>
5:13 pm - Tuesday April 19, 9110

የአዲስአበቤ የገደል ጫፍ እንቅልፍ! (ቴዎድሮስ ጸጋዬ - ከኢትዮጲስ ጋዜጣ)  

የአዲስአበቤ የገደል ጫፍ እንቅልፍ!
አንዲት ፍሬ መብቱን አሳልፎ የሰጠ ጎተራ ሙሉ መብቱን እንዳስረከበ ይቆጠራል!!!
ቴዎድሮስ ጸጋዬ – ከኢትዮጲስ ጋዜጣ  
1   መግቢያ
ያለሁት በአዲስአበቤና አዲስአበባ ላይ ከረበበው የዘውግ ፖለቲካ ቁማር በሚመነጭ ስጋትና፤ ነገ ላይ በኢትዮጵያዊ ብሄረተኞች (አዲስአበቤዎች) ቁርጠኛ ትግል እንደሚሰፍን በማምነው የእኩልነትና ነጻነት ተስፋ መሀል ተወጥሬ ነው፡፡
ባለፉት አስርት አመታት በኢትዮጵያዊ ብሄረተኝነትና የዝያ ርዕዮት አንድ የማታጠራጥር ፖለቲካዊ መሰረት በሆነች በአዲስአበባ ላይ የተሰራውን መዋቅራዊና ፖለቲካዊ ሸፍጥ እዚህ ላይ መዘርዘር አልሻም፤ ከማንም የማይሸሸግ ሀቅ ነውና፡፡ የምመዝዛቸው የሀሳብ ሰበዞችም ያንን “ህግ”ና መዋቅር ሰራሽ  ምስቅልቅል ከመገንዘብና አሁንም መባባሱን ከማወቅ ቀጥሎ ነው፡፡
2  ትርጓሜና አንድምታ
ለዚህች መጣጥፍ አላማ
2.1 አዲስአበቤ ማለት
ሀ) የአዲስአበባን ከተሜ Urbane ማንነት ህልውና የሚያውቅና ህጋዊና ህገመንግስታዊ ከለላ እንደሚያስፈልገው የሚያምን፣
ለ) የአዲስአበቤን ብሄር ተሻጋሪ Post Ethnic ስነልቡና የሚጋራ፣
ሐ) የአዲስአበባን እሴቶች እንደእሴቶቹ የሚቀበልና
መ) በአዲስአበቤነት ሊገለጽ የሚፈቅድ ማናቸውም ኢትዮጵያዊ ማለት ነው፡፡
ዝርዝሩ በሌሎች ጽሁፎች ይብራራል፡፡
2.2 እዚህ ላይ ስለአዲስአበባም ሆነ አዲስአበቤዎች ፍላጎት፣ ጥቅም፣ አጀንዳና ሁናቴ ሲወሳ ጸሀፊው በየማእዘናቱ ያሉትን አሁን በስራ ላይ ያለው የዘውግ መዋቅር ያገለላቸውን በርካታ ከተሞችና ነዋሪዎቻቸውን ታሳቢ ያደርጋል፡፡
2.3 የትኛውም የአዲስአበቤዎችና የአዲስአበባ ጥቅም የትኛውንም የኢትዮጵያውያንና የኢትዮጵያን ጥቅም በማናቸውም መልኩ እንደማይቀናቀንና እንደማይጻረር ጸሀፊው አጥብቆ ያምናል፡፡
2.4 ኢትዮጵያዊ ብሄረተኝነት ፍጹም ሰላማዊ በሆነ ቁርጠኛ ትግል እንጂ በመሸማቀቅና ዘውጌ ልሂቃንን በመለማመጥ ከተስፋይቱ ምድር ማለትም የዜግነትና እኩልነት ማርና ወተት ከሚፈስስባት ከነአኗ ኢትዮጵያ ሊደርስ እንደማይችልም ይረዳል፡፡
3   መዝለቅያ
ይኸውና የለውጥ ነፋስ እየነፈሰ ለመሆኑ ከተነገረ፣ በሚሊዮኖች ልብ ውስጥ የመሻል ተስፋ አድሮ ከነበረ ጊዜ እምብዛም አልሸሸም፡፡ በዚህ አጭር ጊዜ ውስጥ አዲስአበቤ ነገን በጉጉት ለመጠበቅ የሚበቁ የለውጥ ፍላጎት ተግባራዊ ምልክቶችን በማየቱ ተስፋ የመቋጠሩን ያክል፣ ስም ሊሰጣቸው ግራ የገቡት፣ መነሻቸውን ሊረዳቸው ያልቻለ… (ያልፈለገ) ከጠቅላይ ሚኒስትሩ አንድነት ሰባኪ አንደበት ጋር አብረው የማይሄዱ ውሳኔዎችና እርምጃዎችን  አስተውሏል፡፡ እንደሚታወቀው የለማ ቡድን ቅቡልነት የመነጨው ኢትዮጵያ ከተሰኘ ሀያል ስምና ሀሳብ ነው፡፡ የለማን ቡድን ለስልጣን ያበቃው ስለኢትዮጵያዊነት የማያወላውል አቋም እንዳለው በህዝብ ዘንድ መታመኑ መሰላል ሆኖት እንደሆነ ከቶ ጥርጥር የለውም፡፡ ቡድኑ ስልጣኑን የገዛው ኢትዮጵያዊ ብሄረተኝነት ያለውን ሰፊ ድጋፍና የፖለቲካ ካፒታል መንዝሮ ነው፡፡ ከዳር እዳር የሀገሪቱን ህዝብ ሰፊ ድጋፍና ልብ በማግኘት ረገድ የኖረበት የዘውግ ርዕዮት አንዲት ጋት ሊያራምደው ባልቻለ ነበር፡፡ ስለሆነም፣ የለማን ቡድን ተግባራት፣ ህግጋት፣ ውሳኔዎች፣ አፈጻጸምና አቅጣጫ የምንመዝነው በዚሁ እራሱ በመደረከው የኢትዮጵያዊነትና የአንድነት ትርክት መለክያ ሊሆን ግድ ነው፡፡ አዲስአበቤም ታድያ በዚሁ ልኬት  መሰረት ተስፋውን አወፍሮ ሲጠባበቅ፣ ሲፈጸሙ የሚታዘባቸውን የለማ ቡድን ተከታታይ የተሳሳቱ እርምጃዎች ለመቃወምም ሆነ ለመደገፍ ተቸግሮ፣ ንግግርና ተግባር አልተገናኝቶ ሆኖበት በመቁረጥና በመስጋት መሀል ተይዞ አለ፡፡ እነኚህ ለዘመናት ተርቧቸው የቆዩ የጠቅላይ ሚኒስትሩ “ኢትዮጵያ” ባይ ውብ ዲስኩሮች ቀላል የማይባል ቁጥር ባላቸው  ታጋይና አይታክቴ አዲስአበቤዎች የልቡና አይኖች ላይ የሚያናውዝ እንቅልፍ አስፍነዋል፡፡ አደገኛና አያዘልቄ የደህንነት ስሜትም ፈጥረዋል፡፡ እኔም ታድያ ነባራዊው ሀቅ ላይ ብርሃን እንዲበራ ይረዳ ዘንድ እነሆ አሳስባለሁ፡፡ የለማ ቡድንን እውነተኛ ገጽ ሊያይ የሚወድ ቢኖር፣ ንግግሮቻቸውን ትቶ  ተግባራቸውን ብቻ ያጢን፡፡ ተግባር ይበልጥ በግልጽና በጉላት ይናገራልና፡፡
4   “ለውጥ?”
 በዚህ አጭር ጊዜ የለውጥ መዝሙሮች በስፋት በአየሩ መናኘታቸው እውነት ነው፡፡ በተለይ እንዲያ በብረት እጅ ተጨምቆ ለተያዘ ህዝብ አንጻራዊ ፋታ የሰጡ፣ ሃሴትን የመገቡ፣ ተስፋን ያለመለሙ ጠንካራ አዎንታዊ ምልክቶች መታየታቸው አያከራክርም፡፡ ለውጡ ግን እገደል አፋፍ የደረሰችን አገር ከገደሉ ፈቀቅ ያደረገ ሳይሆን ገደሉን ፊት ለፊት ከማየት ለገደሉ ጀርባ ሰጥቶ ግን እዝያው የመቆም አይነት ነው፡፡ የአቋቋም እንጂ የቆምንበት ስፍራ ለውጥ የለም፡፡ ፊትን ያዞረ እንጂእግርን ያራመደ ለውጥ አልተመለከትንም፡፡ ምክንያቱም በለውጥ መዝሙሩ ውስጥ፣ መዋቅራዊ ለውጥን የሚያወሱ ስንኞች የሉበትም፡፡ በህዝብ ተሳትፎና  በገለልተኛ አካል መሪነት እውነተኛ ተቋማዊ ማሻሻያን የሚያመለክቱ መስመሮች አልተካተቱበትም፡፡ ኢህአዴግም የተሟላና ይፋ የፖለቲካ መስመር ለውጥ አጀንዳዎቹ አይደሉም ብቻ ሳይሆን፣ ዘንድሮም በጉባኤው ይህንን የቋንቋ የፌደራል መዋቅርና ህገመንግስት እንከን አልባና አማራጭ የለሽ እንደሆነ በማያሻሙ ቃላት አውጇል፡፡ ታድያ፣ አስተዳደራዊ መዋቅር ስለመቀየር የማይነጋገር፣ ህገመንግስት እንዲሻሻል ፍላጎትና መልካም ፈቃድ የሌለው፣ መሰረታዊ የፖለቲካና ኢኮኖሚ  ርዕዮት ለውጥ የማያደርግና ስር ተከል ተቋማዊ መሻሻልን ሊያከናውን የማይሻ ቡድን እንዴት አድርጎ መዋቅርና ስርአት ሰራሽ ችግሮችን እንዲፈታና አገሪቱን ከህልውና ስጋት በአስተማማኝ ደረጃ እንዲያርቃት ይጠበቃል? የለውጡ  ሂደት እውነተኛ ተቋማዊ መሻሻልን አስመልክቶ አገራዊ ምክክርና ስራ እስካላስጀመረ፣ አገሪቱን ወደከፋ የግጭት አበላ የደፈቃትን ህገመንግስት ስለማሻሻል የዜጎች ውይይት እንዲለኮስ እስካላደረገ፣ ብሄራዊ መግባባትን ለማስፈን ተደምጦ የሚጣል ዲስኩር ሳይሆን ተጨባጭ እርምጃ እስካልወሰደ፣ ለውጥ ተብሎ መጠራት ይበዛበታል፡፡ ሽግግርም ካለ የተሻገርነው ገደሉን ፊት ለፊት እያዩ በሰቀቀን ከማለቅ ፊትን አዙሮ ለገደሉ ጀርባ ሰጥቶ ወደማንቀላፋት ነው፡፡
5   የእንቅልፍ ኪኒኖች
 እንደዘውጌዎቹ ግምት አዲስአበባ የኢትዮጵያዊነት አስቸጋሪና የመጨረሻ ምሽግ ናት፡፡ በማናቸውም ስልትና ዘዴ (በጉልበትም በማባበልም፣ በይፋ አዋጅም በድብቅ ሴራም፣ በመድረክ ጨዋታም በጅምላ አፈሳም…) አዲስአበባን ማንበርከክ የዘውግ ርዕዮታቸውን ዘልአለማዊ የበላይነት ማረጋገጥ ነው፡፡ እንደእነርሱ ስሌት አዲስአበባን መቆጣጠር ኢትዮጵያዊ ብሄረተኝነትን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ግብአተ መሬቱን መፈጸም ነው፡፡ እኛ ታድያ፣ በተመረጡ ቃላት ቀምመው በጥቃቅን ተግባራት ለውሰው ያዘጋጁልንን የእንቅልፍ ኪኒኖች ሳንመጥንና ሳንመረምር በመውሰዳችን ድካም ተጭኖናል፡፡ እንቅልፍ ከብዶብናል፡፡ እነኚህ የተሳሳቱ እርምጃዎች አልፎ አልፎ ቆንጠጥ እያደረጉን ከምንባንነው በቀር አዲስአበቤዎች የገደል ጫፍ ላይ እንቅልፉ የተመቸን ይመስላል፡፡ ዘውገኞቹ የዳግማዊ ምኒሊክን ሀውልት ሊያፈርሱ መቃጣታቸውና የምናፈቅራትን ባንዲራ እየነቀሉ መጣላቸው  ትእግስታችንን ቢፈትነውም ቡራዩና ሌሎች አካባቢዎች  ላይ የተፈጸመው አሰቃቂ ፍጅት ሰላምና ፍትህ  ወዳድ መንፈሳችንን አቅለሽልሾት በብዛት ጎዳናውን ብናጥለቀልቅም፤ በርካታ የአብይ አስተዳደር ዝንፈቶችንና ግልጽ የህግ ጥሰቶችን ከእንቅልፋችን እንዳንናጠብ በምንፈጥራቸው ሰበብ አስባብ እየተከለልን አይቶ እንዳላየ ሰምቶም እንዳልሰማ መሆንን መርጠናል፡፡ በዚህም አገራችንንና መብቶቻችንን ከመጠበቅ ተዘናግተን አይኖቻችንን ከድነናል፡፡ በዚህ የድካም እንቅልፍ ሳብያ በልቀት፣ በጽናትና በሰላማዊ ግን ቁርጠኛ ትግል የአገራችንን እጣ ፈንታ የመወሰን እድላችንን እንደዋዛ ጥለናል፡፡ እንዲያውም፣ መብታችንን አሳልፈን በሰጠን ቁጥር ለውጡን እየረዳን እንደሆነ የምናስብ  አሳዛኝ ህብረሰብ ሆነናል፡፡ መብትን ለማረጋገጥ የተደረገን ትግል መብትን በመሰዋት እንደምን መርዳት ይቻላል? አላማን ለማሳካት እራሱን አላማውን መሰዋት እንዴት ስሜት ይሰጣል?
6   የህወሀት ስህተትና የለማ ቡድን ትምህርት
 የህወሀት መንግስት የከተማ ፖለቲካ የተካነውን አዲስአበቤን ሊቆጣጠር የደከመው በጫካ ጠመንጃ ነበር፡፡ ነዋሪውም የህወሀትን ግልጽ ጠመንጃ በሀሳቡ የልቀት ሰይፍ ስለተቋቋመ ህወሀት የአዲስአበቤን መንፈስ ማለዘብም ሆነ የአዲስአበቤን ልብ ማማለል ጨርሶ አልሆነለትም፡፡ ከዚህ የህወሀት ስህተት በሚገባ የተማሩት የለማ ቡድን አባላት ለአዲስአበቤ ስነልቡና በሚስማማ ተውኔት የኢትዮጵያዊነትን ካባ ደርበው፣ የዘውግ ርዕዮታቸውን ግን ሳይቀይሩ  እፊቱ ቆሙ፡፡ በህወሀት ላይ በተገቢ ምክንያት የጎሸ ልቡን አለዘቡት፡፡ “መልካም ሊሆኑ  ባይቻልም መልካም መስሎ መታየት ግን ለመሪዎች ወሳኝ ነው” እንዲል ኢጣልያዊው አሳቢ ኒኮላይ ማክያቬሊ፡፡  እናም፣ ህግ ጥሰውና የነዋሪውን የመምረጥ መብት ሽረው አዲስአበባ ላይ ያቄመ ጽንፈኛ አክራሪ ግለሰብ ምክትል ከንቲባ አድርገው ሲሾሙ ለምን የማይል፤ ቅሬታውን ሊገልጽ ሰልፍ በወጣበት የጸጥታ ሀይላቸው ያልታጠቁ ሰላማዊ ወጣቶችን ተኩሶ ሲገድል በገለልተኛ አካል እንዲጣራ የማይጠይቅ፤ በሺህ የሚቆጠሩ ልጆቹን ወታደራዊ ማሰልጠኛ አሳጉሮ እቤቱ የሚገባ፣ የፖሊስ ኮሚሽነሮቻቸውና ቃል አቀባዮቻቸው  በአደባባይ በስም ጠርተው ሲዘልፉት አልበዛም እንዴ ሲል የማይቃወምና ክብሩንም መልካም ስሙንም የማይከላከል  ለማዳ አደረጉት፡፡ ያሳዝናል፣ አዲስአበቤ በአብይ አህመድ መልካም ቃላት ዋና ዋና ትጥቆቹን ማለትም ለነጻነት ያለውን ቀናኢነትና እምቢ ባይነቱን በተኛበት ተዘርፏል፡፡  “አንዳንዴ ደግሞ መስፍኑ የተለበጠ ማንነት ሊኖረው ይገባል፡፡ ሰዎች የሚያውቁት የላዩን ብቻ ሲሆን አስፈላጊ የሆነ ጊዜ ግን ሁለተኛውና ድብቁ ማንነት ይገለጣል፡፡” እንዲል እርካብና መንበር የተሰኘው መጽሀፍ፡፡ ስለዚህም አሁን ከምን ጊዜውም በላይ አዲስአበቤ የመዲናውና የሀገሩ ባለቤት የመሆን መብቱ በስልጣን ላይ ያሉም የሌሉም ዘውጌ ፖለቲከኞች የጥቃት ቀስት የቅርብ ኢላማ ሆኗል፡፡
7   አምባገነን ማዋለድ
 በዜጎቻቸው ላይ በነፍስወከፍ ሰላይ ሊያሰማሩ የሚቃጣቸው፣ እንኳን ሀሳብ የመግለጽ መብትን ሊያከብሩ በተገዢዎቻቸው አእምሮ ውስጥ ያደረውን ሃሳብ ሳይቀር ሊቆጣጠሩ የሚጥሩ ፍጹም አምባገነን ገዢዎች በአንድ ሌሊት  እዝያ ደረጃ ላይ አይደርሱም፡፡ እነኚህን ፍጹም አምባገነኖች አንከብክቦ እዝያ ጨለማ ማንነታቸው ጋር የሚያደርሳቸው ወይም እንዲያ አድርጎ የሚፈጥራቸው መብቱን አሁንና ዛሬ የማይጠይቅ ማህበረሰብ ነው፡፡ አዲስአበቤም ለአስርት አመታት ከህወሀት ጠመንጃና ማባርያ ከሌለው የተባበሩት ዘውጌዎች ጸረኢትዮጵያዊነትና አዲስአበቤነት  ፕሮፖጋንዳ ጋር ባካሄደው ትግል ተሰላችቶ ይመስላል፣ ኢትዮጵያ የምትሰኝ የአዲስአበቤን ልብ የምታቀልጥ ጨዋታና በጎ ቃላትን ታጥቀው ጠመንጃቸውን እንደተማሪ ደብተር ከጀርባ ሸሽገው)ለመጡት አብይ አህመድ አገሩን፣ መብቶቹን፣ ጥቅሞቹን፣ አጀንዳዎቹንና አሁን አሁን ደግሞ ህልውናውን፣ ማንነቱን ሳይቀር በአደራ ሰጥቶ አንቀላፍቷል፡፡ አገር እንዲሸከም የሚጠበቅ የአዲስአበቤ ጫንቃ አብይ አህመድንና ቡድናቸውን  አዝሎ በጊዜ ህግ ሲጥሱ በተቃውሞ ባለመቆንጠጥ፣ አለፍርድ ወጣቶቹን በጅምላ ሲያስሩ በግሳጼና ፊት በመንሳት ባለመሸንቆጥ፣ ጥቅሙን የሚጻረሩ ውሳኔዎቻቸውን በልዩ ልዩ የተቃውሞ ስልቶች ደግሞው እንዳይሞክሩት ባለመቅጣት እንደቀዳሚዎቻቸው ሁሉ እርሳቸውንም ወደአምባገነንነት ጉርምስና እያሳደገ ነው፡፡ አይጥ ጥርሷ አድጎ ህይወቷን እንዳያቋርጠው ስትል ከተገኘ ቁስ አካል ጋር በማፋጨት ጥርሷን መሞረድ አለባት አሉ፡፡ አምባገነንም እንዲያ ነው፡፡ ጥርሶቹን በህዝብ ላይ ካልሞረደ በህይወት እንደማይሰነብት ያውቃል፡፡ የህዝብ ፍርሀት የእድሜው ዋስትና፣ የህዝብ ስቃይም የአገዛዝ አይቀሬ ውጤት ነው፡፡ አንዲት ፍሬ መብት አሳልፎ አለመስጠት እንግዲህ መሪዎች ይህንን አይጥማ የአምባገነንነት ጥርስ ገና ሳያበቅሉ ለመከላከል ነው፡፡
7   ደወሎች
 በእንቅልፍ የተያዘ ጆሮአችን አልሰማቸውም እንጂ የማስጠንቀቅያ ደወሎቹስ እየተደወሉ ነው፡፡
ሀ) ጽንፈኛ አቋም እንዳላቸው የሚታወቁ  በርካታ ግለሰቦች የአዲስአበባ ከተማን መስተዳድር፣  የክልሎችንና  የፌደራል መንግስትን የስልጣን እርከኖች እንዲቆጣጠሩ ተደርጓል፤ እየተደረገም ነው፡፡
ለ) የመንጋ ፍርድ በርክቷል፡፡ የዜጎች ከገዛ አገራቸው መፈናቀል ተባብሶ ቀጥሏል፡ መንግስት ግን የመንጋ ፍርዱንም ሆነ በሚሊዮኖች የዜጎችን መፈናቀል ባለመከላከሉ የከፈለው ዋጋ የለም፡
ሐ) አለአንዳች ትጥቅ ቅሬታቸውን ሊያሰሙ የወጡ ሰላማዊ ወጣቶች በጠራራ ጸሀይ ተገድለዋል፡፡
መ) ከ1400 በላይ ወጣቶችን አለፍርድ ቤት ትእዛዝና አለተገቢ የህግ ሂደት Due process of law ወታደራዊ ማሰልጠኛ ውስጥ የማጎር ድፍረት መታየቱ ዛሬም እንደህወሀት መራሹ ወቅት ሁሉ የእያንዳንዱ ተቃውሞ የሚያሰማ አዲስአበቤ እጣ ምን ሊሆን እንደሚችል ፍንጭ ሰጥቷል፡፡
ሠ) የአዲስአበባ ዳግም ቆርቋሪ ብርሀን ዘኢትዮጵያ እቴጌ ጣዪቱን ሀውልት የማቆሙ ውጥን ተሰርዟል፡፡
ረ) ኦሮሚያ በአዲስአበባ ላይ “አለኝ” ስለሚለው ልዩ ጥቅም እርግጠኛ አቋማቸውን ከመግለጽ ታቅበዋል፡፡
ሰ)  ወንጀል ባልሆኑ ድርጊቶች በሺዎች የሚቆጠሩ  የአዲስአበባ ወጣቶች ታፍሰዋል፤ እየታፈሱም ነው፡፡
ሸ) ከተለያዩ ሀገራት ጋር የተደረጉ የሀገሪቱን ዘላቂ ጥቅሞች የሚወስኑ ስምምነቶች ለህዝብ ይፋ አልተደረጉም…፡፡
አዲስአበቤ ሆዬ፣ የትላንቱ የህወሀት ጠመንጃ፣ የጨበጠው እጅ ተቀይሮ፣ በአማላይ ስብከት ተጋርዶ አሁንም እዝያው በቦታው መኖሩን ልብ አላልን ኖሮ፤ የ“ይሁንልህ/ልምምጥ ፖለቲካውን ” (Poletics of appeasement) አድርተነዋል፡፡ ነገር ግን፣ የሰው ልጅ ታሪክ ሳያዛንፍ እንደሚነግረን ቅንጣት ፍሬ መብቱን የገበረ ለጎተራ ሙሉ መብቱ አንዳችም ዋስትና የለውምና፣ ለውጡ አፈናን በነጻነት የመተካት ሳይሆን አፋኝ እጅ የመቀየር እንዳይሆን ያሰጋል፡፡ “በመልካሙ ጊዜ ህዝብን በፍቅር መያዝ አስፈላጊ ነው፡፡ ፍላጎታቸውን በመፈጸም የልብ ትርታቸውንም በማዳመጥ ደስ የሚያሰኛቸውንም ነገር በማድረግ በህዝብ ልቦና ውስጥ ተደላድሎ መቀመጥ ይቻላል፡፡ ነገር ግን ይህ አካሄድ አንዳንዴ ችግር አያጣውም፡፡ ታድያ የአመጽና የመከዳት ምልክት በታየ ጊዜ በሁለተኛውና በተለበጠው ማንነት መገለጥ ተገቢ ይሆናል፡፡” ከላይ የሰፈሩት መስመሮች እርካብና መንበር ከተሰኘው መጽኀፍ መቀንጨባቸውን ልብ ይሉአል፡፡ የአዲስአበቤ ስህተቱ መብት በሰላማዊ ትግልና ጽናት በቀር በምጽዋትና ቸርነት እንደማይገኝ አለባህሪው መርሳቱ፤ የአዲስአበቤ ጥፋቱ እጅጉን መንቃትና መስላት ባለበት ወቅት ማንቀላፋቱ፤ የአዲስአበቤ
ጥፋቱ እውነትን በሙሉ አይን ፊት ለፊት አለመመልከቱ፤ የአዲስአበቤ ስህተቱ አንዲት ቅንጣት መብቱን ሲያባክን የሚኖርባትን ከተማ ባለቤትነት በጽንፈኞች ሊነጠቅ እንደተዳረሰ አለመረዳቱ ከረሜላ  ቃላትን ከሚመርሩ ተግባራት አለመለየቱ ነው፡፡
8   መጠቅለያ
አዲስአበቤ በአስቸኳይ ከእንቅልፉ ነቅቶ የቀደመ ሰላማዊ ግልጽ ኢትዮጵያዊ ርእዩን ወልውሎና የነበረ ጠያቂነቱን ቀስቅሶ ካልተነሳ ፊቱን እንዳዞረ የሚያናውዘው የገደል ጫፍ ሸለብታ ወደሚፈራው ገደል የኋሊት ጨምሮት ከተማውንና አገሩን እንዳይከስር ያሰጋል፡፡ “ሊነጋ ሲል ይጨልማል” እያለም ከሆነ የማለዳ እንቅልፍ ክፉም ጣፋጭም፣ አደንዛዥም አዘናጊም መሆኑን ላስታውሰው እወዳለሁ፡፡ ምነው ቢሉ፣ ዛሬም እንደትላንት ከረፈደ መንቃትን ካበቃለት በኋላ በከንቱ ቁጭት መንደድን ያስከትላልና፡፡
የመብትም የአገርም ባለቤት ለመሆን፣ መደራጀት አሁን፤ መደራደር ዛሬ ነው፡፡አዲስአበቤነት ይለምልም፤ ኢትዮጵያዊነት ለዘልአለም ይኑር፡፡
Filed in: Amharic