>

የኢትዮጵያ ህዝብ የማይሆን ነገር ሲመጣ፣ ሲሰማ እና ሲያይ እምቢ አሻፈረኝ ይበል!!! (ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም)

 

የኢትዮጵያ ህዝብ የማይሆን ነገር ሲመጣ፣ ሲሰማ እና ሲያይ እምቢ አሻፈረኝ ይበል!!!

 

ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም ለኢትዮጲስ ጋዜጣ ከተናገሩት…

 

~ ለውጡ በእነ ለማ፣ አቢይ እና ባልደረቦቻቸው በጣም ድፍረት እና ወኔ በተሞላበት እርምጃ የመጣ ለውጥ ነው።

እኔ እነዚህ ሰዎች ከእግዚአብሔር የተላኩ እንጂ ፖለቲከኞች አልመሰሉኝ ነበር።

አሁንም ስለእነዚህ ሰዎች እንደዚሁ ነው የሚሰማኝ።

~ አሁንም የኢትዮጵያ ህዝብ ትብብር ያሳየው እስከ ማድፈጡ ድረስ ብቻ ነው።

ከደፈጣው በኋላ፣ ግፈኞችን ከአወረደ በኋላ ግን አዲስ ስርዐት ለመገንባት ሲንቀሳቀስ እየታየ አይደለም።

~ ጠ/ሚ አቢይን አንድ ስብሰባ ላይ አግኝቻቸው ለጥቂት ደቂቃዎች ቁጭ ብለን አውርተናል።

“ምነው መሀል አገሩን (የኢትዮጵያን ውስጥ ሰላም፣ ደህንነት እና ፀጥታ) ረሱት፣ ዳር ዳሩን ከአረብ ሀገራት እስከ ኤርትራ ድረስ ብዙ ሲሰሩ?” አልኳቸው።

“ያንን እደርስበታለሁ” አሉኝ። እሳቸው እስከሚደርሱበት ግን ሌሎች ደረሱበት። ቀደሟቸው።

ይኸው ብዙ ስራ እየሰሩ ነው። ትግል፣ ጦርነት እና ግድያ እየተደረገ ነው።

~ አቢይና ለማ ስለ ኢትዮጽያ ያላቸው አመለካከት ጥሩ ነው። የጎሰኝነት ጠባይ አያሳዩም። እንዲያውም ሊያደበዝዙት የሚፈልጉ ናቸው።

~ ኢትዮጽያ ሰው አጥታ አታውቅም። የህብረት የመተባበር ጉዳይ ነው ከሀገር የጠፍው።

~ የሽግግር መንግስት የሚሉት የዛሬ 40 አመት እድሉ ያመለጣቸው ናቸው።

እነሱ አርጅተዋል፤ ለስልጣን ያላቸው ፍቅር ግን አላረጀም። ትክክል አይመስለኝም።

እነዚያ ሰዎች ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን ድህነት፣ ውርደት እና ክስረት ያመጡት እነሱ ናቸው።

~ ለዶ/ር አቢይ እና ለማ የምለው ያመጣችሁት ለውጥ ቀላል አይደለም። የኢትዮጵያ ህዝብ ሲናፍቀው የነበረ ነው። ወደ መጨረሻው ግብ ሳትሰለቹ፣ ለእበላ ባዮች እጃችሁን ሳትሰጡ ተጓዙ

ደህና ደህና ሰዎችን እየመረጣችሁ፣ በጎረምሳ ብቻ ሳይሆን፣ ሽማግሌዎችንም እየፈለጋችሁ እያነጋገራችሁ፣ ጎረምሶች ከልምድ የሚገኝ እውቀት ያንሳቸዋልና ከሌሎች ያንንን እየወሰዳችሁ እንድትቀጥሉ ነው።

እግዚአብሔር ሰጥቷችኋልና ለወሮበሎች አስረክባችሁ እንዳትሄዱ እለምናችኋለሁ።

~ ተቃዋሚዎች ዘመን መለወጡን ይገንዘቡ። ዘመን የተለወጠው እንዴት ነው? ከላይ በኩል እየተቧደኑ እየመጡ ቁጭ ማለት ቀረ።

ከታች የህዝቡን ፈቃድ እየጠየቁ፣ የህዝብ ውክልና እያገኙ፣ እየተመረቁና እየተመረጡ ስልጣን የሚያዝ መሆኑን ይረዱ፤ ይወቁት፤ ይመኑበት።

~ የኢትዮጵያ ህዝብ ዝም ብሎ የመጣውን ነገር መቀበል እምቢ ይበል። የመጣውን ሁሉ ዝም ብሎ አይቀበል።

የማይሆን ነገር ሲመጣ፣ የማይሆን ነገር ሲሰማ እና ሲታይ እምቢ አሻፈረኝ ይበል። ይተባበር።

አንድ ላይ ይሁን። ትብብሩ እንዲሁ ለማደናቀፍ ብቻ አይሁን። የኢትዮጵያ ህዝብ ያለው ኃይል ህብረቱ ነው። ይህንን ህብረቱን ይጠቀምበት።

ለስልጣን መወጣጫ ብለው በዘር፣ ሀይማኖት እና ጎሳ የሚመጡበትን “አንለያይም በዘር፤ አንለያይም በቋንቋ፤ አንለያይም በኃይማኖት” ሊላቸው ይገባል።

ከማድፈጥ ይውጣ። ይተባበር። በማህበር ይደራጅ። ድምፁን ያሰማ።

Filed in: Amharic