>

በታጣቂዎች የተከበቡት የአሰቦት ገዳም መነኰሳት የድረሱልን ጥሪ እያሰሙ ነው!!

በታጣቂዎች የተከበቡት የአሰቦት ገዳም መነኰሳት የድረሱልን ጥሪ እያሰሙ ነው!!
ሀራ ተዋህዶ
 
የወረዳው አስተዳዳሪ “ለቃችሁ ውጡ” በማለት እገዛ ለማድረግ አልፈቀደም
• ከጥቅምት 7 ጀምሮ በየምሽቱ ከታጣቂዎቹ ጋራ የተኩስ ልውውጥ በማድረግ ላይ ናቸው፤
• ታጣቂዎቹ፣“የኦነግ ወታደሮች ነን”ቢሉም ተከፋይ ሁከተኞች ሊኾኑ እንደሚችሉ ተነግሯል፤
• የወረዳው አስተዳደሪ፣ ጥበቃ እንዲያደርግላቸው በዞኑ የተላለፈለትን ትእዛዝ አልፈጸመም፤
• በሶማሌ ክልል ወሰን በኩል የመከላከያ ድጋፍ ቢጠየቅም የኦሮሚያ መፍቀድ አለበት፤ተብሏል፤
• አንዱ በሌላው ሲያመካኝ፣ የግንቦት 1984 ዐይነቱ ወረራና እልቂት እንዳይደገም አስግቷል፤
• በስብሰባ ላይ ያለው ቅዱስ ሲኖዶሱ፣ በአስቸኳይ የኦሮሚያን ክልል እገዛ ሊጠይቅ ይገባል፤
• ፓትርያርኩ በመክፈቻቸው እንዳሉት፣ በተጽዕኖና በማፈናቀል ከማዳከም ስልቶች አንዱ ነው፤
• ከጸጥታና ፍትሕ አካላት ጋራ በመቀናጀት፣ ጥቃቱን ከወዲሁ ለማምከን መፍጠን ያስፈልጋል፡፡
***
ማንነታቸው በውል በማይታወቁ ታጣቂዎች የጥቃትና ወረራ ስጋት ውስጥ ቀናትን ያስቆጠሩት ጥንታዊው የአሰቦት ደብረ ወገግ ጻድቁ አቡነ ሳሙኤል ገዳም ማኅበረ መነኰሳት፣ ለቤተ ክርስቲያንና ለመንግሥት አካላት የድረሱልን ጥሪ እያሰሙ ነው፡፡
በምዕራብ ሐረርጌ ሀገረ ስብከት በሜኤሶ ወረዳ የሚገኘው የገዳሙ መነኰሳት እንደተናገሩት፣ ታጣቂዎቹ ከጥቅምት 7 ጀምሮ በየምሽቱ ወደ ገዳሙ በመተኰስ ማኅበሩን ለማሸበር እየሞከሩ ሲኾን፤ የወረዳውና የዞኑ አስተዳደር ጥበቃ እንዲያደርጉላቸውና ከይዞታቸው እንዲያስወጡላቸው ያደረጉት ጥረት ውጤት ባለማስገኘቱ የክልሉ መንግሥት አስቸኳይ መፍትሔ እንዲሰጣቸው ጥሪ አሰምተዋል፡፡
ገዳማውያኑ እንዳስረዱት፣ በቁጥር ከ25 ያላነሱ ታጣቂዎቹ ከመስከረም አጋማሽ ጀምሮ የገዳሙ ይዞታ ወደኾነው ደን ውስጥ ገብተው ድንኳን ተክለው ተቀምጠዋል፡፡ ስለማንነታቸው ሲጠየቁ፣ የኦነግ ወታደሮች እንደኾኑና የመጡበትም ምክንያት፣ “የሶማሌ ወታደሮች ወደዚህ ይገባሉ ተብለን ወደ እነርሱ ነው የምንሔደው፤” ብለዋል፡፡ ቀደም ሲልም ጫካ ውስጥ ገብተው ወደ ገዳሙ በዘፈቀደ የሚኩሱ፣ ዐጸዶቹን የሚቆርጡ ሁከተኞች እንደነበሩ ያወሱት ገዳማውያኑ፣በኦነግ ስም ቢጠሩም በብጥብጥ ለመጠቀም የፈለጉ ተከፋዮች ሊኾኑ እንደሚችሉ ጠቁመዋል፡፡
በተለይ ባለፉት ሦስት ቀናት በየምሽቱ በተኩስ ለማሸበር የሚያደርጉትን ሙከራ አጠናክረው እንደቀጠሉና መሰል አጸፌታ ከመስጠት ውጭ ምንም ማድረግ እንዳልቻሉ መነኮሳቱ አስረድተዋል፡፡ ባለፈው ሰኞ ምሽት ከምሽቱ 2 እስከ 4 ሰዓት የቀለጠ የተኩስ ልውውጥ እንደነበርና በትላንትናው ዕለት ሌሊትም ኹለት አብሪ ጥይቶችን ወደ ገዳሙ በመተኰሳቸው መጠነኛ አጸፌታ እንደሰጡ አክለዋል፡፡
የችግሩ ምልክት እንደታየ መነኰሳቱ ጥያቄያቸውን ያቀረቡለት የሜኤሶ ወረዳ አስተዳዳሪ፣“የያዛችሁት የሰው ቦታ ነው፤ ለምን ለቃችሁ አትወጡም” በማለት እንደሚያመናጭቃቸው ገዳማውያኑ ተናግረዋል፤ ለዞኑ ባቀረቡት አቤቱታ፣ ጥበቃ እንዲያደርግላቸውና መፍትሔ እንዲሰጣቸው ቢታዘዝም ሓላፊነቱን ለመወጣት ፈቃደኛ እንዳልኾነ አስታውቀዋል፡፡
ገዳሙ ከሶማሌ ክልል በሚዋስንበት አቅጣጫ ለሚገኘው የመከላከያ ኃይል ድጋፍ መጠየቃቸውን መነኰሳቱ ጠቅሰው፣“የኦሮሚያ ክልል በመኾኑ ፈቃድ ካላገኘን መግባት አንችልም፤ክልሉን ደጋግማችሁ ጠይቁ፤ የሚል ምላሽ ብቻ ነው የሰጡን፤” ብለዋል፡፡ አንዳችም ጥበቃ እየተደረገላቸው ባለመኾኑ የክልሉ መንግሥት እና ጠቅላይ ቤተ ክህነቱ፣ ለድረሱልን ጥሪያቸው አፋጣኝ ምላሽ እንዲሰጧቸው ተማፅነዋል፡፡
ከጻድቁ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ሐዋርያ ዘኢትዮጵያ ደቀ መዛሙርት አንዱ በነበሩት ጻድቁ አቡነ ሳሙኤል በ13ኛው መ/ክ/ዘ የተመሠረተው ገዳሙ፣ በግራኝ ወረራ ጊዜ ከጠፉት ገዳማት አንዱ ነበር፡፡ እንደገና የቀናው እጅግ ዘግይቶ በ1911 ዓ.ም. ሲኾን፣ አቅኝውም የታወቁት ሊቅ አለቃ ገብረ መድኅን ናቸው፡፡ በ1912 ዓ.ም. የጻድቁ አቡነ ሳሙኤልን ቤተ ክርስቲያን በሣር ክዳን ሠሩ፡፡ በ1918 ዓ.ም. ደግሞ የቅድስት ሥላሴ ቤተ ክርስቲያንን መሥራት ጀምረው፣ ፍጻሜውን ሳያዩ ቢያርፉም በ1919 ዓ.ም. የሕንፃ ቤተ ክርስቲያኑ ሥራ ተጠናቋል፡፡
በ1929 ዓ.ም. በሶማልያ በኩል በገባው የፋሽስት ኢጣልያ ጦር ገዳሙ ተዘርፏል፤ የቅድስት ሥላሴ ቤተ ክርስቲያንም ፈርሷል፡፡ በወቅቱ በገዳሙ ከነበሩት 500 መነኮሳት መካከል ከፊሉ ታቦቱን ይዘው ወደ ደብረ ሊባኖስ ገዳም ሲሸሹ ከፊሎቹ ደግሞ ወደ ሞቃዲሾ ተወስደው ታስረዋል፡፡ ወራሪው ከተባረረ በኋላ መነኮሳቱ በ1936 ዓ.ም. ተሰባስበው ወደ አሰቦት መጡ፡፡ ከ22 ዓመት በኋላ ደግሞ የቅድስት ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን በግርማዊ ቀዳማዊ ንጉሠ ነገሥት ዐፄ ኃይለ ሥላሴ ትእዛዝ በ1952 ዓ.ም. ተሠራ፡፡ ግንቦት 16 ቀን 1984 ዓ.ም.፣ የኦሮሚያ ነጻነት እስላማዊ ግንባር(ጃራ) የተባለ አክራሪ ኃይል፣ ገዳሙን ወርሮ በዙሪያው የሚኖሩ መነኮሳትንና 16 ክርስቲያን አባወራዎችን አርዷል፡፡
ካህናትንና ክርስቲያኖችን በተጽዕኖና በጥቃት ማፈናቀል፣ ቤተ ክርስቲያንን የማዳከም አንዱ ስልት እንደኾነ በቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ የመክፈቻ ንግግራቸው የጠቀሱት ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ፣ በየአካባቢው ከሚገኙ የፍትሕ እና ጸጥታ አካላት ጋራ በመቀናጀት ጥቃቶችን አስቀድሞ የማምከንና ሲደርሱም የመከላከል አሠራር እንደሚቀየስ ጠቁመዋል፡፡ የታጣቂዎቹ ፍላጎት፣ ድምፃቸውን አጥፍተውና መነኮሳቱን አጋዥ አሳጥተው ገዳሙን ማጥፋት እንደኾነ መነኮሳቱ እየተናገሩ በመኾኑ፣ ከክልሉ መንግሥትና ከወረዳው አስተዳደር ጋራ በመነጋገር ለድረሱልን ጥሪያቸው አፋጣኝ ምላሽ እንዲሰጣቸው መፍጠን ያስፈልጋል፡፡
Filed in: Amharic