አሰፋ ሀይሉ
* ድሮም፣ ዘንድሮም፣ አሁንም፣ ወደፊትም – ኑሮም፣ ጉልትም፣ ማጀትም፣ ጣሪያም፣ ግድግዳም… ያው ሆነው ይቀጥላሉ፡፡ የዚህ “አፍአዊ” የሆነና “ከራሴ-በቀር!” ለሌላው “ምንተዳዬ” የሚለው አምልኮተ-እኔነት እየነገሠበት የመጣው ትውልድም “ባለ-ዲግሪው-ጦጣ!” እንደሆነ እያጨበጨበ የወደፊቱን ጉዞ ይቀጥላል!!
የኢትዮጵያ ሕዝብ በዓለም ተደጋግሞ እንደሚነገረው “ለዕለት-ጉርሱ-የሚበቃ-ኑሮ” (“Self-subsistence-living”) ሲገፋ የኖረ ሕዝብ ብቻ አይደለም፡፡ ከራሱ የዕለት ጉርስ አልፎም ለገበያ አውጥቶ ሲገበያይ የኖረ የሺህ ዓመታት የመገበያየት ባህልን ያዳበረ – “people with thousands of years of commercial exchanging culture” ያለው – ሕዝብ ነው፡፡ ያም ማለት ትርፋማ ለሆነ ሕይወት የሚንቀሳቀስና ኑሮውን ከሌሎች ጋር ተባብሮ ለማሻሻል የሚጣጣር ሕዝብ ነው ማለት ነው ሕዝባችን፡፡
የኢትዮጵያ ሕዝብ ከትምባሆ እስከ እንቁላል፣ ከዶሮ እስከ ሸንኮራ፣ ከእህል እስከ ጥጥ፣ ከቡና እስከ ሱፍ፣ ከኮረሪማ እስከ ጥቁር አዝሙድ፣ ከትርንጎ እስከ ጊሽጣ፣ ከማር እስከ ቃርያ…. ሁሉን በያይነቱ እያመረተ… ከጥንት ዘመነ ጋርዮሽ እስከ አሁኑ እስካለንበት ዘመን ከልጅ እስካዋቂው ሲገበያይ የኖረ፣ ስለመገበያየት ጥቅም ጠንቀቆ የሚገነዘብ፣ በግልፅ ገበያ ዋጋ ተምኖ በዋጋ የመገበያየት የዘመናት ባህል ያለው ሕዝብ ነው – የኢትዮጵያ ሕዝብ፡፡ ሴቱም ወንዱም፣ ወጣቱም አዛውንቱም ዕድሜ ፆታ ሳይወስነው ያለችውን፣ ከዕለት ጉርሱ የተረፈችውን ይገበያያል ሀበሻ፡፡
ይህን እርስ በርሱ ከየጓሮው ያለችውን ይዞ በየአጥቢያው ጉልት ቀን ቆጥሮ፣ ዋጋ ተምኖ፣ ከወገኑ ጋር ተሳስቦና አቅም ለክቶ የሚገበያይ ድፍን የሀበሻ ህዝብ – ወደ ዘመናዊ ግብይት የሚያሸጋግረው (“streamline” የሚያደርገው) የተማረ ኃይል፣ ህዝባዊ ይሉኝታ ያለው ዘመናዊ ተቋም፣ ለህዝቡ ለወገኑ የሚያስብና ኑሮውን ለማሳደግ የሚጨነቅ – ታላቅ ራዕይን የሰነቀ እውነተኛ ለሕዝብ ደራሽ የሆነ፣ እውነተኛ ዕውቀትና ልቀትን ያነገበ – በየገበያው በፀሐይ ላይ ተሰጥተው አንድና ሁለት መደብ ድንችና ቃሪያ ጎልተው ተጎልተው በፀሐይ ሲንቃቁ ለሚውሎ ወገኖቻችን ቅን አሳቢ የሆነ – እውነተኛ ሀገራዊ፣ ወገናዊ፣ ትውልዳዊ የንግድና የግብይት ሥርዓት በዚህች ምድር ሲመላለስ አላየንም፡፡ እስካሁን አልታየም፡፡ ለወደፊቱም እንጃ፡፡
በተለይ በተለይ… እና ከምንም በላይ… ይሄን ከሰሜን እስከ ደቡብ – ከምስራቅ እስከ ምዕራብ – ዕድሜ ሳይገድበው – ሕዝባችን በየጉልቱ ተሰጥቶ እየዋለ ያለችውን ሽንኩርትም ሆነች ቃሪያ እያወጣ ሲገበያይ – “አለሁልህ! መጣሁልህ!” ብሎ ከጎኑ እያቀፈ-እየደገፈ፣ ጥሪትና ዕውቀት እያስተባበረ የሚያበረታውና ወደተሻለ ትርፋማ የሥኬት ኑሮ ሊያደርሰው የሚችል ወገን-ወዳድ የተማረ ኃይል፣ ከራሱ የግል ደመወዝና ኑሮ፣ ሥልጣንና ከበሬታ ከመጨነቅ ለአፍታ ወጣ ብሎ ለዚህ በቃሪያና በርበሬ፣ በኑሮና በሐሩር፣ በብዝበዛና በቁር ተጠብሶ ለኖረው እና ላኖረው ወገኑ የሚያስብ፣ የሚተጋ፣ የሚጨነቅ፣ የሚሣሣ፣ የሚያዝን ሀበሻዊ ትውልድ የመመናመኑ ሃቅ – ላሰበው ሁሉ እንደ ኮሶ ይመርራል፡፡
ህዝባችን ከድሮ እስከ ዘንድሮ ከወሬ የዘለለ ጠብ የሚል ነገር ያላመጡ አያሌ “አለሁልህ፣ መጣሁልህ” ባዮችን አስተናግዷል – ከድሮ እስከ ዘንድሮ፡፡ ይህ በየማጀቱ ወገቡን ጠበቅ፣ አንጀቱን እስር አድርጎ የሚኖረው ምስኪኑ ሕዝባችን – በእነዚህ ሁሉ “አለሁልህ፣ መጣሁልህ” ባይ ትውልዶች ያተረፈው አንዳች ጠብ የሚል ለውጥ የለም፡፡ ይኸው በመዲናችን ሣይቀር አዳሜ ለመኪና ሲጋፋ እየረጋገጠ የሚያልፈው – በየትም ቢኬድ እንዲሁ ለእርግጫ ቅርብ ሆኖ ነው የሚኖረው ሕዝባችን፡፡
ምስኪኑ ሕዝባችን – ድሮም፣ ዘንድሮም – ትውልዱ ከጊዜ ወደጊዜ የህዝቡን ኑሮ አይቶ ለማሻሻልና ለማገዝ ከመጣጣር ይልቅ – የግል ኑሮ ጥማቱን ለማርካት፣ የቁስ ረሃቡን ለማስታገስ፣ የገንዘብ አምሮቱን ለመሙላት፣ የዕለት ከርሱን ለመሙላት በሚሯሯጥ ትውልድ ሀገር ምድሩ ከመሞላቱ የተነሣ – ይኸው ድሮም ሆነ ዘንድሮ አልሞት-ባይ ተፍጨርጫሪ የቋፍ ተጓዥ ሕዝብ ሆኖ ቀርቷል፡፡
ከጊዜ ወደ ጊዜ በዚህች ሀገር ላይ የሚፈጠር ትውልድ ሁሉ – የገዛ ሕዝቡን፣ ይህን እልፍ አዕላፍ የሆነውን ምስኪን ሕዝቡን ጥረት አይቶ – የሕዝቡን የሚለበልብ ኑሮ፣ እንደሚጥሚጣ የሚፋጅ ህይወት፣ አቃጣይና አንገብጋቢ የኑሮ ደረጃውንና ጉስቁልናውን ለማሻሻልና ቀና ለማድረግ ከመጣር ይልቅ – ሕዝቡን እንደቃሪያ ስንግ እየሰነገ – በሕዝቡ አላዋቂነትና ድህነት ለመክበር የሚፈልግ – ለህዝቡ ብሶትና መፍጨርጨር አንዳችም የእኔነት ስሜት የማይሰጠው – ትውልድ እየሆነ እንደመጣ – ምንም መስካሪ አያስፈልገውም፡፡
ትውልዱ (“ኬሪዳሽ ጄነሬሽኑ”) በእዚሁ ዓይነት መልኩ ለመጪዎቹም ዓመታት – “ስለ ሰው ፤ ቀድጄ ልልበሰው!” እያለ – የዕለት ኑሮውን ብቻ እያሣደደ – ከርሱንና ነዳጁን እየሞላ – “ቅዱስ ገብርዔል ተከተለኝ!” እያለ – የጀመረውን ራስ-ቢትወደዳዊ “የብቻ-ጉዞ” ከቀጠለ – እነዚህ ባለቻቸው አቅም ከድሮ እስከ ዘንድሮ ከጉሮሮአቸው አልፈው ለሌላው ጉሮሮ በሚዛን እየተገበያዩ ሲወተረተሩ የኖሩ ወገኖቻችን – በዚህችው የአልሞት-ባይ-ተጋዳይ ኑሮአቸው መሐል ከዘመን ወደ ዘመን እንደቃሪያ እንደተሰነጉ መኖራቸውን እንደሚቀጥሉ ምንም ጥርጥር የለውም፡፡
ለሕዝባችን ድሮም፣ ዘንድሮም፣ አሁንም፣ ወደፊትም – ኑሮም፣ ጉልትም፣ ማጀትም፣ ጣሪያም፣ ግድግዳም… ያው ሆነው ይቀጥላሉ፡፡ የዚህ “አፍአዊ” የሆነና “ከራሴ-በቀር!” ለሌላው “ምንተዳዬ” የሚለው አምልኮተ-እኔነት እየነገሠበት የመጣው ትውልድም “ባለ-ዲግሪው-ጦጣ!” እንደሆነ እያጨበጨበ የወደፊቱን ጉዞ ይቀጥላል፡፡ የወደፊቱ ዘመን ባለሥልጣናት፣ የዚህ ትውልድ መሪዎች፣ የነገ አገር ተረካቢዎችስ – ይቺን ሚጥሚጣ ቃሪያ የሆነች… አንገብጋቢዋን የወገናቸውን ኑሮ… እንደቃሪያ በወሬ ሰንገው የሚያወራርዱ ተስፈኛ ዝሆኖች (“የቀን-ጅቦች”) ላለመሆናቸው… ምን ተስፋ-ሰጪ ዋስትና ይኖራል??? – አምላክ ቅን ቅኑን ያመላክታቸው ማለቱ ይሻላል እንጂ፡፡
ይህን የህዝባችንን “ባለህበት እርገጥ” “እንቆቆ-እንቆቆ” የሚል ኑሮ – ላሰበው፣ ላስተዋለው፣ ላሰላሰለው፣ ከልቡ ለመረመረው ሁሉ – በየአደባባዩ፣ በየጉልቱ፣ በየመንገዱ፣ ጧት-ማታ በየማጀቱ ላላፊ አግዳሚው የሚታየው እውነታ፣ የሚሰማው የኑሮ ሃቅ፣ በወገኖቻችን ፊት ላይ በየመንገዱ በየጉልቱ የሚታየው “የትውልድ ያለህ…!” ጥሪ፣ የወገን ቃል-አልባ የወቀሣ መልዕክት – ያማል፡፡ ልብን ይፈነቅላል፡፡ በቁጭት ያንገበግባል፡፡ በኃፍረት ምሬት ሃሞትን ያንገፈግፋል፡፡ አንገትን ብቻ ሣይሆን – ቅስም ላለውም ትውልድ – ቅስምን ያሰብራል፡፡ ፈጣሪ ትውልዳችንን ይባርክ፡፡ አሜን፡፡