>

መጠየቅ ካለብን የምንጠየቀው በጋራ ነው!!!  (አቶ አባይ ፀሐዬ) 

መጠየቅ ካለብን የምንጠየቀው በጋራ ነው!!!

 አቶ አባይ ፀሐዬ 

 

ከህወሓት መስራቾች አንዱና የገዢው ፓርቲ ኢህአዴግ ከፍተኛ አመራር የነበሩት እንዲሁም በተለያዩ ከፍተኛ የመንግሥት የኃላፊነት ቦታዎች ላይ የሠሩት አቶ አባይ ፀሐዬ ከወራት በፊት ተጀምሮ በኢትዮጵያ እየተካሄደ ስላለው ፖለቲካዊ ለውጥና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ከቢቢሲ አማርኛ ጋር ቆይታ አድርገዋል:-

ቢቢሲ፡ አሁን በኢትዮጵያ ባለው ለውጥ ላይ ህወሓት እንደ እንቅፋት ተደርጎ ይቀርባል። ለውጡን እንዴት ያዩታል ?

አቶ አባይ ፀሐዬ፡ አሁን በኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ለውጥ ኢህአዴግ ‘ብዙ በድያለሁ፤ አጥፍቻለሁ’ ብለው አራቱ ኣባል ድርጅቶች ገምግመው ህዝብን ይቅርታ ጠይቀው የተጀመረ ነው። ኢህአዴግ በዚህ ደረጃ ራሱን እንዲፈትሽ፣ መፈትሄ እንዲያሰቀምጥና ህዝብን ይቅርታ እንዲጠይቅ ህወሓት የጎላ ድርሻ ተጫውቷል።

የህወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ ግምገማ በጣም ጥልቀትና ስፋት ነበረው። ሌሎችም እንደ ፈር ቀዳችና እንደ ማሳያ ነው የወሰዱት። ስለዚህ ህወሓት የለውጥ ጀማሪ፣ በለውጡ የነቃ ተሳትፎና አብነታዊ ሚና ተጫውቷል። ከዚያ በፊት ህወሓት በትግራይ ህዝብ ተአማኒነት እስኪያጣ ድረስ የከፋ ችግር ነበረበት፤ በአገር ደረጃም የኢህኣዴግ አካል ሆኖ ብዙ ስህተት የፈፀመ ድርጅት ነው። ስለዚህ ስህተት አልፈፀምኩም፣ ጉድለት የለኝም፣ ያልተገባ ነገር አልሰራሁም አላለም። ይሄን ሁሉ ዘርዝሮ ለኢህአዴግ አቅርቧል፤ ለህዝቡም ይፋ አድርጓል።

ከዚያ በኋላም ህወሓት የህአዴግ አካል ሆኖ ለተሰሩ ስህተቶችም ከግምገማና ከሂስ አልፎ ዶክተር ዐብይ ሊቀመንበርና ጠቅላይ ሚኒስትር ሆኖ ሲመረጥ፤ በጋራ የመረጥነውን መሪ በፀጋ ተቀብሎ ደግፏል። በፓርላማም ድምፁን ሰጥቶ ‘የጋራ መሪያችን ነው፤ የጋራ ለውጥ ነው’ ብሎ በቅንነት በህግ አክባሪነት ለውጡን ደግፏል።

በተሰሩ መልካም ሥራዎች ላይም ህወሓት ጉልህ ሚና ነበረው። ለምሳሌ ከኤርተራ ጋር የተደረገው የሰላም ስምምነት፣ በውጭ የነበረሩ ተቃዋሚዎች እንዲመጡ፣ በነፍጥ ሲፋለሙ የነበሩ ወደ ሰላም እንዲመጡ የተደረገው ጥረት መነሻው የኢህአዴግ ሥራ አስፈፃሚና የኢህኣዴግ ምክርቤት ውሳኔ ነው።

አፈፃፀሙ ላይ ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዶክተር ዐብይ ላቅ ያለ ጥረት አድርገው ውጤታማ እንዲሆን ሰርተዋል። ይህንንም ህወሓት አድንቆና አመስግኖ ተቀብሎታል። ከዚያም አልፎ የእሰረኞች መፍታት አድንቆና ተቀብሎ ነው የሄደው።

እንዲሁም የባለስልጣናት ሽግሽግ ሲደረግ፤ በርካታ ከስልጣን የተነሱ ሰዎች ከሚኒስትርነትም፣ ከዚያ በታች ባሉ የሲቪል ኃላፊነት ቦታዎችም፣ ከሠራዊትም በርካቶች ከህወሓት ነው የተነሱት። ይሄንንም በፀጋ ነው የተቀበለው። ዲሞክራሲያዊ ነን በሚሉ አገሮች አንድ ፓርቲና አንድ ግለሰብ ከሠራዊት ወይም ከድህንነት ኃላፊነት ሲነሳ ስንት ኩርፍያና ግርግር ይፈጠራል። ህወሓት ግን አካሄዱ ላይ ይስተካከል ብሎ አስተያየት ሰጥቷል፤ ነገር ግን ተግባራዊ አድርጎታል። የቱ ጋ ነው ለውጡን የተቃወመው ?

አፈፃፀም ላይ የታዩ ግድለቶች ነበሩ እንሱም ደግሞ ይታረሙ ብሏል። ያለፈውን 27 ዓመት ምንም እንዳልተሰራ ይነገራል “ይሄ ትክክል አይደለም፤ አብረን ነው የሰራነው” በሎ ሃሳብ አቅረቧል። እንዴ ህወሓት ነው እንዴ የሰራው? ህወሓት ብቻ ነው እንዴ የሚከፋው? ሌላው የኢትዮጵያ ህዝብም’ኮ የለፋበት ነው። ይሄ ሲነቋሸሽ ህወሓትና የትግራይ ህዝብ ልዩ ቅሬታ ልዩ መከፋት የሚሰማቸው መስሎ የሚታያቸው ካሉ ትክክል አይደሉም። ይሄ ሚዛኑን ይጠብቅ ማለት ለውጥ መቃወም አይደለም።

ቢቢሲ፡ ለምሳሌ የኢትዮ ኤርትራ ጉዳይ ላይ ህወሓት ተቃውሞ አሰምቶ ነበር

አቶ አባይ ፀሐዬ፡ ኢትዮ ኤርትራ ሰላም አፈፃፀሙ ላይ የተወሰኑ ጉድለቶች ነበሩ። ህዝብን ብናማክር ይጠቅም ነበር። በትግራይ በኩል ያለው በር ይከፈት፤ ግንኙነቱ ከአዲስ አበባ ብቻ አይሁን፤ አሰብ ብቻ ሳይሆን ምፅዋም ይከፈት። የትግራይ ድንበሮች ክፍት ይሁኑ የሚል ነው። ይህንን ሃሳብ ማቅረብ ለውጡን መቃወም አይደለም።

ቢቢሲ፡ በውጭ የነበሩ የታጠቁ ኃይሎች አገርቤት ሲገቡስ ደስተኞች ነበራችሁ?

አቶ አባይ ፀሐዬ፡ ውጭ የነበሩት ተቃዋሚ ኃይሎች በአጭር ግዜ እንዲገቡ መደረጉ ህወሓትም የትግራይ ህዝብም አድንቋል። ኣብዛኛው በይቅርታና በፍቅር መንፈስ፤ አንድነትን በመፍጠርና ዲሞክራሲን በማስፋት መንፈስ ነው የመጣው። ጥቂቶቹ ግን ከነቂም በቀላቸው ነው ያሉት። ኢህአዴግ ላይ በጠቅላላ ቂምና በቀል ሊወጡ የሚፈልጉ አሉ። ይሄ ደግሞ ፡ የለውጡ መፈክር፡ በፍቅርና በይቅርታ እንዲሄድ የሚለው ሃሳብ ይፃረራል። ስለዚህ ይሄም ትክክል አይደለም ‘ተው’መባል አለባቸው። ጥቂቶች ናቸው። ስለዚህ ይሄ ይታረም ማለቱ መንድነው ክፋቱ?

ቢቢሲ፡ ህወሓት ለውጡ እንዴት ነው የሚረዳው? በተደጋገሚ የህግ የበላይነት ይከበር ስትሉስ ምን ለማለት ነው?

አቶ አባይ ፀሐዬ፡ ለውጥ ሲባል እናጨብጭብ ማለት አይደለም። ጥሩ ፈር ይዞ የሄደውን እናጨብጭብለት። ዳር እናድርሰው። በስመ ለውጥ ያልሆነ ነገር ተደባልቆ የሚደረግ ከሆነ፤ ተቀላቅሎ የሚፈፀም ሌላ ጤነኛ ያልሆነ ነገር ካለ ደግሞ “ይሄ እንከን አለው፤ ይሄ ለውጡን ያኮላሸዋል። ይሄ አይደለም የለውጡ መንፈስና ይዘት” ብሎ የሚያርም ለውጡን ከጉድለት የፀዳ እንዲሆን ማድረግና ይሄን በይፋ እንዲታረም መጠየቅ ለውጡን ያጎለብታል እንጂ ለውጡን ማደናቀፍ አይደለም።

ስለዚህ ላለፈውም ዋነኛው ተጠያቂ ህወሓት፤ የህግ የበላይነት ሲባልም የትግራይ ተወላጆች ላይ የሚያነጣጥር ከሆነ የትም አያደርሰንም። የህግ የበላይነት በሁሉም ክልል፣ በሁሉም ድርጅቶች፣ በሁሉም ፌደራል መንግሥት መስሪያ ቤቶች፣ በእኩል ዓይን በህግና በጠራ መረጃ ብቻ ፖለቲካዊ ዓላማ በሌለው፤ አድልዎ በሌለው መንገድ ይፈፀም ነው እያለ የለው የትግራይ ህዝብና መስተዳደር።

ይሄ ለውጡን መቃወም ነው? አይደለም። ህወሓት ላይና የትግራይ ተወላጆች ላይ አነጣጥሮ ሌላውን ነፃ አድርጎ ሸፍኖና ከልሎ ከሆነ ይሄ የህግ የበላይነት አይደለም። ህግ የማስፈን ጉዳይ አይደለም። ህዝብ እንዲያኮርፍና እንዲያገል የሚያደርግ ካልሆነ የትም አያደርስም።

አንድን ህዝብን ማግለልና ማስከፋት የጀመረ መንግሥት ሌላውንም ማስከፋቱን ማገለሉ አይቀርም። የግዜ ጉዳይ ነው። የኦሮሞ ህዝብ እንዲከፋ እንዲተራመስ ማንም አይፈልግም። ያ ሁላ መስዋዕትነት የተከፈለው የትግራይ ህዝብ፤ ያ ሁላ ትግል ያካሄደው ህወሓት፤ ለኦሮሞ ህዝብ ለአማራ ህዝብ ለመላ የኢትዮጵያ ህዝቦች ነፃነት ነበር።

በምን ተአምር ነው አሁን በየቦታው ለሚፈጠረው ችግር ወያኔ/ህወሓት ምክንያት ተደርጎ የሚነሳው? እንደዚህ ዓይነት አንድ ብሄር የሁሉም ችግር ምክንያት አድርጎ መመልከት አደገኛ ነው፤ አገርም ያፈርሳል።

ጣት የምንቀስርበት ብሄር ወይም ደግሞ የህብረተሰብ ክፍል መኖር የለበትም። እንቀፈው እናድምጠው፤ ምን አጎደልን ብለን እንጠይቀው። እንመካከርና እናርም። አለበለዝያ በየቦታው ግጭት፣ በየቦታው ጥርጣሬና ስጋት እየሰፋ የሚሄድበት ሁኔታ በጣም ያሰጋል።

ቢቢሲ፡ ትግሉን በመምራት፣ ፌደራላዊ ሥርዓቱን ተግባራዊ በማድረግና አጠቃላይ ሥረዓቱን (በኢህአዴግም ቢሆን) በበላይነት ይመራ የነበረው ህወሓት ነው። በተሰራው ስህተት ላይ ተጠያቂነቱ ከፍ ቢል የሚጠበቅ ነገር አይደለም ይላሉ?

አቶ አባይ ፀሐዬ፡ ፈረንጆች ‘ዳብል ስታንዳርድ’ የሚሉት አለ። አንደኛ አረመኔው የደርግ መንግሥት ተወግዷል፣ ልማት መጥቷል፣ ሰላም መጥቷል፣ አገራችን አንገቷን ቀና አድርጋ በዓለም እውቅና አግኝታ አካባቢዋን አረጋግታ እራሷን ማልማትና ማረጋጋት ጀምራለች ይላል ብዙ ሰው። በዚህ መንግሥት ውስጥ ህወሓት ከሆነ የአንበሳው ድረሻ የነበረው መመስገን አለበት። ጉድለት ላይ ሲሆን ህወሓት ነው ዋናው ተጠያቂ፤ ስኬቱ ላይ ደግሞ ‘እኛ’ኮ ነው የሰራነው፤ አለንበት’ የሚል ይመጣል።

የህወሓት መዳከምና ወደ ብልሽት መግባቱ፤ እንደ ትጥቅ ትግሉ ጊዜ፣ እንደ ሽግግሩ ጊዜ ህዝብ አመኔታ የሚያሳድርበት መሆኑ እየቀረ እያሽቆለቆለ መሄዱ ትግራይን ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያን በአጠቃላይ ደግሞ ሥርዓቱን መጉዳቱን ገምግሞታል። የእኛ መዳከም ለሥርዓቱ መዳከም ትልቅ ድርሻ አለው ብሎ ነው የገመገመው።

ይሄ ማለት ግን ህወሓት አድራጊ ፈጣሪ ነበረ ማለት አይደለም። ስልጣንን ሰብስቦ የያዘው ህወሓት ነው ማለት አይደለም። በሚኒስትሮች ምክርቤት ውስጥ ሦስት አራት ሚኒስትሮች፣ ፓርላማ ውስጥ ስድስት ወይም ሰባት በመቶ ነው። እኚህ ኣካላት ናቸው ፖሊሲ የሚያፀድቁ ህግ የሚያወጡ። እዛ ላይ ደግሞ አብላጫ ድምፅ ያላቸው ብዙ ወንበር፣ ብዙ ሚኒስትር ያላቸው ትልቁ ድርሻ አላቸው። ፍትህ አካላት ላይም ደግሞ እንደዚሁ። ብዙም የትግራይ ሰዎች አልነበሩበትም።

በፖሊስና በሠራዊት አመራር ላይ አዎ ነበሩ። ደህንነትም ላይ እንደዚሁ። ባለፉት ሰባት ስምንት ዓመታት ግን በአበዛኛው የሌላ ብሄር ተወላጆች ናቸው ያሉት። ኤታማዦር ሹምና የድህንነት ኃላፊ የትግራይ ሰው ከሆነ በቃ! ሁሉም ነገር በዚያ ይመዘናል።

ስለዚህ አገሪቱ ለገባችበት ችግር፣ ኢህአዴግ ላጋጠመው ቀውስ፣ የህወሓት አስተዋፀኦ ትልቅ ነበረ፤ ትክክል። ነገር ግን ለሁሉም ነገር ህወሓት ተጠያቂ መሆን ነበረበት የሚል ትክክል አይደለም። ምክንያቱም ህወሓት አናሳ ነው ድምፁ። የኢህአዴግ ሥራ አስፈፃሚና ማዕከላዊ ኮሚቴ ሲወስኑ አንድ አራተኛው ነው ድምፁ። ፓርላማም ውስጥ ከአስር በታች ነው ድምፁ። ሚኒስትሮች ምክር ቤት ውስጥም እንደዚሁ።

ስለዚህ ዋናው ተጠያቂ ኢህአዴግ የራሱ ሥራ አስፈፃሚ ነው ብሎ ነው የገመገመው። ህወሓት ነው ብሎ አልገመገመም። ምክንያቱም ፌዴራል መንግስቱን ስንመራ የነበረው፤ ሠራዊቱንም ደህንነቱንም ሲመራ የነበረው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከዚያ ቀጥሎ መከላከያ ሚኒስትሩና ኢታማዦር ሹሙ ናቸው። ስለዚህ ጠቅላይ ሚኒስትር የነበረው ከህወሓት ከሆነ፡ እሱ በነበረበት ጊዜ ተጠያቂ ይሆናል። ሌላው በነበረበት ጊዜ ድግሞ ሌላው ይጠየቃል።

ቀደም ብለን ማድረግ ይገባ የነበሩብን አሁን የተደረጉ ለውጦች አሉ፤ የሚል ከሆነ እቀበላለሁ። ለምሳሌ እስረኞችን መፍታት የጠቅላይ ሚኒስትሩር ለውጥ እስኪደረግ ድረስ ለምን አላደረግነውም? እዚህ ላይ ሁላችንም ድርሻ አለን እቀበላለሁ። ህወሓት ብቻ ለሁሉም ነገር ተጠያቂ ነው የሚል ግን መነሻው፤ የህወሓትና የትግራይ የበላይነት ነበረ ከሚል ነው የሚነሳው። ነገር ግን ከመረጃና ከሃቅ አይደለም ሚነሳው።

እንደሱ ቢሆን ለምን የትግራይ ህዝብ የተለየ ነገር አላገኘም? አንድ ሚሊዮን ህዝብ በየዓመቱ በረሃብ የሚጠቃ ነው። ህወሓት ራሱን በማያዳግምና ያለምህረት ሂስ አድርጓል። ለማስተካከል ልባዊ ጥረት አድርጓል። አሁንም ለውጡን ደግፎ በሙሉ ልብ እየሄደ ነው። አንዳንድ ጉድለቶችና ዝንፈቶች ደግሞ ቢስተካከሉ በይፋ በኢህአዴግ መድረክ ላይ እያረመ ነው እየሄደ ያለው።

ከዚያ በተረፈ ስለግለሰቦች ከሆነ የሚነገረው ስለሌሎች ግለሰቦችም ይነሳ። እያንዳንዱ ክልሉን ሲያስተዳደር የነበረ ይጠየቅ። ክልሉን ካላለማ፣ ካተራመሰ ህወሓት ነው የሚጠየቅለት? ለምን? ህወሓት ሲያስተዳድረው የነበረው ክልል አለ ከትግራይ ውጭ?

ስለዚህ ‘የጎደለ ነገር ካለ በዋናነት የሚጠየቀው እዚያ ያለው ፓርቲ ነው’ ብለን ነው በኢህአዴግ ውስጥ የገመገምነው። ለምንድነው ወደ ህወሓት ጣት የሚቀሰረው? አንቀበልም፤ ድርጅቱም እንደዚያ ብሎ አልገመገመም።

በፌደራል ደረጃ ላለው ችግር ደግሞ የምንጠየቀው በጋራ ነው። ለዚያውም ዋናው ተጠያቂ የኢህአዴግ ሥራ አስፈፃሚ ነው። ከዚያ በመቀጠል ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይሆናል ብለን ነው የገመገምነው።

Filed in: Amharic