>

ከፊታችን ያለው እውነት ነጻነት ነው ወይንስ ነጻነት የሚመስል ባርነት?!? (ዲሜጥሮስ ብርቁ)

ከፊታችን ያለው እውነት ነጻነት ነው ወይንስ ነጻነት የሚመስል ባርነት?!?
ዲሜጥሮስ ብርቁ
ቻይና እና አረቦች የኢትዮጲያን ኦኮኖሚ ጠፍንገው ጢባጢብቤ እየተጫወቱበት ሲሆን ፖለቲካችን ( እና ባህል) ደሞ የአሜሪካ አንጡራ ሃብት እንደሆነ ቡዙ ምልክቶች እየታዮ ነው፤ ፖለቲካው የአሜሪካ ከሆነ የፖለቲካ ተቋማቱ የኢትዮጵያ የሚሆኑበት እድል ትንሽ ነው ( እድሉ ካለ)።
ዛሬ ደሞ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የአፍሪካ ህብረት ባንዲራ “ከኢትዮጵያ ባንዲራ” ጋር አብሮ እንዲውለበለብ ጥናት እያደረኩ ነው ብሏል።  ይሄም የምዕራቦቹ ፕሮጀክት ነው እስከሚገባኝ።
በዚህ ላይ እንደሚታወቀው አብዛኛው የኢትዮጵያ ክፍል በኢንቨስትመት ስም እየተሸጠ አየተለወጠ ነው ፤ ከአዲስ አባባ አቅም እምብርቷ ለአረቦች ተሸጧል ጊዚያዊ የውጭ ምንዛሬ ችግር ለመቅረፍ ሲባል።
የቅኝ ግዛት ዘመኑን የአፍሪካ ቅርምት ያስነሳው የኢኮኖሚ ጉዳይ ነው ፤ ሌላ አይደለም።  በቅርምቱ ሂደት የጥቅም ግጭት ተነስቷል ፤ የአንደኛውም የዓለም ጦርነት ከተፋፋመበት ምክንያት አንዱም እሱ ነው።
አሁን ባለው ሁኔታ ሶስት ኃይሎች ጉዳያቸውን እያጧጧፉ ነው።
ቻይና ኢኮኖሚው ላይ በማተኮር በሂደት እንደ አንዳንድ የ አፍሪካ ሃገሮች ቻይናን በኢትዮጵያ ዋነኛ የኢኮኖሚ ተዋናይ በማድረግ ስሌት እይሰራች ነው ፤ ፎርክሎዠር ሁሉ ሊያምራት ይችላል። ግጭት ሲነሳ ያደርሰኛል ፤ ወታደራዊ አቅሙ አለኝ የሚል እሳቤም አይጠፋትም።
አሜሪካ እና ሸሪኮቿ ደሞ የኢትዮጵያን ፖለቲካ እና ባህል ሙሉ ለሙሉ ሳይቆጣጠሩ ኢኮኖሚውን መቆጣጠር አይቻልም በሚል ስሌት በመስራት ባህሉንም ፖለቲካውንም በመቆጣጠር ስኬታማ ሆነው  ወደ መጨረሻው ምዕራፍ እየደረሱ ነው ፤ በዚህ አንጻር ሚዲያ እና አክቲቪስቶች (በተንታኝነት እና በኤክስፕርትነት ሂሳብ እንደ አስተሳሰብ መሪዎች ለራሳችን የሚሸጡልንን ጨምሮ -የሃገሩን ሰርዶ በሃገሩ በሬ እንዲሉ) የአሜሪካን ማሊያ በአደባባይ ባይለብሱትም ለምዕራባውያኑ ግብ በኢትዮጵያ መሳካት ያደረጉት ሚና ወደር የለውም፤  ኢትዮጵያ በ አጭር ጊዜ ውስጥ ለረዢም ዘመን በቅኝ እንደተገዙ ሀገሮች አይነት ሆናለች ፤ በወሬ የሚፈታ እና ግልብነት የሚያጠቃው ትውልድ ፤  የአሰቃቂ ወንጀሎች መበረከት እና በህዝብ ሃብት ላይ የተጧጧፈው ሌብነት ከብዙ በጥቂቱ ሁኔታውን የሚያስረዱ ነገሮች ናቸው።
አረቦቹ ከፖለቲካ ይልቅ ኢኮኖሚ እና ባህል ላይ ትኩረት በማድረግ ሰርተዋል ፤ የእነሱ አጀንዳ አክቲቪስት አላስፈለገውም።
ኢትዮጵያን ወደዚህ አጣብቂኝ ውስጥ ያስገባት ማን ነው? በዋነኛነት የጎሳ ፖለቲካ ። ያለምንም ጥርጥር ህወሓት ቀዳሚ ሚና አለው።  የተቃዋሚ ፓርቲ የሚባሉትም (ሃገራዊ) በ አንድ ወይንም በሌላ በኩል የምዕራቡ ዓለም ጥገኛ ከመሆናቸው የተነሳ ትውልዱን እንዳያስብ ያደረገውን የምዕራብ አስተሳሰብ እና ዘየ በማዛመት ረገድ የራሳቸው አስተዋጾ ነበራችው።
እነዚህን ነገሮች ግምት ውስጥ ስናስገባ ከፊት ለፊታችን ያለው እውነት ነጻነት ነው ብዥታ ወይንስ ነጻነት የሚመስል ባርነት ፤ ኢትዮጵያስ ንብረትነቷ የማን ይሆናል የሚለውን እና መሰል ጥያቄዎች ሂሳቡን ምቱት።
Filed in: Amharic