>
7:48 am - Wednesday December 7, 2022

አንዳችን ስንነሳ:ሌሎቻችን መቀመጥ የለብንም! (ቹቹ አለባቸው)

አንዳችን ስንነሳ:ሌሎቻችን መቀመጥ የለብንም!
ቹቹ አለባቸው
አሁን በብዙ ከተሞቻችን ሰልፍ መካሄዱ አይቀሬ እንደሆነ እዉን ሆኗል።  ሆኖም ሰልፎቻችን አቃፊ እንዲሆኑ ቢደረግ ጥሩ ነዉ። ሰላማዊ ሰልፍን እና አድማን በተመለከተ: ከኦሮሞ ወንድሞቻችን የምንወስደዉ ትምህርት ያለ ይመስለኛል። ይሄዉም : ሁላችንም እንደምናስተዉሰዉ: የኦሮሞና አማራ አመጽ በተቀሰቀሰበት ወቅት: ኦሮሞዎች አድማም ሆነ ሰላማዊ ሰልፍ ሲጠሩ: ሙሉ በሙሉ ካልሆነም: አብዛኞቹ ከተሞቻቸዉ: በተመሳሳይ አጀንዳና በተመሳሳይ ወቅትና ስአት ነበር የሚያደርጉት።
በአንጻሩ ደግሞ: የአማራን ህዝባዊ እንቅስቃሴ ስናስተዉስ: ወጣ ገባ የበዛበት ነበር። በተወሰነ መልኩ ጎንደርና ጎጃም በተናበበ መልኩ ለመንቀሳቀስ የሞከሩ ሲሆን: ወደ ወሎ አካባቢ መቀዛቀዝና ዘግይቶ ትግሉን መቀላል(ስ/ወሎ ) የነበረ ሲሆን: ወደ ደቡብ ወሎና ሰ/ሽዋ ስንመጣ ደግሞ: ከነጭራሹ የመንቀሳቀስ ዉስንነት ታይቷል። ይሄ የሆነዉ: የነዚህ አካባቢወች አማራ : የአማራ ጥያቄ የኔም አይደለም ከሚል ሳይሆን: በወቅቱ የነበረዉ ከባድ የመንግስት አፈናና ትግሉን የሚያስተባብር ሀይል በአካባቢወቹ አለመገኘቱ ነበር። በርግጥ አንድ የማንክደዉ እዉነታም ነበር: ይሄዉም በወቅቱ በአንዳንድ  የብአዴን ከፍተኛ አመራሮች ጭምር : “የግጨውና የወልቃይት ጉዳይ ለሌላዉ ምኑ ነዉ” የሚል ቅስቀሳ ያደርጉ ስለነበር: የአማራ ህዝብ በወቅቱ: በአንድ ልብ: በአንድ ወቅትና በአንድ አጀንዳ እንዳይሰለፍ አድርጎት እንደነበር እናስተውሳለን። ለዚህ ነበር ጎንደርና ጎጃም ሲነሳ: ወሎ ግራ ይጋባ የነበረው: ለዚህ ነበር ወሎ ሲነሳ ደግሞ: ጎንደርና ጎጃም: አሻግሮ ምንድን ነዉ ነገሩ ይል የነበረው። በወቅቱ የነበረዉን  የደ/ወሎና ሰ/ሽዋ ነገር ደግሞ ሁላችንም የምናስተዉሰዉ ነዉ።
ዛሬ ላይ ነገሮች የተሻሻሉ መሰለኝ። ይሄዉም: ሰሞኑን በሚካሄዱት ሰልፎች ከሞላ ጎደል: በሁሉም የክልሉ ዋና ዋና ከተሞች :በተመሳሳይ አጀንዳ: በተመሳሳይ ቀን ሰልፎች እንደሚካሄዱ መረጃወች እየወጡ ነዉ። ይሄ ጥሩ ጅምር ነዉ። ነገር ግን: ንቅናቄዉ  አሁንም በቂ አይመስለኝም። ብዙዎቹ ከተሞችና ወረዳዎች የዚህ ሰልፍ አካል ስለመሆናቸዉ እጠራጠራለሁ: መረጃ ካለ ስጡኝ።  በዚህ አማራዊ አጀንዳን ባነገበ ሰለላማወዊ ሰልፍ፤ ሁሉም የክልሉ ወረዳወችና ከተሞች መሳተፍ አለባቸዉ። በተለይም: የትግራይ ደንበርተኛ አካባቢወች ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ ሊሳተፉ ይገባል።
በመንግስት ላይ በጎ ተጽእኖ መፍጠር የሚቻለዉ: ድምጽን በተባበረ ሁኔታ ማሰማት ሲቻል ብቻ ነዉ። ስለሆነም: አንዱ የአማራ አካቢቢ ሲሰለፍ: ሌላኛዉ አካባቢ: የማይነሳና አብሮ ድምጹን የማያሰማ ከሆነ: ዛሬም ቢሆን አልተግባባንም ማለት ነዉ።
መዉጫ:-
1. የሰልፎቻችን ሞፈክሮች ተመሳሳይነት እና ተገቢነት እንዲሁም ህጋዊነት: በደንብ ይፈተሽ።
2. በነገዉ እለት የማይሳካላቸዉ : ወይም ስልፍ ለማካሄድ ሀሳብ ያልነበራቸዉ አካባቢወች: የራሳቸዉን ፕሮግራም አዉጥተዉ: በትኩሱ እንዲቀጥሉበት ቢደረግ ጥሩ ነው እላለሁ: ምክንያቱም”  ወይ ባልዘፈንሽ: ከዘፈንሽም ባላሳፈርሽ” ነዉ ነገሩ ብለናልና። አንዱ የአማራ አካባቢ ተነስቶ: ሌላኛዉ አካባቢ ሳይነሳ ከቀረ: ችግር ነዉ። አንድ አማራ ነን የሚለው አባባል፡ ዲስኩር ብቻ ሆኖ ቀረ ማለት ነው፡፡አማራ የሆነ ሁሉ፤ አማራዊ  አጀንዳዎች ሲቀረጹ፤ በጋራ ይቆማል እንጅ፤አሻግሮ አይመለከትም፡፡
3. ሰልፎቹ: የህግ የበላይነት የሚንጸባረቅባቸዉ:በጨዋነት ተጀምረዉ በጨዋነት የሚቋጩ መሆን አለባቸዉ።
Filed in: Amharic