>

…የንግግሩ ደረጃ በእጅጉ ቀለለብኝ (ከይኄይስ እውነቱ)

…የንግግሩ ደረጃ በእጅጉ ቀለለብኝ

 

ከይኄይስ እውነቱ

ጠ/ሚር ዐቢይ ለምውት ‹ሸንጓቸው› በጥያቄ እና መልስ መልክ የሰጡት ማብራሪያ ከይዘትም፣ ከመልእክትም ሆነ ከተአማኒነት አኳያ በእጅጉ ወርዶብኛል፡፡ በእኔ ሚዛንና አተያይ በእጅጉ ቀልሎብኛል፡፡ ለአብነት ያህል አንዳንዶቹን አለፍ አለፍ እያልኹ ለማንሳት እሞክራለኹ፡፡

1ኛ/ የአግአዚን ዐድማ በሚመለከት

  • ጠ/ሚሩ ዐድማው እንደተፈጸመ ወጥተው የተናገሩትና አሁን ለ‹ሸንጓቸው› ባቀረቡት ንግግር መካከል ልዩነት የታየው ባገር ውስጥም ሆነ በውጭ ከሚገኙ ኢትዮጵያውያን የቀረቡ የሰሉ ትችቶችን በማስተባበል ማረሚያ/ማስተካከያ ለማድረግ ነው ወይስ ትክክለኛ አቋማቸው? ኤታማዦር ሹሙ የት ነበር? በዐድማው የተሳተፈውን አጥፊ ኃይል ‹ሕፃናት› እያሉ ማቅለል ተገቢ ነው ወይ? ባለፉት 27 ዓመታት የተፈጸሙ ሰቆቃዎችን በግንባር ቀደምትነት የሕወሓት ቀኝ እጅ/ታማኝ መሣሪያ ሆኖ ሲያገለግል የቆየ ‹ሕገ ወጥ ኃይል› አይደለም ወይ? ዐድማውን በመሩት ብቻ ሳይሆን በተራው ተሳታፊዎች ላይ ምን ርምጃ ተወሰደ? የሚለው ለንግግራቸው ተአማኒነት ወሳኝ ነጥብ ይመስለኛል፡፡

 

  • ውስጤ እርር ድብን እያለ ተዝናንቼና እየሳቅኹ የተናገርኹት መንግሥታችን ሊፈርስ ነው ብሎ ‹‹…ከቡራዩ፣ ከሰበታ፣ ከለገጣፎ አርሶ አደር ወጣት ተደራጅቶ …ሊዋጋ፡፡›› እየመጣ መሆኑን ስለሰማሁ ነው፡፡ የሚለው ንግግር ጠ/ሚሩ የበሰለ አማካሪ እንደሌላቸው የሚያሳይ ነው፡፡ እዚህ ላይ ለማንሳት የፈልገኹት ቁም ነገር በአዲስ አበባ ዙሪያ የሚገኙ የኦሮሞ ወጣቶች ቤተመንግሥቱን ከዐድመኛ ‹ወታደሮች› ለመታደግ መንቀሳቀሰቸው እውነት ነው ሐሰት የሚለው አይደለም፡፡ ይልቁንም ጠ/ሚሩ በፖለቲካ ቋንቋ (አስበውበት ይሁን ዳኅፀ ልሳን) ለሕዝብ ያስተላለፉትን መልእክት ነው፡፡ ይኸውም የእኔ መሠረትና ታዳጊዎች የኦሮሞ ወገኖቼ ናቸው የሚል የዘረኝነት አንደምታ ያለው ይመስላል፡፡ በአብዛኛው ሕዝብ ተቀባይነት ያለው የአገር ‹መሪ› በተለይም የለውጥ ‹መሪ (ባገር ሰፍኖ ያለው የዘር ፖለቲካ፣የሚመራውም በዘር የተደራጅ ፓርቲ ቢሆን እንኳ) በየትኛውም ጊዜ አንድን ጎሣ/ነገድ ለይቶ በበጎም ሆነ በክፉ ማንሳት መጥፎ ምሳሌነትን ትቶ ስለሚያልፍ በይፋ የሚደረጉ ንግግሮች ብርቱ ጥንቃቄ ያሻቸዋል፡፡ ጠ/ሚሩ በሕዝብ ባይመረጡም እንኳን በዓለ ሲመታቸውን ተከትሎ በአብዛኛው ኢትዮጵያዊ ያገኙት ድጋፍ የእገሌ ጎሣ ‹መሪ› የሚያሰኛቸው አይደለምና፡፡ እንዲህ ዓይነቱ ንግግር ‹ጊዜው/ተራው የእኛ ነው› ለሚሉ ጎሣ አምላኪዎች የሚያስተላልፈውን መልእክት በጥንቃቄ መመርመር ይገባል፡፡

2ኛ/ የአገርን ሰላምና ፀጥታ የማስከበር ጉዳይ

ጠ/ሚሩ መንግሥት በአገራችን የሚታዩ ግጭቶችና የሰላም ችግሮች እንዲፈቱ 3ት መሠረታዊ አቅጣጫዎችን በመከተል እየሠራ ነው ሲሉ በገለጹበት ንግግራቸው በኦጋዴን፣ በቤንሻንጉል-ጉምዝ፣ በአዋሳ፣ በቡራዩ/አሸዋ ሜዳ ወዘተ. በዜጎች ላይ ዘርን መሠረት ያደረጉ ግጭቶች ያስከተሏቸው ግድያዎች፣ የአካል ጉድለት እና ከቤትና ንብረት በገፍ የመፈናቀል ክስተቶች አገዛዙ የቅድሚያ ጥንቃቄ ርምጃዎች ባለመውሰድ፣ ድርጊቶቹ ከተፈጸሙ በኋላም በሕግና ፀጥታ አስከባሪ ኃይሎች ቸልተኝነት፣ አንዳንዴም ሆን ተብሎ የችግሮቹ አካል በመሆን ጭምር እንደሆነ የጥቃቶቹ ሰለባዎችና አብዛኛው ሕዝብ የሚስማሙበት ሆኖ ሳለ በዚህ ረገድ ጠ/ሚሩ የሰጡት ማብራሪያ ግን ተአማኒነት የጎደለውና በማድበስበስ የተሞላ ሆኖ አግኝቼዋለሁ፡፡ የችግሩ ውስብስብነት ከጎሣ ፌዴራሊዝሙና ከጠንቀኛው የ‹ክልል› አወቃቀር ጋር የተያያዘ መሆኑ ቢታወቅም (ጉዳዩ የይስሙላ ሕገመንግሥቱን መቀየር/ማሻሻል ይጠይቃል – ይህ ደግሞ በጎሣ ፓርቲዎች የተዋቀረው ድርጅታቸው ፍላጎት አይደለም) ሰበብ ከማብዛት ይልቅ ሕግና ሥርዓት በማስከበሩ ረገድ ድክመት መኖሩን ቢያምኑ የተሻለ ነበር፡፡ የሕዝብንና በድርጅታቸውም ውስጥ ያሉ እውነተኛ የለውጥ ኃይሎችን በማስተባበር (የሚታመኑ ኃይሎችና  አቅሙም ከሌለ ለዚህ ዓላማ ሲባል ማደራጀት እየተቻለ) ሜዳ ላይ የሚፈነጩትን ሽብርተኞች (ወያኔ ትግሬና ተረፈ-ወያኔዎችን) በሕግ ቊጥጥር ሥር በማዋል መሠረታዊ የሰላምና ፀጥታ ችግሩን በእጅጉ መቀነስ/መቆጣጠር ሲቻል እልቂቱና መፈናቀሉ አሁንም ቀጥሏል፡፡ በቀጣይም ዋስትና የለም፡፡

3ኛ/ የካቢኔ አባላትን ስየማ በሚመለከት

ጠ/ሚሩ በቅርቡ የሾሟቸውን የካቢኔ አባላት ለመምረጥና ለማስፀደቅ እልህ አስጨራሽ ፈተና እንደነበረባቸው በንግግራቸው ገልጸዋል፡፡ ፍየል ወዲህ ቅዝምዝም ወዲያ እንዲሉ የሕዝብ ፍላጎትና የነውረና ድርጅታቸው ፍላጎት ለየቅል መሆኑን በሚገባ የሚያውቁት ይመስለኛል፡፡ ይህ ለኢትዮጵያ ሸክም የሆነ ድርጅት በአዋሳ ጉባኤው ለውጡ ‹‹ሕዝባዊ፣ሕገመንግሥታዊ እና ኢሕአዴጋዊ›› ነው ሲል የተለመደ ቅጥፈቱን በመግለጫው አሰምቷል፡፡ የለውጡ ባለቤት የኢትዮጵያ ሕዝብ መሆኑን ካመንን፣ ሕዝቡ የታገለው አገራችንና ሕዝቧን አደጋ ላይ የጣለውን የወያኔ የይስሙላ ‹ሕገመንግሥት› ለመቀየር እና ወያኔ/ኢሕአዴግ ከተባለ ፋሺስታዊ ድርጅት ባርነት በመላቀቅ ኢትዮጵያውያን በሙሉ ነፃነታቸው ተከብሮ በእኩልነት የሚታዩበትና ማኅበራዊ ፍትሕ የሰፈነበት ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለማምጣት ነው፡፡ በለውጡ ሂደት ውስጥ የነለማ ቡድን ዓይነተኛ አስተዋጽዖ ማድረጉ የታወቀና ተገቢው ዋጋ የተሰጠው ቢሆንም፣ በእነኚህ የለውጥ መሪዎች ሽፋን ነውረኛው ድርጅት በአገራችንና ሕዝቧ ሕይወት አሁንም አዛዥ ናዘዥ ሆኖ እንዲቀጥል ግን የሕዝብ ፍላጎት አይደለም፡፡ ስለሆነም ለውጡ ሕዝባዊ ግን ኢ-‹ሕገመንግሥታዊ› እና ኢ-ኢሕአዴጋዊ ነው፡፡ በመሆኑም የዐቢይ አገዘዝ ‹ሸንጎ›ም ሆነ ካቢኔ (በውስጣቸው ባሉ የጎሣ ፓርቲዎች የሚደረገው ሽኩቻ የስልቻ ቀልቀሎ ጉዳይ ሆኖ ነው የሚታየኝ – ኦዴፓ፣ አዴፓ፣ ደሕዴን፣ ሕወሓት ለሕዝቡ ምኑ ናቸው? ከነዚህ ዘረኛ ድርጅቶች ሴት/ወንድ የካቢኔ አባል ሆነ አልሆነ ትርጕሙ ምንድን ነው? ለውጡን ለራሳቸው ህልውና ማጽኛ እና ሥልጣን ማደላደያ እየተጠቀሙ ያሉ ነውረኛ ድርጅቶች በጉልበት ካልሆነ በስተቀር የኢትዮጵያ ሕዝብ ውክልና ስለሌላቸው ተሿሚው ጉደታ ሆነ አሸብር፣ ላታሞ ሆነ መረስ ምን ለወጥ ያመጣል? የኔ መንደር ሰው አልተሾመም ከሚባል ‹አብናዊ› ድንቁርና በስተቀር)፡፡ መሥፈርቱ ብቃትና ቅንነት እና  የሞራል ልዕልና እና ሕዝብን በማገልገል የሚገለጽ የአገር ፍቅር ከሆነ ኢትዮጵያዊ እስከሆነ ድረስ ምን ያሰጨንቀናል፡፡ ከዚህ ጎሣ በዝቷል፣ ከዚህ ጎሣ አንሷል እያልን ለጎሣ አማልክት እስከመቼ እንሰግዳለን?

ነገሩ የተበላሸው ኢትዮጵያ በለውጥ ማግስትም አገር አጥፊ የይስሙላ ‹ሕገመንግሥት›፣ የውሸት ፌዴራላዊ ሥርዓት እና በድን ‹ፓርላማ› በተከለ ድርጅት እንድትገዛ ሲፈረድባት እንጂ ሥርዓቱ ፕሬዚዳንታዊ ስላልሆነ ብቻ አይደለም፡፡ የይስሙላ ‹ሕገ መንግሥቱን› መቀየር አጥብቀን የምንጠይቀውም ከዘር ፖለቲካው መውጣቱ መሠረታዊው ጉዳይ ሆኖ፣ ሥርዓቱንም ፕሬዚዳንታዊ ለማድረግ ጭምር ነው፡፡

በዚህ ረገድ ጠ/ሚሩ የችግሩ ምንጭ የራሳቸው ድርጅት ሆኖ ሳለ ሕዝብ ካልፈለገኝ … በሚል ያሳዩት የብስጭት መንፈስ (frustration) ‹ሰዋዊ› መሆኑን ብንቀበልም ለቦታቸው የሚመጥን ሆኖ አልታየኝም፡፡

4ኛ/ በቁጥጥር ሥር የዋሉትን የአዲስ አበባ ወጣቶች በተመለከተ

ሥርዓቱ በሕግ ቁጥጥር ሥር የሚውሉ ሰዎችን አጣርቶ የመያዝ ሙያዊ ብቃት ብቃትም ሆነ ልምዱ  አለመኖሩን መግለጻቸው ተገቢና ተጨባጩን ሁኔታ የሚያሳይ መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ፤ ይህ ሥርዓታዊና ተቋማዊ ድክመት በሕገ ወጥ መንገድ የተያዙትን የአዲስ አበባ ወጣቶች ጉዳይ በየትኛውም መመዘኛ  ሕጋዊ አያደርግም፤ ትክክለኛና ምክንያታዊ ነው ብሎ ለመቀበልም ማረጋገጫ አይሆንም፡፡ ‹‹…እነዛ ሰዎች መጥተው ካነጋገሩኝና መረጃ ካገኘሁ በኋላ የተረጋገጠ ማስረጃ ያለባቸው ሰዎች ለፍርድ እንዲቀርቡ፤ አብዛኛው ግን ሳያውቅ በስሜት ትናንሽ ብሮ ወስዶ የተቀላቀለ ደግሞ የተወሰነ ሥልጠና ተሰጥቶት እንዲለቀቅ ነበር አቅጣጫ የተቀመጠው፡፡›› ‹‹በዚህ ሂደት የተጎዱ ወጣቶች፣ አለአግባብ የታሰሩ ወጣቶች 10ም÷ 50ም÷ 100ም ካሉ የለውጥ አካል አድርገው ማሰብ አለባቸው፡፡››

ከተያዙት ውስጥ አብዛኞቹ ጥፋተኞች እንዳልነበሩ ማመን አንድ ጉዳይ ሆኖ፤ ተጨባጭ ማስረጃ የተገኘባቸው ለፍርድ ይቅረቡ፤ ትንሽ ብር ተቀብለው ባለማወቅና በስሜት ጥፋት የፈጸሙት ሥልጠና ተሰጥቷቸው ይለቀቁ የሚለው ውሳኔ የዳኝነት አካላት ወይስ የጠ/ሚሩ? የንግግሩ መሠረታዊ ስህተት እዚህ ላይ ነው፡፡ ፖሊስ፣ ዐቃቤ ሕግም ሆኑ ፍርድቤቶች በሕግ የተሰጣቸውን ሥልጣንና ተግባር የሚያከናውኑት ጠ/ሚሩን እየጠየቁ ከሆነ ለወደፊቱም አደገኛ ምሳሌነትን (precedence) ትቶ የሚያልፍ ጉዳይ ይሆናል፡፡ በዚህ ረገድ የጠ/ሚሩ መግለጫ የተምታታና በተቃርኖ የተሞላ ብቻ ሳይሆን በወጣቶቹ ላይ የተወሰደው ርምጃ ፖለቲካዊ (ለዚህም በቂ ምክንያት ካለ) ከምንለው በቀር አንዳች ሕጋዊ መሠረት የለውም፡፡ አንድን በወንጀል የሚያስጠይቅ ጥፋት ተፈጽሞ ከተገኘና በማስረጃ ከተረጋገጠ ያስከስሳል/አያስከስስም የሚለው ጭብጥ ተመርምሮ የሚወሰነው በዐቃቤ ሕግ ሲሆን፤ ጉዳዩ ያስከስሳል ተብሎ ሥልጣን ባለው ፍ/ቤት ክስ ከተመሠረተ ደግሞ ‹‹ ባለማወቅ፣ በስሜታዊነት እና ትንሽ ገንዘብ ተቀብለው…›› የሚለው ጉዳይ ማስረጃን መዝኖ የጥፋተኝነትን ውሳኔ የሚያስተላልፈው የዳኝነት አካል ለቅጣት ማቅለያነት ከግምት ውስጥ የሚያስገባቸው ነጥቦች እንጂ የፌዴራሉ አስፈጻሚ አካላት የበላይ ኃላፊ ድርሻና ውሳኔም አይደለም፡፡

ስለሆነም አብዛኞቹ ወጣቶች ከመነሻው አላግባብ ነው የተያዙት ካልን ከወጣቶቹ ፈቃድ ውጭ ማናቸውም የመንግሥት አካል ሥልጠና የመስጠት መብት የለውም፡፡ ዓላማው ሥልጠና ቢሆን ኖሮ እንኳን ንጹሐኑን ማስረጃ ተገኝቶባቸዋል የተባሉትን ሌሎች ተጠርጣሪዎች (እነሱም ፍ/ቤት ቀርበው የጥፋተኝነት ውሳኔ እስኪተላለፍባቸው ሕገ መንግሥታዊ የንጽሕና ግምት ባለመብቶች በመሆናቸው) ሕይወታቸውን ላደጋ የሚያጋልጥ በርሃ መውሰዱ በሕግም በሞራልም ተቀባይነት የሌለው ርምጃ ነው፡፡

በዚህም መሠረት ጠ/ሚሩ በሕግ አስከባሪዎቻቸው የተፈጸመውን ነውር በመሸፈን እንደ ኃላፊዎቻቸው የተደራረበ ስህተት በመፈጸም ራስን በመከላከል/በማስተባበል ላይ የተመሠረተ አቋማቸው የሚያስተዛዝብና የቅንነት ገጽታቸውን በእጅጉ የሚያጠቁር ሆኖ አግኝቼዋለሁ፡፡ ጠ/ሚር ዐቢይ፤ ድፍረቱና ቅንነቱ ቢኖር ትክክለኛው ርምጃ ልጆቹን፣ ቤተሰቦቻቸውንና በዚህ አስነዋሪ ተግባር በተሳተፉ ጋጠ ወጥ ኃላፊዎችዎ ቅር የተሰኘውን የኢትዮጵያ ሕዝብ በይፋ ይቅርታ መጠየቅና ልጆቹንም መካሥ ይገባ ነበር፡፡ በሕግ ማስከበር ስም ጥፋት የፈጸሙ ባለሥልጣናትን ቢያንስ በሕግ እንዲጠየቁ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡

በሥርዓቱ፣ በተቋማቱና የሕግ ማስከበሩን ተግባር በሚመሩ ኃላፊዎች ድክመት በተፈጸመ የሕግ ጥሰት ሰለባ የሆኑትን ወጣቶች ‹‹በዚህ ሂደት የተጎዱ ወጣቶች፣ አለአግባብ የታሰሩ ወጣቶች 10ም÷ 50ም÷ 100ም ካሉ የለውጥ አካል አድርገው ማሰብ አለባቸው፡፡›› ብሎ ማፌዝ ከአንድ ሺ በላይ ወጣቶችን ነፃነት ማጣት ዋጋ አለመስጠት ነው፡፡ ነገ ተነገወዲያም ጋጠ ወጥና ደናቁርት ኃላፊ በሕግ ማስከበር ሽፋን ጥፋት ሲፈጽም ለለውጡ የሚከፈል መሥዋዕትነት ነው እያለ እንደማይቀልድብን ምን ዋስትና አለን?

Filed in: Amharic