>
7:17 am - Tuesday December 6, 2022

ልደቱ አያሌው ለምን ፊቱን ለምርጫ 97፣ ጀርባውን ለመደመር መስጠት እንደመረጠ አይገባኝም!!!  (ዶ/ር በድሉ ዋቅጅራ)

ልደቱ አያሌው ለምን ፊቱን ለምርጫ 97፣ ጀርባውን ለመደመር መስጠት እንደመረጠ አይገባኝም!!!
 ዶ/ር በድሉ ዋቅጅራ
.
የልደቱ አያሌው አላማ አልገባህ አለኝ፡፡ አሁን ሀገራችን በአዲስ ለውጥ ላይ ሆና በርካታ ውስብስብ ችግር፣ ተስፋና አደጋ ላይ እያለች፣ ነጋ ጠባ በየብዙሀን መገናኛው እየቀረበ ስለምርጫ 97 የሚብከነከነው ለምን እንደሆነ አልገባህ አለኝ፡፡
.
ልደቱ አብዝቶ የሚያወራው ዶ/ር ብርሀኑ፣ ኢንጅነር ሀይሉ . . . ሌሎቹም አብዛኞቹ በወቅቱ ስህተት እንደሰሩና፣ እሱ ብቻ ትክክል እንደነበረ ነው፡፡ ስለምርጫ 97 ልደቱና ዶ/ር ብርሀኑ ነጋ መጽሀፍ ጽፈዋል፤ እኛም አንብበናል፡፡ በሁኔታው ስለተሳተፉ የሁለቱም መጽሀፍ ‹‹ለራስ ሲቆርሱ. . .›› እንደማያጠው እንገምታለን፤ ስናነብም እንመረምራለን፡፡  ወደፊት ግን ምርጫ 97 በታሪክ ጸሀፊዎች መጻፉ አይቀርም፤ ጉዳዩን ለን ለታሪክ ጸሀፊዎች አይተወውም፤ ‹‹እኔ ትክክል ነበርኩ›› እያሉ ህዝብን ማደንቆር ምንድነው? ልደቱ ይህን ውትወታውን እንዲያቆም ፣  ህዝብ ሰላማዊ ሰልፍ ወጥቶ ሀሳቡን መቀበሉን ማረጋገጥ አለበት?
.
ልደቱ በምርጫ 97 የተደገመ እስኪመስል ድረስ፣ በየሚዲያው ዘመቻውን ተያይዞታል፡፡ በምርጫ 97 የተነጠቅነው ለውጥ አሁን በትግል ሲገኝ፣ አቶ ልደቱ ለምን ጉልበቱንና ጊዜውን የተገኘው ለውጥ ችግሮችን ለመታደግ እንደማያውለው፣ ለምን ፊቱን ለ97፣ ጀርባውን ለመደመር የለውጥ ጉዞ መስጠት እንደመረጠ አይገባኝም፡፡
.
በእኔ አስተያየት ልደቱ አያሌው በምርጫ 97 ማግስት (በተደረገበት የስም ማጥፋትም ይሁን እውነት ተግባሩን ፈጽሞ) በደረሰበት ህዝባዊ መተፋት እዚያው 97 ላይ ቀርቷል፤ ዛሬ በወቅቱ አብረውት የነበሩ ሰዎች የመደመር ለውጥ አካል ሆነው ሲመጡ፣ መቀበል የተሳነው ይመስለኛል፤ እናም እነዚህን ሰዎች ጎትቶ ወደ 97 ለመመለስ መከራውን እያየ ነው፡፡
.
እውነት ልደቱ ለህዝብ የሚያስብ፣ የሀገሪቱም ጉዳይ ጉዳዩ ከሆነ ጊዜውንና እውቀቱን ለምን እጃችን ስለገባው ለውጥ ችግሮች. . . . ስለሚያምሰን የጎሳ ግጭት፣ ስለ 8 ሚሊየን ተፈናቃይ፣ ስለሚሞቱ ንጹሀን አያውለውም?   . . .  እስቲ ምታውቁት ምከሩት፡፡
Filed in: Amharic