>

የዛሬ ሰላም  ለነገ ምርጫ፤ የነገ ምርጫ ለዘላቂ ሰላም!!! (ያሬድ ሀይለማርያም)

የዛሬ ሰላም  ለነገ ምርጫ፤ የነገ ምርጫ ለዘላቂ ሰላም!!!
ያሬድ ሀይለማርያም
ከፊታችን የሚጠብቀንን ምርጫ በተመለከተ ውይይት ሊያጭሩ የሚችሉ ሃሳቦችን ለማንሳት እና በተከታታይ በማወጣቸው ጽሁፎች ሃሳቦቼን ለማካፈል ቃል በገባሁት መሰረት ይህ ሁለተኛው ምርጫ ተኮር ጽሁፍ ነው። የመጀመሪያውን ቅኝቴን ‘ነጻነት እና ምርጫ’ ያላቸውን ቁርኝት በመዳሰስ ጀምሬያለሁ። የዛሬው ዳሰሳ ሰላም እና ምርጫ ላይ ያተኮረ ይሆናል።
ሰላም እና መረጋጋ ባልሰፈነበት፣ የእርስ በርስ ግጭቶች በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ተደጋግመው እየተስተዋሉ ባለበት፣ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎች ከመኖሪያ ቅያቸው በተፈናቀሉበት፣ በአንዳንድ የአገሪቱ ክልሎች የታጠቁ ቡድኖች ከመንግስት ታጣቂዎች ጋር እየተጋጩ እና የተወሰኑ ወረዳዎችንም ተቆጣጥረው ፈላጭ ቆራጭ በሆኑበት እና መንግሥት የአገሪቱን ሰላም ለማስጠበቅ በቂ አቅም መፍጠር ባልቻለበት በዚህ ሁኔታ ውስጥ አገሪቱ ከአንድ አመት በኋላ ምርጫ ማካሄድ ትችላለች አትችልም ብሎ መከራከር በራሱ ትክክል ነው ወይ ብሎ ጥያቄ ማንሳት ይቻላል። እሱን እንዳለ ይዘን በአሁን ሰዓት ሁለት እሳቤዎች በዚህ ዙሪያ እየተንጸባረቁ ነው። የመጀመሪያው አሁን አገሪቱ ያለችበትን አጣብቂኝ ከግምት በማስገባት ምርጫው በዚህ ሁኔታ ውስጥ ሊካሄድ አይገባውም። ተቃዋሚዎችም በቂ የመዘጋጃ ጊዜ ሰልሚያስፈልጋቸው ምርጫው የሚካሄድበት ወቅት ይራዘም የሚል ነው።
በሌላ በኩል አገሪቱ ካለችበት አስቸጋሪ ሁኔታ ልትወጣ የምትችለው ምርጫውን በታቀደለት ጊዜ ውስጥ ማካሄድ ስትችል ነው። ምርጫው አገር እንዲረጋጋ እና የታጣውም ሰላም እንዲመጣ ይረዳል የሚል ምልከታም ያላቸው ሰዎች ድምጻቸውን አጉልተው እያሰሙ ነው። ለዚህ እሳቤያቸው መደገፊያ አድርገው የሚያቀርቡትም አንዱ እና ዋናው የመሟገቻ ነጥብ በሥልጣን ላይ ያለው መንግስት በሕዝብ ያልተመረጠ ስለሆነ ለሰላም እጦቱ ምክንያት ከሆኑት ነገሮች አንዱ እሱ ነው። በአንዳንድ ሥፍራዎች ሕዝቡ ባልመረጥናቸው ሰዎች አንገዛም እያለ ነው። ይህ አይነቱ ችግር በተለይም በኦሮሚያ ክልል የታየ መሆኑን የክልሉ ተቃዋሚ መሪዎች ደጋግመው ገልጸዋል። ስለዚህ ምርጫው በአፋጣኝ መካሄዱ ይህን ችግር ይቀርፈዋል የሚል ጠንካራ እምነት አላቸው።
በሁለቱም አሳቦች ዙሪያ እውነቶች አሉ። ነገር ግን ብቻቸውን የምርጫው ሂደት በታቀደለት ጊዜ ውስጥ ይካሄድ ወይስ ይራዘም ለሚለው ጥያቄ ምንክንያት ሊሆኑ አይችሉም። እርግጥ ነው ሰላም በሌለበት ሁኔታ ምርጫ ማካሄዱ ሂደቱን ከማደነቃቀፉም ባሻገር ነጻና ፍትሐዊነቱንም ጥያቄ ውስጥ ይከተዋል። በሌላ መልኩ የምርጫ ሂደት መዘግየትም በራሱ ዘርፈ ብዙ የሆኑ ችግሮችን ሊያስከትል ይችላል። በእነዚህ ሁለት አጣብቂኝ ውስጥ ላለችው አገራችን መፍትሔውን ከወዲሁ መሻት ግን የግድ ይላል።
እንደ እኔ እምነት አሁን ያለው የሰላም እጦት እና በተለያዩ ክልሎች ውስጥ የሚታየው የእርስ በርስ ግጭት እና መፈናቀል ጊዜያዊ ግችሮች ይመስሉኛል። መንግስት እነዚህን ችግሮች በአፋጣኝ ለመፍታት የሚያስችለውን ቅድመ ዝግጅት በማድረግ ሕብረተሰቡ ባሳተፈ መልኩ አደጋውን መጋፈጥ ከቻለ መፍትሔው እሩቅ እና ከባድ አይሆንም። በአገሪቱ ውስጥ ከመንግስት ቁጥጥር እና ከሕግ ሥርዓት ያፈነገጠ አንዳንችም ክልል ወይም ከዛ በታች ያለ የግዛት መዋቅር ሊኖር አይገባውም። መንግስት በሁሉም የአገሪቷ ክፍሎች እኩል ሥርዓት የሚያሰፍንበት፣ ሕግ የሚያስከብርበት እና ፖሊሲዎቹን የሚያስፈጽምምበት፤ እንዲሁም እስከ ቀበሌ ባሉ መዋቅሮች ውስጥ ለውጡ በእኩል ደረጃ ሰርጾ መግባቱን እና በተሿሚዎቹም ዘንድ የለውጡ መንፈስ በደንብ ተቀባይነት ያገኘ መሆኑን ሊያረጋግጥ ይገባል።
የተወሰኑ ክልሎች እስካሁ እንደታየው ለተወሰኑ ቡድኖች እና ፖለቲካ ፓርቲዎች ብቻ ክፍት ሆነው የተወሰኑትን ያገለሉበትን እና አናስጠጋም ያሉበት ሁኔታ በግላጭ እየታየ ነው። በተለይም በኦሮሚያ እና በትግራይ ክልል ያለው ሁኔታ ለዚህ ጥሩ ማሳያ ነው። በኦሮሚያ ክልል ውስጥ የኦሮሞ ፖለቲካ ድርጅቶች ሕዝብን ለማወያየትም ሆነ ለመሰብሰብ ያላቸውን ያህል ነጻነት ሌሎቹ ድርጅቶች የላቸውም። በአንዳንድ የኦሮሚያ ክልል ከተሞች ኦሮሞ ያልሆኑ ድርጅቶች እንዳይንቀሳቀሱ እና ሕዝቡንም እንዳያወያዩ በአካባቢው ባለሥልጣናት ጭምር ወከባ እና እንግልት የደረሰባቸው መሆኑን ደጋግመው በሚዲያዎች ሲገልጹ ሰምተናል።
በትግራይ ክልል ደግሞ ከኦሮሚያውም እጅግ በከፋ ሁኔታ ከህውሃት በስተቀር በክልሉ ውስጥ ሌሎች ተቃዋሚ ድርጅቶች ሕዝቡን ማግኘትም ሆነ የአደባባይ ውይይቶች እና ሰልፎች ማካሔድ እንደማይችሉ ይታወቃል። የትግራይን የተለየ የሚያደርገው እዛው በክልል ደረጃ የተዋቀሩ እንደ አረና አይነት ድርጅቶች ጭምር በነጻነት መንቀሳቀስ የማይችሉ መሆኑ ነው። በተመሳሳይ ሁኔታም በአማራ እና በትግራይ ክልል አዋሳኝ በሆኑ እና የማንነት ጥያቄ በተነሳባቸው ሥፍራዎች ያለው አሳሳቢ ሁኔታም ይህን ምርጫ ተኮር የሆነውን የፓርቲዎች እንቅስቃሴ ክፉኛ የሚጎዳው ነው።
በሌሎች አንዳንድ የአገሪቱ ክፍሎችም ተመሳሳይ የጸጥታ ሁኔታ ስላለ ተቃዋሚ ድርጅቶች በነጻነት ተንቀሳቅሰው ሕዝብን ማወያየት እንዳልቻሉ መረጃዎች ይጠቁማሉ። ይህ አይነቱ የዲሞክራሲያዊ ሂደትን ሊያደናቅፍ እና የተጀመረውም ለውጥ ላይ ጥላ ሊያጠላ የሚችልን ችግር የፌደራል መንግስቱ ከክልል መንግሥታት ጋር በመተባበር ከወዲሁ በአፋጣኝ ሊያጸዳው ይገባል። እንደ እኔ እምነት እነዚህ ችግሮች ቀላል ባይሆኑም ሊቀረፉ የሚችሉ ግን ናቸው።
የፌደራል መንግሥቱ በቀጣዮቹ ስድስት ወራት ውስጥ እነዚህን ችግሮች ሙሉ በሙሉ ሊባል በሚችል መልኩ መቅረፍ ከቻለ ምርጫው ጊዜውን ጠብቆ ሊካሄድ የሚችልበትን ሁኔታ ይፈጥራል። በእነዚህ ስድስት ወራት ውስጥ ፓርቲዎች እራሳቸውን በማዘጋጀት እና ድርጅታዊ ብቃታቸውን በማጎልበት ሥራ ላይ ሊጠመዱ ይችላሉ።
እነዚህ በአገሪቱ የተለያዩ ክልሎች የሚታዩት ችግሮች በቀጣዩቹ ስድስት ወራት ውስጥ ካልሰከኑ እና መንግሥትም ሊቆጣጠራቸው ካልቻለ ግን የምርጫው ሂደት ብቻ ሳይሆን ሙሉ በሙሉ የተጀመረውም ለውጥ አደጋ ላይ ሊወድቅ ይችላል። በመሆኑም ከዚህ የሚከተሉት ጉዳዮች ላይ አትኩሮች ሰጥቶ መስራት የግድ ይላል፤
– በቡድን ወይም በፓርቲ ደረጃ የተደራጁ እና እስከ አሁን ትጥቃቸውን እንዳነገቡ ያሉ ኃይሎች በአፋጣኝ ትጥቅ እንዲፈቱ ማድረግ እና በማናቸውም መልኩ መንግስት ከእነዚህ ኃይሎች ጋር የሚያደርጋቸው ስምምነቶች ትጥቅ ይዞ መቆየትን የማይጨምር መሆኑን ማረጋገጥ። በተጨማሪም የተደረጉትን ስምምነቶች ለሕዝብ ይፋ ማድረግ፤
– የግጭት ቀጠና በሆኑት እና ተደጋጋሚ የሰላም መታጣት ባለባቸው አካባቢዎች የፌደራል ኃይል እንዲሰፍር እና አካባቢዎቹ ከክልል ታጣቂዎች ነጻ እንዲሆኑ ማድረግ፤
– ከላይ እስከ ታች ላለው የመንግስት መዋቅር ላይ የተቀመጡ ሰዎች የተቃዋሚ ፓሪቲዎችን እንቅስቃሴ የሚገድብ ምንም አይነት እርምጃ እንዳይወስዱ እና ይህን በሚተላለፉ የክልል ባለሥልጣናት ላይ አፋጣኝ እርምጃ መውሰድ፤
– አንዳንድ ክልሎች ውስጥ ሕዝቡን ለአመጽ የሚጋብዙ እና የተወሰኑ ተቃዋሚዎችን ኢላማ ያደረጉ ወይም በጠላትነት ሕዝቡ እንዲያያቸው የሚያደርጉ የአደባባይ ቅስቀሳዎችን የሚያደርጉ የብሄር ድርጅቶች ከአድራጎታቸው እንዲታቀቡ እና ይህን ካላደረጉም አስፈላጊውን እርምጃ መውሰድ። ፓርቲዎችም በጋራ በጀመሩት የውይይት መድረክ ላይ በዚህ አሳብ ዙሪያ ተወያይተው እና ተማምነው አንድ የጋራ መግለጫ እና የስምምነት ቃል ኪዳን እንዲያወጡ ማድረግ፤
– መንግስት ለሁሉም ተቃዋሚ ድርጅቶች ተገቢውን የገንዘብ፣ የቁሳቁስ፣ የጽ/ቤቶች እና የጥበቃ ድጋፍ ማድረግ ይኖርበታል።
እንደሚታወቀው ገዢው ፓርቲ ሙሉ በሙሉ የአገሪቱን መንግስታዊ መዋቅሮች፣ የመንግስትን በጀት እና በመንግስት ደሞች የሚንቀሳቀሰ ሰፊ የሰው ኃይል ያለው እና በሁሉም ዘርፍ የፈረጠመ ተቋም ነው። ይህን ኃይል ሊገዳደሩ እና በምርጫም ሊፎካከሩት ከጎኑ የቆሙት ድርጅቶች ከሚሱ ከዘመናት የበርሃ ህይወት ተመልሰውና ጠመንጃቸውን ጥለው ቢሮ ለማደራጀት እና አባላት ለማፍራት ደፋ ቀና የሚሉ ናቸው። ቀሪዎቹም በአገር ውስጥ ቢቆዩም በነበረባቸው ጫና የተነሳ መሪዎቻቸው ገና ከእስር የወጡ፣ ቢሮዎቻቸውም ተዘግተው ወይም ተዳክመው የቆዩ እና ሰነዶቻቸውም አቧራ ቅመው እሱን እያራገፉ ያሉ ናቸው። እነዚህ ድርጅቶች እንደገና ከትቢያ ተነስተው እስኪጠናከሩ ድረስ ተገቢውን የተወሰኑ ወራትን ይፈልጋሉ።
መንግስት የአገሪቱን ሰላም ከማስከበር ጎን ለጎን የአፈናው ሰለባ ሆነው ለተዳከሙት ድርጅቶች ማጠናከሪያ የሚሆኑ እርምጃዎችን ከወዲሁ ሊወስድ ይገባል። ዛሬ መንግስት ከሕዝቡ ጋር ሆኖ የሚያሰፍነው ሰላም እና መረጋጋት ምርጫው ሳይስተጓጎል በጊዜው እንዲካሄድ የሚረዳውን ያህል፤ ምርጫውም በታቀደለት መልኩ ከተጠናቀቀ የአገራችን ዘላቂ ሰላም ማጽኛ ምህላቅ ይሆናል።
የዛሬውስ ሰላም ለነገው ምርጫ፤ የነገው ምርጫ ለዘለቄታ ሰላማችን መሰረቶች ናቸው።
በቸር እንሰንብት!
Filed in: Amharic