>

የተገነባውን መተማመን በግብዝነት እያፈረሰው ነው!!!  (ስዩም ተሾም)

የተገነባውን መተማመን በግብዝነት እያፈረሰው ነው!!!
 
 ስዩም ተሾም
የአንድ ብሔር ተወላጆችን ጥቅምና ተጠቃሚነትን የማረጋገጥ ዓላማ ይዞ ወጣቶችን በወገንተኝነትና ተበዳይነት ስሜት እየኮረኮሩ መጋለብ ቀላል ነው፡፡ ነገር ግን ኢትዮጵያ ውስጥ በዚህ መልኩ ብዙ አመት ብትጋልብ የፖለቲካ ስልጣን መቆጣጠር አትችልም፡፡ ለውጥ ማቀንቀን ብቻ ሳይሆን የሌላ ብሔር ተወላጆች አብረውህ ባያቀነቅኑ እንኳን ለውጡን ለመቀበል ዝግጁ መሆን አለባቸው፡፡ በመሆኑም በተለያዩ ብሔር ተወላጆች መካከል የመተማመንና ትብብር መንፈስ መፍጠር የግድ አስፈላጊ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ ለውጡ ከአንድ ወገን የበላይነት ይልቅ እኩልነትና ፍትሃዊ ተጠቃሚነትን ዓላማ ያደረገ እንደሆነ ያለመታከት በመናገርና በማስረፅ በሌሎች ዘንድ ተቀባይነት እንዲያገኝ ማስቻል ይጠይቃል፡፡ በዚህ ረገድ ከኦቦ ለማ እና ዶ/ር አብይ በስተቀር እዚህ ግባ የሚባል አስተዋፅዖ ያበረከተ የኦሮሞ ልሂቅ ማግኘት ከባድ ነው፡፡
በተለይ ደግሞ ኢ/ር #ታከለ_ኡማ ወደ ስልጣን ከመጡበት እለት አንስቶ ይህን በስንት መከራ የተገነባውን የአብሮነትና የመተባበር መንፈስ በመሸርሸር ረገድ ከፍተኛ ጉዳት አድርሰዋል፡፡ ከዚያን ግዜ ጀምሮ በስንት ትግል የተገነባው የመግባባትና መተማመን መንፈስ በከፍተኛ ፍጥነት እየተሸረሸረ መጥቷል፡፡ በአንፃሩ ቀድሞ የነበረው የጥርጣሬና መጠላለፍ አባዜ በከፍተኛ ፍጥነት እያቆጠቆጠ ይገኛል፡፡ ለራሳችን ደጋግመን የነገርነው ውሸት ሺህ ግዜ በሚዲያ ቢያሽሞነሙኑት እውነት አይሆንም፡፡ ዛሬ የሁሉም ዓይንና ጆሮ #አዲስ_አበባ ላይ ነው፡፡ ለራሳችሁ የነገራችሁትን ውሸት ትታችሁ እውነታን መጋፈጥ አለባችሁ፡፡ አዲስ አበባ ውስጥ እየተደረገ ያለው ነገር ላለፉት 27 አመታት ሲደረግ ከነበረው ጋር ተመሣሣይ ነው፡፡ እባካችሁ በስንት መከራ የተገነባውን የመተማመን መንፈስ በአጉል ግብዝነት አታፍርሱት?!
Filed in: Amharic