>
5:13 pm - Monday April 19, 1013

...ሸገር ደርሶ መልስ (ክንፉ አሰፋ)

...ሸገር ደርሶ መልስ

ንፉ አሰፋ

 

“እጅግ ብዙ መጻህፍት፤  በጣም ጥቂት ጊዜ…” እንዲል ፍራንክ ዚፓ!  በባለፈው ማስታወሻዬ ላይ እነሱ የሚነግሩን እድገት እና  እኛ የተመለክተነውን  እድገት በስሱ ለማሳየት ሞክሬያለሁ። የዶ/ር አብይ አስተዳደር ስልጣን ከመያዙ ጥቂት ወራት በፊት አንድ ከፍተኛ የደህንነት ሰው በተንቀሳቃሽ ስልኬ ላይ ደውሎልኝ ነበር።

“ሃገሪትዋን እድገት እና ትራንስፎርሜሽን ምን ላይ እንደደረሰ ሃገር ቤት በአካል ሄደህ ተመልከት።ለጉዞህ ዋስትና እንሰጥሃለን… ምኑንም ሳትመለከት መተቸቱ ተገቢ አይደለም።”

ነበር ያለኝ የደህንነቱ ሰው። ሰውዬው አንዴ በሼክስፒር ፈይሳ በኩል ሌላ ግዜ በወዳጆቸ በኩል እየደጋገመ ወተወተኝ።  

እድገቱን ከሩቅ ሳይሆን ከቅርብ፤  በጆሮ ሳይሆን በአካል እየተመለከቱ ይዘግቡ የነበሩ ጓደኞቼን ቅሊንጦ እና ዝዋይ እስር ቤት ውስጥ አጉሮ፤ እኔን መጋበዝ ስድብ እንደሆነ ነግሬው ነበር የተለያየነው። ግዜ የማይፈታው የለምና በአካል አየሁት። እሱም ቢሆን ዛሬ ቀን ሲጥለው የጨበጣ እድገቱን በውጭ ሳይሆን በውስጥ አይኑ እየተመለከተ፤  እንደ ካሮት ቁልቁል በሚወርደው እድገት ይሳቀቅ ይሆናል ብዬ አስባለሁ።

***

በጉዞዬ ላይ አንድ ነገር አስተዋልኩ። ማንኛውም ዲያስፖራ ስለሃገሪቱ የሚኖረው የመጀመርያ እይታ ውሎ ሲያድር እንደሚቀየር። የመጀመርያ እይታ እጅግ ይጋነናል። ያስደነግጥማል። ውሎ ሲያድር ግን ሁሉም እየተለመደ ይሄዳል። በመጀመርያ እይታዬ ቆሻሻ መንገድ ላይ ሲጣል አይቼ ደንግጬ ነበር። ሰዎች በአደባባይ ቆመው ሽንት ሲሸኑ ስመለከት ደግሞ የቆሻሻው ነገር ምንም አላስገርም አለኝ። ማየት ማመን ነው። መቆየት ደግሞ መላመድ ይሆናል።

***

አትላንቲክን ተሻግሬ ሃገሬን ለማየት በቅጽበት የወሰንኩት፤ አራቱ የኦሮሞ ድርጅቶች መግለጫ ስላሳሰበኝ ነበር። ነገ ሚሆነው ነገር አይታወቅም። በምድር ላይ ስንኖር፤ አጋጣሚ እና ግዜ ወሳኝ ነገሮች ናቸው።  በሕይወት ውስጥ አንዴ ከሄዱ የማይመለሱ ነገሮች!  ንብረት ሳይኖራቸው፤ አየር ንብረት እያማረራቸው ሃገር ቤት የገቡ ወንድሞቻችን አዲስ ህግ አውጥተው በላያችን ላይ ሳይጭኑብን ይህችን አጋጣሚ መጠቀሙ ነው የሚበጀው።

አጋሮ ላይ ነበር ያቆምኩት።…

በከተማው ከንቲባ እና በቄሮ መካከል የነበረው ፍጥጫ ለሁለተኛ ቀናት ሲቀጥል፤ ፌደራል ፖሊስ ጣልቃ ገብቶ ቄሮ ላይ መተኮስ ጀመረ። በቶክሱ የአንድ ወጣት ህይወት ማለፉም ተነገረ። ጠቅላይ ሚንስትሩ በእኔ ዘመን ግድያ አይደለም የሚሰደድ እና የሚያሳድድ አይኖርም ያሉትን ቃል ፌደራል ፖሊስ አፈረሰባቸው።  ሲኖር ኢትዮጵያውያዊ ያልነበረውን ቄሮ፣ ፖሊስ በአንድ ጥይት “ኢትዮጵያ” ያደረገበትን ትእይንት በዚያች ቅጽበት ልታዘብ ቻልኩ። ድርጊቱ እጅግ ያሳዝን ነበር።  መረጃው ግን አሁንም እንደታፈነ ነው።

በዚህ ወጣ-ገባ የፖለቲካ፤ ጥፋትና ሃጥያቱን “ለውጡን ለማደናቀፍ ቆርጠው ተነስተዋል”  ለተባሉ ተዋንያን ብቻ ትቶ ማለፍ አግባብ አይሆንም።  የ “አሸናፊ ነን” ፖለቲከኞችና አክቲቪስቶች ጥቃቅን እጆችም የችግሩ አዋላጆች ሆነው አይተናል። ትልቁ ስህተት የኦነግ መግባትና የህወሀት ዘራፊዎች አለመታሰር እንደሆነ በስፋት ይነገራል።  የሴራ ፖለቲካ የሚያጎነጉነው  ዳውድ ኢብሳ እንደ አብዲ ኢሌ ከርቸሌ መግባት እንዳለበት የሚናገሩ ጥቂት አይደሉም። የአዲስ አበባው የአኦነግ ሰርግ እና ምላሽ የህወሃት ኢንቨስትመንት ውጤት እንደሆነ በስፋት ይነገራል።  በሚሊዮኖች ወጪ ተደርጎበታል።   እርግጥ ነው ኦነግ በጅማ እና አጋሮ ላይ ክስረት ባይደርስበት ኖሮ ይህንን አናምን ይሆናል። ኦነግ በጂማ ስታድየም የጠራው ስብሳባ ስላልተሳካ ዜናው በመገናኛ ብዙሃን ላይ እንኳ እንዳይወጣ ሆኗል። ጃዋር መሃመድ አይወክለንም የሚሉ ቄሮዎች ቁጥርም እጅግ ብዙ ነው። በሃገሪቱ ሁለት መንግስት እንዳለ ሲናገር ነበር የዚህ ሰው ውስጣዊ ፍላጎት የተባነነበት። በከተማ እና በገጠሩ ሁሉ ተለጥፎ የሚታየው የለማ እና አብይ ፎቶ እንጂ የዳውድ ወይንም የጃዋር አለመሆኑ ራሱ የክስረታቸው ምልክት ነው።

የባንድራ አይነቶች፤ ፎቶ እና ምስሎች በየ ግድግዳው እና በየ ታክሲው ላይ ተለጥፈው ይታያሉ።  በአንድ ግድግዳ ላይ የተለጠፈ ምስል ስመለከት አልበርት አንስተይንን ጥቅስ አስታወሰኝ። “ህይወትን ለመምራት ያሉት መንገዶች ሁለት ብቻ ናቸው።  አንደኛው ተዓምር የሚባል አንዳች ነገር እንደሌለ በማሰብ ሲሆን፤  ሌላኛው ደግሞ ሁሉም ነገር ተዓምር ነው በሚል ነው!”። ቀልቤን የሳበው አንድ የመከረኛ የዲያስፖራ ፎቶ ነበር። የ“ቀን ጅብ”  ከሚሏቸው ሰዎች መሃል በተለጠፈው በዚህ ፎቶ ስር፤ “የለውጥ አደናቃፊዎች!” የሚል ተጽፎበታል። ምናልባት ልጁ ፎቶውን ሲልክ እንዴት እና ከነማን ጋር መውጣት እንዳለበት ያለማስተንቀቁን ተረዳሁ። ለፎቶ ለጣፊዎች ማንም ይሁን ምን ፎቶው መውጣቱ ነው ግድ የሚላቸው። የልቅሶም ይሁን የታክሲ ሰልፍ ላይ ይዘው ፎቶ መነሳት።   የዋናውን ሰው ፎቶ ሲያጡ የወንድሙን ከለጠፉበት ክስተት የባሰ በይሆንም ከሌቦቹ ተርታ መሰየሙ ጉዳይ ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ ያመዝናል።  

እዚያው እያለን ቤተ-መንግስት እንደተከበበ ሰማን። ኢንተርኔት ተቋረጠ። በአራት ኪሎ መስመር ትራንስፖርት ተቋረጠ። መንገድም ተዘጋ። ይህ በተራው ለማህበራዊ ሜድያው ግምቶች እና ሁነታዊ ትንተናዎች ቀዳዳ በር ከፈተ። ነጻ ናቸው የተባሉ መገናኛ ብዙሃን እንደቀድሞው ዝምታን መረጡ።

የመንግስት መገናኛ ብዙሃን ገና ከፍርሃት አልወጡም። በይዘትም ሆነ በቅርጽ አልተለወጡም። በአመለካከትም አልተለወጡም።  በአካልም ቢሆን ከዚህ በፊት የምናየውን ፊት ነው አሁን የምንመለከተው። ከዲያስፖራው አባላት ጋር የሚደረጉ ቃለ-ምልልሶችን ይቆራርጣሉ።  ትችቶችን ሳንሱር እያደረጉ አያስተላልፉም። ልክ እንደ ቀድሞው፤ ከማለዳ እስከ ሌሊት እየደጋገሙ የዶ/ር አብይን የአዋሳ ንግግር ያቀርቡልናል። አድርባይነት ካልሆን በቀር ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህንን አይነቱን አሰራር የሚሹ አይመስለኝም። ፕሮፓጋንዳ ህዝብን በእጅጉ ጎድቷል። ለመንግስትም አልበጀም።  ገንቢ ትችት ያሳድጋል እንጂ አያጠፋም።  የመንግስት ጋዜጠኞች ገና ብዙ ይቀራቸዋል።

ጠቅላዩን ለመግደል ቤተ-መንግስቱን የከበቡት ወታደሮች በሰልፊ ፎቶ ሲነሱ ምሽት ላይ አሳዩን። ወታደሮቹ  ዶ/ር ዐብይን አግተው ፎቶ ተነሱ የሚለው ወሬ የቀኑ ቀልድ ሆኖ አልቀረም። ረፍዶም ቢሆን እውነቱ ወጣ።  ጠቅላይ ሚኒስትሩ ፓርላማው ላይ የተናገሩት መራራ ሃቅ የማህበራዊ ሜዲያውን ግምት አረጋግጧል።   መገናኛ ብዙሃን በዚህ መልኩ የሚቀጥል ከሆነ፤ ማህበራዊ ሜድያውን ከመምራት ይልቅ ራሱ በማህበራዊ ሜዲያ ተመሪ ይሆናል። ይህ ደግሞ አደጋ አለው።

***

ሕዝብ አሁንም በተስፋ ነው ያለው። ከለውጡ በኋላ በኑሮው ላይ የተለወጠ ነገር የለም። ብልጭ እያለ እንደሚጠፋው መብራት ተስፋውም እንዲያው ይመጣና ይሄዳል።  ትንሽ ትልቁ “ተጧሪ” በሆነበት ዘመን፤ ሕዝቡ በተስፋ ብዙ የቆየ ይመስላል። ተስፋ ደግሞ መንፈስን እንጂ ሆድን አይሞላም። ለውጡ ከቃል አልፎ የሕዝቡን ህይወት እስካልቀየረው ድረስ ጉቦ እና ማጭበርበር ሊቆም አይችልም። ይህ ደግሞ ትንሽ ግዜ ይጠይቃል።

አንድ ምሽት ላይ የአዲስ አበባ ትልቁ “የጉርሻ” ምግብ መሸጫ ስፍራ ወጣ ብለን ታክሲ ጠራን።

“የት ላድርሳችሁ?”

“ሸራተን”

“መቶ ሃምሳ ትከፍላላችሁ?”

“እሺ፤ ይሁን” ብለን ተሳፈርን።

ባለታክሲው ግን ወደ ሸራተን አቅጣጫ ሳይሆን ወደ ጊዮርጊስ ይዞን ይጓዝ ጀመር። ሁላችንም ግራ በመጋባት ጠየቅነው።

“ወዴት እየወሰድከን ነው?”

“ሸራተን ምግብ ቤት ነዋ። ይኸው ደርሰናል።”  ብሎ ሲመልስልን ነበር ሸራተን የሚባል ምግብ ቤት እንዳለ የተገነዘብነው።  እኛ የፈለግነው የሼኩ ሸራተን እንደሆነ ሲረዳ ግን ሂሳቡን በሶስት እጥፍ ጨመረ። የሸገር ታክሲዎችን ታሪፍ የሚወስነው፤ በጉዞ ርቀት ሳይሆን በሚሄዱበት ስፍራ ነው።  ባለታክሲውን “ወደ ሂልተን ውሰደኝ” ካሉት ፈጥኖ የሚተይቀው “ውስጥ ወይንስ ውጭ?” ይሆናል። መልሱ ውስጥ ከሆነ፤ ዋጋውን ያንረዋል።

ከሸራተን ሆቴል ሳንወጣ አንድ የታዘብኩትን ነገር ማስታወሻዬ ላይ አሰፍረኩት። “ሰንሴት” የተባለች ባር ውስጥ ያለች አንዲት የሼኩ ወንበር ላይ እስካሁን የተቀመጠባት ሰው አልነበረም። ተፎካካሪ ፓርቲዎች እና አክቲቪስቶች ሲገቡ ግን ወንበርዋ ተደፈረች። የዘመኑ ባለ ሃብቶች እና አክቲቪስቶች ወንበርዋ ላይ ጉብ ብለው ቀርቶ የነበረውን የአዝማሪ ሽልማት እንደቀጠሉት ሰማን።  ልክ እንድ ሼኩ፤  ብር እየመዘዙ ይበትኑ እንደነበር ተነገረን። አቦይ ስብሃት ነጋ እና ጌታቸው አሰፋ እንደ ግል ሃብታቸው ይዘው ይጠጡባት የነበረ ወንበር፤ አሁን በእነ ሌንጮ ቁጥጥር ስር ውላለች። የአርባ እና ከዚያ በላይ ትግል ዋና አላማ ይህ ነበር እንዴ ብለው የሚጠይቁ ታዛቢዎች ጋር ፊት ለፊት ተጋፈጥን። ሌላው ሲያደርገው የምናወግዘውን ነገር፤ እና ስናድርገው ግን ጽድቅ የሚሆንበት እንቆቅልሽ!

***

በተለምዶ ቺቺንያ ተብሎ የሚጠራው ሃያ ሁለት ማዞሪያ አካባቢ የሚገኝ ሰፈር አሁንም እንደ ጋለ ነው። ገላቸውን እየሸጡ የሚኖሩ ውብ ኮረዳዎች መንገድ ላይ ተኮልኩለዋል። የአዝማሪ ቤቶችን ለማሞቅ የተሰለፉ ውድ የሚባሉ ተሽከርካሪዎች እዚህ ስፍራ ይታያሉ።  ከሱ ትንሽ ወረድ ብሎ የተመሰረተው የ”ፂፂኒያ” መንደር አልፎ አልፎ የትግርኛ ዘፈን ከመሰማቱ ውጭ ቀዝቀዝ ብሏል።  የግዜ ጀግኖች ተሰባስበው መቀሌ ላይ ባይከትሙ ኖሮ በዚያ ስፍራ መደማመጥ እንዳማይቻል፤ ማለፍያ እንኳ እንደማይገኝ ተነገረን።

አንድ ያስደሰተኝ ነገር ቢኖር ሰዎች በችግራቸው ላይ መቀለዳቸው ነው። ሰው ሁሉ በራሱ ላይ ይቀልዳል፣ በኑሮ ይቀልዳል፣ በባለግዜዎችም ላይ ይቀልዳል።  

“ኦሮሚያ እና ትግራይን የሚያዋስን ቦታ ጥራልኝ!” ብሎ ጠየቀኝ አንዱ ቀልደኛ።  

በጂኦግራፊ ላይ ትግራይን ከኦሮሚያ የሚያዋስን ስፍራ እንደሌለ መለስኩለት።

“ለገጣፎስ?” አለኝ እየሳቀ። ህወሃት እና ኦህዴድ ከኦሮሞ ገበሬ እዚህ ግባ በማይባል ገንዘብ እየነጠቁ ስፍራውን ለትግራይ ተወላጆች መስጠታቸውን ተገነዘብኩ።  

ሰዎቹ ይሉኝታ ቢስ፤ ህሊና ቢስ ሲሆኑ የሌላው ብስጭት ለግዜው ከጣርያ አላለፈም ነበር። ሰዉም ቢሆን ወዶ አይደለም።  አንድ ታክሲ ላይ ያነበብኩት ጥቅስ ሁኔታውን ይገልጸዋል። “ክቡራን ተሳፋሪዎቻችን። በአገልግሎት አሰጣጣችን ላይ አስተያየት፣ ቅሬታ ወይንም መሻሻል አለበት የምትሉት ነገር ካለ አንቀበልም። ከታክሲው ላይ መውረድ ይቻላል።” ይላል ጥቅሱ።  

ሃገር እንደ ግል ታክሲ በሆነበት አለም ውስጥ፤ ሁለት አማራጭ አለ። ወይ የጫካውን ህግ ትቀበላለህ፤ አልያም ትወገዳለህ። ሁሉንም በደል “አሜን” ብሎ የተቀበለ ሕዝብ ብሶቱ ጫፍ ሲደርስ እንደሚነሳ እንኳ አያውቁም።

በሌላ ታክሲ ሌላ ጥቅስ አየሁ። “ጡትና መንግስት ጊዜውን ጠብቆ መውደቁ አይቀርም!”

ይቀጥላል

(ከኢትዮጲስ ጋዜጣ እትም 6 የተወሰደ)

Filed in: Amharic