>
11:10 pm - Sunday November 28, 2021

ወደ ጎታቹ ፣ አግላዩና አሮጌው ስርአት አንመለስም! (ወሰን ሰገድ ገ/ኪዳን)

ወደ ጎታቹ ፣ አግላዩና አሮጌው ስርአት አንመለስም!
 
ወሰን ሰገድ ገ/ኪዳን
 
ወደ አለፈው ወደነቀዘው ሥርዓት አንመለስም! ወደ አግላይ ሥርዓት አንመለስም! አሳታፊ ሥርዓት ለመገንባት የምናደርገውን መውተርተር ለማጨናገፍ በሚፈጥሩት ሁከት ተስፋ አንቆርጥም!  ወደ ኋላ አንመለስም! ጉዞአችን ይቀጥላል፡- ወደፊት! ወደ አሳታፊ ሥርዓት!
ከአግላይ ወደ አሳታፊ ስርዓት ለመሸጋገር መውተርተር ከጀመርን ስምንተኛ ወራችንን ይዘናል፡፡ ይሁን እንጂ የስምንቱ ወራቶች የመውተርተር ጉዞአችን “ጤነኛ” ሊሆን አልቻለም፡፡ በሃገሪቱ የተለያዩ አቅጣጫዎች እዚህም እዚያም ግጭቶች እየተከሰቱ ነው፡፡ ዜጎች አላግባብ እየተፈናቀሉ ነው፡፡ ሌሎችም የሕጋዊነት ጥያቄ የተላበሱ ሚመስሉ ጥያቄዎች የሁከት፣የብጥብጥና የዕልቂት ሰበብ እየሆኑ ነው፡፡ በኦሮሚያና ፣ በኦሮሚያና በቤንሻጉል መሃከል፣ በደቡብ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች፣ እንዲሁም በአንዳንዳንድ ዩኒቨርስቲዎች .. የዜጎችን ሕይወት ያስከፈለ ሁኔታ እየታየ ነው፡፡ ዛሬ እንኳን በኦሮሚያና ጉምዝ /ቤኒሻንጉል አዋሳኝ ከ17 በላይ የመንግስት ፖሊሶች በተፈፀመባቸው ጥቃት ሕይወታቸውን አጥተዋል ተብሏል፡፡
.
ይህንን መሰሉ ሁከት፣ ብጥብጥና ጥቃት በርካታ ምክንያት ሊኖረው ይችላል፡፡ ዋነኛው የችግሩ መሰረት ግን ልንለውጠው ከምንፈልገው አግላይ ሥርዓት ጋር የተቆራኘ “አሮጌ አስተሳሰብ” ይመስለኛል፡፡ ላለፉት 27 ዓመታት አግላይ የፖለቲካ ስርዓት ገንብተው፣ አግላይ የኢኮኖሚ ሥርዓትን አንሰራፍተው እንዳሻቸው ሲዘባነኑ የኖሩ ወገኖች፣ እንዲሁም ከእነሱ ስር ተኮልኩለው የጥቅም ፍርፋሪ ሲለቅሙ የነበሩ ኃይሎች፣ አሳታፊ ሥርዓት ለመገንባት የምናደርገውን ጥረት ለማሰናከልና፣ ተስፋችንን ለመንጠቅ የማይፈነቅሉት ድንጋይ፣ የማይምሱት ጉድጓድ እንደሌለ መናገር ለቀባሪው ማርዳት ነው፡፡ ያለፈው ታሪካችን የሚነግረን ሐቅ ነውና፡፡
.
ባለፉት 50 ዓመታት በሃገራችን የነበሩ ገዢዎች አዲስ ሥርዓት ወይም አዲስ ጎዳና ውስጥ መግባት እንደማይሆንላቸው በእኛ ዕድሜ በተደጋጋሚ አይተናል፡፡ የዚህ ዋነኛ ምክንያት አሮጌ እምነቶችና አመለካከቶች በቀላሉ የማይሞቱ በመሆናቸው ነው፡፡ ይህም ብቻ አይደለም፤ ካለፈው ሥርዓት ይዘው የሚመጡት ቅራንቅቦ አዲሱን ወይም ተተኪውን ስርዓት ስለሚበክለው ጭምር እንጂ፡፡ በሌላ አነጋገር፣ አንድም፤ ባለፉት 27 ዓመታት በገነቡት አግላይ ስርዓት የተበኩሉና የተጀመረው የአሳታፊ ስርዓት ግንባታ ያልጣማቸውና ጥቅማቸውን የሚያሳጣቸው፤ አንድም በተፈጠረው አጋጣሚ ወይም ክፍተት ሥልጣን ለመቆናጠጥ የሚሹ የአሮጌ አስተሳሰብ ተሸካሚ ኃይሎች ሰበብ ነው ሁከት እየገጠመን ያለው፡፡
.
እነዚህ ወደኋላ፣ ወደ አንገፈገፈን አግላይ ሥርዓት ሊመልሱን የሚፈልጉ ኃይሎች፣ ባላምባራስ ማሕተመስላሴ “ዕንቅልፍ ለምኔ” በተሰኘው መፅፋቸው፤ የከተቡትን ”አሮጌ ውሻ” ተረክ  ያስታውሰኛል፡፡
.
“አሮጌው ውሻ”
.
በቆፍጣናነት ሲያገለግል ስለነበር አንድ ውሻ ታሪክ ይነግሩናል ደራሲው በዚህ መፅሐፋቸው፡፡ ይህ ውሻ ዕድሜው እየገፋ ሄዶ ተገቢውን አገልግሎት መስጠት ባለመቻሉ አሳዳሪዎቹ አታስፈልግም ብለው አባረሩት፡፡ ይኼኔ ከቅጥሩ ራቅ ብሎ የሚገኝ አንድ ጉብታ ላይ ቁጭ ብሎ ያዝን ይተክዝ ገባ፡፡ በዚህ አጋጣሚ በጫካው ውስጥ ሲያገድም ያየው አንድ ቀበሮ አየውና ጠጋ ብላ ምን እንደሆነ ጠየቀችው፡፡ ውሻውም እያዘነ፤ አሳዳሪዎቹ ቡችላ አምጥተው እንደተኩትና እሱን እንዳባረሩት ነገራት፡፡ ቀበሮዋ በሰማችው ነገር ተደንቃ እንዲህ አለችው፡-
.
“….ምንም እንኳ በእኔና በአንተ ዘር መሃል ፀብ ቢኖርም መጠቃትህ በጣም አሳዝኖኛል፡፡ በስተርጅና እዚህ ጫካ ተገፍተህ በችግርና በችጋር መሞትህን ማየት አልፈልግምና ወደ ቀደመው ስፍራህ /ቤትህ/ የምትመለስበትን ዘዴ ልምከርህ”
.
ውሻው ከድባቴው መንፈስ ነቃ ብሎ ያዳምጣት ገባ፡፡
.
“.. ከጌቶችህ ምህረት የምትፈልግ ከሆነ እንዲህ አድርግ፤ ነገ ጠዋት አሳዳሪዎችህ ከቤት ሲወጡ እኔ ልምጣና ሕፃኑ ልጃቸውን ልውሰደው፡፡ በዚህ ጊዜ እንደምንም ብለህ እየተጎተትክ ተከተለኝ፡፡ …. እዚያ ታች የሚገኘው ፈፋ አጠገብ ስደርስ እኔ ልጁን ጥዬልህ እኔ ራቅ ብዬ እቆማለሁ፤ ከዚያም አሳዳሪዎቹ ወሮታህን እንዲያውቁልህ ከልጁ አጠገብ ቁመህ ፊትህን ወደ እኔ አዙረህ እንደልማድህ ጩህ፤ አሳዳሪዎቹ ይህንን ድርጊትህን አይተው ይምሩሃል” አለችው፡፡ ውሻው በሃሳቧ ተስማማ፡፡ የተመከረውንም አደረገ፤ ተመልሶም ወደ አሳዳሪዎቹ ቤት ገባ፡- ይላል ተረቱ፡፡
.
የተረኩ ተምሳሌታዊነት
ይህ ተረክ የውሻን ባህርይ እንድናጤን ግድ የሚል ይመስለኛል፡፡ ውሻ፣ ጥቅመኛ ፍጥረት ነው፡፡ የአሮጌው ወይም ስርዓት አከንፋሾችም እንደዚያው ናቸው፡፡ ከፈላጭ ቆራጩ አግላይ ሥርዓት ያገኙትን ጥቅም ብቻ ነው የሚያስቡት፡፡ አዲስ ወይም አሳታፊ ሥርዓት ከመጣ የለመዱት ስርዓትና ጥቅም ይቀርባቸዋል፡፡ ያ “ጥቅም” ሲቀርባቸው ልክ እንደ አሮጌው ውሻው ይሆናሉ፡፡ ጥቅማቸው ተነክቶባቸዋልና “ከደም መጣጭ ተኩላ” ጋር ለማበር ወደ ኋላ አይሉም፡፡ “ከተኩላው” ጋር የቀደመ ስምምነት ወይም መግባባት ኖራቸው አልኖራቸው ግድ የላቸውም፡፡ በዚህ የተነሳ ቀደም ሲል ያገለግሉበት የነበረውን “ቤት” ለጠላት አሳልፎ ከመስጠት ወደ ኋላ አይሉም፡፡ በተረካችን እንደተጠቀሰው አሮጌ ውሻ፣ “ልጆቻችንን ለተኩላ” አሳልፈው ይሰጣሉ፡፡ አሁን በየዩኒቨርስቲው የተከሰተው ሁከት ለዚህ ተምሳሌታዊ ተረክ ማሳያ ይመስለኛል፡፡ ከተማሪዎቹ የእርስ በርስ ግጭት ባሻገር የምናየው ይህንን ዓይነት አሮጌ እና ዝተት አስተሳሰብ ይመስለኛል፡፡ ተማሪዎችን ለእርስ በርስ ሁከት በመዳረግ አሮጌውን አስተሳሰብ ወይም አግላዩን ሥርዓት መመለስ ነው ሕልማቸው፡፡
.
ነገር ግን አይሆንም! ወደ አለፈው ወደነቀዘው ሥርዓት አንመለስም! ወደ አግላይ ሥርዓት አንመለስም! አሳታፊ ሥርዓት ለመገንባት የምናደርገውን መውተርተር ለማጨናገፍ በሚፈጥሩት ሁከት ተስፋ አንቆርጥም!  ወደ ኋላ አንመለስም! ጉዞአችን ይቀጥላል፡- ወደፊት! ወደ አሳታፊ ሥርዓት!
Filed in: Amharic