>

ከዩኒቨርሲቲ ተማሪዎቻችን የምንጠብቀዉ... (አዲሱ አረጋ ቂቲሳ)

ከዩኒቨርሲቲ ተማሪዎቻችን የምንጠብቀዉ…
አዲሱ አረጋ ቂቲሳ
በተለይም አሁን ባለንበት ተጨባጭ ሀገራዊ ሁኔታ ከዩኒቨርሲቲ ተማሪዎቻችን የምንጠብቀዉ ጠንካራ ዴሞክራሲያዊ ስርዓትን መገንባት፣ ብሄራዊ መግባባትን ማጠናከር፣ ዕርቀ ሰላም እና ወንድማማችነትን ማጎልበት የሚያስችሉ ሀሳቦችን እንዲያፈልቁ፣ ሀገርን ወደ ላቀ ድል የሚያመሩ አጀንዳዎችን እንዲያስጨብጡን እንጂ ልዩነትን በሚፈጥሩ ነገሮች ሁሉ ጎራ ለይተዉ መደባደብ እና መጎዳዳትን ታናናሾቻቸዉን የሚያወርሱ የታላላቆቻቸዉን የለዉጥ ብሩህ ተስፋ የሚያጨልሙ እንዲሆኑ አይደለም።
እኛ ከነርሱ የምንጠብቀዉ ሗላ ቀሩን የፖለቲካ ባህላችንን ሊያሻሽሉ የሚያስችሉ ንድፈ ሀሳባዊ ትንታኔዎች፣ በሀሳብ ልዕልና ተሟግቶ መሸናነፍን፣ በሀሳብ ተሸናንፎ ተቃቅፎ በሰላም፣ በወንድማማችነትና በፍቅር አብሮ መኖር እንደሚቻል አርአያነታችዉን እንዲያሳዩ ነዉ።
እኛ ከነርሱ የምንጠብቀዉ በአሻጥር እና በመጠላለፍ የጎበጠዉን የፖለቲካ ባህላችንን በቅንነትና በመተባበር በዘመናዊ የስልጣኔ ዕሳቤ እንዲዋጁ እንዲያቃኑት እንጂ ወንድም ደሃ ወንድሙን በመግደል ጀብደኛ ሆኖ የመታየት የጨለማ ዘመን ታሪካችንና ሗላ ቀርነታችንን እንዲያስቀጥሉልን አይደለም።
ከተማሪዎቻችን የምንጠብቀዉ ተባብረዉ አስበዉና ተመራምረዉ የድሃ ህዝባችንን ኑሮ የሚያቀልሉ፣ አርሶ አደሩን ከሞፈርና ቀንበር የሚያላቅቁ፣ አረም በቀላሉ ማስወገድ፣ ምርት ላይ እሴት በመጨመር ወደ ተሻለ ኑሮና ብልፅግና የሚያደርሱ ቴክኖሎጂዎችን እንዲያመነጩልን እንጂ ተቧድነዉ አሸናፊና ተሸናፊ የሌለበት ስሜት እንጂ እዉቀትና ብልሃት የማይጠይቅ በስሜት ብቻ በሚመራ አላስፈላጊ ንትርክ ዉስጥ እምቅ የፈጠራ አቅማችዉን ጨርሰዉ የድህነትን እድሜ እንዲያራዝሙብን አይደለም።
በአጭሩ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎቻችን ለሀገራችን ህዝቦች ሁለንተናዊ ችግሮች መፍትሄ ሊሆኑ የሚችሉ፣ ሀገራችንን ወደስልጣኔ የሚወስዱ አዳዲስና ዘመናዊ አስተሳሰብ፣ ዕዉቀትና ግኝት እንዲያመነጩልን ነዉ የምንጠብቀው።
ዩኒቨርሲቲዎቻችን የአዳዲስ አስተሳሰቦች ጥናቶች፣ ቴክኖሎጂዎች መገኛና የመፍትሄ ብስራት የሚሰማባችዉ የሀገር እሴት እንዲሆኑ እንጂ የፀብ፣ የሗላ ቀር አስተሳቦች፣ ወንድም ወንድሙን በድንጋይ ቀጥቅጦ ያለርህራሔ የሚገድልበት፣ የጥላቻና ቋት የሀገር ዕዳ እንዲሆኑ አይደለም የምንጠብቀው።
Filed in: Amharic