>

ለነገ የምትባለው የአድማስ ማዶውን ሀብት የማስመለሱ ዕርምጃ!!! (አጎናፍር ገዛኽኝ)

ለነገ የምትባለው የአድማስ ማዶውን ሀብት የማስመለሱ ዕርምጃ!!!
አጎናፍር ገዛኽኝ
የዓለም አቀፉ ግሎባል ፋይናንሻል ኢንተግሪቲ መረጃ እንደሚያሳየው ከኢትዮጵያ ከ1996 እስከ 2003 ዓ.ም ከአገሪቱ ከ26 ቢሊዮን ዶላር በላይ  በህገ ወጥ መንገድ ወጥቷል። በ2009 ዓ.ም ብቻ ደግሞ  ሦስት ነጥብ 26 ቢሊዮን ዶላር በህገ ወጥ መንገድ እንደወጣ አስታውቋል!!!
 
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ አህመድ ባለፈው ግንቦት ወር በሸራተን አዲስ ሆቴል ከንግዱ ማህበረሰብ ጋር ውይይት ባደረጉበት ወቅት ከኢትዮጵያ ተዘርፎ በተለያዩ አገራት የሚገኝውን ገንዘብ ለማስመለስ መንግሥት ጥረት እያደረገ መሆኑን ይፋ አድርገዋል፡፡ ሆኖም በህገ ወጥ መልኩ ወደ ውጭ የወጣውን ገንዘብ ማስመለስ ቢቻልም እንኳ ሂደቱ ቀላል አይሆንም፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመንግሥት በኩል በህገ ወጥ መንገድ ከአገር የወጣውን ገንዘብ የማስመለስ ጥረት መጀመሩን ጠቅሰው ነበር። ምሁራን በአንድ በኩል በህገ ወጥ መልኩ ከአገር የወጣውን  ገንዘብ ለማስመለስ የምታደርገው ጥረቷ  ቢሳካ እንኳን ለማስመለስ ሂደቱ ከምታወጣው ገንዘብ አይበልጥም። ስለዚህ ለማስመለስ ጊዜና ጉልበት ማጥፋት አይገባም ይላሉ። ሌሎች ምሁራን  ደግሞ በህገ ወጥ መንገድ ወደ ውጭ የወጣውን ገንዘብ  የማስመለስ ሥራው አስቸጋሪ ቢሆንም የተከፈለው መስዋዕትነት ተከፍሎ ሊመለስ ይገባል ይላሉ። ምክንያታቸውም ደግሞ ከዚህ በኋላ መሰል ድርጊት እንዳይፈጸም አስተማሪ ይሆናል የሚል ነው።
የኢኮኖሚና የፖለቲካ ምሁሩ አቶ ካህሳይ ገብረየሱስ እንደሚገልጹት፤ መንግሥት ከአገሪቱ ተዘርፎም ሆነ በህገ ወጥ መልኩ ወደ ውጭ አገራት የሚወጣውን ገንዘብ ለመቆጣጠር የሚያስችል ስርዓት እስከአሁን አልዘረጋም። የአገሪቱ  የፍትህ ተቋማትም በዓለም አቀፍ ደረጃ ካላቸው ተሰሚነት አንጻር  ጫና ፈጥረው  በህገ ወጥ መልኩ የወጣውን ገንዘብ ለማስመለስ የሚችሉ አይደሉም።  በዓለም አቀፍ ህጎች መሰረት በክርክር አሸንፎ ገንዘቡን ለማስመለስ ጠንካራ፣ የተደራጀና ተዓማኒነት  ያለው የአገር ውስጥ መረጃና አሠራር ያስፈልጋል። ይህን መረጃ የሚያመነጭ ተቋምና አሠራር ሳይፈጠር ከአገር የወጣውን ገንዘብ ለማስመለስ መሞከር ውጤታማ አያደርግም። ምክንያቱም የምታሰመልሰውን ገንዘብ ለማስመለስ በሚደረገው ሂደት ከምታወጣው ገንዘብ አይበልጥምና። ስለሆነም ዛሬ ላይ ለማስመለስ መሞከሩ አዋጭ አይደለም ይላሉ።
የሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ የህግ ምሁሩ ረዳት ፕሮፌሰር ሽመልስ አሻግሬ ግን በአቶ ካህሳይ ሀሳብ አይስማሙም። በኢትዮጵያ እየተስፋፋ የመጣው ሙስና  አገሪቱን ዋጋ እያስከፈላት ነው። በሌቦች የሚመዘበረው ገንዘብም  ማረፊያው  ወንዝ ተሻግሮ በተለያዩ አገራት ባንኮች ውስጥ ነው። መንግሥት ሙስናን በቁርጠኝነት እዋጋለሁ ካለ በአገር ውስጥ ብቻ ሳይሆን  በህገ ወጥ መንገድ ተዘርፎ በተለያዩ አገራት ባንኮች የሚገኘውንም ገንዘብ ጭምር ማስመለስ እንደሚኖርበት ያነሳሉ። በህገ ወጥ መልኩ የሄደውን ገንዘብ ለማስመለስም ዓለም አቀፍ ህጎች ይደገፉታል። በዚህ መልኩ ማስመለስ ከተቻለ ከህዝብና ከአገር ዘርፎ የትም ማምለጥ እንደማይቻል ይገልጻሉ። ሆኖም ተመዝብሮ አድማስ ማዶ የሚሻገረውን ገንዘብ ለማስመለስ መደራደር የሚችሉ ጠንካራ ተቋማት መገንባት ያስፈልጋል ይላሉ።
የወለጋ ዩኒቨርሲቲው የህግ ምሁር አቶ ኑርልኝ ሙሉጌታ በበኩላቸው፤ መንግሥት በህገ ወጥ መንገድ ከአገር የወጣውን ገንዘብ ለማስመለስ መሠራት እንዳለበት ያምናሉ። ገንዘቡን ለማስመለስ ገንዘቡ ተዘርፎ ከሚቀመጥባቸው አገራት ጋር ጠንካራ የዲፕሎማሲ ግንኙነት፤ ትብብርና  ሥራ እንደሚያስፈልግ ያብራራሉ።
እሳቸው፤ እንደሚሉት የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ መንግሥት ከአገሪቱ በህገ ወጥ መንገድ የወጣውን ገንዘብ  ለማስመለስ የፖለቲካ ቁርጠኝነት አለው። ይህን ለማድረግም የተለያዩ ዓለም አቀፍና አህጉራዊ ህጎች ይደግፉታል። ኢትዮጵያ የተዘረፈ ገንዘቧን የማስመለሻ ስልት ነድፋ ብታስመልስ  በርካታ የአፍሪካ አገራትና ሌሎች አገራትም  በውጭ አገራት ባንኮች የሚገኘውን በባለስልጣናትና ባለሀብቶች በህገ ወጥ መልኩ የወጣውንና የተዘረፈውን ሀብታቸውን  በማስመለስ ረገድ ከኢትዮጵያ ትምህርት ይወስዳሉ። ኢትዮጵያን ጨምሮ የብዙ የአፍሪካ አገሮች የተዘረፈ ገንዘብ ከተከማቸባቸው እንደ ስዊዘርላንድ፣ ሲንጋፖርና ሌሎች አገራት ጋር በመደራደርም ከአገሪቱ የወጣውን ገንዘብ ሙሉ ለሙሉ ማስመለስ ባይቻል እንኳ በከፊልም ቢሆን አመርቂ ውጤት እንደሚገኝ ይናገራሉ።
እንደ አቶ ኑርልኝ ገለጻ ተዘርፎ ወደ ውጭ የሄደውን ገንዘብ ከማስመለስ ጎን ለጎን አሁንም የህዝብና የመንግሥት ሀብት ተመዝብሮ ወደ ውጭ እንዳይወጣ መከላከል ይገባል። በተለይ የፍትህ አካላትን አቅም ማጠናከር፤ በተቋማቱ መካከል ያለውን ቅንጅትና መናበብ ማጎልበት ፤ ከአገር በህገ ወጥ መንገድ የሚወጣውን ገንዘብ የሚገድብ ህግ፣ ስርዓትና  አሠራር መዘርጋት፤ የንግድ ተቋማት ገንዘብ እንዳያሸሹ ትክክለኛ ገቢና ወጪያቸውን የሚያሳወቁበት አሠራር መዘርጋትና የአገሪቱን ገንዘብ ዘርፈው በህገ ወጥ መንገድ ወደ ውጭ አገራት በሚያስወጡ  የመንግሥት ባለስልጣናት ላይ አስተማሪ ዕርምጃ መውሰድ ያስፈልጋል።
ከኢትዮጵያ በየዓመቱ ተመዝብሮ ወደ ውጭ የሚወጣው ገንዘብ የአገሪቱን በጀት እንደሚሸፍን የዓለም ባንክና የዓለም የገንዘብ ድርጅት ይገልጻሉ የሚሉት የኢኮኖሚና የፖለቲካ ምሁሩ አቶ ካህሳይ፤ ሰዶ ከማሳደድ ይልቅ ገንዘቡ ከአገር እንዳይወጣ መሥራት የመንግሥት ዋናው የቤት ሥራ መሆን ይገባዋል ይላሉ። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ውጭ ገንዘቡን ያሸሹ ግለሰቦች  በህገ ወጥ መንገድ የወጣውን ገንዘብ  አምጥተው በአገር  ውስጥ  ቢያለሙበት ተጠያቂ እንደማይሆኑ ጥሪ ማቅረባቸውም ጠቃሚ ነው። ምክንያቱም  በህገ ወጥ መንገድ የሄደውን ገንዘብ ማስመለስ  በአሁኑ ጊዜ ብዙም አዋጪ አይደለም ብለዋል።
ምሁሩ እንደሚሉት፤ ከአገሪቱ በህገ ወጥ መንገድ የሚወጣውን ገንዘብ  ለመቆጣጠርና ለማወቅ የሚችሉ እንደ ብሔራዊ ባንክ፤ የገንዘብና የገቢዎች ሚኒስቴር፣ እንዲሁም የጉምሩክና ኢንቨስትመንት ኮሚሽንና ሌሎች ተቋማት ስርዓት ዘርግተው በአገሪቱ የሚንቀሳቀሰውን ገንዘብ በማወቅ በወቅቱ ከአገር እንዳይወጣ መሥራት አለባቸው። የፋይናንስ ደህንነት ተቋማትም ቁጥጥር ማድረግና ህገ ወጥ ሁኔታ ሲፈጸም አስተማሪ ዕርምጃ መውሰድ ይኖርባቸዋል።
የዓለም አቀፉ ግሎባል ፋይናንሻል ኢንተግሪቲ መረጃ እንደሚያሳየው ከኢትዮጵያ ከ1996 እስከ 2003 ዓ.ም ከአገሪቱ ከ26 ቢሊዮን ዶላር በላይ  በህገ ወጥ መንገድ ወጥቷል። በ2009 ዓ.ም ብቻ ደግሞ  ሦስት ነጥብ 26 ቢሊዮን ዶላር በህገ ወጥ መንገድ እንደወጣ አስታውቋል። በህገ ወጥ መልኩ ወደ ውጭ አገራት ከሚወጣው ገንዘብም አብዛኛው የተመዘበረ መሆኑን  አመላክቷል።
ከአገሪቱ በህገ ወጥ መንገድ በየጊዜው የሚወጣውን ገንዘብ መከላከል ካልተቻለ ድህነት ይስፋፋል፤ የህግ የበላይነት ጥያቄ ውስጥ ይወድቃል፡፡ አገሪቱ የጀመረችው ልማት እንዳይፋጠን እክል በመፍጠርም ሰላምና ዴሞክራሲ እንዳይኖር ያደርጋል። በውጤቱም በአገሪቱ ህልውና ላይ  አደጋ ይደቅናል።
Filed in: Amharic