>

“ሥርዓት እና ሕግ አልባው” የኢትዮጵያ የጦር መሣሪያ አያያዝ!!! (ውብሸት ሙላት)

“ሥርዓት እና ሕግ አልባው” የኢትዮጵያ የጦር መሣሪያ አያያዝ!!!
ውብሸት ሙላት
አነስተኛ እና ቀላል የጦር መሣሪያን የሚመለከት በቂ ሕግ ከሌላቸው አገራት መካከል ኢትዮጵያ አንዷ ናት፡፡ መንግሥት፣ በመግዛትም ይሁን በማመረት የመከላከያ ሠራዊቱን፣ ሚሊሻውን፣ የፖሊስና እና ሌሎች የጸጥታ ሠራተኞችን የጦር መሣሪያ ያስታጥቃል፡፡
 ከእነዚህ በተጨማሪም፣ በተለያዩ ምክንያቶች ሌሎች ግለሰቦችም (ባለሥልታናት፣የጥበቃ አባላት ወዘተ) እንዲሁ ከመንግሥት ግምጃ ቤት የሚወጣ አነስተኛ የጦር መሣሪያ ሊታጠቁ ይችላሉ፡፡ ግለሰቦችም በግል ጥረታቸው ያገኙትን መሣሪያ አስመዝግበው በይፋ ካልሆነም በድብቅ ይይዛሉ፡፡ ግለሰቦች የሚይዙት እና የሚታጠቁት የጦር መሣሪያ በምን ሁኔታ በእጅ እንደሚገባ፣ የሽያጭ እና ግዥ ቦታውን ወይንም ገበያውን በውል እና በገልጽ ለይቶ ማመልከት ቢቸግርም መግዛት የሚፈልግ ሰው ግን አያጣም፡፡
መንግሥትም በግለሰቦች እጅ የሚገኙትን  “የትም ፍጭው ዱቄቱን አምጭው” በሚል ብሂል ዓይነት ከየት እንደተገኙ ሳያጣራ ፈቃድ ይሠጣል፡፡ ሲያሰኘውም ይነጥቃል፡፡ይህ ጽሑፍ ዜጎች የጦር መሣሪያ ሊይዙ እና ሊታጠቁ የሚችሉበትን ሁኔታ በመፈተሸ ከዚሁ ጋር የተያያዙ በርካታ ጉዳዮችን በተመለከተ ተጨማሪ ሕግ አስፈላጊ መሆኑን ይጠቁማል፡፡ በርዕሱ ላይ ሕግ አልባ የሚል ሐረግ መኖሩ ያሉት ሕጎች ካለመኖር የማይሻሉ በመሆናቸው እንጂ ፈጽሞ ሕግ የለም በሚል በሚል አይደለም፡፡
የአነስተኛ እና የቀላል ጦር መሣሪያ ነገር በኢትዮጵያ በሌሎች አገራት!
“አነስተኛ የጦር መሣሪያ” በመባል የሚታወቁት አንድ ሰው ከቦታ ቦታ ሊያንቀሳቅሳቸው የሚችሉትን ሲሆን፣ በበርካታ ሰዎች ተሳትፎ የከቦታ ቦታ ሊዘዋወሩ የሚችሉት ደግሞ “ቀላል የጦር መሣሪያ” በመባል ይታወቃሉ፡፡ አገራት በሕጋዊ መንገድ ለዜጎች የሚፈቅዱት አነስተኛ የጦር መሣሪያዎችን ሲሆን ከእነዚህም ውስጥ ሙሉ በሙሉ አውቶማቲክ የሆኑትን የሚከለክሉ አሉ፡፡ ቦንቦችም በዚሁ በአነስተኛ የጦር መሣሪያ ምድብ ውስጥ ነው የሚገኙት፡፡
በኢትዮጵያ፣ ከመከላከያ ሠራዊቱና ከሕግ አስከባሪዎች ውጭ ባሉ ዜጎች እጅ በሕጋዊም ይሁን በሌላ መንገድ የገባ፣ ወደ 350,000 ገደማ የጦር መሣሪያ እንዳለ ይገመታል፡፡ በሕጋዊም ይሁን ሕጋዊ ባልሆነ መንገድ የተያዘው፤ ከ100 ሰው አንጻር ሲሰላ 0.4 ብቻ  ነው፡፡  በጦር መሣሪያ ብዛት ደግሞ ከ178 አገራት 101ኛ ፣ ከ100 ሰው ውስጥ መሣሪያ በመታጠቅ ከ178 አገራት 174ኛ ናት፡፡
በሕግ አስከባሪዎች እጅ የሚገኝው 104,847 ሲሆን፤በወታደሩ እጅ የሚገኘው ደግሞ 1.1 ሚሊዮን ይገመታል፡፡ በመንግሥት እጅ የሚገኘው በዜጎች እጅ ከሚገኘው አራት እጥፍ አካባቢ ይበልጣል፡፡ይህ ከባድ የጦር መሣሪያዎችን አያካትትም፡፡ ከ20002-2004 (እ.ኤ.አ) ብቻ ከጦር መሣሪያ ጋር በተገናኘ 9,531 እስራት እና ክስ ነበሩ፡፡  11,500 አነስተኛ የጦር መሣሪያ፣3,000 የእጅ ቦንቦች፣170,000 ጥይቶች እ.ኤ.አ. በ2006 ተወግደዋል፡፡
የጦር መሣሪያ በግል ማማረት ክልክል ነው፡፡ ሙሉ አውቶማቲክ የሆኑ የጦር መሣሪያዎችን በግል መያዝን የሚከለክል ሕግም የለም፡፡ ፈቃድ ለማውጣት፣ ጠያቂው በቂ ምክንያት ለምሳሌ አደን፣ራስን ለመጠበቅ ወዘተ መሆኑን ማሳየት ይጠበቅበታል፡፡ በግልጽ ያልተቀመጠ፣ ወይንም ይዘቱ ምን እንደሆነ መገመት የማይቻል፣ የኋላ ማንነት መለኪያን ማለፍ ግድ ይመስላል፡፡ በኢትዮጵያ ፈቃድ ለማግኘት  የሦስተኛ ወገንን ምስክርነት (Reference) ማግኘት አስፈላጊ አይደለም፡፡ ፈቃድ ለማግኘት ንድፈ-ሐሳባዊ እና የተግባር ሥልጠና አስቀድሞ ያገኘ መሆንንም አይጠይቅም፡፡
በግል መሸጥ እና ማስተላለፍ ክልክል ነው፡፡ የመሣሪያውን ዳና መከተታያ ሥርዓት የለም፡፡ የጦር መሣሪያን መሸጥ እና ለሌላ ሰው ማስተላለፍም አይቻልም፡፡ዜጎች በጥረታቸው ያገኙትን ማንኛውም ንብረት የመጠቀም፣ የመሸጥ፣ የመለወጥ እና የማስተላለፍ መብት እንዳለቸው ሕገ-መንግሥቱ አንቀጽ 40(1) ላይ በግልጽ አስፍሯል፡፡ የጦር መሣሪያም ቢሆን በራስ ጥረት የተገኘ እስከሆነ ድረስ የንብረት አካል እንዳይሆን የሚያግድ ሕግ የለም፡፡
ይሁን እንጂ ዜጎች ከንብረት ባለቤትነት የሚመነጩ መብቶችን እንዳይጠቀሙ የሚገድብ ሕግ ሊኖር ይችላል፡፡የዜጎች መብት መከበሩ የሕዝብን ጥቅም የሚጎዳ ሲሆን ሊገድብ ይችላል፡፡ ከላይ የተጠቀሰው አንቀጽ ይሄንኑ መሥፈርት አስቀምጧል፡፡በመሆኑም፣ አነስተኛ የጦር መሣሪያ ባለቤት መሆንን ወይንም ባልተቤት ከሆኑ በኋላ አንዳንድ ጉዳዮችን የሚገድቡ ሕጎች ሊኖሩ ይችላል፡፡
አገራት፣ የጦር መሣሪያ መያዝ እና መታጠቅን የሚገድቡ እና የሚከለክሉ እንጂ የበለጠ የሚያጠናክሩ የሕግ ማእቀፍን ሲያሰፍኑ አይስተዋልም፡፡ኢትዮጵያም ደግሞ በግልጽ ያስቀመጠችው ወንጀል የሚሆንባቸው ሁኔታ ብቻ ነው ማለት ይቻላል፡፡
በነፍስ ወከፍ የጦር መሣሪያ ከሕዝብ ብዛት አንጻር ሲሰላ ከአሜሪካ ሕዝብ 89 በመቶ በመታጠቅ ቅድምናውን ይወስዳሉ፡፡ ከመቶ ሰው መካካል ሰማኒያ ዘጠኙ የጦር መሳሪያ አላቸው፡፡ከአሜሪካ በመቀጠል በመቶኛ ሲሳላ እስከ አስረኛ ደረጃ የሚይዙት ደግሞ የሚከተሉት አገራት ናቸው፡፡
የመን (61%) ፣ ስዊትዘርላንድ (46%) ፣ፊላንድ (45%)፣ሰርቢያ (38%)፣ ቆጵሮስ (36%) ፣ሳውዲ አረቢያ (35%)፣ ኢራቅ 34(%)፣ ኡራጓይ (32%)፣ ሲውዲን (32%)  ናቸው፡፡ የአፍሪካ ቀንድ አገራት ደግሞ የሱዳን ዜጎች 2 ሚሊዮን ገድማ ሲኖራቸው፣ ከመቶው 5.5 ይሆናል፡፡ በመንግሥት እጅ 450 ሺ ገደማ ይገኛል፡፡
ግብጽ በበኩሏ 2 ሚሊዮን የሚሆነው ሕዝቧ የታጠቀ ሲሆነ ከመቶ ሲሰላ ደግሞ 3.5 ይሆናል፡፡ ከ178 አገራት 37ኛ ከሰው ብዛት ደግሞ 115ኛ ናት፡፡ በመንግሥት እጅ 2.5 ሚሊዮን የሚገመት መሣሪያ አለ፡፡
ኤርትራ በዜጎች እጅ የሚገኘው 20,000  ከመቶው ሲሰላ 0.5 ሲሆን፤ በመንግሥት እጅ ደግሞ  ከ800 ሺ በላይ ነው፡፡
 ደቡብ ሱዳን በግምት ከ1-3 ሚሊዮን ዜጎቿ የታጠቁ ሲሆን ፣ ከመቶው ደግሞ 28.2 ነው፡፡ በመንግሥት እጅ 300 ሺ ገደማ ይገኛል፡፡ ኬንያ በዜጎች እጅ 650 ሺ ገደማ የሚገኝ ሲሆነ፣ ከመቶው 1.4 ገደማ ነው፡፡ ፣ሶማሊያ 9.1% የሚሆኑት ዜጎቿ ባለመሣሪያ ሲሆኑ፣ አጠቃላይ ቁጥሩ ደግሞ 650 ሺ  ይገመታል፡፡ በመንግሥት እጅ ደግሞ 130 ሺ  ይሆናል፡፡
 ጂቡቲ  በበኩሏ 2.8 ከመቶው ዜጎቿ የታጠቁ ሲሆን  ናቸው፡፡ ከላይ ከቀረበው መረጃ አንጻር የኢትዮጵያ እጅግ ዝቅተኛ የሚባል ነው፡ በዓለም ላይ በየዓመቱ 12 ቢሊዮን ጥይቶች እና 8 ሚሊዮን የጦር መሣሪያ ተመርቶ ወደ ገበያ ይቀላቀላል፡፡ ከዓለም ሕዝብ ደግሞ 10 ከመቶው ታጥቋል፡፡
የዜጎች የጦር መሣሪያ ባለቤትነት ጉዳይ!
የዜጎችን የጦር መሣሪያ መያዝ እና መታጠቅ ፍላጎትን ማስከበር እና መብት ማድረግ በርካታ ጠቀሜታዎች አሉት፡፡እርግጥ ነው እንደ ብዙዎቹ የመብት ዓይነቶች ሁሉ ገድብ ሊኖረው ይገባል፡፡በአሜሪካ፣ የጦር መሣሪያ መያዝ እና መታጠቅ ሕገ መንግሥታዊ መብት ነው፡፡ የዚህን መብት ዋጋ እና ጠቀሜታ ጆርጅ ዋሽንግተን እንደሚከተለው ገልጾታል፡፡ “ከራሱ፣ ከሕገ መንግሥቱ ቀጥሎ እጅግ በጣም ጠቃሚ አለ ከተባለ የጦር መሣሪያ ነው፡፡ለአሜሪካ ሕዝብ የነጻነት/liberty/ ጥርስ እንዲሁም ከቅኝ ግዛት በመላቀቅ ነጻነትን/independence ለመጎናጸፍ ያበቃን የመሠረት ድንጋያችን ነው፡፡”
ስለዚሁ ጉዳይ የሚደነግገው የአሜሪካ ሕገ መንግሥት፣ ማሻሻያ ቁጥር ሁለት፣ “የሕግ ትዳር የተበጀለት ሚሊሻ፣ለአንዲት ነጻ አገር ዋስትና አስፈላጊ በመሆኑ፣ ሕዝብ የጦር መሣሪያ የመያዝ እና የመታጠቅ  መብቱ መቼም ቢሆን አይነካም፡፡”  በማለት ጥበቃ አድረጓል፡፡ የዚህ ድንጋጌ መነሻው ሕዝብ በመንግሥት ላይ ያለው ጥርጣሬ ነው፡፡
በተለይም መሣሪያ የታጠቀ ተጠባባቂ የጦር ሠራዊት ካለ መንግሥት ባሰኘው ጊዜ ሕገ መንግሥቱ ላይ የተቀመጠውን የሥልጣን ገድብ ለማለፍ ማበረታቻ ይሆነዋል፡፡ ዜጎችም መብታቸው በመንግሥት አላግባብ ሲቀሙ የሚያስከብሩበት ጉልበት አይኖራቸውም፣ ከሚል መነሻ ነው፡፡  ከቅኝ  ግዛት ለመላቀቅ አገልግሏል፡፡ ከጨቋኝ መንግሥታት ለመጠበቅም ዋስትና ይሠጣል፡፡
ከሕገ መንግሥት ግቦች ውስጥ ሁለቱ የመንግሥትን ሥልጣን መገደብ እና የግለሰቦችን መብት ማስጠበቅ ነው፡፡ በመሆኑ መንግሥትን ጉልበቱን አፈርጥሞ ዜጎችን ለመጨቆን የሚጠቀመው የጦር መሣሪያ የታጠቀ ፖሊስ፣ ወታደር እና የጸጥታ ሠራተኞች ስለሆነ እነዚህን ኃይሎች ለመገዳደር ወይንም እንዳሻቸው የሕዝብን መብት እንዳይጥሱ ሕዝቡ የግድ  የጦር መሣሪያ ሊኖረው ይገባል፡፡ በዚህ መንገድም መብቱን ማስጠበቅ ይችላል፡፡
መንግሥት እንኳን ቢፈርስ እና አገር በጠላት እጅ ብትወድቅ ሕዝብ ካልታጠቀ ከጠላት ባርነት ሊላቀቅ አይችልም፡፡ ኢትዮጵያ በጣሊያን እጅ በወደቀች ጊዜ በአርበኞቿ ነጻ እንደወጣችው ማለት ነው፡፡
መንግሥት የሕዝብ ተወካይ ነው ቢባልም ሁልጊዜም እንደወኪል ብቻ በመሥራት ታማኝ ነው ማለት ግን ዘበት ነው፡፡ ላለመታመናቸው ደግሞ ታሪክ ምስክር ነው፡፡ኦቶማን ተርኪይ (ቱርክ) ከ1915-1917 ባሉት ጊዜያት 1.5 ሚሊዬን በተለይ ክርስቲያን አርመኖችን፤ሶቪየት ኅብረት ከ1929-1945 ወደ 20 ሚሊዮን የሚጠጉ የተቃዋሚ ፓርቲ አባላት እና ገበሬዎችን፤ ናዚ ጀርመን ከ1933-1945 ባሉት ጊዜያት 20 ሚሊዮን ተቃዋሚ ፖለቲከኖችን፣ ጂፕሲዎች፣ አይሁዶችን፣ በማናቸውም ሁኔታ መንግሥትን የሚተቹትን፤ ቻይና ደግሞ 40 ሚሊዮን ገደማ የሚሆኑ የመንግሥት ጠላት የሚባሉት፣ የገጠር ሕዝብ፣ ተቃዋሚ ፖለቲከኞችን፤ኡጋንዳም ከ1971-1979 ድረስ  ሦስት መቶ ሺ ክርሥቲያን የፖለቲካ ተቃዋሚዎች፤ካምቦዲያ ከ1975-1979 ድረስ 2 ሚሊዮን ዜጎችን፤ ሩዋንዳ በ1994 ብቻ 800 ሺ ቱትሲ፣ደርግ በርካታ ሺ ሰዎችን ገድለዋል፡፡
የታጠቀ እና ጉልበተኛ የሆነ መንግሥት ከተሰጠው ወሰን በማለፍ የዜጎችን መብት እና ነጻነት ይጥሳል፡፡ ይህንን ለመከላከል ወይንም በሕዝብ እና በመንግሥት መካከል ያለውን ውል ለማስከበር የዜጎች መታጠቅ ወሳኝ ነው፡፡ በተለይ የአሜሪካ የሕገ መንግሥት አባቶች የሚባሉት አምባገነነን መንግሥትን መቋቋምን/መገዳደርን መቻልን እንደ ትልቅ ቁምነገር ቆጥረውታል፡፡ ሕዝቡም እስካሁን ድረስ ይህንን መብቱን ላለማስነጠቅ የተጋ ይመስላል፡፡ ሕዝብ ካልታጠቀ በስተቀር የታጠቀ መንግሥትን መቋቋም ፈጽሞ አይችልም፡፡
የጦር መሣሪያ ከመንግሥት ብቻ ሳይሆን ከሌሎች ጥቃቶች ራስን ለመከላከልም ይጠቅማል፡፡ በኢትዮጵያ ደግሞ ከዚህ ባለፈም የክብር እና የጀግንነት መገለጫም ነው፡፡
“መስኮብ የያዘ ሰው አትለፍ በደጄ፣
እንደ ገላባ እሳት ትጠፋለህ በእጄ፣
ወጨፎ የያዘ ይንኮሻኮሽብኝ፣
ምንሽር የያዘ እራሱ ይምጣብኝ፣ 
አልቢን የያዘ ሰው ይሁነኝ ውሽማ፣
   መውዜር አይገዛም ወይ ባሌ እንዲሆንማ፡፡”
ዜጎች የጦር መሣሪያ ባልተቤት ሲሆኑ!
ሕዝቡ በዘመናት ተጋድሏቸው ያስከበሯቸውን መብቶች እና ጥቅሞች ሊነጥቃቸው ከሚመጣ ማናቸውም ኃይል መከላከል ከሚችሉባቸው ተቋማት ዋነኛው ሚሊሺያ ሲሆን በአንድ በኩል ዜጎች በስፋት የሚሳተፉበትን ሁኔታ ማማቻቸት ሕዝባዊ ባሕርይውን  እና የታጠቀ ኃይል በመሆኑ ደግሞ  ልዩ ባሕርይውን የሚደንግግ ሕግጋት አላቸው፡፡ ክልሎች ሚሊሻን የሚመለከቱ ሕግጋት አሏቸው፡፡
 ከላይ የቀረበው ሐሳብ የተወሰደው ከአማራ ክልል “የሚሊሻ መተዳደሪያ ደንብ” በሚል ከወጣው ሕግ ነው፡፡ ይህ ሕግ ሲጀምር ሚሊሻ ሕዝባዊ እንደሆነ፣ የውጭም ይሁን የውሥጥ ኃይሎች መብቶቻቸውን እንዳይጥሱ ለመከላከል ሲባል እንደተቋቋሙ ይገልጻል፡፡
በመሆኑም፣ ከዚህ መረዳት የሚቻለው የታጠቀ ሕዝብ ‘ሚሊሻ’ እንደሚባል እና ዋና ዓላማውም ዜጎች ታጥቀው የሕዝብ መብትን ማስከበር እንጂ የመንግሥትን ትዕዛዝ እየተቀበለ የሚፈጽም ተቋም አለመሆኑን ነው፡፡ ይሁን እንጂ፣ይህ ደንብ ወደ ውስጥ ገባ ብሎ ላጤነው የመንግሥት ታዛዥ እና የመንግሥት ተቋም መሆኑን ነው፡፡
ምንም እንኳን ዜጎች ሚሊሻ የመሆን መብት ቢኖራቸውም አወቃቀሩም ይሁን ከተሠጡት ተልእኮዎች እና ግዴታዎች አንጻር ሲታይ ግን ዜጎች ራሳቸውን ከመንግሥት እና ከሌሎች ጥቃት የሚከላከሉበት ተቋም አይደለም፡፡ የመንግሥት የራሱ ተቋም ነው፡፡ ይህ ደግሞ የሚሊሻን ባሕርይ የሚቃረን ነው፡፡ የሌሎቹ ክልሎችም ከዚሁ የሚለይ አይደለም፡፡
በመሆኑም፣ በኢትዮጵያ፣ ዜጎች ራሳቸውን ከመንግሥት ጥቃት እና በደል ሊከላከሉ የሚችሉበት ወይንም ሕዝቡን ፈርቶ እና አክብሮ እንዲሠራ የሚስገድዱበት ሁኔታ የለም፡፡ ይልቁንም ባለፈው ዓመት መጨረሻ ኣካባቢ ላይ መሪዎቻችን ሲናገሩ እንደተደመጡት “መንግሥት የሕዝብ ዓመጽን እንደማይፈሩ እና የመቆጣጠር ሙሉ ኣቅም እና ዝግጁነት አለው” የሚል ነው፡፡
አሜሪካኖች ሕዝብ መሣሪያ የመያዝና እና የመታጠቅ መብታቸውን የማስከበራቸው ምክንያት መንግሥት ሕዝብን ፈርቶ እንዲኖር ለማድረግ ነው፡፡ በአንድ ወቅት የሕንዱ የነጻነት አባት ማኅተመ ጋንዲ እንዲህ ብሎ ነበር፡፡ “እንግሊዞች ሕንድ ላይ ካደረሱት በደል ሁሉ የከፋው ሕዝቡን ትጥቅ ማስፈታታቸው ነው፡፡” የታጠቀን ሕዝብ ፖሊስም ይሁን ሌላ የጸጥታ ሠራተኛ እንዳሻው መብቱን ሊጥስበት አይችልም፡፡
በእኛም፣አገር የተወሰኑ አካባቢዎች በምሳሌነት ማንሳት ይቻላል፡፡ አፋር፣አርማጨሆ ወዘተ ፖሊስ ሕዝቡን እንዳሻው ማድረግ ይገደዋል፡፡ የቀዳማይ ወያኔን፣የጎጃም ገበሬዎችን፣የባሌ አመጽን የሚያወድስ አካል ሕዝብ እዳይታጠቅ መከልክል እርስ በርሱ ይጋጫል፡፡ ነገር ግን የጦር መሣሪያ አያያዝ ተገቢ የሆነ የሕግ ትዳር ሊበጅለት ግድ ነው፡፡
የጦር መሣሪያ መያዝና እና መታጠቅ በርካታ ጉዳቶችም አሉት፡፡ የበርካታ ዜጎችን ሕይወት እና ንብረት ማውደሚያ ሆኗል፡፡ የጦር መሣሪያ በራሱ የግጭት መንሥኤ ባይሆንም ያባብሳል፡፡ የጉዳትንም መጠን ይጨምራል፡፡በአሸባሪዎች እጅ ሲጋብ ደግሞ ጉዳቱ እጥፍ ድርብ ይሆናል፡፡የዕርስ በርስ ግጭት እና ጦርነትንም ያባብሳል፡፡ የጦር መሣሪያ ዝውውርን እና ባልተቤትነትን በእግባቡ ካለመቆጣጠር የሚመጣን ጣጣ ለማስወገድ ወይንም ለመቀነስ ሲባል መንግሥት ለበርካታ ችግሮች ይጋለጣል፡፡
የጦር መሣሪያ ሁኔታ በኢትዮጵያ! 
ኢትዮጵያ፣አነስተኛ የጦር መሣሪያ መሥራትን፣ወደ ውጭ መላክንም ሆነ ማስገባትን፣ወደ ሌላ አገርም ሆነ ሰው ማስተላለፍን የሚመለከት የሕግነት ቅርጽ ይዞ የወጣ አዋጅ፣ደንብ ወይንም መመሪያ ወይንም የማስተዳደሪያ ሥርዓት የላትም፡፡ በሕጋዊ መንገድ በብቸኝነት ወደ አገር ውስጥ ማስገባት የሚችለው የፌደራል መንግሥት ብቻ ነው፡፡
 በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 55(1)(ሸ) ላይ እንደተገለጸው የጦር መሣሪያ አያያዝን በተመለከተ ሕግ የማውጣት ሥልጣን ያለው የፌደራሉ መንግሥት ነው፡፡ክልሎች በወሰናቸው ውስጥ ያለውን ጸጥታ ለማስፈን ፖሊስ እና ሚሊሻ የማቋቋም ሥልጣን ቢኖራቸውም ሊያስታጥቋቸው የሚችሉትን የጦር መሣሪያ ዓይነት፣ ብዛት፣ አቅርቦት እና የመሳሰሉትን ጉዳዮች የሚወስንላቸው ግን የፌደራሉ መንግሥት ነው፡፡
 የአጼ ኃይለ ሥላሴ መንግሥትን ጨምሮ ከዚያ በፊት በነበሩት ጊዜያት ግን በውጭ አገር ዜጎች ደላላነት እና አስመጭነት በየጠቅላይ ግዛቱ የነበሩ ባላባቶች አንዳንዴ በንጉሠ ነገሥቱ  ብዙ ጊዜ በራሳቸው ፈቃድ ከውጭ ማስገባት ይችሉ ነበር፡፡
የጦር መሣሪያ አቅራቢው መንግሥት ብቻ ከሆነ፣ በራሱ መልካም ፈቃድ ካልሆነ በስተቀር ዜጎች መታጠቅ አይችሉም ማለት ነው፡፡ የደርግ መልካም ፈቃድ ለአባላቱ እና ለጥበቃ ጓዶቹ፣ ኢሕአዴግም የፓርቲው አባል ሆነው ሥልጣን ላላቸው እና ለሚሊሻዎች ነው፡፡ ይህ ደግሞ የመንግሥትን ዋስትና እንጂ ለዜጎች ከመንግሥት ለመጠበቅ የሚያበረክተው አንዳች ነገር የለም፡፡ስለሆነም ቀሪዎቹ ዜጎች በሕገ ወጥ መንገድ ለመያዝ ይገደዳሉ፡፡
የመሣሪያ ደላላነትን ወይንም ነጋዴነትን የሚፈቅድ ሕግ የለም፡፡ በእርግጥ የንግድ ምዝገባ አዋጁ መሣሪያ ለመጠገን፣ጥይቶችን እና ፈንጅዎችን ለመሸጥ እና ለመለወጥን  የንግድ ፈቃድ ማውጣት እንደሚቻል ታሳቢ ያደረገ ይመስላል፡፡
ይሁን እንጂ አሁን ባለው አሠራር በመሣሪያ መነገድ ወይንም ማዘዋወር  ክልክል ከመሆኑም ባለፈ በወንጀል  ሕጉ አንቀጽ 481 መሠረት እስከ አስራ አምስት ዓመታት የሚደርስ እስራትን ያስከትላል፡፡ ፈቃድ ሳይኖር ይዝዞ መገኘት ብቻ ከሆነ በደንብ መተላለፍ እስከ ስምንት ቀናት የሚደርስ እስራት ወይንም የ100  ብር ቅጣት ሊያመጣ ይችላል ፡፡
የጦር መሣሪያ በብቸኝነት የማቅረብ ሥልጣኑ የፌደራል መንግሥት ቢሆንም የመሸጪያ ገበያ ግን የለም፡፡ ሕዝቡን ግን ከመሸጥ እና ከመግዛት መከልለከል አልተቻለም፡፡ ከደርግ በፊት በነበሩት መንግሥታት ሕጋዊ የመሣሪያ ነገዴዎች  እና የታወቁ የመሸጪያ ቦታዎች እንደነበሩ ታሪክ ያስረዳናል፡፡
አሁን ደግሞ ነጋዴዎች እና የመሸጪያ ቦታዎች አሉ፤ነገር ግን የሕግ ዕውቅና እና ጥበቃ የላቸውም፡፡ ፈቃድ የሌላቸው ነጋዴዎች፣ መንግሥት እንዳላየ ዝም ያላቸው፣ ገዥ እና ሻጭ የሚገበያይባቸው ቦታዎች በርካታ ናቸው፡፡
የጦር መሣሪያ ማስገባትን እና የማቀናጀት ተግባርን የሚወጣው ተቋም የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ሲሆን፣የተለያዩ ዓለማቀፍ ይዘት ያላቸውን ስምምነቶች እና ሌሎች ድርድሮች ደግሞ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ይሳተፋል፡፡ በተለይም በአጼ ምኒልክ ጊዜ በርካታ የውጭ ዜጎች መሣሪያ በማስገባት ኢትዮጵያ ውስጥ ይሸጡ ነበር፡፡ አሁን ግን በሀሜት ካልሆነ በስተቀር እነማን እንደሚነግዱ እና እንደሚደልሉ አይታወቅም፡፡
የጦር የመሣሪያ ፈቃድ መሠጠት ያለበት  ከያዙ በኋላ ሳይሆን ለመያዝ ነው ፡፡ በአገራችን፣ ሕጋዊ የጦር መሣሪያ መሸጫ ስለሌለ ማንም እንዳሻው ካገኘበት ይገዛል፡፡ ከዚያም የሚያስገድድ ሁኔታ ካጋጠመው  ከሚሊሻ ጽሕፈት ቤት ወይንም ደግሞ ከፖሊስ ጣቢያ (እንደ ክልሎቹ ይለያያል፡፡) ፈቃድ ያወጣሉ፡፡
ክልሎች ባለመሣሪያዎችን ፈቃድ እንዲያወጡ ሲጠይቁ፣ ሕዝቡ መንግሥትን ስለማያምን አንዱን ካስመዘገበ ሌላ የማያስመዘግበው ይገዛል፡፡ መረጃዎች እንደሚያሳዩት ምዝገባ በሚኖርበት ጊዜ የመሣሪያ ዋጋ ይንራል፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ከተመዘገበ አንድ ቀን መንግሥት ትጥቅ ማስፈታቱ አይቀሬ ነው የሚል ፍራቻ በብዙዎች ዘንድ ስለሠረጸ ነው፡፡
ሰዎች ስለሚይዙት የጦር መሣሪያ አጠቃቀም ዕውቀት ሊኖራው ይገባል፡፡ ፈቃድ ሲሰጥም፣ ልክ እንደ መንጃ ፈቃድ ንድፈ-ሐሳባዊ፣ ባሕርያዊ እና ተግባራዊ ችሎታዎች መመዘን ይኖርባቸዋል፡፡ኢትዮጵያ የፈረመችው እና ያጸደቀችው የናይሮቢ ፕሮቶኮልም ይሄንኑ ይጠይቃል፡፡ዜጎችም የሚለማመዱበት ቦታ እና የሚያሰለጥኑ ተቋማት ሊኖሩ ይገባል፡፡
በርካታ አገራት ዜጎች የጦር መሣሪያ አተኳኮስ እና አጠቃቀም የሚሠለጥኑባቸው ተቋማት አሏቸው፡፡ ዜጎች መሣሪያ መያዛቸው ካልቀረ ስለሚይዙት  መሣሪያ ባሕርይ ማወቅ ይገባቸዋል፡፡ በተለይም ከአያያዝ ጉድለት እና ከጥንቃቄ ማነስ የሚመጡ ጉዳቶችን ለመቀነስ ልምምድ የግድ ይላል፡፡ ከላይ የተጠቀሰው ፕሮቶኮልም ይህ እንዲሆን ግዴታ ይጥላል፡፡
የጦር መሣሪያም ይሁን ጥይት መለያ ቁጥር (ንምራ) ወይንም ሌላ ምልክት ያስፈልገዋል፡፡ ስንት መሣሪያ፣በማን እጅ፣ የት አካባቢ እንዳለ ማወቅ የሚያስችል አሠራር ማስፈን የመንግሥት ግዴታ ነው፡፡ ይህ ዓይነቱ አሠራር ወንጀል በሚፈጸምበት ጊዜ የድርጊቱን ፈጻሚ በቀላሉ ለመለየት ያስችላል፡፡ በአጼ ምኒሊክ ዘመን ወደ አገር ውስጥ የገቡ መሣሪያዎች፣ ቢያንስ የተወሰኑት እንዲህ ዓይነት መለያ እንደነበሯቸው ንጉሠ ነገሥቱ ከጻፏቸው ደብዳቤዎች መረዳት ይቻላል፡፡
የተሰረቁ መሣሪያዎችም በሌሎች ሰዎች እጅ ከገቡ በኋላ፣ምልክታቸውን በመጠቀም፣ ተመልሰዋል፡፡ ኢትዮጵያ፣ለተባበሩት መንግሥታት ድርጂት ከዘጠኝ ዓመታት በፊት ካቀረበችው ሪፖርት እና ካለው ልምድ ሲታይ ግን መንግሥት በግለሰቦች እጅ የሚገኝ መሣሪያን ዳናውን ማግኘት (tracing and tracking) የሚችልበትን ሁኔታ አልዘረጋም፡፡
ከዚህ በተጨማሪም የጦር መሣሪያ ደብቆም ይሁን በገሀድ ሊያዝ የሚከለከልባቸውን ቦታዎች (ለአብነት ቤተ እምነቶች፣ትምህርት ቤቶች፣የገበያ ቦታዎች፣ ጭፈራ ቤቶች ወዘተ) የሚለይ ሕግ ያስፈልጋል፡፡
ኢትዮጵያ፣ በታላላቅ ሐይቆች እና በአፍሪካ ቀንድ አነስተኛ እና ቀላል የጦር መሣሪያዎችን ክልከላ፣ቁጥጥር እና ቅነሳ የሚመለከተውን የናይሮቢ ፕሮቶኮል ፈራሚ ናት፡፡ በዚህ ፕሮቶኮል መሠረት ደግሞ ፈቃድ ሳይኖር በእጅ የገቡ አነስተኛ እና ቀላል የጦር መሳሪዎችን በመውረስ የማስወገድ ግዴታ አለባት፡፡
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት  አነስተኛ እና ቀላል የጦር መሣሪያ ሕገ ወጥ ንግድን ለመከላከል፣ለማስወገድና ለመዋጋት የወጣውን የድርጊት መርሐ ግብር አጽድቃለች፡፡ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሕገ ወጥ የጦር መሣሪያ ማምረት እና መነገድን ለመከላከል የወጣውን ፕሮቶኮል ተቀብላ አጽድቃለች፡፡
በተለይ የናይሮቢው ፕሮቶኮል፣ ዜጎች ያለምንም ገድብ አነስተኛ የጦር መሣሪያ ባለቤት የሚሆኑበትን አሠራር ይከለክላል፡፡ቀላል እና አውቶማቲክ  የጦር መሣሪያዎች በዜጎች እጅ መግባት እንደሌለባቸው ይደነግጋል፡፡ በዜጎች እጅ የሚገኝን ማንኛውም ዓይነት የጦር መሣሪያ በአንድ ቋት መመዝገብን ይጠይቃል፡፡
የጦር መሣሪያ እንዴት መቀመጥ እንዳለበት እና የመያዝ እና የመጠቀም ብቃትን አስቀድሞ ማረጋገጥ አስፈላጊ እንደሆነ ይገልጻል፡፡ፈቃድን መቆጣጠር እና ኦዲት ማድረግ ብሎም አንድ ሰው ምን ያህል መሣሪያ መያዝ እንዳለበት ቁጥጥር የማድረግ ግዴታን ይጥላል፡፡ የጦር መሣሪያን ማስያዣ በማድረግ ገንዝብ መበደርን ይከልክላል፡፡
የግል የጥበቃ እና የደኅንነት ድርጅቶች የሚይዟቸውን መሣሪያዎችም መመዝገብ እና መቆጣጠርም የመንግሥት ኃላፊነት እንደሆነ ያስቀምጣል፡፡ ኢትዮጵያ፣ ከላይ የተገለጹትን ግዴታዎች ለመወጣት ቃል ብትገባም ወይንም ፕሮቶኮሉን ብታጸድቅም የተጣሉባትን ግዴታዎች መወጣት የሚያስችሏትን የሕግ ማእቀፎች ግን አልዘረጋችም፡፡
በአጠቃላይ ሲታይ ኢትዮጵያ  የጦር መሣሪያ አያያዝን በተመለከተ በቂ ሕግ የላትም፡፡ የሕግ ማእቀፍ አለመኖሩ ዜጎች መሣሪያ እንዳይኖራቸው አላደረገም፡፡ላላቸውም መሣሪያ ጥበቃም አላደረገም፡፡ ዜጎችም የጦር መሣሪያ የመያዝና እና የመታጠቅ መብታቸው በግልጽ ተለይቶ አልተደነገገም፡፡ ዴሞክራሲን ለማስፈንም በሚውል መልኩ ሥርዓት አልተበጀለትም፡፡
 እንደውም ግጭት ለማባባስ  እና የግለሰቦችን ኪስ ለማደለብ እየዋለ ነው ማለት ይቻላል፡፡ ሕጋዊ ቢሆን ኖሮ ከግብር እና ቀረጥ ሊገኝ ይችል የነበረው አገራዊ ጥቅምም አልተገኘም፡፡ ያለ ግብር እና ቀረጥ ይሸጣል፡፡ ገቢውም ለምን እንደሚውል በግልጽ አይታወቅም፡፡
 ይህ ሁኔታ ደግሞ በተለይ ከጦር መሣሪያ ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ያላቸው ተቋማት በዚህ ተግባር እንዲሠማሩ ስለሚያደርግ ለሕግ ማስከበር ፈተና መሆኑ ጥርጥር የለውም፡፡ምናልባትም በዚህ ሕገ ወጥ ተግባር ላይ የተሰማሩ ሰዎች ይሆኑ እንዴ ሕግ እንዳይወጣ ያደረጉት የሚል ጥርጣሬ ማስነሳቱ አይቀርም፡፡
Filed in: Amharic