>
7:21 am - Tuesday July 5, 2022

ይድረስ ለምታውቀኝ... ለማውቅህ ወንድሜ "እሞታለሁ..." አትበል! (ሰለሞን ለማ ገመቹ)

ይድረስ ለምታውቀኝ… ለማውቅህ ወንድሜ
“እሞታለሁ…” አትበል!
ሰለሞን ለማ ገመቹ
 ያኔ ዕንኳን “ዘብ ይቁም! ሁሉም ለሃገሩ…” ተብሎ ስንቶቹ እንደቆሙብን እና እንዳስቆሙብን… የምትዘነጋው አይመስለኝም። 
 
* ተው ወንድሜ ተው…!  ባልጠራው ነገር ላይ ነሸጥ አያርግህ!…  ለሁሉም ሲጠራና ሲለይለት ትደርስበታለህ… አንተ ማጥለያ አይደለህም!… አንተ ክሎሪን  አይደለህም!…
ለወገንህ …. ለሃገርህ ኢትዮጵያ ከዚህ በፊት ደምተሃል። ቆስለሃል። አካልህን ገብረሃል። … ይሄም ሁሉ ሆኖ የሃገርና የወገን አልኝታነትህ… በአላዋቂዎችና በኢትዮጵያዊነት ጠላቶች፤ እንደ ግለሰብ አገልጋይነት ተቆጥሮ ከሞቱት በላይ ቆመናል ከሚሉትም ሰዎች በታች እጅግ በጣም ተዋርደህ! ተሸማቀህና ተደብቀህ… እንድትኖር ተፈርዶብሃል….
ያም ቢሆን አንተ ለእናት ሃገር  እና ለኢትዮጵያውያን ሁለንተናዊ ነፃነትና ክብር እንጂ ለግለሰብ ለመሞት ሸነጥ… የሚያደርግህ አይደለህም። ..
 ያኔ ዕንኳን “ዘብ ይቁም! ሁሉም ለሃገሩ…” ተብሎ ስንቶቹ እንደቆሙብን እና እንዳስቆሙብን… የምትዘነጋው አይመስለኝም።
ተው ወንድሜ ተው…!  ባልጠራው ነገር ላይ ነሸጥ አያርግህ!…  ለሁሉም ሲጠራና ሲለይለት ትደርስበታለህ… አንተ ማጥለያ አይደለህም!… አንተ ክሎሪን  አይደለህም!…
 አንተ … በብዙ ሃገራዊ ህመም ማጥ ውስጥ አልፈህ… በራስህ ለወገን በጎ በማሰብ ደዌ እየተጠቃህ… ማንም ማንነትህን በጠራ መነፅሩ ሊመለከትልህ ሳይፈቅድ በፈጣሪ ድጋፍ እዚህ የደረስክ… መልካም አሣቢ… ግን ክፉዎች. እበላ ባዮች. ሴረኞች. አዋሻኪዎች… ሊነግዱብህ የሚፈልጉ… ሆዳቸውንም ሲሉ ንቀው የሚያልፉህ… መልካም ኢትዮጵያዊ ሰው ነህ።  እጅግ ንፁሕ የሆነ ክብረ-ሕሊና ባለቤት።
 እሳት የሚተፋ የጦር መሣሪያ… በእጅህ ሳለ፤ ወገኔን! ሃገሬን… አልዘርፍም! አልነጥቅም!… ብለህ በመወሰን… መራብ! መጠማትን! መታረዝን! ቤት አልባ መሆንና በይጎዳናውና በየወንዙ ዳር…ውዳቂ ላስቲክ ወጥረህ… የበለጠውን የስቃይና የሰቆቃ ንሮ መኖርን የመረጥክ።…. ይህ ሁሉ ሲሆን ማንም አባ ከና… ያላለህ…
እና ዛሬ… ግርግርና ሁካታ በበዛበት… ሁሉም ጥቅሙን እያሰበ የሌሎችንም የራሱንም ሰላም ለማደፈራረስ በሚዶልትበት…. ነጠርና ፀዳ ያለ ነገር ለመኖሩ ርግጠኛ መሆን በማይቻልበት… እንዴት “ልሙት…” ትላለህ?…
 ከአጠገብህ የነበሩ እነዛ የጀግና ሁሉ ጀግናዎች … ወጣት ተወርዋሪ ነብሮች… ሳተናዎች… የእሳት እራት ሆነው እንዲቀሩ የተደረገበትን ሁኔታዎች እነማን እንደፈጠሯቸው…  ዘወር ብለህ በዓይነ-ሕሊናህ ለመመልከት አትሞክርምን?…
 ተው ወንድሜ “እሞታለሁ…” አትበል!!!…   የደማህላትና የተጎሳቆልክላት ሃገር … ፤  ዛሬም ቢሆን ያ ልጇ ወደየት ነው ያለው? ብሎ ለፍለጋ የሚወጣ አንድ ሁለት እፍኝ ሰው መውለድ መፍጠር አልቻለችም።…
ተው ወንድሜ…. ተው!  … ግራ ቀኝ የቆመውን ቁርጠኛ የሃገርና የወገን ተፋላሚ ሳታይ… ሁሉም ዱታ… ነኝ በሚልበት በዚህ ድብልቅልቁ ነገር በበዛበት ጊዜ  …  እገሌን ማን ነክቶት… በሚል ራስህን ለሞት አታዘጋጅ….
ብታምንም ባታምንም …በዛሬይቱ ኢትዮጵያ  ወቅታዊ ሁኔታ፤ የአንተ መሞት… አያስፈልግም! …. እሞትለታለሁ የምትለው ሰው … ለራሱ ይሁን በሚል… ገና ሳይፈጠርም በፊት የሚያውቀው ያቆመለት ጠባቂ አለው… እና “እሞታለሁ …” አትበል… ሌሎች ዝርዝር ጉዳዮችን ሌላ ጊዜ … የሃገሬን ዘራፍ ባዮችና የወላድ መካኗን ኢትዮጵያ ርምጃ እያይሁ… ደግሞም አያስተዋልኩ….  እጽፍልሃለሁ።
 ጥቅምት ዘጠኝ ቀን ሁለት ሺኅ አሥራ አንድ ዓመተ ምህረት.
አዲስ አበባ ኢትዮጵያ.
Filed in: Amharic