>

አዲስ ህገ-መንግስት ያስፈልገናል (ዶ/ር በቃሉ አጥናፉ ታዬ)

 

አዲስ ህገ-መንግስት ያስፈልገናል

 

ዶ/ር በቃሉ አጥናፉ ታዬ

ኮተቤ ሜትሮፖሊን ዩኒቨርስቲ

“ወልቃይትን ወደ ጎንደር፣ ራያን ወደ ወሎ ለመመለስ መሞከር ፀረ-ህገ መንግስት ነው፡፡”

“የወልቃይት ጥያቄ ህገ መንግስታዊ አይደለም::”

እነዚህ አባባሎች በወያኔ ካድሬዎች በብዛት የሚዘወተሩ ንግግሮች ናቸው፡፡ ነገሩ “ሞኝ እና ወረቀት የያዘውን አይለቅም “ ሆነብኝ፡፡ አብዛኛው ካድሬ የሚባለውን እንደ ገደል ማሚቶ ማሰተጋባት እንጅ የነገሩን መነሻ እና መድረሻ በውል አይረዳውም፡፡ የወልቃይት እና የራያ ጥያቄ የማንነት እንጅ የህገ-መንግስት ጉዳይ አይደለም፤ ህገ-መንግስታዊ ጉዳይ ማድረግ ካስፈለገም ህገ-መንግስቱ እራሱ ህጋዊ መሰረት የለውም፡፡ ስለዚህ የተነሳው ጥያቄ ፀረ-ህገ መንግስት ሳይሆን እራሱ ህገ-መንግስቱ ፀረ-ህዝብ እና ፀረ-ኢትዮጲያ ነው፡፡

በመሰረቱ ህገ መንግስቱ የማን ነው? እውን ኢትዮጲያ ዜጎችዋ የመከሩበት ህገ መንግስት አላት ወይ? በ1987 ዓ.ም. ፀድቆ እየተሰራበት ያለው ህገ-መንግሰት  የኢትዮጲያ ህገ-መንግሰት ተብሎ ለመጠራት የሚያስችለው ቁመና የለውም፡፡ ህወሃት ለእኩይ አላማው የሚጠቅሰው፣ ለሸፍጥ ተግባሩ የሚመዘው፣ ለዘር ወይም ለክልል ቆጠራው እንደማጣቀሻ የሚጠቀምበት  ሰነድ እንደሆነ ይታወቃል፤ ህገ መንግስቱ ኢትዮጲያን ለሚያህል ታላቅ እና ታሪካዊ አገር የሚመጥን አይደለም፡፡ ህገ-መንግስቱ በህወሃት ጠባብ አስተሳሰብ የተሰፋ ሲሆን ህገ-መንግስቱ መገንጠልን እንደ ህግ፣ ጥላቻን እንደ-መርህ፣ ዘር-መቁጠርን እንደ-ቢሂል የሚተርክ ከሳይንሳዊ እና ከመንፈሳዊ ዕውቀት ነፃ በሆኑ ሰዎች የተቀረጸ፤ ኢትዮጲያዊነትን አደብዝዞ ብሄርተኝነትን የሚያጎላ እና ለዘር-ተኮር ፖለቲካ ህጋዊ ሽፋንን የሰጠ  ከመሆኑም በላይ ህገ-መንግስቱ የአንድን የፖለቲካ ድርጅት ፍላጎት ለማስፈፀም የተቀረፀ ሰነድ እንጅ ኢትዮጲያውያን የእኔ የምንለው የጋራ ህግ አይደልም፡፡

በዘር ፖለቲካ ቅኝት የተቃኘ ስለሆነ ከዜግነት ፖለቲካ ይልቅ ብሄርን መሰረት ያደረገ አደረጃጀትን ስለሚያራምድ ግጭትን ያባብሳል፣ አንድነትን ያዳክማል፣ አገርን ይበትናል፡፡የህገ-መንግስቱን አንቀፅ 39፡1 እንደ ምሳሌ ብንጠቅስ ከአንድንት ይልቅ መለያየትን ከህብረት ይልቅ  መገንጠልን የሚያራምድ በዓለም ብቸኛው ህገ-መንግስት ነው፡፡ የመገንጠል መብትን የሚያቀነቅን የፌደራል ስርዓት ደግሞ የፌደራል ስርዓትን ንድፈ-ሀሳብ የሚጥስ እና በፌደራል ንድፈ ሀሳብ እሳቤ ተቀባይነት እንደሌለው የዘርፉ ባለሙያውች ያትታሉ(ዳችሲክ፡ 1987)፡፡

የዚህ ህገ-መንግስት አጀንዳ የተቀረፀው ህወሓት ያሳለፈውን የ17 ዓመታትን የትግል ወቅት መሰረት አድርጎ ነበር(ያንግ፡1996)፡፡ ስለዚህ ህገ-መንግስቱ የአንድ የፖለቲካ ድርጅት ማኒፊስቶ እንጅ አገራዊ ቅኝት የለውም፡፡ ሌላው ቀርቶ ህገ መንግስቱ ህግን የመተርጎም ስልጣንን የሰጠው ለፍ/ቤት መሆኑ ቀርቶ ለፌደሬሽን ምክር ቤት ነው፡፡ ለፌደሬሽን ም/ቤት ህግን እንዲተረጉም መስጠት በየትኛውም አገር የፌደራል ስርዓት የተለመደ አይደለም (አላን፡1994)፡፡ ለድንበር ግጭቶች እና ለድንበር ወሰን መካለል የዳኝነትን ሚና የሚጫወቱት ፍ/ቤቶች ሳይሆኑ የፖለቲካው አካል የሆነው የፌደሬሽን ም/ቤት ነው፡፡ይህ ደግሞ የህወሃት የፖለቲካ ሸፍጥ ነው፡፡

ህገ-መንግስቱ ህብረተሰቡ ያልመከረበት፣ በህወሓት ስብስብ ብቻ የተቀረጸ እንደሆነ በርካታ ተመራማሪዎች ገልፀዋል፤ ለምሳሌ አላን እንደገለፀችው ህገ-መንግስቱን የመቅረፅ ሂደት አሳታፊ እንዳልነበረ እና ሂደቱ ሙሉ በሙሉ በኢህአዲግ ተጽዕኖ ስር እንደነበር ገልፃለች(አላን፡1994)፡፡ ስለሆነም ህዝብ ያልተሳተፈበት ህገ-መንግስት ህጋዊ መሰረት ስለሌለው የዶ/ር አብይ አስተዳደር ኢትዮጲያውያን የመከሩበትን አዲስ ህገ-መንግስት ይቀርፃሉ ብለን ተስፋ እናደርጋለን፡፡

References

Aalen, Lovise 2002. Ethnic Federalism in a Dominant Party State: The Ethiopian Experience 1991-2000. Michelsen Institute.

Duchacek, I.D. 1987. Comparative Federalism: The territorial dimension of politics. Lanham,  Md.: University Press of America.

Young, J. (1996). Ethnicity and power in Ethiopia. Review of African Political Economy. No.70: 531-542.

Filed in: Amharic