>
3:31 pm - Sunday August 7, 2022

በሌሎች የሃገሪቱ አካባቢዎች እስረኞች ሲፈቱ በትግራይ አልተፈቱም!!! (አቶ ገብሩ አስራት)

 

በሌሎች የሃገሪቱ አካባቢዎች እስረኞች ሲፈቱ በትግራይ አልተፈቱም!!!

 

አቶ ገብሩ አስራት

 

አለማየሁ አምበሴ አዲስ አድማስ

  • ሁሉም የኢህአዴግ ድርጅቶች ከመቼውም ጊዜ በላይ ፅንፈኛ ብሔርተኛ ሆነዋል
• የኢህአዴግ አመራር ለውጥ እንዲመጣ ያስገደደው፣የአንድ አካባቢ ትግል ብቻ አይደለም
• አዴፓ እና ኦዴፓ በአብዮታዊ ዲሞክራሲ ላይ ቁርጥ ያለ አቋም አልወሰዱም

የህወሓት መስራች፣ የመጀመሪያው የትግራይ ክልላዊ መንግስት ፕሬዚዳንት የነበሩትና የአረና አመራር ሆነው ያገለገሉት አቶ ገብሩ አሥራት፣ከሚዲያ ከጠፉ ከረዥም ጊዜ በኋላ ከአዲስ አድማስ ጋር በወቅታዊ አገራዊ ጉዳዮች ላይ ሰፊ ቆይታ ለማድረግ ፈቃደኛ ሆነዋል፡፡ ሁሉም የኢህአዴግ ድርጅቶች ጽንፈኛ ብሄርተኛ እየሆኑ መምጣታቸውን፣ ከህወሓት ውጭ
ሌሎቹ በአብዮታዊ ዲሞክራሲ ላይ ቁርጥ ያለ አቋም አለመውሰዳቸውን፣ ለራያና ወልቃይት አካባቢ ችግሮች መፍትሄው ዲሞክራሲን ማስፋት እንደሆነ— እና በሌሎችም ጉዳዮች
ዙሪያ ከአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ ጋር ተከታዩን ቃለ ምልልስ አድርገዋል፡፡

ለረዥም ጊዜ ከሚዲያ ጠፍተዋል፡፡ ከዚህ አንፃር የዶ/ር ዐቢይ አህመድን አመራርና የተመዘገቡ ለውጦችን እንዴት ይመለከቷቸዋል—?

በኢህአዴግ ዙሪያ የሚደረገውን እንቅስቃሴ በሙሉ እኔ በጥሞና ነው የምከታተለው፡፡ ኢህአዴግ ህዝብ የሚፈልገውን ለውጥ ለማምጣት የርዕዮተ ዓለም ለውጥ አድርጓል ወይ? የሚለው ጥያቄ መሰረታዊ ነገር ይመስለኛል፡፡ ለምን ቢባል የመንግስት መዋቅር በአጠቃላይ የህዝብም አወቃቀር የሚወሰነው፣ ስልጣን ላይ ያለው አካል በሚከተለው ርዕዮተ ዓለም ነው፡፡ ከዚህ አንፃር ኢህአዴግ ሲጀምር አብዮታዊ ዲሞክራሲ ብሎ ነው፤ የሃገሪቱ መንግስት ስሪትም የተዋቀረው ይሄን ተከትሎ ነው፡፡ የአብዮታዊ ዲሞክራሲ ዓላማ ደግሞ ጥርነፋ ነው፡፡ አጠቃላይ የመንግስት መዋቅሮች፣ ሚዲያውና ሌላው የህዝብና የመንግስት መዋቅሮች በዚህ አስተሳሰብ ተቃኝተው የተዋቀሩ በመሆኑ፣ በመጀመሪያ በአስተሳሰብ ላይ የሚመጣ ግልፅ የሆነ ለውጥ ያስፈልጋል፡፡ እስካሁን ድረስ እንዲህ ዓይነት ለውጥ አላየሁም፡፡ በሃዋሳውም ጉባኤ ቢሆን ርዕዮተ ዓለሙን አልቀየሩትም፡፡ ይህ ርዕዮተ ዓለም ደግሞ ከዲሞክራሲ ጋር በግልፅ የሚጣረስ ስለሆነ በመጀመሪያ ለውጡ ሁለንተናዊ፣ ተቋማዊ እንዲሆን አብዮታዊ ዲሞክራሲ መለወጥ አለበት፡፡

በሌላ በኩል፤ በኢህአዴግ ውስጥም ህዝቡ የሚፈልገውን አይነት ለውጥ ፈላጊዎች እንዳሉ አስተውያለሁ፡፡ ዶ/ር ዐቢይ ከእዚህ ለውጥ ፈላጊዎች አንዱ ናቸው፡፡ ፓርቲያቸው ለውጥ እንደሚፈልግ አስቀድመው ነው ያወጁት፡፡ በትክክልም በእሳቸው ፓርቲ ውስጥ ለውጥ ማምጣት የቻሉም ይመስለኛል፡፡ ገና የምንጠብቃቸው ለውጦች ያሉ ቢሆንም፣ እስካሁን ድረስ ሶስት በዋናነት ስጠብቃቸው የነበሩ ለውጦችን አምጥተዋል፡፡ እስረኞች ፈትተዋል፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሃገር ቤት መጥተው (በትጥቅ ሲታገሉ የነበሩ ሳይቀር) እንዲንቀሳቀሱ ፈቅደዋል፣ ሚዲያውም ከፈት እንዲል አድርገዋል፡፡ እነዚህ መሰረታዊ ናቸው፡፡ ነገር ግን ለውጡ በአስተማማኝ ደረጃ ግቡን እንዲመታ በርዕዮተ ዓለም ደረጃ እየተከተሉት ያለው አስተሳሰብ ላይ ለውጥ ለማድረግ ዝግጁዎች ናቸው ወይ? ምክንያቱም የችግሮቹ ሁሉ መነሻ ይሄ ርዕዮተ ዓለም ነው፡፡ የችግሮች ሁሉ መነሻ የሆነውን ርዕዮተ ዓለምና አስተሳሰብ ይዞ ደግሞ በዚያው አስተሳሰብ ዘላቂ መፍትሄ ማበጀት አይቻልም፡፡ እሳቸው የሚተልሙትን ለውጥ ወደ ተቋም ለማውረድ ምን ያህል አስቻይ አስተሳሰብና ሁኔታ አለ? ሚዲያው ተቋማዊ ለውጥ ይፈልጋል፣ የፍትህ ስርአቱ ፍፁም ተቋማዊ ለውጥ ይፈልጋል፣ የምርጫ ስርዓቱ ፍፁም ተቋማዊና አስተሳሰባዊ ለውጥ ይፈልጋል፡፡ ቀጣዩን ምርጫ ነፃና ዲሞክራሲያዊ ለማድረግ፣ የምርጫ ሂደቱን የሚያስፈፀሙትን በሙሉ ነፃና ገለልተኛ ፍትሃዊ ተቋማት አድርጎ ለመገንባት ፍፁም የአስተሳሰብ ለውጥ ያስፈልጋል፡፡

ከተስፋው ባሻገርም ስጋቶች አሉ፡፡ የፈነጠቁት የለውጥ ሃሳቦች ተስፋን የሚያጭሩ ሲሆኑ መንግስትና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋሞች ከተዋቀሩበት ርዕዮተ ዓለም ጀምሮ እስከተወሰዱት የፖለቲካ ማሻሻያ እርምጃዎች ድረስ ተቋማዊ ስለመሆናቸው ስጋት አለኝ። እነዚህን ማሻሻያዎች ተቋማዊ መሰረት ለማስያዝ ደግሞ ኢህአዴግ ብቻውን አይችልም፡፡ እንኳን ኢህአዴግ ብቻውን ቀርቶ በሀገሪቱ ያሉ የፖለቲካ ድርጅቶች ባለድርሻ ሆነውም እንኳ የሀገሪቱን ችግር ለመፍታት አስቸጋሪ መሆኑ ነው የሚገባኝ፡፡ ከዚህ አንፃር ስጋት ይሰማኛል፡፡

ህወሓት አብዮታዊ ዲሞክራሲ ርዕዮተ ዓለምና የድርጅት መስመር አይነካም የሚል አቋም ሲይዝ፣ ቀሪዎቹ የግንባሩ አባላት ደግሞ በርዕዮተ ዓለም ጉዳይ ላይ ምንም ውሳኔ አላሳለፉም፡፡ ይህ ሁኔታ በአካሄዳቸው ላይ ምን  አንድምታ ይኖረዋል?

እኔ ይሄን የምረዳው፣ አራቱ ድርጅቶች አሁንም ግልፅ የሆነ የጋራ አቋም ሳይኖራቸው በማቻቻል መንገድ መቀጠላቸውን ነው፡፡ በሃዋሳው ጉባኤ የሆነው ይሄ ነው፡፡ ህወሓት ርዕዮተ ዓለሙ በመቃብሬ ላይ  ካልሆነ በስተቀር የማይለወጥ ነው ብሎ አስረግጦ ውሳኔ አሳልፏል፡፡ ሌሎቹ በዚህ ደረጃ ጉዳዩን አልተመለከቱትም፤ ያሳለፉትም ውሳኔ የለም። ነገር ግን አሁን ላይ መከፋፈል ስላልፈለጉ፣ እንደ መሸጋገሪያ አድርገው የተጠቀሙት የማቻቻል መርህን ነው፡፡ ለወደፊት የትኛው ያሸንፋል? የሚለውን ጊዜ የሚለየው ይሆናል፡፡ ይሄ ሁኔታ ግን አሁን የጠራ አስተሳሰብ ይዘው እንዳይንቀሳቀሱ ያደርጋቸዋል፡፡ አዴፓ እና ኦዴፓ የለውጡ መሪዎች ናቸው ቢባሉም፣ አብዮታዊ ዲሞክራሲን ወይ ትተነዋል አሊያም ቀጥለንበታል የሚል ቁርጥ ያለ አቋም አላስቀመጡም፡፡ በዚህ ሁኔታ የሚካሄድ ለውጥ ደግሞ ብዥታ ያለበትና ተግባሩም በብዥታ የታጀበ ይሆናል የሚል ስጋት አለኝ፡፡ ህወሓት ቁርጥ ያለ አቋሙን አሳውቋል፡፡ ሌሎቹ ደግሞ እስከሚቀጥለው የግንባሩ ጉባኤ ድረስ በለሆሳስ፣ አብዮታዊ ዲሞክራሲን በማቻቻል መርህ ተቀብለው ቀጥለዋል ማለት ነው፡፡

የለውጡ ኃይል ናቸው የሚባሉት ድርጅቶች አሁኑኑ አካሄዳቸውን ማጥራት አለባቸው ብለው ያምናሉ?

እስካሁን ድረስ አንዳንድ ህጎችን የመለወጥ አዝማሚያ እያሳዩ ነው፡፡ ይሄ ርዕዮተ ዓለሙን ሳይጠቅሱ ነው፡፡ ርዕዮተ ዓለሙን እየረገጡ፣ ህጎችን ማሻሻል የሚቀጥሉ ከሆነ፣ ለውጡን ለማምጣት አይሳናቸውም። ርዕዮተ ዓለሙን እየተጫነ የሚሄደው አካል፣ አብዛኛውን ቁጥር ከያዘ፣ ለውጥ ለማምጣት የሚሳነው ነገር የለም፡፡ ከአሁን በፊትም የለውጥ ኃይሉ በድፍረት የወሰዳቸው እርምጃዎች ከአብዮታዊ ዲሞክራሲ ጋር የሚፃረሩ ናቸው፡፡ አብዮታዊ ዲሞክራሲ የአፈናና ጎራ ለይቶ፣ ሌላውን ጠላት አድርጎ ፈርጆ ስልጣን የመያዝ አካሄድን የሚከተል ነው፡፡ ይህን የጣሰ በርካታ እርምጃ በለውጥ ኃይሉ ተወስደው አይተናል፡፡ በጀመሩት መንገድ የሚቀጥሉ ከሆነ፣ ርዕዮተ ዓለሙን እየረገጡ፣ ለውጡን ሊያስቀጥሉ ይችላሉ፡፡ በአንፃሩ “አብዮታዊ ዲሞክራሲ ወይም ሞት” ያለው ኃይል ሚዛን የሚደፋ ከሆነ፣ በታሰበው መንገድ ላይሄዱ ይችላሉ፡፡

በአመዛኙ የለውጥ ኃይል ናቸው የሚባሉት ብአዴን እና ኦህዴድ የስም ለውጥ ጭምር በማምጣት ሰፊ መዋቅራዊ ለውጥ ሲያደርጉ፣ በአንፃሩ ህወሓት አሁንም የነፃ አውጪነት ስያሜን ይዞ የቀጠለው ለምን ይመስልዎታል?

እንደኔ ዋናው ጉዳይ የስም ለውጥ አይመስለኝም። ዋናው ይዘቱ ነው፡፡ የቅርፅና የስም ለውጥ የራሱ አስተዋፅኦ ሊኖረው ይችላል፡፡ አሁን ሁለቱ ድርጅቶች በአመዛኙ የስም ለውጥ ነው ያደረጉት፡፡ በሌላ በኩል ግን ኢህአዴግ ሆነው ነው የቀጠሉት፡፡ ኢህአዴግ የሚከተለውን አፋኙን አብዮታዊ ዲሞክራሲ አንቀበልም አላሉም፡፡ ስለዚህ ለውጡ ከስም የተሻገረ አይሆንም፡፡ በዚህ መሃል ዋናው ቅራኔ ሊፈጠር ይችል የነበረው፣ የይዘት ለውጥ ቢያደርጉ ነበር፡፡ እውነተኛና የጠራ  ለውጥ ሊፈጠር  ይችል የነበረውም በዚህ መንገድ ነበር፡፡ እስካሁን ድረስ ብአዴንም፣ ኦህዴድም አብዮታዊ ዲሞክራሲን ትቻለሁ ብለው አላወጁም፡፡ የስም ለውጥና የቅርፅ ለውጥ፣ ሊከተሉ የሚፈልጉትን አቅጣጫ የማመላከት አቅም ይኖረው ይሆናል፡፡ ህወሓት ደግሞ የስምም የመስመርም፣ የርዕዮተ ዓለምም ለውጥ አላደርግም፤ በነበርኩበት ነው የምቀጥለው ብሏል፡፡

ድርጅቶቹ የየራሳቸውን አቋም ሲወስዱ ምክንያታቸው ምን ሊሆን ይችላል?

እንግዲህ ሁሉም የየራሱ ምክንያት ይኖረዋል፡፡ ህወሓት ምናልባት በነበርኩበት ካልተጓዝኩ በትግራይ ውስጥ ያለኝን ተቀባይነት ላጣ እችላለሁ ብሎ ስላመነ ሊሆን ይችላል፡፡ ሌሎቹ ደግሞ የድሮውን ስያሜ ይዘን መቀጠል አንችልም፤ በዚህ ስያሜ ተጠልተናል ተቀባይነት አላገኘንም፤ ስለዚህ ሌላ ስምና ቅርፅ መያዝ አለብን  በሚል የወሰኑ ይመስለኛል፡፡ ሌላው እዚህ ላይ አስረግጬ መናገር የምፈልገው ግን፣ አሁን ሁሉም ድርጅቶች ከመቼውም ጊዜ በላይ ፅንፈኛ ብሔርተኛ ሆነዋል፡፡ ከዲሞክራሲና ከአስተሳሰብ ይልቅ ዋነኛ ጉዳይ ያደረጉት የብሔር ፅንፈኝነት ጉዳይ ነው፤ የድንበር ጉዳይ ነው፡፡ በዚህ ላይ ነው አሁን ያለው ግጭት፡፡ 


ይሄን በማስረጃ አስደግፈው ሊያብራሩልኝ ይችላሉ?

አዎ! ለምሳሌ የብአዴን ጉባኤ አንዱ ውሳኔ፣ የአማራ መሬቶችን ማስመለስ የሚል ነው፡፡ ግዛትን የማስከበር ጉዳይ አንዱ የጉባኤው ውሳኔ አካል ነበር፡፡ ይሄ ደግሞ በህወሓት በኩል፣ ህዝቡ ላይ ስጋትና ፍርሃት ለመፍጠር ያግዘዋል፡፡ ህወሓት የፖለቲካ ቅቡልነቱን ለማሳደግ ይሄን አጋጣሚ ነው የሚጠቀምበት፡፡ ሁሉም እየቀሰቀሱ ያለው የብሔር ፅንፈኝነትን ነው፡፡ ሁሉም የየክልላቸውን ብሄርተኝነት ይዘው ሲንቀሳቀሱ እንጂ በዲሞክራሲ መርህ ሲንቀሳቀሱ እያየን አይደለም፡፡ የወሰን ወይም የግዛት ጉዳይ በዲሞክራሲ መርህ ሊፈታ የሚችል ቢሆንም፣ ሁሉም በየፊናው እየቀሰቀሰ፣ በስልጣን መቆየት የሚችልበትን ሁኔታ ለመፍጠር ሲንቀሳቀስ እየታዘብን ነው፡፡

በእርስዎ እምነት ህወሓት ምን ያህል ነው ለውጡን የተቀበለው?

ይሄ ግልፅ ነው፡፡ ህወሓት ውስጥ ሁለት ጫፎች አሉ፡፡ በአንድ በኩል ያለው፣ ለውጥ ጭራሽ የማይፈልግ እንዲያውም አፈናን ከድሮው በበለጠ አጠናክሮ ለመቀጠል የሚፈልግ ነው፡፡ ይሄ ቡድን በአመዛኙ የድሮ አመራሮችን የያዘ ነው፡፡ በትግራይ ህዝብ ላይ የበለጠ አፈናን ለማጠናከር ነው በየጊዜው እየተንቀሳቀሰ ያለው፡፡ በሌሎች የሃገሪቱ አካባቢዎች እስረኞች ሲፈቱ እኮ በትግራይ አልተፈቱም፡፡ በሌላው አካባቢ ተቃዋሚዎች ገብተው በነፃነት እንዲንቀሳቀሱ ሲደረግ፣ በትግራይ ድምህት መጥቶ እንኳ ወደ ካምፕ ነው በቀጥታ የገባው፡፡ አብዮታዊ ዲሞክራሲን ተቀበል ብለው ሊያስጠምቁት ነው እየጣሩ ያሉት፡፡ ሁሉንም በእነሱ አስተሳሰብ ዙሪያ ለማጥመቅ ነው የሚሞክሩት። በሌላ በኩል ደግሞ ለውጥ አስፈላጊ ነው ብለው አምነው፣ ለለውጥ የሚንቀሳቀሱ ኃይሎች አሉ፡፡ እነዚህ በአመዛኙ ወጣቶች ናቸው፡፡

እስካሁን ህወሓት በትግራይ ጠንካራ የህዝብ ተቃውሞ እንዳልገጠመው ይነገራል፡፡—ከዚህ አንፃር የህወሓት ዕጣ ፈንታ ምን ይሆናል ብለው ይገምታሉ?

ትግራይ ውስጥ ጠንካራ ተቃውሞ የለም የሚለው ትክክል አይደለም፡፡ በሁሉም መንገድ ትግራይ ውስጥ የሚደረግ የተቃውሞ እንቅስቃሴ ከበፊት ጀምሮ አለ። አረና በሰላማዊ መንገድ በሚያደርገው ትግል ብዙ መስዋዕትነት ከፍሏል፡፡ አክቲቪስቶች ብዙ እንቅስቃሴ እያደረጉ ነው፡፡ ከዚህም አልፎ እጅግ የጠነከረው የትጥቅ ኃይል ያለው ትግራይ ውስጥ ነው፡፡ 2500 የታጠቀ የደምህት ኃይል ነው ከአስመራ የገባው። የኦነግ 1300 ነበር፡፡ ጠንካራ የትጥቅ ትግል ይካሄድ የነበረው በትግራይ ነው፡፡ በሌላ በኩል፣ በክልሉ ውስጥ በህዝቡ ላይ አፈናው ብርቱ ነው፡፡ ከፍተኛ አፈና ነው ያለው፡፡ በዚህ ስር ሆኖ በርካቶች በሰላማዊም በትጥቅም ከፍተኛ ትግል ሲያደርጉ ቆይተዋል፡፡ በዚህ መሃል የህወሓት ማስፈራሪያም መረሳት የለበትም፡፡ ህወሓት መሰረቴ ነው ብሎ ስለሚያስብ፣በክልሉ ላይ ማንኛውንም መንገድ ተጠቅሞ አፈና ያደርጋል፡፡ ይሄን መገንዘብ ያሻል፡፡

በኦሮሚያና በአማራ ክልል ለውጡን ለማምጣት ብዙ ወጣቶች ከፍተኛ ተቃውሞ አድርገዋል፤ ህይወታቸውንም ገብረዋል፡፡ በዚህ ልክ የተደረገ ተቃውሞ በትግራይ አልታየም የሚሉ ወገኖች አሉ …         
ይሄም መነሻው ስህተት ነው፡፡ አረና የጠራው ሰልፍ እኮ በተለያዩ የትግራይ አካባቢዎች ተደርጓል፡፡ በነገራችን ላይ በሌላው አካባቢም ቢሆን አሁን በስልጣን ላይ ያለው ኢህአዴግ ነው፡፡ በትግራይ ህወሓትን በመቃወም ብዙ ሰልፎች በአረና አስተባባሪነት ተደርገዋል፡፡ እነዚህን መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ አሁን ያለው ፖለቲካ በአጠቃላይ፣ የትግራይን ተቃውሞ እንደ ተቃውሞ ያለማየት፣ ህወሓትን እና ህዝብን አንድ አድርጎ የመመልከት ችግር ያለ ይመስለኛል። በበርካታ አካባቢዎች ሰልፎች ይደረጋሉ፤ ነገር ግን እይታ እንዳያገኙ ወዲያው ይታፈናሉ፡፡ ሚዲያዎችም የሚዘግቧቸው አይደሉም፡፡ አስቀድሞ ህወሓት እና የትግራይ ህዝብ አንድ ነው ተብሎ ስለተፈረጀ፣ ህዝብ ለሚያደርገው ተቃውሞ ሽፋን የሚሰጠው ሚዲያ ማግኘት ሳይችል ቀርቶ እንጂ በርካታ ተቃውሞዎች ሲደረጉ ነበር፡፡ የትግራይ ህዝብ ሰፊ ትግል እያደረገ ቆይቷል፡፡

ትግሉ ህዝቡ የሚፈልገውን ለውጥ አምጥቷል ብለው ያስባሉ?

በአጠቃላይ ዛሬ በኢትዮጵያ የመጣው ለውጥ እኮ የአንድ አካባቢ እንቅስቃሴ ብቻ አይደለም፤ በኦሮሚያና በአማራ ክልል በስልጣን ላይ ያሉት አሁንም የኢህአዴግ ድርጅቶች ናቸው፤ በትግራይም ህወሓት ነው ያለው፡፡ እርግጥ ነው በድርጅቶቹ ውስጥ ያለው የለውጡ ደረጃ የተለያየ ነው፡፡ በየአካባቢው ለመጣው ለውጥ ግን የሁሉም ትግል አስተዋፅኦ አለበት፡፡ ነገር ግን ህወሓት ትግራይ መሰረቴ ነው ብሎ ስለሚያስብ፣ አፈናው የበረታ ሊሆን ይችላል እንጂ ትግል አልተደረገም ማለት አይደለም፡፡ ዛሬ የመጣው ለውጥ ውጤት ደግሞ የሁሉም ድምር ትግል ውጤት ነው፡፡ እኔ የአንድ አካባቢ ትግል ውጤት ብቻ አድርጌ አልወስደውም። የኢህአዴግ አመራር ለውጥ እንዲመጣ ያስገደደው የአንድ አካባቢ ትግል ብቻ አይደለም፡፡ ምናልባት በሚዛን ሊለያይ ይችላል፡፡ ኦሮሚያ ውስጥ ሚዛኑ ከፍ ሊል ይችላል እንጂ ዛሬ የመጣው የለውጥ ተስፋ የሁሉም ኢትዮጵያውያን የትግል ውጤት ነው፡፡ ሁሉም አካባቢ የየራሱ አስተዋፅኦ አለው፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ አዲስ ባዋቀሩት ካቢኔ ላይ ምን አስተያየት አለዎት? 

እኔ የብሔር ተዋፅኦ ላይ የፈለገ ቢሆን ችግር የለብኝም፡፡ አንድ ሰው በደንብ እስከሰራ፣ ዲሞክራሲያዊ እስከሆነ ድረስ በተዋፅኦ ላይ ብዙም ትኩረት አላደርግም፡፡ ዞሮ ዞሮ በሁላችንም ላይ የሚወሰን መዋቅር ስለሆነ ዋናው የሚታየውና መመዘን ያለበት በዲሞክራሲያዊ አሰራሩ ነው፡፡ የኔ ብሄር አልተወከለም ማለት፣ ስልጣንን የመቀራመት አስተሳሰብ እንጂ፣ የተሾመው ሰው ኃላፊነቱ፣ ሁሉንም ዜጋ እኩል የማገልገል ነው፡፡ እርግጥ ነው ተዋፅኦ መኖሩ አስፈላጊ ነው፡፡ እኩልነትን፣ ሃሳብን በነፃነት የመግለፅ መብትን ሊያመላክት ይችላል፡፡ በአጠቃላይ እንግዲህ በኢህአዴግ በርካታ የካቢኔ ለውጦች ተደርገዋል፡፡ በዶክተሮች የተሞላ ካቢኔም ተሹሞ ያውቃል፡፡ ይሄ አልሰራም፡፡ ምክንያቱም መሰረታዊ መዋቅራዊ ለውጥ እስካልተደረገ  ድረስ ሰው መመደብ ብቻውን ፋይዳ የለውም፡፡ የተመደበው ሰው ከፍተኛ ብቃት ቢኖረው እንኳ የተበላሸው መዋቅር እስረኛ ነው የሚሆነው፡፡ ሰውየው አዋቂና ብልህ ቢሆን እንኳ በመዋቅሩ ስር ነው የሚሆነው፡፡ ከዚህ አንፃር ካቢኔ ለውጥ እንዲያመጣ የመዋቅር ለውጥ ያስፈልጋል፡፡ ሴቶች ወደ አመራር መምጣታቸው በእጅጉ የሚደገፍ ነው፡፡ ነገር ግን ዋናው ጉዳይ የሚሰሩበት መዋቅር ምን ያህል የተስተካከለ ነው የሚለው ነው፡፡ እንደ ድሮው በኢህአዴግ ማዕቀፍ የሚሰሩ ከሆነ ለውጥ አይመጣም። ህዝብ እያሳተፉ ህዝብ በነፃነት ሲንቀሳቀስ፣ እነሱም በፓርቲ መዋቅር ሳይተበተቡ፣ በነፃነት ሲሰሩ ነው ኃይልና ጥንካሬ የሚያገኙት፡፡ ምናልባት በዚህኛው ካቢኔ  ሴቶች ወደ ስልጣን መምጣታቸው በጎ ሊሆን ይችላል፡፡ አጠቃላይ የመንግስት መዋቅር ለዲሞክራሲ የሚያመች ካልሆነ ግን ሥራቸው ከንቱ ድካም ነው የሚሆነው፡፡ የለውጡ ሃሳብ በመዋቅር ደረጃ ገና ታች አልደረሰም፡፡ ያለው መዋቅራዊ አሰራርና አስተሳሰብ በፊት የነበረው ነው፤ የተለወጠ ነገር የለውም፡፡ የካቢኔ ለውጥ ብቻ ሳይሆን የመዋቅርና የአስተሳሰብ ለውጥ ያስፈልጋል፤ ለውጥ የሚመጣውም ይህ ሲሆን ነው ብዬ አምናለሁ፡፡

በአሁኑ ወቅት በወልቃይትና በራያ አካባቢ ከማንነት ጥያቄዎች ጋር በተያያዘ ግጭቶች እየተባባሱና የሰዎችን ህይወት እየቀጠፉ ነው፡፡ እርስዎ መፍትሄው ምንድን ነው ይላሉ?

እኔ ከዚህ በፊትም ተናግሬያለሁ፡፡ ለእንዲህ ያሉ ችግሮች ዋንኛ መነሻው ኢህአዴግ ራሱ ነው፡፡ ብአዴንም ህወሓትም አካባቢያቸውን፣ ህዝባቸውን በአግባቡ መምራትና ማስተዳደር ስላልቻሉ የተፈጠረ ችግር ነው፡፡ በየአካባቢው ዲሞክራሲን ማስፈን ስላልቻሉ፣ የመረጡት መንገድ ህዝቡን በመለያየት ማጋጨትን፣ በዚህ ደግሞ በስልጣን መቀጠልን ነው የፈለጉት፡፡ የሁለቱ ድርጅቶች ኢ-ዲሞክራሲዊ አካሄድ ነው በወልቃይትና በራያ ችግር እየፈጠረ ያለው፡፡ ነፃነት ካለ ለእንዲህ ያለው ችግር የራሱ መፍትሄ አለው። ህዝቡ በነፃነት መንቀሳቀስ የሚችል ከሆነ፣ ባለው ህገ መንግስትም ቢሆን መፍትሄ መስጠት ይቻላል፡፡ ህዝቡ ተነጋግሮ ጥያቄ ያቀርባል፤ ለጥያቄው በውይይት መልስ መስጠት እንጂ አፈና ዘላቂ መፍትሄ አይሆንም። በሌላው አካባቢም እንዲህ ያለ ጥያቄ ይነሳል፡፡ እንዲህ ያለው ጥያቄ መነሳት ያለበት ከመርህ አንፃር ነው፡፡ ኢትዮጵያ የተዋቀረችበትን አጠቃላይ መዋቅር ማጤን ያስፈልጋል፡፡ ከኢህአዴግ በፊት ኦሮሚያ፣ አማራ፣ ደቡብ፣ ትግራይ፣ ሶማሌ የሚባል ክልል አልነበረም፡፡ ኢህአዴግ ያመጣው ብሄርን መሰረት ያደረገ አከላለል ነው፡፡ አሁን ያለውን አከላለል ህዝቡ ለመለወጥ ከፈለገ ሃሳቡ መደመጥ አለበት፡፡ ነገር ግን ይሄ በህገ መንግስት የተከለለ አከላል ሳይለወጥ ጊዜን መሰረት አድርጎ፣ “ይሄ የኔ መሬት ነው” ማለት ትክክል መስሎ አይታየኝም። ለማንኛውም ለዚህ ሁሉ ችግር ህዝቡን ማሳተፍና ህዝቡ እንዲወስን ማድረግ እንጂ ልሂቃኑና ገዥዎቹ የሚያደርጉት ቅስቀሳ ተገቢ አይደለም፡፡ ህዝቡ ሲወስን መፍትሄ ያገኛል እንጂ በብአዴን ወይም በህወሓት ውሳኔ የሚመጣ መፍትሄ የለም፡፡ እነሱ ጭራሽ ለህዝቡ የግጭት አጀንዳዎችን እያመረቱ ነው ያለው፡፡ ስልጣናቸውን ለማስቀጠል የሚፈጥሩትን ግጭት ልንቀበለው አይገባም፡፡ ስርአትና ወግ ባለው መልኩ ጥያቄዎች ማቅረብ፣ በዚያው ወግና ስርአት ምላሽ መስጠት ያስፈልጋል፡፡ እንዳለመታደል ሆኖ ግን ይሄ ነገር በኛ ሃገር አልተፈጠረም፡፡

የትግራይ ክልል ከተዋቀረ በኋላ የመጀመሪያው የክልሉ ፕሬዚዳንት እርስዎ ነበሩና—በወቅቱ አከላለሉ እንዴት ነበር? ጥያቄ የሚነሳባቸው አካባቢዎችስ እንዴት ነው ወደ ትግራይ የተካለሉት?

በሽግግሩ ጊዜ ይሄን የሚያስፈፅም ኮሚሽን ተቋቁሞ ነበር፡፡ ክልሎች ሲፈጠሩ ከሁሉም ተውጣጥቶ በተቋቋመው ኮሚሽን ስሪት ነው፡፡ ኮሚሽኑ ነው ያካለለው፡፡ በዋናነት  ቋንቋን መሰረት አድርጎ ነው ያካለለው፡፡ በወቅቱ የነበረው ዋነኛ መመዘኛ፣ አካባቢው በስፋት ምን ቋንቋ ይነጋገራል የሚለው ነበር፡፡ በዚህ መሰረት ነው ሁሉም ክልል የዛሬ ቅርፁን የያዘው፡፡ በወቅቱ እንደውም በአፋር የነበሩ በርካታ ወረዳዎች፡- ዳሎል፣ በራይሌ፣ አፍዴራ ሁሉ በትግራይ ክፍለ ሃገር ስር ነበሩ፡፡ ነገር ግን በአካባቢው የሚነገረው ቋንቋ አፋርኛ ስለሆነ ወደ አፋር ክልል ተወሰዱ፡፡ የራያና ወልቃይት አካባቢም አብዛኛው ትግርኛ ተናጋሪ በመሆኑ ነው ኮሚሽኑ ያካለለው፡፡ እንግዲህ ያኔ፣ ይሄን ያህል የጎላ ጭቅጭቅ አልነበረም፡፡ እየቆየ ሲሄድ ነው ጭቅጭቁ የተፈጠረው፡፡ አሁን ጥያቄው ከአስተዳደር ጉዳይ አልፎ ፖለቲካዊ ሆኗል፡፡ ያኔ ግን የተካለለው፣ በአንድ ኢትዮጵያ ስር ያለ የአስተዳደር ወሰን በሚል ነው፡፡ አሁን ግን ድንበሩ ልክ እንደ ሀገር ነው እየተወሰደ ያለው፡፡ የብሄርተኝነቱ ፅንፍ ከፍተኛ ደረጃ በመድረሱ፣ እንደ ሃገር የመካለል ፍላጎት በማየሉ አሁን ጥያቄው ከአስተዳደር ወደ ፖለቲካዊ ጥያቄ አድጓል፡፡ ለኔ አሁንም ቢሆን መሬቱ ሳይሆን ህዝቡ ነው ወሳኙ፡፡ ይሄ አስተሳሰብ ቢጎለብት መልካም ነው፡፡

ይሄ ችግር ብዙ ቁርሾና ደም መፋሰስ ሳያስከትል ሊፈታ የሚችለው እንዴት ነው ይላሉ?

ይሄ ጉዳይ በአጠቃላይ በሀገሪቱ ያለው ፖለቲካ የፈጠረው ነው፡፡ የትኛው ፖለቲካ አይሎ ይወጣል የሚለው በቀጣይ የሚታይ ቢሆንም፣ ቋንቋን መሰረት ያደረገ አከላለል አያስፈልግም የሚሉ በአንድ ወገን፣ አሁን ያለው ተጠናክሮ መቀጠል አለበት የሚሉ በሌላ ወገን አሉ፡፡ ነገር ግን በመሰረታዊ ደረጃ ውሳኔው ለህዝብ ነው መተው ያለበት፤ ህዝቡ እንዲወስን መደረግ አለበት፡፡ በጦርነት መፍትሄ አይመጣም፡፡ የፈለገ ኃይል ቢኖር ትርፉ ጥፋት ነው፡፡ በጦርነት እስከዛሬ የመጣም የሚመጣም ትርፍ የለም፡፡ አከላለሉ የአስተዳደር ነው እንጂ በአንድ ሃገር ስር ነው ያለነው፡፡ ለዚህ እንዴት ወደ ጦርነት ይገባል? የህዝብ ውሳኔ መከበር አለበት፡፡ ለዚህ ደግሞ መንግስት ዲሞክራሲውን ማስፋት አለበት። ህዝቡ ዲሞክራሲ እንዲመጣ ነው ትግል ማድረግ ያለበት፡፡ ዲሞክራሲ ሲመጣ ህዝቡ ራሱ እየተገናኘ ይወስናል፡፡ በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል ህዝብ መገናኘት መጀመሩ የፈጠረውን ነገር ማየት ለዚህ በቂ ነው፡፡ ሁሉም ወገን  የጥላቻ ግንብ ከመገንባት መታቀብ አለበት፡፡ የዲሞክራሲ፣ የፍትህ፣ የነፃነትና የመልካም አስተዳደር እጦት ነው ይሄን ሁሉ የፈጠረው የሚል እምነት አለኝ፡፡ መሬቱ እኮ በአንድ ፌደራላዊት ሃገር ስር ያለ ነው፡፡ ህዝቡም በዚያ ስር ያለ ነው፡፡ በዚህ አይነት ግጭቶች ውስጥ የክልል መንግስታት ተሳትፎ አድርገዋል፡፡ ነገር ግን በኢህአዴግ ውስጥ እስካሁን ለእነዚህ ጥፋቶች፣  መፈናቀሎች —- ኃላፊነት ወስዶ፣ ተጠያቂ የተደረገ የመንግስት ባለስልጣን አላየንም፡፡

አሁን ያለው የፌደራሊዝም አከላለል ለችግሩ አስተዋጽኦ አድርጓል የሚሉ ወገኖች አሉ፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ የእርስዎ  አቋም  ምንድን ነው?

የኔ አቋም ግልፅ ነው፡፡ ከአላለሉ አይደለም ችግሩ። ክፍለ ሃገር ቢባልም ይሄ ግጭት አይቆምም፡፡፡ ክፍለ ሃገር በተባለበት ወቅት ነው፣ የብሔር ጥያቄ ይነሳ የነበረው፡፡ ህወሓት፣ ኦነግ፣ አፋር፣ ሶማሌ — መሳሪያ ያነሱት ክፍለ ሃገር በነበርን ጊዜ ነው፡፡ ስለዚህ መሰረቱ የአከላለል ጉዳይ አይደለም፡፡ ችግሩ ለክልላዊ ማንነትና ሃገራዊ ዜግነት የተሰጠው ትኩረት የተለያየ መሆኑ ነው። ለክልላዊነት የበለጠ ትኩረት ተሰጥቶ ነው የቆየው፡፡ አንዱ ችግር ይሄ ነው፡፡ ሚዛን አለመጠበቁ ነው ትልቁ ችግር፡፡ ለኔ አሁን ያለው አከላለል ችግር የለውም፡፡ ነገር ግን  ይሄ አከላለል በህዝብ ውሳኔም ሊቀየር ይችላል፡፡

አሁን በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል የተፈጠረውን ግንኙነት እንዴት ያዩታል?

ህዝቡ ግንኙነቱን ፈልጎታል፡፡ በግልፅ እየታየ ያለ ነገር ነው፡፡ ህዝቡ እድሉ ሲከፈትለት ማንም ሳይገፋው፣ ድንበር ጥሶ ነው ወደ ኢትዮጵያ የመጣው፡፡ የኢትዮጵያ ህዝብም በኤርትራ ውስጥ ጥሩ እየተንቀሳቀሰ ነው፡፡ ይሄ ህዝቡ ምን እንደፈለገ በግልፅ የሚያሳይ ነው፡፡ አሁን ያለው የህዝቡ ግንኙነት በሁለት ሃገር ሳይሆን በአንድ ሃገር ያለ ያህል ነው፡፡ የህዝቡ ግንኙነት ሲታይ፣በሁለት ሃገር ውስጥ የነበሩ አይመስሉም፡፡ በዚያው ልክ ደግሞ ሁለት ሉአላዊ ሃገሮች መሆናችን መረሳት የለበትም፡፡ ሁለት ሃገር ስለሆንን በሚገባ አለማቀፍ ህግ፣ ደንብ ኖሮ እንቅስቃሴውና ግንኙነቱ ቢጠናከር መልካም ነው፡፡ አሁን ላይ ሁለቱ መንግስታት በዝርዝር የተስማሙባቸውን ጉዳዮች በግልፅ አናውቅም። ይሄን የማወቅ መብት አለን፡፡ አካባቢው ስሱ ጂኦ-ፖለቲካዊ አካባቢ ነው፡፡ ከዚህ አንፃር እያንዳንዱ ግንኙነት መታየት አለበት፡፡ ኢትዮጵያ ከዚህ ግንኙነት ምን አገኘች የሚለው በደንብ መታየት አለበት። ከአሁን በፊትም ለጦርነቱ መንስኤ የሆነው ግልፅ ያልሆነ ግንኙነት መፈጠሩ ነው፡፡ ከዚያ በመማር አሁን ግንኙነቱን ግልፅና ዓለማቀፋዊ ህግጋትን የተመሰረተ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ መልክ መያዝ አለበት፡፡

በርካታ የፖለቲካ ድርጅቶች ወደ ሃገር ቤት ከመመመለሳቸው አንጻር፣ በሀገሪቱ ምን አይነት የፖለቲካ ሁኔታ ሊፈጠር ይችላል ብለው ያስባሉ?

አሁን ባለው ሁኔታ ፖለቲካችን ወዴት አቅጣጫ ሊያመራ ይችላል፣ አሰላለፉስ ምን መልክ ይኖረዋል የሚለውን ለመገምገም አስቸጋሪ ነው፡፡ ሁለት የፖለቲካ አቅጣጫዎች ግን በፖለቲካ አውዱ ላይ ቀርበዋል፡፡ አንደኛው አሁን ያለውን የብሄር ብሄረሰቦች ፖለቲካ መሰረት አድርገን  ወደፊት እንጓዝ የሚል ሲሆን በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ ይሄ የብሄር ፖለቲካ ኢትዮጵያን ለኪሳራ ስለዳረጋት የሚያስፈልጋት የዜግነት ፖለቲካ ነው፤ ክልላዊ አከላለሉም ለዜግነት ፖለቲካ ችግር የፈጠረ ስለሆነ መፍረስ አለበት የሚሉ አሉ፡፡ ሁለቱ የፖለቲካ አቅጣጫዎች አሁን በሀገሪቱ የተፋጠጡ ይመስለኛል፡፡ በኔ አስተያየት ሁለቱም ሳይጣረሱ መታረቅ አለባቸው፡፡ የብሄር ፖለቲካና የዜግነት ፖለቲካ እኩል ቦታ የሚያገኙበት አማራጭ መፈለግ አለበት፡፡ ምክንያታዊ ፖለቲካ፣ ሃሳባዊ ፖለቲካ እየተደፈጠጠ፣ ብሄር ላይ የተንጠለጠለ ያውም ፅንፍ የብሄር ፖለቲካ  ኃይልና ተሰሚነት ያገኘበት ሁኔታ ነው አሁን የተፈጠረው፡፡ በሀገር አንድነት አምናለሁ ሲል የነበረ ሳይቀር ብሄሩን እየፈለገ የመሸገበት ሁኔታ እየታየ ነው፡፡ ለኢትዮጵያ ቀጣዩ ተግዳሮት፣ የፅንፈኛ ብሄርተኝነት ፖለቲካ ነው፡፡ የብሄርና የዜግነት ፖለቲካ ሚዛን ጠብቀው የሚሄዱበት ሁኔታ  እንዴት ይፈጠር የሚለው ነው ዋናው ጥያቄ፡፡ አሁን ሁሉም ሃይሉን የማሳየት ሁኔታ ውስጥ ነው ያለው፡፡ ያም ቢሆን እኔ እንደ ፖለቲከኛ እነዚህ ሁሉ ጊዜያቸውን ጠብቀው ይረግባሉ በሚል ተስፋ ነው የምመለከተው፡፡ መፍትሄ ለማምጣት ግን  ቁጭ ብሎ መነጋገር መደማመጥ ያስፈልጋል፡፡ ይሄ ካልሆነ ግን ሃገሪቱ ወዳልሆነ አቅጣጫ ልታመራ  ትችላለች፡፡

አሁን ባለው ሁኔታ  የ2012 ብሔራዊ ምርጫ የሚካሄድ ይመስልዎታል?

እስካሁን ስለ ምርጫው ምንም እየተባለ አይደለም። ዝግጅትም እየተደረገ አይደለም፡፡ በዚህ ሁኔታ ከቀጠልን ደግሞ ከዚህ ቀደም የነበረው የሚደገም ይመስለኛል፡፡ ባለፉት ጊዜያት በሀገራችን ምርጫ አልተደረገም፡፡ ኢህአዴግ ራሱ ቆጣሪ፣ ራሱ ታዛቢ፣ ራሱ መራጭ፣ ራሱ ዳኛ ሆኖ ያሸነፈበት ምርጫ፤ እንደ ምርጫ ሊቆጠር አይገባውም፡፡ ምርጫን የሚያስፈፅሙ ተቋማት በቅድሚያ መኖር አለባቸው። እነዚህ በሌሉበት ምርጫ ይደረግ ቢባል ከዚህ ቀደም ከነበረው የተለየ ነገር አይመጣም፡፡ እነዚህ ተቋማት በቅድሚያ መቋቋም አለባቸው፡፡ ተቋማቱ ኢህአዴግ በፈለገው መንገድ አይደለም መቋቋም ያለባቸው፤ ከሁሉም ተቃዋሚዎች ጋር ቁጭ ብሎ መምከር አለበት፡፡ ይሄ ሂደት ከተጀመረና አስተማማኝ ከሆነ በኋላ ለምርጫ የቀረው ጊዜ ዝግጅት ለማድረግ ይበቃል አይበቃም በሚለው ላይ ተነጋግሮ መወሰን ይቻላል፡፡ ምርጫው በመተማመን መራዘሙ ሳይሆን ምርጫውን ለማድረግ የሚያስችሉ ተቋማት ይፈጠራሉ አይፈጠሩም የሚለው ነው መታየት ያለበት፡፡ አሁንም እኔ መፍትሄውን አመጣላችኋለሁ እንጂ እናንተም የመፍትሄ አካል ሆናችሁ በተግባር ተሳተፉ ሲባል እስካሁን አላየሁም፡፡ እኔ በ2012 የሚደረገው አንድ ምርጫ አይደለም አሁን የሚያሳስበኝ፡፡ ዋናው አስፈላጊ የዲሞክራሲ ተቋማት በዘላቂነት ተቋቁመዋል ወይ የሚለው ነው፡፡ ዲሞክራሲያችን ዘላቂነት የሚኖረው እነዚህ ተቋማት በአስተማማኝ መሰረት ሲቋቋሙ ብቻ ነው፡፡

Filed in: Amharic