>

ዛሬ ስለሃገራችን ለውጥ ጉዳይ ሳስብ አንድ ሁለት ነገሮች በተለይ የለውጥ ሃይል ለምንለው መሰንዘር ፈለኩ። (ገለታው ዘለቀ)

ዛሬ ስለሃገራችን ለውጥ ጉዳይ ሳስብ አንድ ሁለት ነገሮች በተለይ የለውጥ ሃይል ለምንለው መሰንዘር ፈለኩ።

 

ገለታው ዘለቀ

1. የለውጥ ሃይሉ ያለውን ፍኖተ ካርታ በግልጽ እንዲያሳውቅ

ባለፉት ስድስት ወራት ግድም የለውጥ ሃይልን ስለመደገፍ ኣለመደገፍ ስናወራ ቆይተናል። ይህ የለውጥ ሃይል በርግጥ ብዙ ተስፋዎችን ኣሳይቶናል በተግባርም እስረኞችን ሲፈታ ተመልክተን ደስ ብሎናል። በቅርብ ጊዜ በአዲስ ኣበባ ወጣቶች ኣካባቢ የታየውን ማውገዛችን ሳይዘናጋ። ይህ የለውጥ ሃይል ታዲያ አንድ ዋና ነገር ያስፈልገዋል። ይሄውም ግልጽ የሆነ road map ነው። ሃገሪቱን ወዴት ሊወስዳት እንዳሰበ ወይ በመጽሃፍ መልክ ኣዘጋጅቶ ሊያቀርብልን ይገባል። አቶ መለስ እንኳን ለውጥ ሲያስቡ የአብዮታዊ ዴሞክራሲ መስመር ብለውም ቢሆን ያስተምሩ ነበር። ሃገር ለውጥ ውስጥ ሲገባ ይሄ ወሳኝ ነው። የለውጡን ሃይል የሚደግፉ የማይደግፉ የሚባለው የሆነ ግልጽ የሆነ የለውጥ አቅጣጫ ሲኖር ነው። እስካሁን የለውጥ ሃይል መሪዎች ያልናቸውን የሚናገሩትን እየሰማን ተደስተናል። እውነተኛ የትርክት ለውጥ ውስጥ የለውጡ ሃይል ገባ የምንለው ግን ይህ የሚነገረው ነገር የፓርቲ ፕሮግራም ሆኖ ሲወጣ፣ ህዝብ የለውጡን አቅጣጫ ሲወያይበት ነው። ምሁራን የለውጡን ሃይል ኣቅጣጫ እያጠኑ ኣስተያየት ለመስጠት ይችላሉ። የለውጡ ሃይል በገዢው ፓርቲ ኣካባቢም እየተወያየ የለውጥ ሃይል የሚባለውና የማይባለው የሚለየው መጽሃፍ ሲኖር ወይ የሆነ ዶክመንት ሲኖር ነው። ስለዚህ የለውጡ ሃይል ንጥር ያሉ ኣቅጣጫዎችን ያሳየን። የፌደራል ስርዓቱን በሚመለከት ያለው ኣቋም፣ የፖለቲካ አሰላለፉን በሚመለከት፣ የብሄር ፖለቲካን እንዴት እንደሚያየው፣ የቡድን ኢኮኖሚን እንዴት እንደሚያየው በአጠቃላይ የማህበረ ፖለቲካችን መግቢያ የት እንደሆነ የሚገልጽ መጽሃፍ ማግኘት አለብን።

2. የሽግግር ስራን ይመለከታል

ከዚህ በፊት በኢትዮጵያውያን ዘንድ ጉልህ ድርሻ የነበረው ኣስተያየት የሽግግር መንግስት ይቋቋም የሚል ነበር። ሃገራችን ወደ ተሻለ ስርዓት እንድትገባ ይህ ያስፈልገናል ብሄራዊ መግባባት ያስፈልገናል የሚል ነበር። ይህ ኣሳብ ኣሁን ቀዝቅዟል። ለምን ቢባል እነ ዶክተር አብይ የሽግግር ስራውን እንሰራዋለን እመኑን በማለታቸው ነው። ልዩነቶች እንዳሉ ሆነው ይህ የለውጥ ሃይል ሊሰራ የሚገባው የሽግግር ስራ መሆኑን ኣይዘንጋ። ከሽግግር ስራ ኣንዱ ምርጫ ቦርድን ማስተካከል። ትልቅ ሃገራዊ የመግባባት ኮንፈረንስ ማድረግ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጽህፈት ቤታቸውን ከፍተው ለምርጫ እንዲዘጋጁ ማድረግ፣ ህግ ማስከበር ይመለከታል። በመሆኑም በዚህ ረገድ ትኩረት ሰጥቶ እንደ ሽግ ግር መንግስት ሊሰራ ይገባል።

3 ስምምነቶችን ሁሉ ግልጽና ህጋዊ ማድረግ

ሃገሪቱ ወደ ለውጥ በምትጓዝበት በአሁኑ ሰዓት የለውጥ ሃይል የምንለው ተቃዋሚውን ኣገር ቤት ይገባ ዘንድ ይጋብዛል። ይሄ ግሩም ነገር ነው። ነገር ግን የተደራጁ ሃይላት ወደ ሃገር ቤት ሲገቡ በይፋ የስምምነት ሰነድ መፈረም ኣለበት። መንግስትና ኦነግ ምን እንደተዋዋሉ ኣይታወቅም ነበር። ኦነግ ገባ፣ ግንቦት ሰባት ገባ ወዘተ ሲባል ከምንሰማው ውጭ ከመንግስት ጋር ባለስንት ኣንቀጽ ስምምነት እንዳደረገ ኣናይም። ሰነድ ያስፈልጋል። ለዚህ ነው ኦነግ ትጥቅ ኣልፈታሁም ሲል የለም ትጥቅ እንዲፈታ ኣውርተን ነበር የሚባለው። በዚህ ላይ ኣሁንም መንግስት መፈራረም አለበት።

4. ፍጥነት

ለውጥ ተገቢ ፍጥነትን ይጠይቃል። እንደ ሁኔታው ማለቴ ነው። ስለዚህ ቅድሚያ የሚሰጣቸውን ቅድሚያ እየሰጠ የለውጡ ሃይል በፍጥነት የሚቀየሩትን ለመለወጥ መስራት ያስፈልጋል። ኣንዳንዶቹን ጥያቄዎች በሚገባ መረዳት ይጠይቃል። ለምሳሌ የአዲስ ኣበባ ጥያቄ ሲነሳ ለብቻው መልስ ኣያገኝም። የስርዓት ጥያቄ ነው። የፌደራል ስርዓቱ ሳይሻሻል ኣዲስ ኣበባ ለብቻዋ ጥያቄዋ ኣይፈታም። የሌሎች ክልሎች ጥያቄዎችም እንደዚሁ ስርዓታዊ ነውና እንዲህ ኣይነት ጥያቄዎች ትእግስት ይሻሉ። ዛሬ የሚፈቱ ኣይደሉም። ስለዚህ ከምርጫው በሁዋላ እንዲህ ዓይነት ጥያቄዎችን ማሳደር ጥበብ ነው እላለሁ። ለምሳሌ የአዲስ ኣበባን ጥያቄ እንመልስ ቢባል ህገ መንግስቱን ብንከተልም መልስ የለም፣ ቢኖርም ያፋጃል። የሰገን፣ የራያ፣ የወልቃይት፣ የሲዳማ፣ ጥያቄዎች ሁሉ ለይደር ቢቀመጡና ከስርዓት ለውጥ ጋር ኣብረው ቢመለሱ ይሻላል። ሌሎች ጉዳዮች ግን ለምሳሌ ምርጫ ቦርድን ማዋቀር፣ ሃገሪቱን ለምርጫ ማዘጋጀት ግን ፍጥነትን ይጠይቃል።

5. ኣሳታፊነት

የተረጋጋ ሽግግር ለማምጣት የለውጡ ሃይል ኣሳታፊ ቢሆን ኣይከስርም። ስለዚህ ተቃዋሚዎችን በአንዳንድ ቦታዎች ላይ ማሳተፍ ተገቢ ይመስለኛል። ይቺው ናት ያለችኝ ኣሳብ። ሰው ያለውን ከወረወረ ይባል የለ……..

 

Filed in: Amharic