>

ነጻነት ለምርጫ፤ ምርጫም ለነጻነት! (ያሬድ ሀይለ ማርያም)

ነጻነት ለምርጫ፤ ምርጫም ለነጻነት!
ያሬድ ሀይለ ማርያም
በብዙ ምስቅልቅል እና ፈታኝ ሁኔታዎች ውስጥ እያለፈች የመጣችው አገራችን የምርጫ ድግስ ከፊቷ ተደግኖ እየጠበቃት ነው። ፖለቲካችን ከመጠፋፋት እና ከመጠላለፍ አዙሪት ትንሽ ጋብ ብሎ የፖለቲካ ድርጅቶች በአንድ ጣራ ሥር ተቀምጠው የመወዳደሪያ ሜዳውን እንዴት እናደላድለው፤ የመጫወቻ ሕጉ ምን ይምሰል፤ የምርጫ አስፈጻሚው አካል እንዴት ይዋቀር፤ ፓሪቲዎች  እንዴት ይቀናጁ፤ የምርጫውን ሂደት ነጻና ፍትሐዊ ለማድረግ በሥልጣን ላይ ካለው ፓርቲ እና ከተፎካካሪዎቹ ምን ይጠበቃል የሚሉ እና ሌሎች ምርጫ ምርሻ የሚሸቱ፤ ውጤት ተኮር በሆኑ ጉዳዮች ላይ የጋራ ውይይትና ምክክር ሲደርጉ ማየቱ እጅግ ሊደገፍ እና ሊበረታታ የሚገባው እርምጃ ነው።
የመጣንበት መንገድ እጅግ የተበላሸ ስለመሆኑ አንዱ ማሳያው ባለፉት ሃያ ሰባት አመታት በአገሪቱ ውስጥ የተካሄዱት ‘ምርጫዎች’ ናቸው። የመጀመሪያዎቹን አምስት ምርጫዎች የመታዘብ፣ ታዛቢዎችን በማሰልጠን እና በማሰማራት፤ እንዲሁም የምርጫ ዘገባዎችን በማዘጋጀት ቀጥተኛ ተሳታፊ ስለነበርኩ ሂደቱን ለመገምገም ጥሩ እድል ፈጥሮልኛል። የመጨረሻዎቹን ሁለት ምርጫዎች ከአገር ውጭ ብሆንም ሂደቱን በርቀት ለመከታተል እና በቂ ግንዛቤም ለመጨበት የሚያስችል እድል ነበረኝ።
ያለፉት ‘ምርጫዎች’ ከመነሻቸውም ሆነ ሙሉ አካሄዳቸው የአገዛዝ ሥርዓቱን እድሜ  በሕጋዊ መንገድ ለማስቀጠል የታለሙ ስለነበሩ በአገሪቱ ፖለቲካ ላይ ጥቁር ነጥብ ጥለው ያለፉ እና ሕዝብ በምርጫ ሂደት ላይ እምነት እንዲያጣ ያደረጉ ነበሩ። አብዛኛዎቹ ምርጫዎች በሁከት፣ በግርግር፣ በወከባ፣ በእስር እና በግድያ የታጀቡ ነበሩ። ስለዚህም ገና ጭርጫ ሲባል ቡዙ ሰው ተናዳፊዋን ንብ እያሰበ ሊያጥወለውለው ይችላል።
ለብዙ ሰዎች ምርጫ ሲባል ድምጽ የሚሰጥበት ቀን ብቻ ነው ወደ አእምሯቸው የሚመጣው። በመሆኑም የአንድ ቀን ሥራ እና ክስተት አድርገው ይወስዱታል። የሚርጫ አብዛኛው እና ዋናው ሥራ የሚሰራው ከድምጽ መስጫው ቀን በፊት እና በኋላ ባሉት ጊዜያቶ ውስጥ ስለሆነ “ቅድመ ምርጫ” እና “ድህረ ምርጫ” በመባል የሚገለጹ የጊዜ ሰንጠረዦችንም የያዘ ነው። ቅድመ ምርጫው ብዙ ጊዜ የሚጀምረው ከእጩዎች ምዝገባ ጀምሮ ቢሆንም እንደ የአገሩ ሁኔታ ከዛም ሊቀድም ይችላል። በትንሹ ከድምጽ መስጫው ጊዜ አንድ አመት በፊት ይጀምራል። የድህረ ምርጫው ጊዜ ደግሞ በተለምዶ የምርጫው ውጤት እስከሚነገርበት ጊዜ ተደርጎ ቢወሰድም ሂደቱ ግን ተመራጮቹ አካላት በተመረጡበት ምክር ቤት ገብተው እና ቃለ መሃላ ፈጸመው ሥራ እስከሚጀምሩበት የመጀመሪያው የሥራ ቀናቸው ድርስ ይቀጥላል።
እንግዲዲህ ተወደደም ተጠላም፤ ጊዜው እረዘመመ ወይም በታቀደለት ቀን ተካሄደ ምርጫው የማይቀር ስለሆነ ከወዲሁ በምርጫ ጉዳዮች መወያየቱ፣ መማማሩ እና ሕዝባችንንም ማስተማሩ አይከፋም። ከዚህ በኋላ በተከታታይ በምርጫ ዙሪያ ለውይይት የሚረዱና ሃሳቦችን የሚያጭሩ፣ ሕብረተሰቡን ሊያስተምሩ እና ሊያወያዩ የሚችሉ ሃሳቦችን በቅደም ተከተል ለማቅረብ እሞክራለሁ። ይህን ጽሑፍ መግቢያ አድርጌ ጀምሬያለሁ። በማነሳቸው ሃሳቦችም ሆነ ከምርጫ ጋር በተያያዘ ጥያቄዎች ያላችሁ ወይም ሃሳብ ማካፈል የምትፈልጉ ሁሉ መድረኩን ልትጠቀሙበት ትችላላችሁ። በዚህ እጅግ ወሳኝ እና ከፍተኛ ግምት በሚሰጣ አገራዊ ጉዳይ ላይ የተለያዩ ሃሳቦች እንጂ ስድቦች አይስተናገዱም። ለሃሳቦቻችን ምላሹ ስድብ የሚወረውር ሰው አይኖርም፤ ካለ ግን መድረኩን እንዳያቆሽሽ በጊዜ ይወገዳል።
ይህን አጭር ማሳሰቢያ ከሰጠሁ በኋላ ለቀጣይ ውይይቶቻችን መንደርደሪያ ይሆን ዘንድ ለዛሬ አንድ መሰረታዊ የሃሳብ መንገድ ላስምር።
በምርጫ እና በነጻነት መካከል ያለውን መሰረታዊ ቁርኝት ልግለጽ። ምርጫ ለማካሄድ ነጻነት ያስፈልጋል። ነጻ መራጭ፣ ነጻ ተወዳዳሪ፣ ነጻ ምርጫ አስፈጻሚ፣ ነጻ የፖለቲካ ምህዳር፣ ነጻ ምርጫ ታዛቢ፣ ነጻ የፍትህ ተቋማት፣ ነጻ ሚዲያ እና ነጻ የጸጥታ አስከባሪዎች ያስፈልጋሉ። እነዚህ አካላት ነጻ ሆነው በሕግ የተጣለባቸውን ግዴታ እና የተሰጣቸውን መብት በአግባቡ ለመወጣት ካልቻሉ ምርጫው ምርጫ አይሆንም። በሌላ መልኩ በጫና ውስጥ የኖረ የህብረተሰብ ክፍል ወይም በማይፈልገው የፖለቲካ ሥርዓት ውስጥ የቆየ ሕዝብ ምርጫን ነጻ የመውጫ በር ያደርጋታል። በ1997 ባይሳካም በአገራችን የተሞከረው ምርጫን ከአንባገነናዊ ሥርዓት ለመገላገል እና ነጻ ለመውጣት እንደተከፈተ በር ነበር።
የምርጫ ሂደት በንግግር ነጻነት፣ በመደራጀት ነጻነት እና ባደባባይ ሃሳብን በመግለጽ ነጻነት ካልተደገፈ ግማሽ ጥሬ ነው። በላዩ ላይ የድምጽ አሰጣጡ እና የድምጽ ቆጠራው ነጻና ፍትሐዊነት ሲጎድለው ሙሉ ጥሬ ይሆናል። የሙሉ ጥሬ ምርጫ ሂደት ደግሞ ውጤቱ ምን እንደሚመስል ለማየት ደግሞ አሁን በሥራ ላይ ያለውን እና የ100% ድል ባለቤት የሆነውን ምክር ቤት ጉዞ መመርመር በቂ ነው። በመሆኑም ነጻነት የአንድ ምርጫ ሂደት ትክክለኛነት እና ፍትሐዊነት መነሻውም መድረሻውም ነው። ነጻ ሆኖ መምረጥና መመረጥ የቻለ ማህበረሰብ የወደፊት ነጻነቱም ባለቤት እሱ ነው። የምርጫው ሂደት ነጻ እና ፍትሐዊ መሆን ከምርጫው በኋላ ለሚኖረው ህይወታችን መሰረት ነው። ቅድመ ሂደቱን ነጻ ካደረግነው እና ምርጫውም በነጻና ፍትሐዊ መንገድ ከተጠናቀቀ ከምርጫው ማግስት ያለው ጉዟችን በነጻነት የተሞላ እንዲሆን ዋስትና ይሰጣል። ሕዝብ በነጻነት የመረጣቸው ሰዎች አገር ሲረከቡ ሕዝም ነጻ ይወጣል።
ስለዚህ ከወዲሁ እያንዳንዱን የፖለቲካ ሂደት፣ የገዢውን ፓርቲ ባህሪያት እና እርምጃዎች፣ የተቃዋሚ ኃይሎችን ብቃት፣ ባህሪ እና ዝግጁነት፣ የተቋማቶችን አወቃቀር እና ነጻነት፤ በተለይም የምርጫ ቦርዱን እና የፍትህ ተቋማቱን ጥንካሬ፣ ብቃት እና ገለልተኝነት፣ የመገናኛ ብዙሃን አጠቃቀም ፍትሃዊነት፣ በተቃዋሚዎች እና በገዥው ፓርቲ መካከል ያለው የአገር እና የሕዝብ አብት አጠቃቀም እና ለምርጫ ዋና የውይይት ማቀንቀኛ የሆኑ ሃሳቦችን ከወዲሁ በአንክሮ መከታተል የግድ ይላል። እያንዳንዱ ሰው የዜግነት ግዴታውን ሊወጣ ከሚገባባቸው አገራዊ ጉዳዮች መካከል አንዱ ወቅቱን ጠብቆ የሚመጣ ምርጫ ላይ በንቃት መሳተፍ ነው። ዜጎች ይህን በሕግ የተረጋገየላቸውን መብት በአግባቡ መጠቀም ሲችሉ ብቻ ነው በዲሞክራሲ የታነጸ እና ሕዝባዊ መሰረት ያለው መንግስት እና ጠንካራ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ሊወጡ የሚችሉት።
እንደምታውቁት እኛ አገር ምርጫ መብት ነው። አንድ ሰው በምርጫ ላይ ባለመሳተፉ በሕግ የሚደርስበት ምንም አይነት ቅጣት ወይም ማዕቀብ የለም። መምረጥ ከሚገባው ውስጥ አብዛኛው ሰው ላይሳተፍ ይችላል። ከሚሳተፈውም ውስጥ አብዛኛው ደስተኛ ሆኖ ሳይሆን በቀበሌ ካድሬዎች የሚደርስበትን ውክቢያና ማስፈራሪያ ለመገላገል ሲል ነው። ዜጎች በምርጫ ላይ ያላቸው ተሳትፎ በተመለከተ አንዳንድ አገሮች ለየት ያለ መንገድ ይከተላሉ። ለምሳሌ በምኖርበት ቤልጂየም በምርጫ ላይ ተሳትፌ ባልውቅም ሂደቱን ላካፍላችሁ። በቤልጂየም አገር አቀፍ ምርጫ ላይ መሳተፍ የሁሉም ዜጎች መብት ብቻ ሳይሆን ግዴታም ጭምር ነው። ዜጎች በምርጫው ላይ የመሳተፍ ግዴታ አለባቸው። ይህን ግዴታቸውን ሳይወጡ ከቀሩ ግን የገንዘብ ቅጣት ይጠብቃቸዋል። በመሆኑም ምርጫው ሲካሄድ በአገር ውስጥ ያሉ ዜጎች ሁሉ ይመርጣሉ። በወቅቱ በአገር ውስይ የሌሉ ደግሞ ባሉበት አገር በሚገኙ የቤልጂየሚ ቆንጽላ ጽ/ቤቶች በኩል እንዲመርጡ ወይም ሊመርጡ የማይችሉበትን ሁኔታ ቀድመው ማሳወቅና ማስረጃ ማቅረብ ይጠበቅባቸዋል። ስለዚህ ቤልጂየም ውስጥ በሚካሄደው ምርጫ ምን ያህል ሰው ሊሳተፍ እንደሚችል ቀድሞ ይታወቃል። ይህ ደግሞ ሌሎች ዝግጅቶችንም ሆነ ጥናቶችን ለማካሄድ ይረዳል።
በእኛ አገር የመራጮች ቁጥር የሚታወቀው የመራጮች ምዝገባ ተጠናቆ ሲያበቃ ነው። አንዳንድ ጊዜ የመራጩ ቁጥር ያንስ እና የምዝገባው ጊዜ እንዲራዘም ይደረጋል። ዜጎች እንዲመዘገቡም ቅስቀሳው በሁሉም አቅጣጫ ይጦፋል። ያም ሆኖ የመራጩ ቁጥር መምረጥ ከሚገባው ጋር ሲነጻጸር ሰፊ ልዩነት ይኖረዋል።
በምርጫ መሳተፍን ግዴታ የሚያደርግ የሕግ ማእቀፍ ባይኖርም እኛን ኢትዮጵያዊያኖችን በምርጫ እንድንሳተፍ የሚያስገድዱን ብዙ የኑሮ ማዕቀፎች ስላሉ ዜጎች ከአሁኑ በንቃት ሂደቱን ቢከታተሉ እና የዜግነት ድርሻቸውን ቢወጡ መልካም ነው። በሌሎች ምርጫ ነክ ጽሑፎች እስክመለስ በቸር ሰንብቱ።
Filed in: Amharic