ያሬድ ሀይለ ማርያም
በዚህ ሳምንት የሚንስትሮች ምክር ቤት እውነት እና ፍትሕ አፈላላጊ የብሔራዊ ዕርቀና ሰላም ኮሚሽን ለማቋቋም ረቂቅ አዋጅ ለተወካዮች ምክር ቤት ማቅረቡን ሰምተናል። ይህ እጅግ የሚደገፍ ትልቅ እርምጃ ነው።
እጅግ የከፋ የመብት ጥሰት በተፈጸመበት፣ ብዙ ዜጎች በአገር እና በመንግስት ላይ እምነት ባጡበት፣ ጥቂት ግፈኞች የአገርና የሕዝብ ሃብት በቁጥጥራቸው ስር አድርገው ብዙ ሚሊዮኖችን የመኖር ዋስትና ባሳጡበት፣ በፖለቲካ አስተሳሰብ ልዩነት እና በዘር ፍረጃ ዜጎች ቁርሾ በተቃቡበት አገር እርቅ እና ሰላምን ለያመጣ የሚችል ብሔራዊ ኮሚሽን እንደሚያስፈልግ ብዙዎች ሲወተውቱ ከርመዋል። ጥያቄው ምላሽ ሊያገኝ መሆኑን መስማት ያስደስታል።
ይህ ኮሚሽን ምን አይነት ቅርጽ ነው መያዝ ያለበት፣ ምን ምን ተግባራትን ነው ሊያከናውን የሚችለው ወይም የሚጠበቅበት፣ በምን መልኩ ነው የሚዋቀረው እና ለምን ያህል ጊዜ ሊቆይ ይችላል የሚሉትን ጥያቄዎች ኮሚሽኑን የሚያቋቁመው ዝርዝር አዋጅ ሲወጣ የሚታይ ይሆናል። ሕዝብ ከኮሚሽኑ ምን ይጠብቅ የሚለውን ሃሳብ ግን ሌሎች ተመሳሳይ ችግር ውስጥ የነበሩ አገሮች ከብሔራዊ ዕርቀና ሰላም ኮሚሽን ያገኙትን ትርፍ እና ጥቅም በማስላት ከዚህ በታች ያሉትን ጉዳዩች የሚሸፍን ኮሚሽን ከሆነ አትራፊዎች ነን ብዮ አስባለሁ።
– ባለፉት አርባ አመታት በአገሪቱ ውስጥ የተፈጠሩትን የፖለቲካ መቋሰሎች፣ የእርስ በርስ እልቂቶች፣ የብሔር ግጭቶችን ያስከተሉ ጉዳዮችን በዝርዝር በማጥናት፣ የደረሰውን የጉዳት መጠን በዝርዝር እና በማስረጃ አስደግፎ በጥራዝ መልክ በማዘጋጀት ይህን የግጭት ታሪካ ምዕራፍ ሊዘጋ የሚቻልበትን መንገድ ማመላከት፤
– ከዚህ ጥናት እና የምርምር ውጤት በመነሳት ተመሳሳይ ግጭቶች እና እልቂቶች እንዳይከሰቱ ሊከላከል የሚችል እና ሁሉም አካል ሊስማማበት የሚችል አንድ የሰላም እና የእርቅ ስምምነት ሰነድ ማውጣት፣
– ባለፉት አሥርት አመታት የተፈጸሙትን የሰብአዊ መብት ጥሰቶች በተመሳሳይ ሁኔታ በማስረጃ አስደግፎ እና ጠርዞ ለታሪክ እና ለትምህርት በሚውል መልኩ ማስቀመጥ። የመብት ጥሰት የፈጸሙ አካላትን በድርጅት፣ በስም እና በሥራ ኃላፊነት ደረጃ ጠቅሱ በዝርዝር በሰንዱ ውስጥ ማስቀመጥ፣
– የመብት ጥሰት የፈጸሙ ወይም በማናቸውም ደረጃ በድርጊት ይሁን በሃሳብ ተሳትፎ የነበራቸው ግለሰቦች በስም ተዘርዝረው ተጠቅሰው ኮሚሽኑ በሚያዘጋጀው አንድ ገጽ የይቅርታ መጠየቂያ ደብዳቤ ላይ እንዲፈርሙ፤ ሕዝብን እና የበደሉትን ሰው በጥቅሉ ይቅርታ እንዲጠይቁ ማድረግ፤
– የመብት ጥሰት ሰለባ የሆኑ ሰዎች፤ በተለይም በእስር የማሰቃየት ተግባር የተፈጸመባቸው ሰዎች በሥነ አዕምሮም ሆነ በአካል ሊያገግሙ የሚችሉበት የስቃይ ሰለባዎች ማገገሚያ ተቋም እንዲቋቋም በማድረግ ተበዳዮቹ ድጋፍ እንዲያገኙ ማድረግ፤
– የመብት ጥሰት ከተፈጸመባቸው ግለሰቦች መካከል የተወሰኑትን በማበረታታት ለአስተማሪነት ይረዳ ዘንድ የደረሰባቸውን የደል አይነት በተለያዩ መገናኛ ብዙሃን ለሕዝብ እንዲያካፍሉ ማድረግ እና የተበዳዮቹን የጉዳት መጠን የሚያሳዩ አጫጭር ታሪኮችን በሰነዱ ውስጥ ማካተት፣
– በሕዝብ መካከል የተፈጠሩ መቃቃሮች እና በፖለቲካ ኃይሎች ፍትጊያ ምክንያት የተፈጠሩ ቁስሎች እንዲያገግሙና ሙሉ በሙሉ እንዲሽሩ ሊረዳ የሚችሉ የውይይት፣ የሥልጠና እና የምክክር መድረኮችን እና የተለያዩ አውዶችን መፍጠር ወይም ማነቻቸት፤
– የፖለቲካ ፓርቲዎች በታሪክ ሂደት በመካከላቸው የተፈጠሩ መቃቃሮችን አክመው ወደ ሰለጠነ የፖለቲካ ፉክክር እንዲገቡ ለማድረግ የሚያስችል የውይይት እና የምክክር መድረኮችን ማዘጋጀት፤ እንዲሁም በጋራ የሚፈርሙት አንድ የእርቅ እና የሰላም ቃል-ኪዳን ሰነድ አዘጋጅቶ እንዲፈርሙ ማድረግ፤
– በቀጣል በሕዝም መካከልም ሆነ በፖለቲካ ኃይሎች መካከል የሚፈጠሩ ግጭቶች እና ቅራኔዎች ሊፈቱ የሚችሉበት፤ የአገሪቱን ባህላዊ እና ሌሎች እሴቶች ታሳቢ ያደረገ የግጭት አፈታት ስልት መንደፍ፤
– ሕዝብን ለግጭት ሲዳርጉ የቆዩ የመንግስት ፖሊሲዎችን፣ ሕጎችን (ሕገ-መንግስቱን ጨምሮ)፣ የአፈጻጸም ስልቶችን፣ የመንግስትን አወቃቀር እና የሚከተለውን የፖለቲካ አስተሳሰብ መስመር፣ በፌደራል እና በክልል መንግስታት እንዲሁም በክልሎች መካከል ያለውን ግንኙነት የሚፈትሽ፤ ዘላቂ ሰላምን ለማምጣት እና እርቅን ለማውረድ የሚረዱ አማራጭ ሃሳብችን የሚያቀርብ፤
– ዕርቅ እና ሰላም መሰረታቸው እውነት እና ፍትሕ መሆኑን አጽነኦት በመስጠት በአገሪቱ ውስጥ በሕዝብ ላይ የተፈጸሙ በደሎችን፣ ዚርፊያቆችን እና የመብት ጥሰት ወንጀሎች ዘርዝሮ እውነቱን የሚያሳውቅ እና ፍትሕ የሚገኝበትን መንገድ የሚጠቁም ኮሚሽን መሆን ይጠበቅበታል።
– ከላይ የተጠቀሱትን ሥራዎቻቸውን ለማከናወን የሚያስችል በቂ ነጻነት እና የሕግ ጥበቃ የሚደረግላቸው፤ እንዲሁም ሥራቸውን ለማከናውን የሚያስችል ተመጣጣኝ የሆነ በሕግ ተዘርዝሮ የተደነገገ ሥልጣን ያለው እና ተጠሪነቱም በአገሪቱ ከፍተኛ ሥልጣን ላለው ለፓርላማው ብቻ የሆነ ጠንካራ ተቋም መሆን አለበት።
እንዲህ ያለውን ታላቅ አገራዊ ኃላፊነት ለመወጣት ኮሚሽኑ፤
– ሁሉንም ባለድርሻ አካላት ሊወክሉ የሚችሉ፣
– በትለያዩ የሙያ ዘርፎች፤ በተለይም በሕግ ሙያ በቂ እውቀት እና ልምድ ያላቸው፣
– በማህበረሰቡ ውስጥ በበጎ ምግባራቸው የሚታወቁ እና ሕዝብ አመኔታ የሚጥልባቸው፤
– በመብት ጥሰትም ሆነ በመህበረሰቡ ውስጥ በተፈጠሩ ግጭቶች ውስጥ ቀጥተኛም ሆነ በተዘዋዋሪ ተሳትፎ ያልነበራቸው እና በየትኛውም አግላይ የሆነ አስተሳሰብ በሚያራምድ ቡድን ውስጥ ተሳታፊ ያልነበሩ፤
ቢሆኑ ሥራቸው የተቃና ይሆናል። በቂ የሕዝብ ድጋፍ እና አመኔታም ያገኛሉ። ሥራቸውም የታለመለትን ፍሬ ያፈራል። የብዙ አገሮች ልምድ ከላይ የተጠቀሱትን ነገሮች ከሞላ ጎደል ያሟላ ሲሆን ጥሩ ውጤትም አስገኝቷል።
መንግስት የጀመረው ቀና እና በጎ መንገድ የሰመረ እንዲሆን ሁሉም ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን አስተዋጸኦ ሊያደጉ ይገባል።
በቸር እንሰንብት!