>
9:59 am - Saturday November 26, 2022

የአምስቱ የኦነግ ፕሮግራም አቀንቃኝ  ድርጅቶች ወግ፡ ትናንትና ዛሬ! (አቻምየለህ ታምሩ)

የአምስቱ የኦነግ ፕሮግራም አቀንቃኝ  ድርጅቶች ወግ፡ ትናንትና ዛሬ!
 
አቻምየለህ ታምሩ
የዐቢይ አሕመድን አገዛዝ  የተጠጉ አምስት  የኦነግ ፕሮግራም አቀንቃኝ ድርጅቶች ባለፈው ሰሞን ያወጡት ጋዜጣዊ መግለጫ  በማኅበራዊ ሚዲያውና በሌሎች መገናኛ ብዙሃን  መነጋገሪያ ሆኖን  መሰንበቱ የቅርብ ጊዜ ትውስታችን ነው። የአምስቱ የኦነግ ፕሮግራም አቀንቃኝ ድርጅቶች መግለጫ ፖለቲካችንን በሩቁ የሚከታተሉትን ሁሉ ስቦ እንዳዲስ ክስተት ያነጋገረ ቢሆንም ቅሉ ታሪካችንን መለስ ብሎ ለተመለከተ  ግን ታሪክ ራሱን እየደገመ እንጂ የተፈጠረ  አዲስ ተዓምር እንደሌለ መገንዘብ ይቻለዋል። በየጊዜው የሚፈጠሩ የኦነግ ፕሮግራም አቀንቃኝ ድርጅቶች በየዘመኑ ወደ ሥልጣን በሚመጡ አገዛዞች ዙሪያ  እየተጠመጠሙ ጠባብ ፍላጎታቸውን  ከኢትዮጵያ ሕዝብ  አንጻር የማስፈጽም የረጅም ጊዜ ልምድ አላቸው። ባለፈው ሰሞን መግለጫ ያወጡት የአምስቱ  የኦነግ ፕሮግራም አቀንቃኝ ድርጅቶች ስብስብም አላማ ከዚህ የተለየ አይደለም።
የ1966ቱን የመንግሥት ግልበጣ ተከትሎ ወደ ሥልጣን የመጣው  ወታደራዊ ደርግ  ቢሆንም መንግሥታዊ ሥልጣኑን   ግን የተጋሩት  ኅብረት የፈጠሩ አምስት ኮምኒስት ድርጅቶች ነበሩ። በርግጥ የኅብረቱ አካል የሆነው አምስተኛው ድርጅት ከወታደራዊው ደርግ የተውጣጡ ወታደሮች ሲቪል «አብዮተኞች»ን ጨምረው የመሠረቱት ድርጅት ነው። የደርግ አገዛዝ ሥልጣን  ተጋሪ የሆኑት  አምስት ድርጅቶች መኢሶን፣ ኢጭአት፣  ወዝ ሊግ፣ ማሌሪድና ሰደድ  ናቸው። በሌላ አነጋገር  ደርግ  የመንግሥት ግልበጣ እንዳደረገ   በመንበሩ የተሰየመው ከነዚህ ድርጅቶች ጋር እንደ አንዱ ኅብረት በመፍጠር ነበር። በደርግ ዙሪያ የተጠመጠሙትና  ሥልጣን ተጋሪ የሆኑ  ድርጅቶች ጋር  በጋራ ጋራ የፈጠሩት ኅብረት «የሕዝብ ድርጅት ጊዜያዊ ጽሕፈት ቤት» ይባላል። የሕዝብ ድርጅት ጊዜያዊ ጽሕፈት ቤት አባላት የነበሩት ድርጅቶች መኢሶን፣ ኢጭአት፣ ሰደድ፣ ወዝሊግና ማሌሬድ ናቸው።
የዚህ ኢትዮጵያን ያስተዳደር የነበረው ኅብረት መሪዎች የአምስቱ ድርጅቶች ሊቀመናብርት ናቸው። የመኢሶን ሊቀ መንበር ኃይሌ ፊዳ፤  የኢጭአት ሊቀ መንበር ባሮ ቱምሳ፤ የወዝሊግ ሊቀ መንበር ሰናይ ልኬ፤ የማለሪድ ሊቀመንበር ለተወሰነ ጊዜ ዲማ ነገዖ ከዚያ ተስፋዬ መኮንን እና የሰደድ  ሊቀ መንበር ደግሞ መንግሥቱ ኃይለ ማርያም ነበሩ። ሲባል የሰማውን የሚደግም አፍ ነጠቅ  ሁሉ  ደርግ የአማራ መንግሥት ይመስለዋል። ሆኖም ግን እነዚህ የደርግ አገዛዝ ሥልጣን ተጋሪ የሆኑ  ድርጅቶች መሪዎች ሁሉ ኦሮሞዎች ናቸው። መንግሥቱ ኃይለ ማርያምና የደርግ አገዛዝ ሥልጣን  ተጋሪ የነበሩ  የአምስት ድርጅቶች መሪዎችና  የሕዝብ ድርጅት ጊዜያዊ ጽሕፈት ቤት በሚል  ኅብረት  ተፈጥሮ  ኢትዮጵያን ይገዛ የነበረው ኅብረት ሊቀመናብርት ሁሉም ኦሮሞዎች ሆነው ሳለ ደርግ ግን የአማራ መንግሥት ነው  እየተባለ አማራ  ባልዋለበት አሳሩን ሲበላና  ፍዳውን ሲያ  እነሆ ሀያ ሰባት  ዓመት ሆነው።
የሕዝብ ድርጅት ጊዜያዊ ጽሕፈት ቤት  በሚል የተፈጠረው የድርጅቶች ኅብረት ከጊዜ በኋላ የሚያራግፈውን አራግፎ የኢትዮጵያ ማርክሲስት ሌኒኒስት ድርጅቶች ኅብረት (ኢማሌድኅ) ወደሚል የግራ ድርጅቶች ስብስብ አደገ። ኢማሌድኅም ልክ እንደ ሕዝብ ድርጅት ጊዜያዊ ጽሕፈት ቤት ሁሉ ማኅበርተኞቹ መኢሶን፣ ኢጭአት፣ ሰደድ፣ ወዝሊግና ማሌሬድ ናቸው።  እንደ ሕዝብ ድርጅት ሁሉ የኢማሌድኅ ሊቀመናብርትም በሙሉ ኦሮሞዎች ናቸው። ኢማሌድኅ እንደ ድርጅት በፕሮግራም ደረጃ የሚያራምደው ርዕዮተ ዓለም ማርኪሳዊ ሌሊናዊ  ግራ ዘመም የፖለቲካ ፍልስፍና  ሆኖ እዋጋዋለሁ የሚለውም ካፒታሊዝምንና ፊውዳሊዝምን ቢሆንም የኢማሌድኅ ድርጅቶች ግን በአገዛዙ መዋቅር ገብተው ይገድሉና ይጨፈጭፉ የነበረው ዐማራን ነበር።
በተለምዶ «የደርግ መንግሥት» በሚባለው አገዛዝ ውስጥ የኢማሌድኅ አባል ሆነ በአገዛዙ መዋቅር በመጠምጠም የኦነግን ፕሮግራም እስከጥቅ ካስፈጸሙበት አምሥቱ የኢማሌድኅ ድርጅቶች መካከል ኢጭአትና መኢሶን ቀዳሚዎቹ ናቸው። እነዚህ ሁለቱ የኢማሌድኅ ድርጅቶች ከተቀሩት የኢማሌድኅ አባል ድርጅቶች ቀደም ብለው በደርግ መዋቅር ውስጥ ስለተጠመጠሙ ከድርሻቸው በላይ የአገዛዙን መዋቅር ከፊት ሆነው ቢጠቀሙና ፍላጎታቸውን በመንግሥትነት ተሰይመው ቢያስፈጽሙም፤ የተቀሩት የኢማሌድኅ አባት ድርጅቶችም የፕሮግራማቸው ደጋፊና ተባብረው የሚሰሩ ነበሩ። ይህ የአምስሥቱ ድርጅቶች መተባበር የጋራ ፕሮግራማቸውን ለማሳከት ሲሉ  አላማቸውን ለማሳካት የሚችል ሰው በተገቢው ቦታ  እንዲመደብ  ለማድረግ የድርጅት አባላትን በዝውውር እስከመለዋወጥ ደርሰዋል።
እዚህ ላይ ከአምሥቱ  የኢማሌድኅ ድርጅቶች መካከል በመኢሶንና በኢጭአት ሽፋን ይንቀሳቀሱ የነበሩት የኦነግ ፕሮግራም አቀንቃኝ ድርጅቶች በመንግሥትነት ተሰይመው በባሌና በሐረርጌ ክፍለ ሐገሮች በሚኖረው የዐማራ ገበሬ ላይ  በጋራ ተንቀሳቅሰው  ያካሄዱበት ጭፍጨፋ ሳይጠቀስ ሊታለፍ አይገባም። መገርሳ በሪ በስም መኢሶንና  በሕዝብ ድርጅት ጽሕፈት ቤት በኩል  የባሌ ክፍለ ሐገር ምክትል አስተዳዳሪ ነበር። መኢሶኑ መገርሳ በሪ  የባሌ ክፍለ ሐገር ምክትል አስተዳዳሪ  ተደርጎ የተመደበው የሕዝብ ድርጅት  ጽሕፈት ቤት አባል በነበረው በኢጭአቱ ባሮ ቱምሳ ነበር። ባሮ ቱምሳ የሕዝብ ድርጅት ጽሕፈት ቤት አባል ሆኖ የኦነግን ፕሮግራም የሚያስፈጽሙ አባላትን ከኢማሌድኅ አባል ድርጅቶች በመመልመል በየክፍለ ሐገራቱ የሚገኙነት  የሕዝብ ድርጅት ጽሕፈት ቤቶች በኦነግ ፕሮግራም አቀንቃኝ ካድሬዎች በመሙለት ከመቻሉም በላይ የአርሲን ጽሕፈት ቤት ሙሉ በሙሉ፣ የሐረርንና የባሌ ክፍለ ሐገራትን ደግሞ በከፊል ለመቆጣጠር ችሏል።  ይህን በሚመለከት ለበለጠ  ማወቅ የሚፈልግ የፍቅረ ሥላሴ ወግደረስ «እኛና አብዮቱ» በሚል ባዘጋጀው  መጽሐፍ ውስጥ ስለ ኢማሌድኅ የጻፈውን ምዕራፍ ያንብብ።
በሕዝብ ድርጅት ጽሕፈት ቤት የሚመደቡ የኦነግ ካድሬዎች በባሮ ቱምሳና በኃይሌ ፊዳ በቀላሉ እየተመለመሉ በክፍለ ሐገር አስተዳድሪነት፣ በክፍለ ሕዝብነትና በጸጥታ ኃላፊነት ይመደቡ የነበሩት የእጩዎቹ ሹመት  በኢማሌድኅ ስብሰባ ላይ ለውውይት ሲቀርብ አብረው ድምጽ በመስጠት ነበር። በዚህ መልክ በመንግሥት መዋቅር ተጠምጥመው የተደራጁት የኦነግ ፕሮግራም አቀንቃኞች አርሲ፣ ባሌና ሐረርጌ የተመደቡት የኢጭአትና የመኢሶን የክፍለ ሐገር አስተዳዳሪዎችና የአውራጃ ጸጥታ ኃይፊዎች  ግንባር ፈጥረው በአካባቢው ሲንቀሳቀሱ ከነበሩ የኦነግ ታጣቂዎች ጋር በመተባበር በየአካባቢዎቹ የነበሩ ኦሮሞ ያልሆኑ ባላገሮች ላይ በተለይም ደግሞ ዐማሮችን «መጤና ነፍጠኛ» የሚል መጠሪያ እየሰጡ በጠመንጃ ኃይል ከእርስት መሬታቸው ማፈናቀልን ዋናው ስራቸው አድርገው ያዙት። በካድሬነት የተሰማሩት  በባሮ ቱምሳ የተመደቡ የሕዝብ ድርጅት አባላት ደግሞ  ተከባብሮና በሰላም የኖረውን ሕዝብ እርስ በእርሲ እንዲቃቃርና እንዲጠፋፋ መቀንቀስን ዋነኛ ሥራቸው አድርገው ወሰዱት። ይህንን ዊክሊክስ ካሾለከውና እ.ኤ.አ. July 25 ቀን 1974 ዓ.ም. የአዲስ አበባው የአሜሪካ ኢምባሲ ወደ አሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ከላከው ሚስጥራዊ መልዕክትና ኦነግ ራሱ እ.ኢ.አ. በ1970/71 ዓ.ም. ከኢትዮጵያ ሰራዊት ጋር ይዋጉ ለነበሩት ከጻፈው ደብዳቤ ማየት ይቻላል።
በዚህ አክኋን በሕጋዊ መንገድ፣ በመንግሥት መዋቅር ተጠምጥመው የኦነግን ፕሮግራም ያስፈጽሙ የነበሩ የኦነግ ፕሮግራም አቀንቃኞች የሆኑት አብዛኛዎቹ የኢማሌድኅ ድርጅቶች እየተፈናቀለ ሜዳ ላይ የሚወድቀው ዐማራ በሚያሰማው የየእለት ጩኸትና ዋይታ ሳቢያ  ዐማራውን በግላጭ «መጤና ሰፋሪ» እያሉ መግደልና ማፈናቀል እንደማይችሉ ሲያውቁት ሌላ የትግል አማራጭ ለመውሰድ ተገደዱ። በካድሬነት፣ በክፍለ ሐገር፣ በአውራጃና በወረዳ አስተዳዳሪነት በሕዝብ ድርጅት በኩል ተመድበት ይሰሩ  የነበሩ የኦነግ ፕሮግራም አቀንቃኞች በአርሲ ክፍለ ሐገር የሕዝብ ድርጅት ጽሕፈት ቤት ኃላፊ በነበረው ክንፈ ኢንዴሳ አስተባባሪነት ተሰባስበው ከባሮ ቱምሳና በኢጭአት ስም ይንቀሳቀሱ ከነበሩ ሌሎች  የኦነግ ፕሮግራም አቀንቃኞች ጋር በመክተት ቀደም ሲል በሕዝብ ድርጅት ጽሕፈት ቤት በኩል እየታገዘ በሐረርጌ ክፍለ ሐገር የደፈጣ ውጊያ ያካሂድ ከነበረው ከጃራ ኃይል ጋር ተቀላቅለው የኦነግን የትጥቅ ትግል ጀመሩ።
በዚህ መልክ የቀጠመው ኢማሌድኅ የሚያራግፈውን አራግፎና ሕቡዕ የገባው ሕቡዕ ገብቶ ለሶስት ዓመታት ያህል ከቀጠለ በኋላ የኢትዮጵያ ሠርቶ አደሮች ፓርቲ አደራጅ ኮሚሽን ወይንም ኢሠፓአኮ ሆነ።  ከአራት አመታት በኋላ ደግሞ  ኢሠፓአኮ  ወደ ፓርቲነት ተለውጦ የኢትዮጵያ ሠራተኞች ፓርቲ ወይንም  ኢሠፓ ሆነ። የዚህ በስተመጨረሻ ላይ የተፈጠረው  ኢሠፓ  የተሰኘው ውህድና አንድ ወጥ ፓርቲ ዋና ፀሐፊ  የሆነው መንግሥቱም ኃይለ ማርያምም ኦሮሞ ነው። ከሕዝብ ድርጅት ጊዜያዊ ጽሕፈት ቤት  እስከ ኢሠፓ ምሥረታና የደርግ ውድቀት  ድረስ የተፈጠሩት ከደርግ ጋር ሥልጣን የተጋሩ ድርጅቶች ሊቀመናብርቶችና በመሪነት የተሰየሙ ግለሰቦች  አንዳቸውም አማራ አይደሉም። ምስኪኑ አማራ ግን ፈርዶበት ከሕዝብ ድርጅት እስከ ኢሠፓ ምስረታ ድረስ አገዛዙን ከላይ እስከ ታች በመንግሥትነት የተሰየሙ የኦነግ ፕሮግራም አቀንቃኞች እየዘወሩትና የየክፈለ ሐገሩንና የየአውራጃውን አስተዳደርም  ዐማራውን «መጤና ሰፋሪ» እያሉ የሚገድሉት፣ የሚያፈናቅሉትና የሚያሳድዱት የኦነግ ፕሮግራም አቀንቃኞች እንደልተቆጣጠሩት  እውነቱን የሚነግርለት ድምጽ አጥቶ ግን በተቃራኒው «ደርግ» እየተባለ ባልዋለበት ሲገዘገዝ እስከ ዛሬ ድረስ ኖረ፤ ተለቅሞ በማይሞላ ጉድጓድ ውስጥ ተጣለ፤ በዱልዱምም ታረደ!
አምስቱ የኦነግ ፕሮግራም አቀንቃኝ ድርጅቶች የደርግን መንግሥት ተጠግው  በመሬት ይዞታና አስተዳደር ሚኒስትር፣ በመርማሪ ኮሚሽን፣ በአገር መከላከያ ሚስንትር፣ በብሔረሰቦች ኢንስቲቲዩት፣ ወዘተ. . . ውስጥ  መንግሥታዊ መዋቅሩን በመያዝ በኢትዮጵያ ላይ የማይሽር ጉዳት አድርሰዋል። በተለምዶ የደርግ የመሬት ይዞታ አዋጅ የሚባለውና የካቲት 1967 ዓ.ም. የታወጀው የመሬት ላራሹ አዋጅ የደርግ አዋጅ ሳይሆን የኦነግ አዋጅ ነው።  ይህ አዋጅ ከጭሰኛነት የወጣውንና ገበሬ የነበረውን የኅብረተሰብ ክፍል መሬቱን ነጥቆ የደርግ ካድሬዎች መጫዎቻ ያደረገ አዋጅ ነው። ይህ ብቻ ሳይሆን   ባለፉት ሀያ ሰባት የወያኔ የአገዛዝ ዓመታት በአዲስ አበባ ዙሪያ  ከመሬቱ የተፈናቀለው የኦሮሞ ገበሬ  ከመሬቱ ላይ የተፈናቀለው  በዚህ አዋጅ አማካኝነት  ነው። በነሐሴ ወር 1967 ዓ.ም. የወጣው የከተማና የትርፍ ቤት አዋጅም የኦነግ አዋጅ ነው። በነዚህ ሁለት አዋጆች ያልተነቀለ ኢትዮጵያዊና ሜዳ ላይ ያልወደቀ ድሃ የለም። የዚህ አዋጅ ፊት አውራሪ በኢጭአት ጭንብል ይንቀሳቀው የነበረው የኦነጉ አስኳድ ዘገዬ አስፋው ነው። የመርማሪ ኮሚሽን አባል ሆኖ ከሻዕብያው በረከት ሃብተ ሥላሴ ጋር በመሆን በነ ፀሐፌ ትዕዛዝ አክሊሉ ሃብተ ወልድ ላይ የሞት ቅጣት እንዲፈጸም አዋጅ ያረቀቀው ሌላው በኢጭአት ካባ ይንቀሳቀስ  የኢማሌዴኅ አመራር የነበረው  የኦነግ መሥራቹ  ባሮ ቱምሳ ነው።  ለበለጠ ማስረጃ የደርግ መሥራች አባልና ቃለ ጉባዔ ያዥ የነበረው ኤርትራዊው ሻምበል ሚካኤል ገብረንጉሥ «Downfall of an Emperor: Haile Selassie of Ethiopia» በሚል የጻፈውን ያነቧል።
ለዘመናት የተገነባውን የኢትዮጵያን መከላከያ ሰራዊት በርዕዮተ ዓለም ልክ ለመስፋት ሲል መከላከያ ሰራዊትን የካድሬ መመልመያና የማርኪሲዝም ሌሊንዝም መሳሪያ አድርጎ ስያሜውን ሳይቀር «ሶሻሊስታዊ ሰራዊት» በሚል ቀይሮ ባሸዋ ላይ የተከለውና ሁለትና ሶስት ማዕረግ እያዘለለ በማርክሳዊ ቁርቁዝና ዕድገት እንዲሰጥ መሠረት የጣለው የወዝሊጉ የኦነግ ፕሮግራም አቀንቃኝ ሰናይ ልኬ ነበር። ሠራዊቱን ትጥቅ ያስፈታው ኮሎኔል  ተስፋዬ ወልደ ኪዳን  ሁለት ማዕረግ ቢያንስ 15 ዓመታት ተጨማሪ የአገልግሎት ጊዜ ይጠበቅበት የነበረውን ማዕረግ በመዝለል ሌተና  ጄኔራል የሆነው ሰናይ ልኬ ባወጣው የሰራዊት ደንብ ነው።
የሽግግር መንግሥት ተብዮው የተመሰረተው ከግንቦት 19 እስከ 20 ቀን 1983 ዓ.ም. በተካሄደው በተለምዶ «የለንደን ኮንፈረንስ» በሚባለው የኸርማን ኮሕን ጉባኤ በተደረሰበት ውጤት መሰረት ነው። በዚህ የኸርማን ኮሕን ኮንፈረንስ ዋነኛ ተሳታፊ የነበሩት አዲስ አበባን ጨምሮ አብዛኛውን የአገሪቱን ክፍል የተቆጣጠረው ወያኔ፣ በአገሪቱ ምስራቅና ምዕራብ አካባቢዎች ብዙ ቦታዎችን የያዘው ኦነግ እና ኤርትራን ሙሉ በሙሉ የተቆጣጠረው ሻዕብያ ነበሩ።
በለንደን የተካሄደው የኸርማን ኮሕን ኮንፈረንስ በተደረሰበት ውጤት መሰረት ወያኔ በሽግግር መንግሥቱ የመሪነት ሚና እንዲኖረው የተወሰነ ሲሆን ኦነግ ደግሞ በመንግሥቱ ውስጥ ዋነኛው የስልጣን ተጋሪ እንዲሆን ተደርጓል። ሆኖም ግን  በኢትዮጵያ ሕዝብ ተጋድሎና በራሱ ጭካኔ ደርግ ተወግዶ ወያኔ ሻዕብያን ተከትሎ አዲስ አበባ ከገባ በኋላ በመሠረተው የሽግግር መንግሥት ውስጥም በሽግግሩ መንግሥት ዙሪያም  የተጠመጠሙ የኦነግ ፕሮግራም አቀንቃኝ ድርጅቶች ቁጥር አምስት ነበር። እነዚህ አምስት ድርጅቶች የኦሮሞ ነፃነት እስላማዊ ግንባር (ኦነእግ)፣ የኦሮሞ አቦ የነፃነት ግንባር (ኦአነግ)፣ የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ)፣ የኦሮሞ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት [ኦሕዴድ] እና የተባበሩት የኦሮሞ ሕዝቦች ነፃነት ግንባር [ተኦሕነግ] የሚባሉ ሲሆኑ መለስተኛ ፕሮግራማቸው ኦነግ እ.ኤ.አ. በ1976 ዓ.ም. ያወጣው ማኒፌስቶ ነው።
እነዚህ አምስት የኦነግ ፕሮግራም አቀንቃኝ ድርጅቶች በወያኔ ዙሪያ ተጠምጥመው የሚፈልጉትን ሁሉ በሽግግር መንግሥት ተብዮው ካስፈጸሙ በኋላ አብዛኛዎቹ  ከሽግግር መንግሥቱ በወያኔ  ቢባረሩም በሀሳብ ልዩነትና በሀብት ክፍፍል እየተናጡ እንደ አሜባ እየተራቡ ላለፉት ሀያ ሰባት አመታት የታገሉለትን የኦነግን ፕሮግራም ከግብ ለማድረስ ያልፈነቀሉት ድንጋይና ወዳጅ  ያላደረጉት የኢትዮጵያ ጠላት የለም። የ1967ቱን የመንግሥት ግልበጣ ተከትሎ ከተፈጠረው የሕዝብ ድርጅት ጽሕፈት ቤት  እስከ ወያኔ ዘመን ድረስ የኦነግን ፕሮግራም እያራመዱ በልዩ ልዩ ድርጅቶች የተሰማሩ አምስት-አምስት የኦነግ ፕሮግራም አቀንቃኞችን የታዘብነውን ያህል ከ1967 ዓ.ም. ጀምሮ እስከዛሬ ድረስ  ከተፈራረቁት አምሥት መንግሥታት ጋርም እየተገለባበጡ በመጠምጠም የኦነግን ፕሮግራም ተቋማዊ ሲያደርጉ የኖሩ ኦነጋውያንም በርካታ ናቸው።
የወያኔን  የሽግግር መንግሥትና የደርግን ጊዜያዊ መንግሥት ጨምሮ  ከቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት ጀምሮ  እስከዛሬ ድረስ ባለው ጊዜ ውስጥ ከአምስት የተለያየ ጠባይ ካላቸው መንግሥታት ጋር የኦነግን ፕሮግራም አንግበው ባሕሪያቸውን እንደ እስስት ቀለም እየቀያየሩ በሚኒስትርነትና በከፍተኛ ባለ ሥልጣንነት ካገለገሉ የኦነግ ፕሮግራም አቀንቃኞች መካከል እንደ ተምሳሌት ልንወስደው የምንችለው ዘገዬ አስፋው ነው። ዘገዬ አስፋው በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት መጨረሻ የልጅ ሚካኤል ካቢኔና በአማን አምዶና ተፈሪ በንቲ ፕሬዝደንትነት ዘመን የመሬት ይዞታና አስተዳደር ሚንስትር ነበር። የልጅ ሚካኤል ካቢኔ ወርዶ ደርግ የራሱን ካቢኔ ሲመሰርት ዘገዬ አስፋው የእርሻና ሕዝብ ማስፈር ሚንስትር ሆኖ ተሾመ። ከሁለት ዓመት በኋላ  ደግሞ መንግሥቱ አጥናፉና ተፈሪን አስወግዶ የመሪነቱን ወንበር ሲይዝና የራሱን መንግሥት ሲመሠርት ደግሞ የፍትሕ ሚንስትር ሆኖ ሶስተኛ አለቃ ቀየረ። የፍትሕ ሚንስትር ሆኖ እየሰራ በነበረበት ወቅት  ሱማሊያና ሱዳን ከመሸገው  ኦነግ ጋር ግንኙነት ሲያደርግ  ተገኝቷል ተብሎ ወደ እስር ቤት ወረደ።
ለአስር ዓመታት በእስር ከቆዬ በኋላ ከእስር ቤት ሲወጣ የመንግሥቱ ኃይለ ማርያም የኢሕዴሪ አገዛዝ ወደ ፍጻሜው ተቃርቦ ነበር። መንግሥቱ ኃይለ ማርያም በግንቦት 1 ቀን 1983 ዓ.ም. የመጨረሻውን የካቢኔ ሹምሽር ሲያደርግ ዘገዬ አስፋው ለአስሥር ዓመታት ያህል አስሮት ለነበረው የመንግሥቱ ኃይለ ማርያም አገዛዝ በካቢኔ ሚንስትነት ተሾመ። የእርሻ ሚንስትር፣ የመንግሥት እርሻዎች ድርጅትና የቡናና ሻይ ባለሥልጣ ባንድ ሚንስቴር  መሥሪያ ቤት ስር ተጠቃልለው   ዘገዬ አስፋው የኢሕድሪ የመጨረሻው የእርሻ ሚንስትር ሆኖ ተሾመ። የዘገዬ አስፋውን ሹመት ልዩና አስገራሚ የሚያደርገው አስር አመት ያሰረውን አገዛዝ ከእስር እንደወጣ ለማገልገል ፈቃደኛ ሆኖ  ሹመቱን እሺ ብሎ መቀበሉ ብቻ ሳይሆን አብዛኛው የአገሪቱ ክፍል ከደርግ ቁጥጥር ውጭ ሆኖ ወያኔ አዲስ አበባ ሊገባ 19 ቀን ሲቀረው የተሰጠውን የሚንስትርነት ሹመት መቀበሉ ነው። ኦቦ ዘገዬ አስፋው  ከእስር ቤት እንደወጣ ለ19 ቀን ያህል በመንግሥቱ ኃይለ ማርያም በሚዘወረው የኢሕድሪ መንግሥት ሚንስትርና  የጠቅላይ ሚንስትር ተስፋዬ ዲንቃ ካቢኔ ሆኖ እንደቆየ ወያኔ ሻዕብያን ተከትሎ አዲስ አበባ ገባ።
ኦቦ ዘገዬ 19 ቀን ያገለገለው የኢሕዴሪ መንግሥት ከተወገድ በኋላ በሎንዶኑ የኸርማን ኮሕን ጉባኤ መሠረት ኦነግ የሽግግሩ መንግሥት አካል ሆኖ በመንግሥትነት ሲሰየም ኦነግን በመወከል በ19 ቀናት ልዩነት አዲስ ጌታ ለማገልገል የወያኔ ሽግግር መንግሥት የእርሻ፣ የአካባቢ ጥበቃና ልማት ሚንስትር ሆኖ ተሾመ። በዚህ ሹመቱ  ኦቦ ዘገዬ ደርግ በኦነግነት ጠርጥሮ  ያሰረው በሥህተት ወይንም በግፍ ሳይሆን  በትክክኛ ማስረጃ ላይ ተመስርቶ እንደነበር በማስረገጥ  በራሱ  ምስክር  ሆነ። ማንም ሰው ሊገምተው እንደሚችለው  አንድ ሰው አንድን ድርጅት ወክሎ  በከፍተኛ አባልነት የሚገኝን የሚንስትነት ማዕረግ  ለማግኘት ቢያንስ ከድርጅቱ ጋር የቆዬ ትውውቅና የረጅም ጊዜ ግንኙነት ሊኖር ይገባል። ኦቦ ዘገዬ ግንቦት 20 ቀን 1983 ዓ.ም. ድረስ የመንግሥቱ ኃይለ ማርያም አገዛዝ ሚንስትር ነበር። ከዚያ የወያኔ ሽግግር መንግሥት ጉባኤ ተብዮው ካለቀ በኋላ በሰኔ ወር 1983 ዓ.ም. ማለትም ከቀናት በኋላ መንግሥቱ ኃይለ ማርያም የሚባልን  ጌታ ቀይሮ ከመንግሥቱ ኃይለ ማርያም ጋር ፍጹም ተቃራኒ አስተሳሰብ ያለውን   መለስ ዜናዊ  አዲስ ጌታ  አድርጎ በርሱ ሥር ሚኒስትር ሆነ።
አምስቱ የኦነግ ፕሮግራም አቀንቃኝ ድርጅቶች የወያኔን የሽግግር መንግሥት ፕሮጀክት ተቀብለው ላለፉት 27 ዓመታትና በዘለቂውም እያመረቀዘ ኢትዮጵያን ሲያቆስል የሚኖር ጉዳት ተክለው አገልግሎታቸውን ጨርሰው ከአገር ውጡ ሲባሉ ሻንጣቸውን ሸክፈው በቦሌ ቢወጡም ባለፉት 27 ዓመታት ግን ወያኔ “ጃዝ” እያለ በሌላው ማኅበረሰብ ላይ በተለይም በዐማራው ላይ ለቆ፣ ሲያሳድዱ፣ ሲገድሉ፣ ሲዘርፉ፣ ሰውን ከነፍሱ ሲቃጥሉ፣ ከኖረበት፣ ከተወለደበት ሲያሳድዱ ከከረሙት መካከል ግንባር ቀደምቶቹ እነሱ ናቸው።
ይህ ብቻ ሳይሆን አብዛኛውን የኦሮሞ ወጣት በፈጠራ ታሪክና የጥላቻ ብሔረተኝነት መርዝ እያጦዙ ያሳደጉት እነሱ ናቸው። የሌለ ታሪክ ተፈጥሮ ሐውልት ተሰርቶለት የዘር ጥላቻ ያለገደብ ሲሰበክ «ፓስተሮቹ» እነሱ ናቸው። እነሱ ይህንን ሲያደርጉላቸው ወያኔዎች ግን አገር እየዘረፉ አዲስ አበባም ሆነ በአካባቢው ከዛም አልፎ ተርፎ በመላው የኢትዮጵያ ከተሞች በሕልማቸውም በውናቸውም አይተውት የማያውቁት ሃብት ሲያፍሱ ባጁ። በዚህ መልክ በግፍ የተደላደሉበት ሥልጣናቸው እንኳን ከሰውና ከግዚአብሄርም በላይ እንደሆኑ እንዲሰማቸው አደረጋቸው። የኦነግ ፕሮግራም አቀንቃኞች ከወያኔ ጋር ሆነው የጥላቻ ስብከት አምርተው እያሰራጩ ሕዝብ ሲከፋፍሉና ሲያቋስሉ የኖሩት በውሸት ታሪክ ላይ የፈጠሩትን ሕልማቸውን እውል የሚያደርጉበት መዋቅር ስለሚያስፈልጋቸው ነው።
ከዚህ በፊት በተደጋጋሚ እንዳቀረብነው የብሔርተኛነታቸው ዓላማ የነጻነትና የእኩልነት መብቶች  እንዲከበሩ ለማድረግ ሳይሆን የሁሉም ኢትዮጵያውያን ሀብት የሆነውን አብዛኛውን የአገሪቱን ለም መሬት ዘርፎ መሄድ የወያኔን ፕሮግራም ተጠቅመው የተስፋይቱን ምድራቸውን መሥርተው የእድሜ ልክ ገዢ ሆነው ለመኖር ነው። የኦነግ ፕሮግራም አቀንቃኞች ሁሉ በጋራ ይህንን ለማሳካት በመጀመሪያ የኦሮሞውን ስለ ልቦና ከሌላው ኅብረተሰብ መነጠል ነበረባቸው። ይህንንም ያደረጉት መንገድ አንዱ ኦሮሞው ከሌላው ማኅበረሰብ ጋር እንዳይግባባ የሚግባባበትን ቋንቋ እንዳይማር በመከልከል ነው። ይህንንም ያደረጉት ከወያኔ ጋር ተጠግተው የትምህርት ሚንስትርነትን ሥልጣን ይዘው በነበረበት ወቅት ነው። ይህ ትውልድ ገደላ እንኳን የሌላውን ማኅበረሰብ ድጋፍ ቀርቶ እውነቱን በትክክል ለተረዳውና በሰው ልጆች ወንድማማችነት ለሚያምን ሰው ሁሉ የሚያሳዝን ድርጊት ቢሆንም ቅሉ ለነሱ ግን ይህንን ጭቡ የተሞላ ዓላማቸውን ለማሳካት ጥሩ እድል ያገኙበት ዘመን ስለነበር እንደ ስኬት ይቆጥሩታል። ወያኔ የኦነግ ፕሮግራም አቀንቃኞች በሌላው ሕዝብ ላይ የፈላጋቸውን እንዲያደርጉ ቢፈቅድላቸውና በኅብረተሰቡ መካከል መከፋፈል እንዲፈጠር ስፖንሰር ቢያደርግም ስልጣኑን ለማደላደል ሲል የፈጠረው ስትራቴጂ ግን በራሱ ላይ ባርቆ የኦነግ ፕሮግራም አቀንቃኞች  በሌላው ሕዝብ ብቻ ሳይሆን በራሱ በወያኔም ላይ ተነስተውበት ወራሴ ሥልጣን  ለመሆን በቅተዋል።
በዐማራና በኦሮሞ ወጣቶች መስዕዋትነት ወደ ጠቅላይ ሚንስርትርነት በመጣው በዐቢይ አሕመድ መንግሥት ዙሪያ ለመጠምጠም ኅበረት የመሠረቱትና «የአዲስ አበባ ጉዳይ የኦሮሞ የአገር ባለቤትነት ጉዳይ ነው» ብለው የአዲስ አበባን ጉዳይ «ኦሮምያ» የሚሏት አገር ባለቤትነት ጥያቄ አድርገው ባለፈው ሰሞን መግለጫ ያወጡት አምስቱ የኦነግ ፕሮግራም አቀንቃኝ ድርጅቶች በአርባ አመታት ውስጥ የተከሰቱ ሶስተኛ የአምስት ድርጅቶች ስብስቦች ናቸው። እነዚህ በዐቢይ አሕመድ ዙሪያ የተጠመጠሙት አምስት ድርጅቶችም ልክ ከዚህ በፊት በመንግሥቱ ኃይለ ማርያምና በመለስ ዜናዊ ዙሪያ እንደተጠመጠሙት ድርጅቶች ሁሉ ዓላማቸው የአገሪቱን አብዛናውን ለም መሬት የኔ ብቻ ነውና አትድረሱብኝ እያሉ ዜጋው መብት ባነሳ ቁጥር የፈጠሩትን የተስፋ ምድር ጉዳይ የአገር ባለቤትነት ጉዳይ አድርጎ ሕዝብን ርስበርሱ ማበጣበጥ ነው።
በኔ እምነት የኦሮሞ ሕዝብ እውነቱ ቀርቦለት ወስን ቢባል የኦነግ ፕሮግራም አቀንቃኞች ኦሮምያ የሚባለውን አካባቢ ጉዳይ «የአገር ባለቤትነት ጉዳይ ነው» እያሉ እንደሚሉት የሌላውን ሕዝብ አገር ዘርፎ፣ አስርቦ ራሱን ብቻ የማኖር ፍላጎት ይኖረዋል ብዬ አላስብም። ይህ የሚሆነው በሁለት ምክንያት ነው። አንደኛ ሰብዓዊነቱ ይከለክለዋል። ሁለተኛ ይህ ዓይነት ሁኔታ ሰላም እንደማያመጣለት ስለሚያውቅ አያደርገውም። ሕዝብ ራሱን ወደጦርነት አያመራም። ምክንያቱም ጦርነት ለሕዝብ የሚያመጣው ምንም ጥቅም የለም፣ ከጉዳት በስተቀር። በርግጥ ከጦርነት እንደ ወያኔ፣ ኦነግ፣ ሻዕብያ፣ ወዘተ አይነት ቡድኖችና ግለሰቦችም ጭምር የሚጠቀሙ ይኖራሉ። በሕዝብና በነ ኦነግ፣ ወያኔ፣ ሻቢያ ያለው ግንኙነትም የዚህ ዓይነት ነው። ለነዚህ ደም ለጠማችው ሰዎች መፍትሄ ደግሞ ወያኔ በፈጠራቸው የአፓርታይድ ክልሎች ዙሪያ ሕዝብን ማስቻል ወይንም ሕዝበ ውሳኔ ማድረግ ነው።  በዚህ ዓይነት ሁኔታ እውነትን ተገን ያደረገ ሃሳብ ብቻ ነጥሮ እንዲወጣና የውሸት ታሪክ እየፈጠሩ ራስን ስልጣን ላይ ለማስቀመጥ የሚሄዱ ሰዎች ውጤት አልባ እንዲሆኑ ያደርጋል።
ወያኔን ለመፋለም የተካሄደው ትግል ያልተማከለ ነበር። ለዚህም ነበር ባለፉት ሶስት ዓመታት ባገራቸው የተለያዩ አካባቢዎች በተለያዩ ግንባሮች የተነጣጠለ ተቃውሞዎች ሲበዙ የነበሩት። ያልተማከለ ትግል አንድ አዛዥና ናዛዥ ስለማይኖረው ትግሉ በየትኛውም ኃይል ቁጥጥር ስር መውደቅ አይችልም። ባጭሩ ትግሉ የሕዝቡ ይሆናል። የሕዝብ የሆነ ትግል ደግሞ በቀላሉ ዓላማውን ሊስት አይችልም። በሕዝብ ትግል ላይ ተጽዕኖ መፍጠር የሚፈልጉ ኃይሎች ሊያደርጉት የሚችሉት ብቸኛው ነገር ሃሳባቸውን ማቅረብ ነው። በዚህ ዓይነት ሁኔታ እውነትን ተገን ያደረገ ሃሳብ ብቻ ነጥሮ ይወጣል ማለት ነው።
ይህ ሕዝባዊ መስመር ግን የውሸት ታሪክ አንግበው ራስን ስልጣን ላይ የማስቀመጥ ዓላማን ይዘው በሚሄዱ ቡድኖርና ግለሰቦች መዘወር ከጀመረ የትግሉ መስዕዋትነት ውጤት አልባ መሆኑ አይቀሬ ነው። የዘንድሮዎቹ አምስቱ የኦነግ ፕሮግራም አቀንቃኝ ድርጅቶች በዐቢይ አሕመድ አገዛዝ ዙሪያ ተጠምጥመው መስዕዋት የተከፈለበትን የሕዝብ ትግል የፍላጎታቸው ማስፈጸሚያ ሊያደርጉትና ራሳቸው በሚጭሩት እሳት ሕዝብ እንዲጫረስ በየቀኑ የጥላቻ መግለጫ ሲያወጡ ይውላሉ። ሕዝባችን ላለፉት አርባ አራት አመታት ሽግግር የሚባል ነገር በመጣ ቁጥር እየተጠጉ በአገርና በሕዝብ ላይ ዘለቂ ጉዳት በማድረስ የካበተ ልምድ ያላቸውን እነዚህ ድርጅቶች ለግላዊ ሥልጣንና ሀብት ሲሉ በሚዘረጉት ወጥመድ ውስጥ ገብቶ መስዕዋትነት የከፈለለት ዓላማ እንዳይነጠቅበት ነቅቶ መጠበቅ ይኖርበታል።
የዘንድሮዎቹ አምስቱ የኦነግ ፕሮግራም አቀንቃኝ ድርጅቶች የጥላቻና የፈጠራ ታሪክ እየደሰኮሩ የጋራችን የሆነውን ምድር ይዘው አገር ለመፍጠር ሲነሱ የአያት ቅድሚያ አያቶቹን ምድር አላስነካም ብሎ ሊፋለም የሚነሳ ትውልድ ያለ አይመስላቸው። የነሱም ሆነ የመለስ ዜናዊ የመንፈስ ወዳጅ የሆነው ፓውል ካጋሜ ለስልጣን ለመብቃት ሲል ተመሳሳይ ዘዴ ተጠቅሟል። ግን ለሰው የተበተበው ሴራ አንባርቆበት ሚሊዮን የራሱን ዘር የሆኑ ቱትሲዎችን አስጨርሶ፣ ሁቱዎቹን ማኖ ካስነካ በኋላ የቀሩትን ቱትሲዎች በ85% ሁቱዎች ላይ አንግሶ የሚቀጥለው እልቂት እስኪመጣ ተንደላቅቆ እየኖረ ይገኛል።
ላለፉት ሶስት ዓመታት የተካሄደው ትግል አንድ ቋሚ የሆነ ለሁላችንም የሚሆን ጥቅም እስኪሰጥ ድርስ በተለይ በግለሰብም ሆነ በቡድን ደረጃ የማንንም ድርጅት አላማና ትዕዛት ያለመቀበል ሕዝባዊ ባህል የበለጠ መዳበር አለበት። ሕዝብ ምን ጊዜም ፍትሃዊ ነው። በስህተት ፍትህ ቢዛነፍ እንኳን ሕዝብ ወሳኝ እስከሆነ ድረስ ወዲያው ይቃናል። ስለዚህ በሕዝብ ላይ እምነት ያለው ሁሉ የሕዝብ የመወሰን ብቃት ለማዳበር የትናንቶቹንም ሆነ የዛሬዎቹን አምስቱን የኦነግ ፕሮግራም አቀንቃኝ ድርጅቶችና የርዕዮተ ዓለም አጋሮቻቸውን የውሸት ታሪኮች ራቁታቸውን እንዲቀሩ ማድረግና በእርስበርስ እልቂት ነጋሪት እየመቱ በማያውቁት አገር ሄዶ «ቁርበት አንጥፉልኝ» እንዳለው አውሬ  በየዘመኑ ሽግግር በመጣ ቁጥር የሚመላለሱ አውሬዎችን በድፍረትና ያለርሕራሔ በማጋለጥ ረገድ ሁሉም ያለምህረት መስራት ይኖርበታል።
Filed in: Amharic