>

ወፌ ቆመች' ለፖለቲካችን! (ያሬድ ሀይል ማርያም)

ወፌ ቆመች’ ለፖለቲካችን!
ያሬድ ሀይል ማርያም
ለመቆም በመታገል ላይ ላለ/ች ሕጻን እንደሚባልለት ፖለቲካችንም እንዲሁ ከመዳህ ወደ መቆም ከመቆም ወደ መሄድ ባለው ተፈጥሯዊ ትንቅንቅ ውስጥ ያለ ይመስላል። ለዚህም ትላንት በአገዛዝ ሥርዓቱ በጥሩ አይን ይታዩ ያልነበሩ ሰዎች እና ድርጅቶች በአገር ግንባታው ሂደት ውስጥ ዋና እና ንቁ ተሳታፊ እንዲሆኑ መደረጉ ጥሩ ጅምር ነው። በመንግስት የተገቡ አጓጊ ቃሎች መሬት ላይ ካረፉ እና በጥሩ መሰረት ላይ ባረፉ ተቋማት ከተደገፉ የመከራ ዘመናችን ይቋጫል፤ የዋጠን ጽልመት ከላያችን ላይ ይገፈፋል፤ ድህነት እና ድንቁር ያደቀቁት ጉልበታችንም ዳግም ይበረታል፤ በአንባገነኖች በትር የዛለው አካላችንም ዳግም ይታደሳል። አዲዮስ አፈና፣ አዲዮስ ጦርነት፣ አዲዮስ ዘረኝነት፣ አዲዮስ ሙስና፣ አዲዮስ ……አዲዮስ …….አዲዮስ…….አዲዮስ ….
የሁሉም የሆነች ኢትዮጵያ፣ ሁሉም ዜጋ ለክብሯ እና ለአንድነቷ የሚቆምላት ኢትዮጵያ ከተሸሸገችበት ብቅ እያለች ይመስላል። የመጣንበት መንገድ በእሾህ እና በገደላ ገደል የተደነቃቀፈ ነው። በጉዟችንም ውስጥ ብዙዎች ከመንገድ ቀርተዋል፣ ብዙዎች በአካልም ሆነ በመንፈስ ክፉኛ ተጎደተዋል፣ ብዙዎች ልክ እንደኔ የአገር አልባ ስደተኞች ፖስፖርት ታቅፈዋል፣ ብዙዎች የሚወዱትን የቤተሰብ አባል ወይም ጓደኛ ወይም ጎረቤት በሕይወት አጥተዋል፣ ብዙዎች ከልጅነት እስከ እውቀት ያፈሩትን ሃብት ተዘርፈዋል፣ ብዙዎች መገለጫ የሌለው ብዙ መከራ አሳልፈዋል።
ዛሬም መከራዎቻችን ከፊታችን እንደተጋረጡ ናቸው። እኛ በዛልን ቁጥር መከራዎቻችን እየበረቱ እዚህ ደርሰናል። ዛሬ እኛ በርትተን እነሱ የሚዝሉበት ጊዜ እየቀረበ ሊመጣ እንደሚችል ተስፋና ምልክቶች እያየን ነው። ለውጥ የለም ወይም ለውጡ ወደ ከፋ አቅጣጫ ነው እየወሰደን ያለው የሚል ሰው ካለ ሊሞግተኝ ይችላል። ለእኔ ከመለስ ዘመን የኃይለማርያም፤ ከኃይለማርያም ዘመን የአብይ በብዙ ብዙ እጥፍ የተሻለ ነው።
ትላንት ይነሱ ያልነበሩ የመብት ጥያቄዎች ዛሬ መነሳት መቻላቸው በራሱ አንድ እምርታ ነው። የተነሱ ጥያቄዎች መልስ እንዲያገኙ መታገል መቻል ሌላ እምርታ ነው። ትላንት ማንም የማያነሳቸው የወልቃይት፣ የራያ እና ሌሎች የማንነት ጥያቄዎች ዛሬ መነሳታቸው፣ እነዚህ ጥያቄዎች መልስ እንዲያገኙ ሰዎች መደራጀት እና በአደባባይ ሰልፍ በማካሔድ መጠየቅ መቻላቸው ትልቅ ለውጥ ነው። ሃሳቡ ትክክል ባይሆንም እንኳ ኦነግ ትጥቅ መፍታት የለበትም ብለው ሰዎች ሰልፍ መውጣታቸው ሌላው የለውጥ መገለጫ ነው። የተነሱት የመብትም ሆነ የማንነት ጥያቄዎች በአጭር ግዜ ውስጥ ምላሽ ስላላገኙ ለውጥ የለም ብሎ ማሰብ ግን በእኔ እምነት ስህተት ብቻ ሳይሆን አገሪቱ ያለችበትን ሁኔታ ብቅጡ መረዳት ያለመቻልም ነው። ጥያቄዎቹ በአግባቡ እና ሳይዘገይ ምላሽ ማግኘት እንዳለባቸው ግን እኔም አምናለሁ።
መብት ብቻውን አልተፈጠረም። ከጀርባው ግዴታ አለው። መብት እና ግዴታ የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታዎች ናቸው። ሳንቲሙን ከአንድ አቅጣጫ ብቻ እያዩ ገጽታው ይሄ ብቻ ነው ማለት አይቻልም። በሳንቲሙ የተለያየ አቅጣጫ የረቀመጡ ሰዎች ለእነሱ የሚታያቸውን ብቻ ብቸኛ እውነት አድርገው ካዩ ሁለቱም ግማሽ እውነት እና ግማሽ ስህተት ይዘው ስለሚቆዩ መቼም አይግባቡም። ሳንቲሙን አገላብጦ ማየት ሙሉ ገጽታ ይሰጣል። የራሳችንን እውነት ብቻ ሳይሆን የሌሎችንም ሃቅ እና እውነት እንድንረዳ ያደርገናል። ያኔ መግባባት አይቸግርም። አሁን የምንጋጭባቸው አብዛኛዎቹ ነገሮች የእይታ ችግር መነሻዎች ናቸው። በራሳችን እውነቶች የታጠርን ነን። በላዩ ላይ የጎሳ፣ የሃይማኖት እና ሌሎች አግላይ የሆኑ የማንነት መገለጫ አጥሮች ሲታከሉበት በመካከላችን የጀርመን ግንብ አይነት አጥር ሰራን ማለት ነው።
በእነዚህ አጥሮች ውስጥ የተከለለ ማህበረሰብ ሁሌም የጎደሉ መብቶቹን ነው ሲቆጥር የሚውለው። እሱ ሊወጣቸው ስለሚገቡ ግዴታዎቹ ለደይቃዎችም አያስብም። ግዴታዎቹን ብቻ ሳይሆን የማያስበው ያገኛቸውንም መብቶች እንዳሉ አይቆጥራቸውም። በሞላው ሳይሆነ በጎደለችዋ ነጥብ ይቆጣል፣ ያለቃሳል፣ እርስ በእርሱ ይጋጫል፣ ደም ይፋሰሳል፣ ደም ይቃባል።
ዳዴ እያለ ያለውን ፖለቲካችንን ቆሞ እና ነፍስ ዘርቶ ወደ ዲሞክራሲያዊ መንገድ እንዲያቀና ከፈለግን ጠያቂ ብቻ ሳንሆን ተጠያቂም እንሁን፤ መብታችንን እንደምንጠይቀው ሁሉ የዜግነት ግዴታችንንም እንወጣ፤ አስተሳሰባችንን የገደቡትን አጥሮች ደረማምሰን በሰፊው ስፍራ መቆማችንን እናረጋግጥ፤ ስህተቶችን ነቅሰን እያወጣን እንደምንነቅፍ እና እንደምናብጠለጥል ሁሉ በጎ የሆነ ነገሮችንም እናድንቅ፣ እናበረታታ፤ ለራሳችን መብት እና ጥቅም ብቻ ሳይሆን ለሌሎች ፍትሕን ላጡ ሰዎች ሁሉ ድምጻችንን እናሰማ።
የወ/ሮ መዓዛ አሸናፊ የአገሪቱ የፍትህ ቁንጮ በሆነው የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝደንት ሆኖ መሾም ትልቅ እርምጃ ነው። በፍትህ እጦት ሲማቅቅ ለኖረውም ህዝብ እፎይ የሚያስብል ዜና ነው። ለሳቸው መልካም የሥራ ዘመን እመኛለውሁ። ለሾሟቸው ለጠ/ሚ አብይም አክብሮቴ እገልጻለሁ።
ቸር እንሰንብት!
Filed in: Amharic