>

የፍቅር ፣ የአንድነት ፣ የይቅርታ ቋንቋ ከአፉ የማይጠፋ መሪ መምጣቱ ትልቅ ፀጋ  ነው!!! (ዶ/ር ኃይሉ አርአያ)

 የዶ/ር ኃይሉ አርአያ ፖለቲካዊ ትንተና          (ተስፋና ስጋታቸውንም ተናግረዋል)

የፍቅር ፣ የአንድነት ፣ የይቅርታ ቋንቋ ከአፉ የማይጠፋ መሪ መምጣቱ ትልቅ ፀጋ  ነው!!!

ዶ/ር ኃይሉ አርአያ

 * ጠ/ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ ከሰማይ የወረደ ፀጋ ነው

የጐሣ ፖለቲካ መፍትሔ ካልተገኘለት፣ የሚደከምለት ነገር ፍሬ አያፈራም
* የጎሳ ፖለቲካ በባህሪው፣ የግጭትና የጠባብነት መፈልፈያ ነው
* የፖለቲካ ድርጅቶች ምስቅልቅል ሁኔታ በእጅጉ ያሰጋኛል

 

አዲስ አድማስ

በጡረታ ላይ የሚገኙት የ82 ዓመቱ የዕድሜ ባለጸጋ አንጋፋው ፖለቲከኛና ምሁር ዶ/ር ኃይሉ አርአያ፤ እርጅና ቢጫጫናቸውም የአገራቸውን ወቅታዊ ፖለቲካ ለመተንተን አቅም አላጡም፡፡ በአካል የደከሙ ቢመስሉም ነፍሳቸው የጎረምሳ ነው፡፡ ጠ/ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይን “ከሰማይ የወረደ ጸጋ ነው” ሲሉ ባልተለመደ መልኩ የሚያደንቁት ዶ/ር ኃይሉ፤ ሦስቱን የኢህአዴግ ዘመን ጠ/ሚኒስትሮች በንጽጽር ያሳዩናል፡፡ አንጋፋው ምሁርና ፖለቲከኛ ዶ/ር ኃይሉ አርአያ፤ ከአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ ጋር በወቅታዊ
የፖለቲካ ጉዳዮች ላይ ተከታዩን ቃለ-ምልልስ አድርገዋል፡፡

ለረዥም ጊዜ ነው ከሚዲያና ከፖለቲካ መድረኩ ጠፍተው የቆዩት—-?
በመጀመሪያ የፖለቲካ ድርጅቴ፣ “አንድነት”፤ በተለያየ ምክንያት መቀጠል ባለመቻሉ፣ራሴን ከፓርቲ ፖለቲካ አገለልኩ፡፡ ሌላው የጤንነት ችግር ነበረብኝ፤ አሁን ግን ታክሜያለሁ፤ ደህና ነኝ፡፡
በአገሪቱ የሚታየውን ለውጥ እንዴት ይገልጹታል?
በጣም ጥሩ ለውጥ ውስጥ ነው ያለነው፡፡ በሃገር ጉዳይ ላይ በሰፊው መወያየት የሚቻልበት መንገድ መፈጠር አለበት በሚል ሰፊ ትግል ተደርጓል። አሁን ያ ትግል ፍሬ እያፈራ ይመስላል። በሀገር ውስጥም በውጪም ያሉ፣ በሀገሪቱ ጉዳይ ያገባናል የሚሉ ሰዎች ተገናኝተው፣ የሚወያዩበትና መፍትሄ የሚያፈላልጉበት ዕድል ተከፍቷል። ይሄ በር እንግዲህ ከረጅም የኢትዮጵያ ህዝብ ትግል በኋላ በድንገት የተከፈተ ነው፡፡ በርካቶች በትጥቅ ሲታገሉ የነበሩ ሃይሎች ጭምርም ወደ ሃገር ውስጥ ተመልሰዋል፡፡ ይሄ የለውጡ ትልቅ ትሩፋት ነው፡፡
የተለያዩ የፖለቲካ ሃይሎች ወደ ሃገር ቤት መመለሳቸው፣ በፖለቲካው ላይ ምን ተጽዕኖ ያሳድራል?
እነዚህ ሃይሎች በያሉበት ቦታ፣ለሃገራቸው የየራሳቸው ሃሳቦች የነበራቸው ናቸው፡፡ አሁን ያንን ሃሳባቸውን ለህዝብ የሚሸጡበት ዕድል ተፈጥሯል፡፡ እንግዲህ የዲሞክራሲ በሩ ተከፍቷል። ወሳኙ እንግዲህ ፓርቲዎቹ ይሄን ዕድል የሚጠቀሙበት አግባብ ነው፡፡ በጥሩ መንገድ ከተጠቀሙበት ዲሞክራሲን የማስፋት ሁኔታ ሊፈጠር ይችላል፡፡ ዲሞክራሲ በሰፋ ቁጥር ደግሞ ሃሳቦች ወደ አደባባይ ይወጣሉ፡፡ ብዙ አማራጮች ይቀርቡልናል፡፡ የዚህ ሃገር ትልቁ ችግር፣ ላለፉት 27 ዓመታት ኢህአዴግ፣ የራሱን መንገድ ብቻ አስይዞ ሲያደናብረን መኖሩ ነው፡፡ የዚህች ሃገር ችግሮች በርካታ ናቸው፡፡ ስለዚህም ብዙ መፍትሄዎች መቅረብ ይኖርባቸዋል፡፡ ፓርቲዎች ሃሳባቸውን እያቀረቡ፣ ህዝቡ የተቀበላቸውና መፍትሄ ይሆናሉ የተባሉት ሥራ ላይ እንደሚውሉ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡
በአሁኑ ወቅት በቅድሚያ ሊሰሩ ይገባል የሚሏቸው ጉዳዮች ምንድን ናቸው?
የሃገሪቷን አንድነት ማጠናከርና አስተማማኝ የማድረግ ጉዳይ ቅድሚያ ተሰጥቶት ሊሰራ ይገባዋል፡፡ ይህቺ ሃገር በተለያየ ምክንያት ችግር ውስጥ ገብታለች፡፡ አንዱ ችግር አንድነታችን መላላቱ ነው፡፡ ኢህአዴግ በሚከተለው የጎሳ ፖለቲካ ምክንያት ሃገሪቱ አንድነቷ ላልቷል። ከዚህ ፀረ-አንድነት የጎሳ ፖለቲካ ወጥተን፣ በዜግነት የምንቆጠርበት ሁኔታ መፈጠር አለበት፡፡ በመጀመሪያ በሰውነታችን፣ ከዚያም በኢትዮጵያዊነታችን፣ በዜግነታችን የምንቆጠርበት ስርአት እንዲፈጠር ከአሁኑ መሰራት ይኖርበታል። ሌላው ዋና ትኩረት ሊሆን የሚገባው፣ የዲሞክራሲያችንን ምህዳር ማስፋት ነው፡፡ ላለፉት 27 ዓመታት በአብዮታዊ ዲሞክራሲ ስም ሃገሪቱ ጨለማ ውስጥ ነበረች፡፡ አሁን የብርሃን ጭላንጭል ታይቷል፤ የዲሞክራሲ ብርሃኑ መስፋት አለበት፡፡ እውነተኛ የዲሞክራሲ ባህሪያትን ያቀፈ ስርአት መፍጠር ያስፈልጋል፡፡
ሃገሪቱ አሁን የምትከተለው የፌደራሊዝም ሥርዓት ችግር አለው ብለው ያምናሉ?
ፌደራሊዝማችን በጎሳ ፖለቲካ ላይ የተመሰረተ ነው፡፡ የጎሳ ፖለቲካ ደግሞ በባህሪው፣ የግጭትና የጠባብነት መፈልፈያ ነው፡፡ የጎሳ ፖለቲካ ጠባብነትን እንጂ ሰፊነትን አይወክልም፡፡ በአንፃሩ ዲሞክራሲ ደግሞ የጠባብነት ጠላት ነው፡፡ ክፍት መሆንን ነው ዲሞክራሲ የሚፈልገው፡፡ አሁን ምርጫችን፤ ጠባብነት ይሻላል ወይስ ዲሞክራሲ? የሚለው ነው፡፡ ዲሞክራሲን ከመረጥን የጠባብነት መፈልፈያ የሆነው ጎሰኝነት መቆም አለበት። እኔ ከፌደራሊዝም ስርአት ጋር ጠብ የለኝም፡፡ እንደውም ለኛ ሃገር ጠቃሚ ነው፡፡ የተበላሸው በጎሳ ላይ የተመሰረተ በመሆኑ ነው፡፡
ሥርዓቱ በምን አይነት መልኩ ቢዋቀር ይበጃል ይላሉ?
በመጀመሪያ ሰው መሆናችንን በማክበር ላይ መመስረት አለበት፡፡ ሁለተኛ ደግሞ ኢትዮጵያዊ በመሆናችን ብቻ የምንደራጅበት ስርአት ሊሆን ይገባል፡፡ ለምሳሌ ባለፈው ስርአት፣ ኢትዮጵያ በ14 ክፍላተ ሃገራት ነበር የተከፈለችው፡፡ ከተከፈለም በጎሳ ሳይሆን ታሪክ በፈጠራቸው ክፍሎች መሆን አለበት፡፡ አሁን ወደዚያ መመለስ ያለብን ከሆነም ተፈትሾ ልንመለስ ይገባል። በአጭሩ ሰዎች ኢትዮጵያዊ በመሆናቸው፣ ሰው በመሆናቸው፣ ዜጎች በመሆናቸው ብቻ መብታቸው የሚከበርበት ሁኔታን ታሳቢ ያደረገ፣ የፌደራል አወቃቀር ያስፈልጋል ነው የምለው። በታሪክ፣ በጂኦግራፊና በባህል ላይ የተመሰረተ እንዲሁም ኢትዮጵያዊነትንና ዜግነትን ብቻ ታሳቢ ያደረገ ቢሆን እመርጣለሁ፡፡ እኛ በዜግነታችን ብቻ የምንቆጠርበት ስርአት መፈጠር አለበት ብዬ ነው የማምነው፡፡
ጠ/ሚኒስትር  ዶ/ር ዐቢይ አህመድ፤ ለእርስዎ ምን ዓይነት መሪ  ናቸው?
ዶ/ር ዐቢይ ለኔ ከሰማይ የወረደ ፀጋ፣ በረከት ነው፡፡ ኢትዮጵያ ከፍተኛ ችግር ውስጥ ባለችበት ወቅት የፍቅር ቋንቋ የሚናገር፣ የአንድነት ቋንቋ የሚዘምር፣ የይቅርታ ቋንቋ ከአፉ የማይጠፋ መሪ መምጣቱ ትልቅ ፀጋ  ነው፡፡ ከመሪዎቻችን ስንመኝ የኖርነው፤ የዚህ ዓይነት የሰላም፣ የአንድነት፣ የፍቅርና የይቅርባይነት ቋንቋን ነበር። በሌላ በኩል፤በየአካባቢው የሚታየው ሥርአት አልበኝነት መወገድ አለበት፡፡ ሥርአት መከበር ይገባዋል፡፡ ሥርአት ሲከበር ግን ኃይልን ብቻ ሳይሆን ፍቅርን፣ ሰላምን፣ አንድነትን አጉልቶ ማውጣት ያስፈልጋል፡፡ በማህበረሰባችን ውስጥ በርካታ እሴቶች አሉ፡፡ ከእነዚህ እሴቶች ውስጥ ፍቅራችንን፣ ሰላማችንን፣ አንድነታችንን፣ ህልማችንን ማውጣት የምንችለው፣ በእንዲህ ያለው የፍቅር ቋንቋና ስሜት ነው፡፡ እኚህ ሰው እነዚህን እሴቶች ይዘው ነው የመጡት፡፡ አሁን ጥያቄው፤ ይሄን የያዙትን መልካም ባህሪ ይዘው እንዲቀጥሉ ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው? የሚለው ነው፡፡ ለዚህ  ደግሞ የኛም ባህሪ ወሳኝነት አለው፡፡
የመደመር ፍልስፍናቸውን እንዴት ይረዱታል?
በእምነትም በታሪክም በመንፈስም የመቀራረብና አንድ የመሆን ነገር ነው፡፡ መደመር ከአንድነት ጋር የተያያዘ ነው፤ ፍልስፍናው። መደመር ማለት አንድነታችንን ማጠናከር ማለት ነው፡፡ የተለያየ ቀለምና ባህሪ ያለው የኢትዮጵያ ህዝብ፤ እንደ አበባ ነው የሚታየው። የተለያዩ አበባዎች ያሉበት ስብስብ ማለት ነው። እነዚህ አበባዎች መልካቸው የተለያየ ቢሆንም ተሰባስበው በጌጠኛ ጠርሙስ ውስጥ ተቀምጠው ሲታዩ ለአይን ይሞላሉ፤ መአዛቸው ይወጣል፣ የመንፈስ እርካታን ይሰጣሉ፡፡ በዚህ የመደመር ፍልስፍናም፤ ኢትዮጵያውያን እንደዚህ የአበባ ስብስብ ነን ብዬ ነው የምረዳው፡፡
በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል ሰላም ሰፍኖ፣ አዲስ ግንኙነት ተጀምሯል፡፡ ግንኙነቱ እስከ ምን ድረስ ሊዘልቅ ይችላል?
ግንኙነቱ እንደገና መጀመሩ ተገቢና አስፈላጊ ነው፡፡ የለውጡ አንድ ትሩፋትም እንደሆነ አስባለሁ፡፡ እኔ እንደ ህልም የማልመው ብዙ ነው፡፡ ህልም ማለም ደግሞ አያስወቅስም፡፡ የኢትዮጵያና የኤርትራ ህዝብ፤ አንድ ዓይነት ባህል፣ እምነት ያለው ህዝብ ነው፡፡ እርግጥ ኤርትራውያን አሁን አዲስ ህልም ፈጥረዋል፡፡ በዚያ ህልም የመሄድ መብት አላቸው፤ግን የኔ ህልም ሁለቱ ሃገሮች አንድ የሚሆኑበት ሁኔታ ቢፈጠር የሚል ነው፡፡ ትናንት አንድ ላይ የነበርን ሰዎች፣በታሪክ አጋጣሚ ተለያይተናል፡፡ ስለዚህ ለኛ የምንመኘውን በጎ ነገር ሁሉ ለእነሱም መመኘት አለብን፡፡ ምክንያቱም አንድ የነበርን ሰዎች ነን፡፡ ሥነ ልቦናችን፣ ባህላችን አንድ ነው፡፡
ባለፉት 27 ዓመታት ሦስት ጠቅላይ ሚኒስትሮች ተቀያይረዋል፡፡ በእነዚህ ሁሉ ጊዜያት ደግሞ እርስዎ የተቃዋሚ ፓርቲ አመራር ነበሩ፡፡ አስቲ ሦስቱን ጠ/ሚኒስትሮች  ያነፃፅሩኛል?
አቶ መለስን በተመለከተ አንዳንዴ ለመናገርም ይከብደኛል፡፡ በእርግጥ ብዙ ስራዎችን ሰርተዋል። ነገር ግን እንደ መሪ፣ ለኢትዮጵያ ችግር ውስጥ መውደቅ ተጠያቂ ናቸው፡፡ ኢትዮጵያውያንን ችግር ውስጥ ያስገቡ መሪ ናቸው ብዬ ነው የማምነው፡፡
እንዴት? እስቲ በማስረጃ ያስደግፉልኝ?
ግልፅ ነው፡፡ አንደኛው፤ ህዝቡን የጎሳ ፖለቲካ ውስጥ መክተታቸው ነው፡፡ ሁለተኛው፤ የሀገሪቱን የውስጥ ባህሪ አለማወቃቸው ነው፡፡ በዚህ አለማወቃቸውም ሳቢያ ብዙ ስህተት ፈፅመዋል። የኢትዮጵያውያንን የውስጥ ባህሪ አያውቁም ነበር። ከተማሪነታቸው ጀምረው ከማርክሲስት ሌኒኒስት፣ ስታሊኒስት አስተሳሰብ ጋር ተቆራኝተው ነው የኖሩት። ከኢትዮጵያ አገር በቀል እውቀትና ባህል ጋር የተያያዘ አመራር አልነበራቸውም፡፡ በውጪ ባህል፣ አመለካከትና ርዕዮተ ዓለም ነው ሲመሩ የነበረው። የቀለም እውቀት ቢኖራቸውም፣ የብስለት ችግር ነበረባቸው፡፡ የሀገሪቱን ውስጠ ባህሪ ባለማወቃቸው የተነሳ ወደ ጎሳ ፖለቲካ ነው የከተቱን፡፡ የጎሳ ፖለቲካው ደግሞ ከማርክሲስት፣ ሌኒኒስት፣ ስታሊኒስት አስተሳሰብ ተንደርድሮ የመጣ ነው፡፡ የዚያ አይነት አስተሳሰብ የኛን ሀገር በእጅጉ ጐድቷታል፡፡ አገር በቀል ጎምቱ አስተሳሰቦችን ትተናቸው፣ ጭልጥ ብለን ወደ ምስራቅ አውሮፓ ፍልስፍና ነው የገባነው። የምስራቅ አውሮፓ የፖለቲካ ባህሪ ደግሞ በአመዛኙ ከፀረ ቅኝ አገዛዝና ከኢምፔሪያሊዝም ጥላቻ ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ለዚህ ነው የምስራቅ  አውሮፓ ፖለቲካ፣ ወደ ፅንፈኛ ሶሻሊዝም የሄደው። ያ የፖለቲካ ባህሪ ደግሞ ወደኛ ሀገር በቀጥታ ተቀድቶ ሲመጣ፣ ከህዝባችን ባህልና እሴት ጋር መዋሃድ አልቻለም፡፡
ባልተዋሃደ አስተሳሰብና አመራር ነበር ስንጓዝ የነበረው፡፡ በኋላ የመጡት አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ ደግሞ ሃይማኖታዊ ሰው ናቸው፡፡ ይሄን አከብርላቸዋለሁ፡፡ የክርስትና አስተሳሰብ ነበራቸው። የክርስትና አስተሳሰብ ደግሞ ስለ ፍትሃዊነት፣ እኩልነት፣ በአጠቃላይ ክርስቶስ ባስተማራቸው ትምህርቶች መመራት ማለት ነው፡፡ እርሳቸው የተዋሃዳቸው የክርስቶስ ትምህርትና በማርክሲስት መንግስት የተቃኘው የኢህአዴግ ትምህርት ደግሞ አብረው አይሄዱም። አቶ ኃይለማርያም በአንድ በኩል የክርስቶስን መመሪያዎች የሚያከብሩ፣ በሌላ በኩል በማርክሲስት ትምህርት የተቃኘውን ኢህአዴግን የሚመሩ፤ ግራ አጋቢ በሆነ ሁኔታ ውስጥ የነበሩ ሰው ናቸው፡፡ ሁለቱ አይጣጣሙም፡፡ አንድ ሰው ለሁለት አለቃ አያድርም የሚባል ነገር አለ። የክርስቶስ ትምህርት መሠረቱ፤ እኩልነት፣ ነፃነት፣ ፍትህ፣ ፍቅር፣ ሠላም፣ ትዕግስት፣ ሃቀኝነት የመሳሰሉ እሴቶችን የያዘ ነው፡፡ በዚህ መመራት ማለት ነው አማኝ ማለት። የኢህአዴግ ፍልስፍና ደግሞ ከዚህ በተቃራኒ ነው። በዚህ አጣብቂኝ ውስጥ ተጨንቀው የኖሩ ሰው ናቸው፤ አቶ ኃይለማርያም፡፡ በኋላም ለወሰኑት የስልጣን መልቀቅ፤ ይሄ ጭንቀታቸው አስተዋጽኣ አድርጓል የሚል እምነት አለኝ፡፡ መወሰናቸውም ተገቢ ነበር። ከራሣቸው ጋር መታረቅ አለባቸው ብዬ አምን ነበር። በውሳኔያቸው ከራሣቸው የታረቁበት አጋጣሚ የተፈጠረ ይመስለኛል፡፡ ውሳኔያቸው አዲስ በር ከፍቷል፤ እሳቸውንም ከራሳቸው ጋር አስታርቋቸዋል፡፡
ዶ/ር ዐቢይ ደግሞ ክርስቶስ ያስተማራቸውን እሴቶችና ባህሪያት በጥልቀት ተከታይ ናቸው እንጂ መሃል ላይ የሚዋልሉ አይደሉም፡፡ የኛ የኢትዮጵያውያን ሥነልቦናን ጠንቅቀው የተረዱ፣ ራሳቸውን የሆኑ ሰው ናቸው፡፡ አሁን የኔ እድሜ 82 ነው፡፡ ዶ/ር ዐቢይን በእጥፍ እበልጣቸዋለሁ። እሣቸው ከእኔ በግማሽ እድሜ አንሰው፣ ሙሉ ባህሪን መያዛቸውና ያንን ባህሪ ማካፈል መቻላቸው አስገርሞኛል፡፡ ኢትዮጵያ እጆቿን ወደ ፈጣሪ ትዘረጋለች ይባላል፤ እውነትም የኢትዮጵያ አምላክ ሰምቷል፡፡ ሰምቶም የሚፈለጉትን ባህሪያት ያካተተ ሰው ሰጥቶናል፡፡ ዶ/ር ዐቢይ፤ ለኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆን ለሰው ልጅ ሁሉ ሊያካፍሉ የሚችሉትን መልካም ባህሪ ይዘው ነው የመጡት፡፡ እኔ ይሄን ዓይነት ባህሪ የያዘ ሰው፣ ይሄን ያህል እድሜ ቆይቼ በማየቴ ደስተኛ ነኝ። የመጡት ለውጦችም ሊበረታቱ የሚገባቸው ናቸው፡፡
በቅርቡ በርካታ ቁጥር ያላቸው ሴት ሚኒስትሮች ተሹመዋል፡፡ ሴቶች ወደ ከፍተኛ የመንግስት ሥልጣን  መምጣታቸው ምን ፋይዳ አለው?
እኔ በጣም ነው ደስ ያለኝ፡፡ የፆታ እኩልነት ጉዳይ በአለም ላይ የሚጮህበት ጉዳይ ነው። አሁን በእነ ዶ/ር ዐቢይ እንቅስቃሴ፤ ሴቶች ወደ ስልጣን በስፋት መምጣታቸው፣ የሃገሪቱን አቅም ለመጠቀም ያስችላል። በመሠረቱ ሠልፍ የማሳመር ጉዳይ አይደለም፡፡ በእውቀት የዳበሩ፣ የመሪነትና አገልጋይነት ባህሪ ያላቸው ሰዎች ናቸው ወደ ሥልጣን መምጣት ያለባቸው፡፡ ሴቶች ሁለት አቅም ነው ያላቸው፡፡ አንደኛ አዕምሮ አላቸው፤ ሁለተኛ የልብ ባህሪ አላቸው፡፡ የአዕምሮ ብሩህነትና የልብ ቀናነት ሲጣመሩ፣ ውጤቱ ጥሩ ይሆናል፡፡ ድርብ ሃይል አላቸው፡፡ ይሄ ለውሣኔ ጥሩ ነው፡፡ ለሀገሪቷ የበለጠ አቅም ይሰጣታል፡፡
ህወሓት የጥንት መስመሬን አልለቅም ብሎ የሙጥኝ ብሏል፡፡ ወደ ለውጥ የሚመጣበት ሁኔታ ይኖራል ብለው ያስባሉ?
የህወሓት ግትርነት አደገኛ ነው፡፡ ሃገሪቱ እዚህ ደረጃ የደረሰችው በዚህ ግትር አቋም ባለው አመራር ነው፡፡ እኔ ተስፋ የማደርገው፤ የህወሓት አመራር ራሱን እንደገና ፈትሾ፣ መርምሮ፣ አሁን እየታየ ባለው ብርሃን ወደፊት ለመራመድ የሚያስችል ባህሪ ይዞ ይወጣል ብዬ ነው፡፡ አቋሙ ትክክል እንዳልሆነ ላለፉት  27 ዓመታት አሳይቶናል፡፡ ለምን ሌላ መንገድ አይሞከርም? የትግራይ ህዝብ ጠንካራ ህዝብ ነው። እሴቶቹ ሌሎችም ኢትዮጵያውያን የሚከተሏቸው ናቸው። ህወሓት ደግሞ ከትግራይ ህዝብ ባህል፣ ታሪክ፣ እሴት የራቀ ነው፡፡ ህወሓት ከህዝቡ ተምሮ እውነተኛ ተሃድሶ ማድረግ ካልቻለ፣ራሱን በራሱ እንደሚያጠፋ ጥርጥር የለውም፡፡ ህዝቡም ህወሓት ተገድዶ ወደ ለውጥ እንዲሄድ መግፋት አለበት፡፡ አለበለዚያ ችግር ውስጥ እንገባለን፡፡
ኢትዮጵያዊነትን እርስዎ እንዴት ይገልጹታል?
በመጀመሪያ ሰው ነኝ፤ ሲቀጥል አሁን ባለሁበት ጂኦግራፊያዊ ክልል ውስጥ ኢትዮጵያ የሚባል አለ፤ በዚያ ውስጥ ህዝብ አለ፤ ያ ህዝብ ደግሞ የራሱ ባህልና ትውፊት ያለው ነው፡፡ እኔም የዚያ ህዝብ ውጤት ነኝ። የዚህን ህዝብ የአንድነቱን ስሜት ቀስሜ የያዝኩ ሰው ነኝ ብዬ አምናለሁ። እኔ የተወለድኩት ማይጨው ነው። እዚያ ብወለድም  እያንዳንዷ የኢትዮጵያ ክፍል የኔ ነች። የትም ቦታ ተንሠራፍቼ የምንቀሳቀስባት ሀገር ነች። እያንዳንዷ ኢንች ቦታ የኔ ነች፡፡ አንድም ቦታ ያንተ አይደለም እንድባል አልፈልግም፡፡ አንተ የለህበትም የምባልበት ማዕዘን መኖር የለበትም፡፡ እኔ የየትኛውም ቦታ፣የኢትዮጵያዊ ቅመም ውጤት ነኝ፡፡
በዚህ የለውጥ ሂደት ውስጥ የእርስዎ ተስፋና ስጋት ምንድን ነው?
ተስፋዬማ አሁን የተጀመረው ነገር ተጠናክሮ ይቀጥላል የሚል ነው፡፡ ጅምሮቹ ጥሩዎች ናቸው። ከዚህ በፊት ያላየናቸው፣ ስንጠብቃቸው ስንመኛቸው የነበሩ ናቸው፡፡ አሁን እነዚህን ማስቀጠል ነው ትልቁ ስራ፡፡ ያንን ማስቀጠል ደግሞ የጥቂት ሰዎች ስራ አይደለም፡፡ ብቅ ብቅ ያሉትን እሴቶች፣ በዘመቻ አጉልተን ወደፊት ማምጣትና የማይቀለበስበት ደረጃ ላይ ማድረስ ያስፈልጋል፡፡ ለዚህ አሁንም ትግል ያስፈልጋል፡፡ በዚህ መሃል ስጋትም አለኝ፡፡ የተለያዩ የፖለቲካ ድርጅቶች መንቀሳቀስ ጀምረዋል፤ ነገር ግን እነዚህ ፓርቲዎች ምን ያህል የሃገሪቷን ችግርና የህዝቡን ፍላጐት አውቀው እየተንቀሳቀሱ ነው የሚለው ያሰጋኛል፡፡ የመሰባሰቡ ጉዳይ ጫጫታ ለመፍጠር ነው ወይስ ጠቃሚና የሠከነ ነገር ለመፍጠር ነው? እንዴት አድርገው ነው በተለያየ ስም የተደራጁ ሃይሎች፣ አስተሳሰባቸውን አሰባስበው፣ ተቻችለው፣ ለዚህች ሀገር የሚጠቅም ነገር መስራት የሚችሉት? የሚለው ያሳስበኛል፡፡ አንዱ የሚያሰጋኝ፣ ይሄ የፖለቲካ ድርጅቶች ምስቅልቅል ነው። የሚሰባሰቡበትንና የሚተባበሩበትን ሁኔታ መፈጠር ካልተቻለ አስጊ ነው፡፡ ሌላው ይሄ የጐሣ ፖለቲካ ጉዳይ ነው፡፡ መፍትሔ ካልተገኘለት፣ አሁን የሚደከምለት ነገር ሁሉ ፍሬ ሊያፈራ አይችልም፡፡ ለአገራዊ አንድነቱ አስጊ ነው፡፡ እንዴት ነው ከጐሣ ፖለቲካ ወጥተን፣ ለኢትዮጵያ ዜጐች ጥቅም የምንሰለፈው የሚለውም ያሳስበኛል፡፡ አንድነትና ሠላም አስፈላጊ ነው፡፡ ሠላም ከሌለ ምንም ነገር ማድረግ አይቻልም፡፡ አሁን ብርሃን ታይቷል፡፡ በዚያ በታየው ብርሃን አንድነታችንን አጠናክረን፣ ችግሮችን በጋራ እያስወገድን፣ህይወታችንን የምናስተካክልበት ሁኔታ መፈጠር አለበት፡፡ የብርሃኑ  አድማስ መስፋት አለበት፡፡
የ2012 አገራዊ ምርጫ አንድ ዓመት ከ6 ወር ገደማ ይቀረዋል፡፡ አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ ምርጫው መካሄድ አለበት ብለው ያምናሉ? አንዳንድ ፓርቲዎች መራዘም አለበት የሚል አቋም አላቸው—
ገና ብዙ ያልተሠሩ ስራዎች አሉ፡፡ በዚህች አጭር ጊዜ ውስጥ በቂ ዝግጅት ለማድረግ  አስቸጋሪ ነው። ዝም ብለን ወደ ምርጫ ከገባን ደግሞ እንደ የመን፣ ሊቢያ፣ ኢራቅ–አገሪቱ የታረሰች  ነው የምትሆነው፡፡ ኢትዮጵያ አሁን በተለያዩ የፖለቲካ ዘውጐች የታጨቀች ሃገር ነች። ይሄም መታሰብ ይኖርበታል፡፡ የኢትዮጵያ ህዝብ አሁን የታየውን ብርሃን እየተጠቀመ፣ ወደፊት የሚጓዝበት ሁኔታ መፈጠር አለበት፡፡ አሁን ያለውን ብርሃን ተጠቅመን በአንድነት ካልሠራን ግን ተመልሰን ወደ ጨለማ ልንገባ እንችላለን፡፡ ይሄን እያንዳንዱ ዜጋ ማሰብ አለበት፡፡ ወደ ምርጫ ከመገባቱ በፊት የምርጫ ህጉን ማስተካከል ብቻ ሳይሆን የአስተሳሰብ ጥመቱንም ማቃናት ያስፈልጋል፡፡ ምናልባት ዘመቻ የሚመስል እንቅስቃሴ ከተደረገ፣ በተያዘው ጊዜ ምርጫውን ማድረግ ይቻል ይሆናል፡፡ ልዩ ጥረት ካልተደረገ ግን ጊዜውን ማራዘሙ ነው የሚበጀው፡፡ በዋናነት የሚወስነው ግን ሂደቱ ነው፡፡
አሁን በዶ/ር ዐቢይና ጥቂት ጓዶቻቸው የተጀመረው የለውጥ እንቅስቃሴ፣ የእነሱ ብቻ ሆኖ መቅረት የለበትም፡፡ ህዝቡ የዚህ ጉዞ አካል የሚሆንበት መንገድ መፈጠር አለበት፡፡ ውይይቶች በየቀበሌው መካሄድ አለባቸው፡፡ ዲሞክራሲ የህዝብ ነው፤ ስለዚህ ህዝቡ የሚወያይበትና ሃሣቡ የሚደመጥበት መድረክ ሊፈጠር ይገባዋል፡፡

Filed in: Amharic