>
10:45 pm - Tuesday July 5, 2022

ከሁለት ነገድ የተወለዱ ኢትዮጵያዉያን ዋነኞቹ የዘረኝነት አቀንቃኞች የመሆናቸዉ ሚስጢር ምን ይሆን?!? (ሸንቁጥ አየለ)

ከሁለት ነገድ የተወለዱ ኢትዮጵያዉያን ዋነኞቹ የዘረኝነት አቀንቃኞች የመሆናቸዉ ሚስጢር ምን ይሆን?!?
ሸንቁጥ አየለ
ከሁለት እና ከዚያ በላይ የሚወለደዉ የኢትዮጵያ ህዝብ ቁጥሩ እጅግ ብዙ ነዉ::በቁጥር ትልልቅ ብሄረሰብ ከሚባሉት የሚበልጠዉ የኢትዮጵያ ህዝብ ዉህድ ነዉ እንጅ ከአንድ ብሄረሰብ ብቻ የሚቀዳዉ ደም የለዉም::ነገስታት ኢትዮጵያዉያን የኢትዮጵያን ህዝብ በታላቅ ፍቅር እና ሀይል አዋህደዉታል::
ሆኖም ባለፉት ሰላሳ አመታት ዉስጥ ያስተዋልነዉ ነገር ይገርማል::ያሳዝናልም::
ከሁለት ነገድ/ብሄር የተወለዱ ኢትዮጵያዉያን ዋነኞቹ የዘረኝነት አቀንቃኞች ናቸዉ::እነዚህ ዉህድ ኢትዮጵያዉያን በዋናነት አንድነትን : ፍቅርን : አብሮነትን ኢትዮጵያዊነትን መስበክ እንዲሁም በሀይል እና በታላቅ ወኔ ማስተማር ሲኖርባቸዉ ጉልበት ያለዉ ከመሰላቸዉ ጋር እየተለጠፉ ዘረኝነትን ያስፋፋሉ::ይሄም ታላቅ የስነልቦና ህመም ነዉ::
አንድ ሰዉ ከሁለት ነገድ ወይም ከዚያ በላይ ነገዶች የማንነቱ ምንጭ ሆነዉ ሳለ በምን መስፈርት ነዉ አንዱን ብሄር መርጦ ነገዴ ይሄ ነዉ ሊል የሚችለዉ?
አንዳንዱ ቀዉስ ነገድ የሚቆጠረዉ በአባት ወገን ነዉ ይላል::ሌላዉ ቀዉስ ደግሞ ነገድ የሚቆጠረዉ በ እናት ወገን ነዉ ይላል::እነዚህ ሁለቱም አባባሎች የቀዉስ ህሳቤ ምንጭ ናቸዉ::
አንድ ሰዉ ዉህድ ከሆነ የሚጥለዉም የሚያነሳዉም ማንነት የለዉም::
የዉህድነቱ መለያ ደግሞ ኢትዮጵያዊነቱ እንጅ የትኛዉምነገድ አይደለም::
ኢትዮጵያ ህዝብ ስነ ልቦና ዉስጥ ተሸንቅሮ አልወጣ ያለ ይሄን ታላቅ በሽታ ኢትዮጵያዉያን ሁሉ ሊዋጉት እና ከማህበራዊ እሴታቸዉ ሊነቅሉት ይገባል::
ዉህድ ኢትዮጵያዉያን ከሁሉም ቀድማችሁ የፍቅርን እና የአንድነት አርማ በማንሳት ወደ ታላቁ የኢትዮጵያዉያን ማማ ላይ ዉጡ እንጂ በዘረኘት እና በጎሰኝነት ካንሰር አንዱን ነገድ በመወገን ሌላዉን ነገድ በመጥላት እርሳችሁን አትግደሉ::
የዘረኝነትን ዘር በኢትዮጵያ እና በኤርትራ ህዝብ መሃል ማን ዘራዉ? ኢሳያስ ዉህድ ነዉ::መለስ እንዲሁ ዉህድ ነዉ::አማራን ከኦነግ ጋር ሆነዉ ያሳረዱት የኦነግ አመራሮች ዉስጥ ከአማራ እና ከኦሮሞ የሚወለዱ ነበሩበት:: አሁንም አንዱን ጠልተዉ አንዱን ወደዉ ጥላቻን የሚያራግቡ ብዙ ናቸዉ::
አሁን ቅማንት እና አማራ : አገዉ እና አማራ: ትግሬ እና አማራ በሚባለዉ ጨዋታ ዉስጥ ገብተዉ ካንዱ ጋር ወግነዉ አንዱን የሚጎዱት ዉህድ ማንነት ያላቸዉ ብዙ ናቸዉ::ባለፉት ሰላሳ አመታት አንዴ ብአዴን ቤት አንዴ ኦህዴድ ቤት አንዴ ህዉሃት ቤት ሲቀላዉጡ እና ዘረኝነት ሲያስፋፉ የነበሩ አሁንም ዘረኝነትን በማስፋፋት የተጠመዱ እጅግ ብዙ ሰዎች ይታወቃሉ::
አንዴ አማራ ነን::አንዴ ኦሮሞ ነን::አንዴ ትግሬ ነን:: አንዴ አገዉ ነን::አንዴ ወላይታ ነን::አንዴም ሲዳማ ነን : አንዴም ሶማሌ ነን::አንዴም አንዴም አፋር ነን እያሉ ማንነታቸዉን እንደ አሸናፊዉ ሁኔታ እየገለባበጡ የሚሞዳሞዱ እጅግ ብዙ ቁጥር ያላቸዉ ዜጎች ከዚህ ከማስመሰል ማንነት ወጥተዉ ወደ ኢትዮጵያዊነት ማማዉ ላይ ቢወጡ የበለጠ የተከበሩ ዜጎች መሆን ይችላሉ::
ለሁሉም የምትመች ኢትዮጵያን ለመፍጠር በሚደረገዉ ትግል ዉስጥ ዋነኛ ተሳታፊ እና አመራር ሰጭ ሆነዉ የትግሉን ከፍታ ማገዝ ሲኖርባቸዉ እራሳቸዉን የአንዱ ነገድ ደጋፊ በማድረግ ኢትዮጵያን በአጠቃልይ የሚጎዳ ስራ የሚሰሩ ዉህድ ማንነት ያላቸዉ ሰዎች እራሳቸዉን ቢፈትሹ ጥቅሙ ለራሳቸዉ ብቻ ሳይሆን ለትዉልዳቸዉምጭምር ነዉ::
ኢትዮጵያዊነት ሁሉንም የነገድ ማንነቶች የያዘ ነዉና ከሁሉም ማንነቶች በላይ የገዘፈ እና ሁሉንም አቃፊ ነዉና ዉህድ ኢትዮጵያዉያን ሆይ ወደ ክብራችሁ ወደ ኢትዮጵያ ተመልከቱ እንጂ አንድኛዉን ነገድ ወግናችሁ ሌላዉን ወገናችሁን ማስጠቃታችሁን እና ማጥቃታችሁን ረግማችሁ ተዉት::
አንዲት ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን የመፍጠሩ ታላቅ የሀላፊነት ሂደት ዉስጥ እራሳችሁን ተሳታፊ አድርጉ እንጂ ከመርዘኛዉ የነገድ እና የጎሳ ጨዋታ እራሳችሁን አዉጡ::
Filed in: Amharic