>
8:49 am - Saturday November 26, 2022

የተስፋዬ ኡርጌ አንደኛው ክስ - የኢትዮጵያን መንግስት ዓለም አቀፍ አሸባሪነት ማሳያ! (ግዛው ለገሰ)

የተስፋዬ ኡርጌ አንደኛው ክስ – የኢትዮጵያን መንግስት ዓለም አቀፍ አሸባሪነት ማሳያ!
ግዛው ለገሰ
– አቃቤ ሕጉ ምን ነክቶት ነው?
«ግለሰቦችን ባልተገባ መልኩ ለሽብር መልምለው ወደ ኤርትራ በመላክ እንደጠረጠራቸው ፖሊስ ለፍርድ ቤቱ ገልጿል።»
ይህንን ከትናንት በስቲያ ፋና ነው ያስነበበን፡፡ ሌሎቹ ክሶች ቶርቸር እና ሙስና (የሰኔ 16 ጉዳይም) እንዳሉ ናቸው፡፡
ይህኛው ወደ ኤርትራ ሽብርተኛ መልምሎ ላከ የሚለው ግን እጅግ የሚያነጋግር ነው! እንግዲህ አቶ ተስፋዬ ኡርጌ ከኢሳያስ ወይም ከኤርትራ ሕዝብ ጋር የግል ጠብ ነበረው ካልተባለ በስተቀር፣ ይህ ድርጊት ተተግብሮ ከነበረ መንግስታዊ ይሁንታ ብቻ ሳይሆን በጀትም ይቆረጥለት የነበረ ተግባር እንደነበር ያመላክታል፡፡
የሚገርመው ግን ኤርትራን ነበር በዚህ ወንጅለን ማዕቀብ ያስጣልንባት፤ አል ሸባብን እና ሌሎች ሀገር-በቀል ሽብርተኞችን እያስታጠቀችብን ነው ብለን፡፡ ኢሳያስ ይህን አላረገም ለማለት ሳይሆን፤ እኛም እያረግነው ነበር ለማለት ነው፡፡
ይሁንና ይህንን ክስ ከወራት በፊት ብንሰማ «ብርቅ ነው እንዴ!» የምንል ብዙዎች ነን፤ ወደ ጠላት ሀገር አይደለም ድብቅ ኃይል በሀላል በጀት እየሄድን የደበደብንበት ጊዜም ነበርና፡፡
በዚህ ጉዳይ ብዙ ማለት ይቻላል፤ አሁን ግን ለማለት የፈለኩት የአቃቤ ሕጉ ይህንን አሸባሪዎች መልምሎ ወደ ኤርትራ የመላክ ክስ ማቅረብ ምን ያህል ፋይዳ ቢስ መሆኑን ነው፦
– ተስፋዬ ኡርጌ የተባሉትን ሽብርተኞች ሲመለምል ኃላፊነቱን እየተወጣ ነበርና ወንጀሉ ላይ የግል ሞቲቨ ነበረው ማለት አይቻልም (ኤርትራ ጠላት ሀገር ስለነበረች እንዲያውም ጀግና የሚያስብለው ተግባር ነበር)፤
– ሆኖም መንግስታዊ ትዕዛዝ ቢኖረውም አንድ ድርጊት ወንጀል ሊሆን ይችላል (ቶርቸር አድርግ ተብዬ ነው ብሎ ነፃ መሆን አይቻልምና፤ ምክንያቱም ቶርቸር ወንጀል ነው)፤
– ግን ደግሞ ሽብርተኛ መልምሎ ወደ ኤርትራ ኤክስፖርት ማድረግ በእኛ የሽብር ሕግ የትኛው አንቀፅ ላይ ነው የሚያስጠይቀው? (የወንጀል ሕጎቻችን፣ የሽብሩን ጨምሮ፣ ዋናው ዓላማቸው የኢትዮጵያን ሕዝብ ሰላም መጠበቅ ነው፤ ኤርትራን አይጨምርም)፣ (እዚህ ላይ የተስፋዬ ኡርጌ መከራከሪያ እራሱ «ይህን ያደረግነው ለኢትዮጵያ ሕዝብ ጥቅም ነው» እንደሚሆን እተነብያለሁ)፤
– ከላይኛው በተጨማሪ ሕጎቻችን በዋናነት ተፈፃሚነታቸው በግዛታችን ብቻ ነው (ይህም መርከብና አውሮፕላኖቻችንን እንዲሁም ቆንስላ ፅፈት ቤቶቻችንን ይጨምራል፤ ኤርትራን ግን አይጨምርም)፤
– በአንድ ሌላ ሀገር ላይ ሽብርተኛ መልምሎ መላክ በርግጥም በዓለማቀፍ ደረጃ ያስጠይቃል፣ ማዕቀብም ያስጥላል (ግን የኢትዮጵያ መንግስትን በአጠቃላይ እንጂ አንድ ተስፋዬ ኡርጌን አይደለም)፤
– ሀገሮቹ ጠላት የሆኑ ጊዜ ግን የተላኩት ሰዎች ሽብርተኛ ሳይሆን «ልዩ ኃይል» ሊባሉ ሲችሉ፣ በሚሽኑ ህይወታቸው ካለፈ ደግሞ መስዕዋት ሆኑ ይባላል፤ እንዲህ ባለ ሚሽን ድንገት ቢያዙ የላካቸው ሀገር ይክዳቸው ይሆናል እንጂ በገዛ ሀገራቸው ከሶ አያናዝዛቸውም፤
– ምን ለማለት ነው፣ እንዲህ ዓይነቱ ክስ ውሃ የማያነሳ ከመሆኑ ባሻገር ሌሎቹንም ዘግናኝ ክሶች የማጠልሸት ሚና ሊኖረው ይችላል (ልክ እንደመርከቦቻችን ዓለማቀፍ ውርደታችንን በይፋ ያመንበት ሁኔታ መሆኑን ትተን)፤
– ለመሆኑ የተመለመሉት ሽብርተኞች ተሳካላቸው? (ወይስ ሄደው የኛዎቹን የቀድሞ ሽብርተኞች ተቀላቀሉ?)
ለማንኛውም ስንት የሰብዓዊ መብት ጥሰት እና የሙስና ክሶችን ዘርዝሮ እስከ እድሜ ልክ ብሎም እስከሞት ማስፈረድ ሲችል፣ አቃቤ ሕጉ ይህን ትርጉም ያጣ ክስ መጨመሩ ምን ነክቶት ነው? ወይስ እንደነዳጁ የማስረጃም እጥረት አለ?
Filed in: Amharic