>
5:13 pm - Monday April 19, 5802

አንጋጊና ተንጋጊ የበዛበት ዘመን!?! (ነጋሽ አቦነህ)

አንጋጊና ተንጋጊ የበዛበት ዘመን!?!
ነጋሽ አቦነህ
አንጋጊዎቹም የአፍዝ አደንግዝ ተውኔት ስልታቸውን እየቀያየሩ ፣ ብዙዎችን ለመሳብ  የማያደርጉት ጥረት የለም። ከብዙ ተሞክሮና ጉዳት በኋላ ፣ ተንጋጊው የነቃ ዕለት ግን ጉድ ይፈላል!
 
በለንደን ከተማ የሚገኘው ፣ የለንደን ብሪጅ ባቡር ጣቢያ ውስጥ ፣ ጥዋት በሥራ መግቢያና ፣ ከሰዓት በኋላ ከሥራ መውጫ ሰዓት ላይ ያለው የሰው ትርምስ እጅግ የሚያስመርር  ነው። ግርር ብሎ የሚወጣውና የሚገባው ወፈሰማይ ሕዝብ መስመሩን ጠብቆ መሄድ ይጠበቅበታል።
አንድ ሰው ትክክለኛውን መውጫና መግቢያ ሳያውቅ በፍጥነት ከሚንጋጋው ጋር ፣ መስመሩን ጠብቆ እንዲሁ በጭፍን ቢጣደፍ ፣ ያሰበበት ወይም የፈለገበት ቦታ መድረሱ አጠራጣሪ ነው። እንዲሁም የሚያስከትለውን ስድብና  ነቀፌታ ፍራቻ ፣ በዚያ ጋጋታ ውስጥ ፣ ወደኋላ መመለስ ቀርቶ መቆም እንኳን ፈፅሞ አይታሰብም።
በዚህ አንጋጊውና ተንጋጊው በበዛበት ዘመን ፣ ቆም ብሎ የሚጠይቅ ሁሉ ፣ ይብዛም ይነስ ፣ ከባድ ነቀፌታና ተቃዉሞ እንደሚደርስበት ፣ በህብረተሰብ ውስጥ የምናየውና ፣ በመገናኛ ብዙሃን ደግሞ በየቀኑ የምንሰማው ጉዳይ ነው።
ብዙ ሰው ፣ የጤና ችግር ሳይኖርበት ፣ በራሱ አንድን ነገር ጠይቆ መረዳት ፣ ወይም አስቦ በራሱ መወሰን ትቶ ፣ እነማን በጉዳዩ ላይ ምን አሉ ፣ ወይም ምን ያህል ህዝብ ደገፈው? በሚለው ላይ በማተኮር ፣ ወይም የፈረደበት ጉግልንና የመሳሰሉትን መጎልጎል እንጂ ፣ ለጥቂት እንኳን የራሱን አዕምሮ ለመጠቀም እንደማይሞክር በቂ መረጃ አለ።
ለሁሉም ነገር ፣ በሆኑ ግለሰቦች ሃሳብ ላይ መንጠላጠል ፣ ወይም ወሬና ሐሜትን ፣ አለዚያም የአብላጫውን ስሜት ተከትሎ መንጋጋት የተለመደ ሆኗል። ለሁሉ ነገር  አቋራጭ ፈላጊና ፣ ባወጣ ያውጣው ብሎ የሚወናጨፍ የበዛበት ጊዜ ነው።
እነእንትና እንደዚያና እንደዚህ ስላሉት ብቻ ፣ ሁሉ ነገር ትክክል እንደሆነ አምኖ በጭፍን መከተል ፣ ጉዳትና ጥፋት  ወይም ኪሳራ ሲያደርስ ብዙ አይተናል።
ድሮ አንድ በኮሙኒስት ሩሲያ ፣ ሆነ ተብሎ የሰማነው ነገር ትዝ አለኝ። አንድ ትልቅ የተዘጋ በር ላይ ደገፍ ብሎ ፣ ጋዜጣ የሚያነብ ሰው ብቻውን ይቆማል።  ሌሎች ጓደኛሞች ደግሞ እሱን ላለመረበሽ በዝግታ እያወሩ ከእርሱ ጀርባ ይቆማሉ። ከዚያ በመቀጠል አንድ በአንድ ፣ የሰው ቁጥር እየጨመረ ይሄድና ፣ ረጅም ሰልፍ ይሆናል። መጨረሻ የደረሰ አንድ ሰው፣ ሰልፉ ስለምን እንደሆነ ይጠይቃል።
ጥያቄው መልስ ስላጣ ፣ ከአንዱ ወደ አንዱ እየተቀባበለ ወደ መጀመሪያው ሰው ከመድረሱ በፊት ፣ ሰውዬው የያዘውን ጋዜጣ ቆሻሻ መጣያ ውስጥ ጨምሮ ፣ በፍጥነት እየተራመደ  ወደሚሄድበት ይሄዳል። ከኋላ የተኮለኮሉትም ፣ በአግራሞትና ራሳቸውን በንዴት እየነቅነቁ ፣ ጊዜያቸውንም በከንቱ በማባከናቸው እየተበሳጩ ፣ ወደየመጡበት እንደተመለሱ ይነገራል።
በዚያን ጊዜ የምዕራባውያን ሸቀጣ ሸቀጥ በኮሙኒስት አገሮች ገበያ ላይ ዕጥረት ሰነበረ ፣ ምንም ዓይነት ሰልፍ ካዩ  የሆነ አዲስ ነገር ቢኖር ነው ብለው ስለሚያስቡና ፤ ማንም ያለ ምክንያት ዝም ብሎ አይሰለፍም የሚል እምነት ስለነበራቸው ፣ ምንም ሳይጠይቁ በጭፍን ይኮለኲሉ እንደነበር ከራሳቸው ሰማን።
አሁን በሰለጠነው ዘመን ፣ በቀጥታ እንደዚያም ባይሆን ፣ ግን የሚመስሉ ነገሮችን እናያለን። በረቀቀ የማስታወቂያ ብዛት፣ ትልልቅ ስም ባላቸው ተቋማት ላይ ሃሳባቸውን ጥለው የሚኖሩና ፣ በአመኔታም የግል ምስጢራቸውን  ሁሉ ዘርግፈውላቸው ለኪሳራና ለዉርደት የተዳረጉ ፣ በብዙ ሚሊዮኖች  የሚቆጠሩ ናቸው።
ስንትና ስንት የሕይወትና የንብረት ጥፋት ካደረሱ በኋላ ተነቅቶባቸው ፣ በህግ ፊት ቀርበው የተቀጡም ብዙዎቹን አይተናል። በተለይ በባንኮችና በፋይናንስ ገበያ ላይ የተፈጠረው ታላቅ ዓለማቀፋዊ ግፍና ኪሳራ የቅርብ ጊዜ ትዝታችን ነው።
በተለያየ መንገድ የሰበሰቡትን ፣ የሰዎች የግል ምስጢርና ገበናቸውን ፣ አንዳንድ ጊዜ ወደ እነርሱ አዙረውት ፣ የሚፈልጉትን ጉዳይ በግድ ለማስፈፀም ሲሉ እነሱኑ ማስፈራሪያ አድርገው እንደጠቀሙበት ይታወቃል።  ከዚያም ባሻገር አልፈው ደግሞ ፣ ለተለያዩ ህገ ወጥ ድርጅቶች እየቸበቸቡት ፣ ለልዩ ልዩ የወንጀል ተግባራት ጥቅም ሲውሉ  ይሰማል።
አንዳንዶች ደግሞ ፣ ሌሎችን በጭፍን ለመከተል ተንጋግተው ከገቡ በኋላ ፣ መውጣት አቅቷቸው ፣ ንብረታቸውንም ተዘርፈው ፣ በመጨረሻም በጉስቁልና ሕይወታቸውን እስከማጣት ይደርሳሉ። በየዘመናቱ ያልፍልኛል ብሎ  እንደ ግሪሳ እየተንጋጋ ለስንት አደጋ የሚማገደው  ህዝብ ብዛትም ቀላል አይደለም።
መጠየቅ የሚያሳፍራቸውም ደግሞ እንዲሁ ብዙ ናቸው። ክብራቸውን የሚነካ እየመሰላቸው ያልገባቸውን ነገር ላለመጠየቅ ሲሉ ፣ ሌሎችን ተከትለው እየተንጋጉ ረጃጅም መንገድ ሲኳትኑና ዘመናቸውን ሲያባክኑ የሚኖሩትም እንዲሁ ብዙ ናቸው።
ከቅርብ አሥርተ ዓመታት ወዲህ ደግሞ በአንዳንድ ቤተ ዕምነታት ዘንድ እየተደረገ ያለው ጉዳይ እጅግ የሚገርምና አንዳንዱም የዕብደት ወይም የመተት አሠራር የሚመስል ነገር አለበት። በተለያዩ የዓለም ክፍሎች ተሞክሮ የከሠረን ግሳንግስ ሁሉ ወደ አፍሪካ ሲገባ እንደ አዲስ ሆኖ ይቀርብና በሺህ የሚቆጠር ሕዝብ ሲንጋጋለት ይታያል።
ከ’መላምት’ ወይም ከ’መሰለኝ’ ተነስተው ፣ አንዱን ነገር ከሌላው ጋር አጋጭተው ፣ ከነባራዊ ሁኔታ የወጣና የሌለ ታሪክ ፈጥረው እያወሩ ፣ የሰውን ሕይወት የሚያመሳቅሉ ፣ ህብረተሰብን የሚያውኩና ፣ ስተው ብዙዎችን የሚያስቱ ፣ የሰላም ጠንቆችም ብዙ ናቸው።
ሰው ፈጣሪን ባይፈራም ፣ ቢያንስ ግን ቢጤውን እያፈረ ለይሉኝታ ሲል ይጠነቀቅ ነበር። ዛሬ ደግሞ እሱም ብርቅ ሊሆን ነው። ጭራሽ በፈጣሪ ስም ብዙ ድፍረትና ማጭበርበር ሲካሄድ በገሃድ ፣ እንዲያውም በመገናኛ ብዙሃን ማየት የተለመደ ሆኗል።
ብዙዎች ለችግራቸው መፍትሔ ያጡ’ና የጨነቃቸው ፣ ከገቡበት ሁኔታ ለመውጣት አቋራጭ ፍለጋ ፣ ሌሎች ደግሞ ለተለያየ ርካሽ ጥቅማ ጥቅም ሲሉ ፣ እርባና ለሌዉ ተውኔት  እንደ ከብት ሲንጋጉ ይታያል።
ዛሬማ ፣ አንድ ሰው ደፍሮ ፣ “..እኔ የነካሁትን ድንጋይ ብትገምጡት ትበለፅጋላችሁ!”..ቢል ፣ ምን ያህሉ ህዝብ በድዱ እስኪቀር ድረስ እንደሚንጋጋለት መገመት አያስቸግርም።
አንጋጊዎቹም የአፍዝ አደንግዝ ተውኔት ስልታቸውን እየቀያየሩ ፣ ብዙዎችን ለመሳብ  የማያደርጉት ጥረት የለም። ከብዙ ተሞክሮና ጉዳት በኋላ ፣ ተንጋጊው የነቃ ዕለት ግን ጉድ ይፈላል።
….
ለማንኛውም ፣ አቅጣጫውና መድረሻው ያልታወቀ ጥድፊያ ወይም ጋጋታ ከንቱ ነውና ፣ በጊዜ ጠይቆ ማወቅ ፣ ወይም ዝም ብሎ ከመንጋጋት ቆም ብሎ በዕርጋታ ማሰብ የሚሻል ይመስለናል..
Filed in: Amharic