንበር ለአስተዳደራዊ ጥቅም ብቻ አገልግሎ እንዲውል መደረግ አለበት፡፡ ድንበር አስተዳደራዊ ፍጆታና ዓላማ ያለው ነገር ነው እንጂ… በፍፁም.. በፍፁም.. ለፖለቲካ ዓላማ ማስፈፀሚያነት… ወይም ለፖለቲካ ማራመጃ.. መዋል የለበትም፡፡ የተጎራባቾችን ግጭት ለማስወገድ ከተፈለገ… ድንበር… ለብሔር አጀንዳዎች ማስፈፀሚያ ወይም ማራገቢያ መሆኑ ማክተም አለበት፡፡››
— ፕሮፌሰር ፍቃዱ አዱኛ፤ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሶሻል አንትሮፖሎጂ ፕሮፌሰር፤ ለቪኦኤ አፍሪካ የድረገጽ የዜና ማሰራጫ ከሰጡት ቃለምልልስ፡፡
ማስታወሻ፡- 
በቀጣይ ክፍል ባጭሩ ለማየት የምንሞክረው ደግሞ ፕሮፌሰር አይራ ዊሊያም ዛርትማን በ2001 ላይ እና በድጋሚ በ2015 ላይ የታተመ.. ‹‹Mediating Conflicts of Need, Greed and Creed›› ከሚል የጥናት ጽሑፋቸው ላይ የተገኘውን እሳቤ — እያዋዛን — ይሆናል፡፡ ፕሮፌሰር ዛርትማን በዓለም ላይ አሉ የተባሉ… ዕድሜ-ልካቸውን.. ከአፍሪካ እስከ ፍልስጥዔም… ከምስራቅ ቲሞር እስከ ኢትዮጵያ… ከኮሶቮ እስከ ሩዋንዳና ቡሩንዲ.. በበርካታ የዓለማችን ስፍራዎች ክሰተቶች ላይ ሁሉ ከፍተኛ ጥናትና ምርምር የሰሩም… ለሰላም መስፈንም ትልቅ ድርሻ ያበረከቱ አንቱ የተባሉ ቀደምት ምሁር ናቸው፡፡ በስተርጅና የጡረታ ዕድሜያቸው እንኳ… ደከመኝ ሳይሉ ስለግጭቶች እና ስለእርቀ-ሠላም.. ለምሳሌ እንደ ጆን ሆፕኪንስ፣ ኦክስፎርድ፣ ፖል ኒቼ፣ ዬል፣ ሣውዝ ካሮላይና፣ ወዘተ ወዘተ ከመሣሠሉት ታላላቅ የዓለማችን ታላላቅ የትምህርት ተቋማት ጋር ሁሉ በክብር እየተገኙ ምርምር ይሠራሉ፣ ያስተምራሉ፣ ያሳትማሉ፡፡ ከሁሉም የሙያዊ ዕውቀትና የክብር ዶክትሬቶችን አግኝተዋል፡፡ የዓለማቀፍ የግጭት አፈታትን ግጭቶችን በተመለከተ አንቱ የተሰኙት ምሁር በሃገራችንም ጨምሮ የሚገኘውን ዓለማቀፉን የፒስ ኤንድ ሰኪዩሪቲ ኢንስቲትዩት መስራችና ዳይሬክተር ናቸው፡፡ ‹ኮንፍሊክት ሪዞሉሽን› በከፍተኛ ትምህርት ካሪኩለም ተቀርፆ በየሃገሩ  እንዲሰራጭ ፋና ወጊ ድርሻ አላቸው፡፡
እና እኚህ ድንቅ ምሁር… ስለግጭቶች የሚሉትንና መፍትሔ ብለው የሚያስቀምጧቸውን ነጥቦች በቀጣይ ጽሑፌ እመለስበታለሁ፡፡ ለጊዜው ግን… ከጊዜና ከቦታ.. ከጉዳዩም ርዝመት እንፃር… አንባቢውን ላለማሰልቸት ስል…  ቸሩን ሁሉ እየተመኘሁ… መሰነባበትን መረጥኩ፡፡ ቻው፡፡
Filed in: Amharic