>

በአዲስ አበባ ዙሪያ የሚሰሙ እሮሮዎችና የታከለ ኡማ ፈተና!!! (ሞሀመድ አሊ መሀመድ)

በአዲስ አበባ ዙሪያ የሚሰሙ እሮሮዎችና የታከለ ኡማ ፈተና!!!
ሞሀመድ አሊ መሀመድ
የአዲስ አበባ ከተማ ም/ከንቲባ ታከለ ኡማ ከታችም ከላይም በሚቀጣጠል የፖለቲካ ትኩሳት እንደቡሄ ዳቦ የሚጠበስ ይመስለኛል፡፡ ባንድ በኩል ከአዲስ አበባ መስፋፋት ጋር በተያያዘ በከተማዋ ዙሪያ የነበሩ አርሶ አደሮች መፈናቀላቸው አስተዳደሩን ክፉኛ ሊንጠው የሚችል የፖለቲካ አጀንዳ ሆኗል፡፡ በዚህ አጀንዳ ዙሪያ ህዝብን ለማሰለፍና ለማንቀሳቀስ ታዋቂ አክቲቪስቶች ጭምር በተቀናጀ መልኩ ውስጥ ለውስጥ እየሠሩ እንደሆነ ይወራል፡፡ በሌላ በኩል በከተማዋ ዙሪያ በህገ-ወጥ መንገድ የተገነባ ነው በሚል ቤታቸው እንዲፈርስ ተደርጎ ሜዳ ላይ የተበተኑ ዜጎች ጉዳይ ሌላ የፖለቲካ ትኩሳት ሆኗል፡፡ አንዳንድ ወገኖች ይህን እርምጃ የአዲስ አበባን የሥነ-ህዝብ ሁኔታ (demography) ለመበወዝ ያለመ አድርገው ይወስዱታል፡፡ በዚህ መሐል ያደፈጠው የአዲስ አበባ ባለቤትነት ጥያቄ ሌላ ሥጋት አርግዞ ቀኑን የሚቆጥር ይመስላል፡፡ እነዚህን ሁኔታዎች ደምሮ ማሰብ ትልቅ ራስ ምታት ሊፈጥር እንደሚችል መገመት ይቻላል፡፡
አዲስ አበባ የማናት?
ይኸ ጥያቄ ከጅምሩ ግራ የሚያጋባና ግራ የሆነ ጥያቄ ነው፡፡ ለዚህ ጥያቄ እስካሁን ድረስ ሁሉንም ወገን ሊያስማማ የሚችል ምላሽ የተገኘ አይመስልም፡፡ አወዛጋቢው የኢፌዴሪ ህገ-መንግሥት ድንጋጌም ቢሆን ከአዲስ አበባ መገኛ ቦታ በመነሳት ከኦሮሚያ መንግሥት ጋር ስለሚኖረው መስተጋብርና የኦሮሚያ መንግሥት ሊያገኘው የሚገባው ልዩ ጥቅም መጠበቁን ከማመልከት ባለፈ በዝርዝር የሚለው ነገር የለም፡፡ ይልቁንም ዝርዝሩ ወደፊት ሊወጣ በሚችል ህግ እንደሚወሰን በጥቅሉ ገልፆት ያልፋል፡፡ ለማንኛውም የህገ-መንግሥቱ አንቀፅ 49(5) አንቀፅ ድንጋጌ፣
“የኦሮሚያ ክልል፣ የአገልግሎት አቅርቦት ወይም የተፈጥሮ ሀብት አጠቃቀምንና የመሳሰሉትን ጉዳዮች በተመለከተ፣ እንዲሁም አዲስ አበባ በኦሮሚያ ክልል መሀል የሚገኝ በመሆኑ የሚነሱ ሁለቱን የሚያስተሳስሩ አስተዳደራዊ ጉዳዮችን በተመለከተ ያለው ልዩ ጥቅም ይጠበቅለታል፡፡ ዝርዝሩ በህግ ይወሰናል፡፡” ይላል፡፡
ለመሆኑ የዚህ ድንጋጌ አንደምታ ምንድነው? “የአገልግሎት አቅርቦት” ሲባልስ ማነው አቅራቢና ተቀባዩ? “የተፈጥሮ ሀብት አጠቃቀም” ሲባልስ ምን ምንን ያካትታል? የመሬት አጠቃቀምን ይጨምር ይሆን? “ሁለቱን የሚያስተሳስሩ አስተዳደራዊ ጉዳዮችስ” ከምን የሚመነጩ ናቸው? “ልዩ ጥቅም” የተባለውስ በምን ይገለፃል? “ዝርዝሩን በህግ” የሚወስነውስ ማነው? የህገ-መንግሥቱ አርቃቂዎች ፍላጎትስ (the intention of the drafters) ምን ይሆን?
ምናልባትም የህገ-መንግሥቱ አርቃቂዎችን ፍላጎት ማግኘት የሚቻለው በቀደሙት የዚህ አንቀፅ ንዑስ አንቀፆች ነው፡፡ አንቀፅ 49 (1) እና (3) ተጣምረው ሲነበቡ “አዲስ አበባ የፌዴራሉ መንግሥት ርዕሰ-ከተማ ስትሆን ተጠሪነቷም ለፌዴራሉ መንግሥት” እንደሆነ አስረግጠው ይናገራሉ፡፡ አንቀፅ 49 (2) እና (4) በፊናቸው “አዲስ አበባ ከተማ ሙሉ በሙሉ ራሱን የሚያስተዳድር ሲሆን ነዋሪው ህዝብ በቀጥታ በፌዴራሉ የህዝብ ተወካዮች ም/ቤት” እንደሚወከል በማያሻማ አኳኋን ይገልፃሉ፡፡ ከዚህ በመነሳት በአዲስ አበባ ጉዳይ ላይ ወሳኙ የከተማው ነዋሪ መሆኑን አስረግጦ መናገር ይቻላል፡፡ ይህም ሆኖ ግን ጉዳዩ አሳሳቢና አነጋጋሪ (sensitive & controversial) መሆኑ አልቀረም፡፡
የአዲስ አበባ ዙሪያ ፖለቲካ፣
የአዲስ አበባ ዙሪያ ፖለቲካ መልኩን እየቀያየረና በየጊዜው እያደገ የሚሄድ ነው ማለት ይቻላል፡፡ በ1993 ዓ.ም የሜጫና ቱለማ መረዳጃ ማህበር መሪዎችን ጨምሮ የኦሮሞ ተወላጅ ለሆኑ በርካታ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች እስርና እንግልት ምክንያት የሆነው የኦሮሚያ ክልል መቀመጫ አዲስ አበባ መሆን አለባት የሚል ጥያቄ ነበር፡፡ ሆኖም ግን፣ ያ ሁሉ መስዋዕትነት ተከፍሎም የኦሮሚያ ክልል መቀመጫ ወደ አዳማ/ናዝሬት መዛወሩ አልቀረም ነበር፡፡ የክልሉ መቀመጫ ወደ አዲስ አበባ የተመለሰው በ1997 ዓ.ም ምርጫ በአዲስ አበባ ከተማ ህዝብ ሙሉ በሙሉ የተመረጠውን ቅንጅትን ፈተና ላይ ለመጣል ታስቦ ነበር፡፡ ይሁንና ቅንጅት የከተማውን አስተዳደር ባለመረከቡ በህገ-መንግሥቱ የተጠበቀው “የልዩ ጥቅም” ጉዳይ ሳይነሳ ቆዬ፡፡
የአዲስ አበባ ጉዳይ እንደገና አነጋጋሪ ሊሆን የቻለው አወዛጋቢው የአዲስ አበባ ማተር ፕላን ይፋ መደረጉን ተከትሎ ነበር፡፡  ጉዳዩ ከፍተኛ ተቃውሞን በመቀስቀሱ የተባለው ማስተር ፕላን ሥራ ላይ ሳይውል ቀርቷል፡፡ የማስተር ፕላኑ አጀንዳ ከተዘጋ በኋላ ሌላው አነጋጋሪ ጉዳይ መሆን የቻለው የኦሮሚያ ክልል ከአዲስ አበባ ከተማ ሊያገኝ የሚገባውንና በህገ-መንግሥቱ የተጠበቀለትን “ልዩ ጥቅም” በሚመለከት ለፓርላማው የቀረበው የህግ ረቂቅ ነበር፡፡ ረቂቅ ህጉን ተከትሎ “አዲስ አበባ የማናት?” የሚለው ጉዳይ እስካሁንም አነጋጋሪ ሆኖ ቀጥሏል፡፡ አሁን ደግሞ በአዲስ አበባ ከተማ ዙሪያ የድሆች መፈናቀልና እሮሮ ሰሞነኛና/አንገብጋቢ አጀንዳ ሆኗል፡፡
የአርሶ አደሮች መፈናቀል፣
በየትኛውም አገር ቢሆን ከተሞች ሲስፋፉ አርሶ አደሮች መፈናቀላቸው የማይቀርና የተለመደ ሂደት (pattern) ነው፡፡ በሀገራችን በአዲስ አበባ ብቻ ሳይሆን በመቀሌ፣ በባህርዳር፣ በአዋሳና በሌሎች (ትላልቅና መካከለኛ ዕድገት ባላቸው) ከተሞች ዙሪያም ከከተሞቹ መስፋፋት ጋር በተያያዘ አርሶ አደሮች መፈናቀላቸው የግድና የሚጠበቅ ነው፡፡ ምናልባት በሌሎች ከተሞች ዙሪያ ለተፈናቀሉ አርሶ አደሮች የሚቆረቆርላቸውና የሚጮህላቸው ጠፍቶ ነው? ወይስ አርሶ አደሮቹ ከከተሞቹ መስፋፋት የሚያገኙት የተለዬ ትሩፋት ይኖር ይሆን? ወይስ ከዚህ ጀርባ ሌላ የተለዬ/የተደበቀ አጀንዳ አለ?
በርግጥ በሌሎች ከተሞች ዙሪያ ለተፈናቀሉ አርሶ አደሮች የሚጮህላቸው ወገን አለመኖሩ በአዲስ አበባ ዙሪያ ለሚፈናቀሉ አርሶ አደሮች መጮህን ጥያቄ ውስጥ ለማስገባት በቂ መነሻ ሊሆን አይችልም፡፡ በተለይም ደግሞ ከሌሎች አንፃር ሲታይ የአዲስ አበባ ከተማ መስፋፋት በብዙ እጥፍ ስለሚልቅ የሚፈናቀሉት አርሶ አደሮች ቁጥርም ያንኑ ያህል ያሻቅባል፡፡ ይሁንና በግለሰብ ደረጃ ካየነው በእያንዳንዱ አርሶ አደር ላይ የሚደርሰው ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጉዳት ተመሳሳይ ነው፡፡ ስለሆነም ከከተሞች መስፋፋት ጋር በተያያዘ ስለሚፈናቀሉ አርሶ አደሮች አንድ ወጥ አገር አቀፍ ፖሊሲ መከተል አስፈላጊ ነው፡፡
አርሶ አደሮቹን ማን አፈናቀላቸው?
ይህን ጥያቄ ማንሳት የሚያስፈልገው አርሶ አደሮች ሊፈናቀሉ የሚችሉት በተለያዬ ምክንያትና መንገድ ስለሆነ ነው፡፡ በኛ ሀገር ሁኔታ ከከተሞች መስፋፋት ጋር በተያያዘ ገበሬዎች የተፈናቀሉት በሁለት መንገድ ነው ማለት ይቻላል፡፡ በአንድ በኩል መንግሥት “መሬቱ ለልማት ይፈለጋል” በሚል አነስተኛ የካሳ ክፍያ በመስጠት ገበሬውን አስገድዶ የሚያፈናቅልበት ሁኔታ አለ፡፡ ገበሬው ከመሬቱ ብቻ ሳይሆን ከኖረበትና ከሚያውቀው የግብርና ሥራ ሲፈናቀል ከባህር የወጣ ዓሣ መሆኑ አይቀርም፡፡ ወደ ከተማ ገብቶ በሌሎች የሥራ ዘርፎች ለመሠማራት ምንም ዓይነት ልምድና ክህሎት የሌለው ከመሆኑም በላይ የሚሰጠው የካሳ ክፍያም ህይወቱን ሊቀይር የሚችልና የሚያወላዳ አይደለም፡፡ ገበሬው ከመሬቱ ሲፈናቀል ኢኮኖሚያዊ ብቻ ሳይሆን ማህበራዊ መሠረቱም ይናጋል፡፡ ስለሆነም መንግሥት በልማት ሥም ገበሬውን ሲያፈናቅል ተያያዥ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ችግሮችን ታሳቢ በማድረግ ዘላቂነት ያለው የመፍትሔ አቅጣጫን አብሮ መቀየስና ማስቀመጥ ነበረበት፡፡
በሌላ በኩል ግን በተለይ በከተሞች ዙሪያ የሚገኘው ገበሬ ወድዶና ፈቅዶ መሬቱን እየሸነሸነ የሚሸጥበት ሁኔታ መኖሩን መካድ አይቻልም፡፡ በህገ-መንግሥቱ መሬትን በግል መሸጥና መለወጥ የማይፈቀድ ቢሆንም ገበሬዎች በይዞታቸው ሥር የሚገኙ መሬቶችን እየሸነሸኑ በሽያጭ ማስላለፋቸው የተለመደና የሚታወቅ ነገር ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት በአዲስ አበባ ከተማ ዙሪያ ከገበሬዎች ላይ የሚገዛ (እስከ 200 ካ.ሜ የሚደርስ) የቤት መሥሪያ (ሰነድ አልባ) ቦታ ዋጋ እስከ ብር 600,000.00 (ስድስት መቶ ሺህ ብር) እንደሚደርስ ይነገራል፡፡ በዚህ ሂሳብ በሄክታር የሚገመት የመሬት ይዞታ ያላቸው ገበሬዎች ምን ያህል ገንዘብ ሊያገኙ እንደሚችሉ መገመት ይቻላል፡፡ በዝቅተኛ ግምትና የካሳ ክፍያ እየተሸነገሉ በልማት ሥም ከተፈናቀሉት አንፃር ሲታይ በግላቸው (በህገ-ወጥ መንገድም ቢሆን) መሬታቸውን እየሸነሸኑ የሸጡት ገበሬዎች ይበልጥ ተጠቃሚዎች ናቸው ለማለት ያስደፍራል፡፡
ይህም ሆኖ ግን፣ የከተሞች መስፋፋት ለአካባቢው ነባር ማህበረሰብ ይዟቸው የሚመጣ ትሩፋቶች መኖር አለባቸው፡፡ ከተሞች ሲስፋፉ የመሠረተ ልማትና የተለያዩ የማህበራዊ አገልግሎቶች አብረው ይስፋፋሉ። ሆኖም ግን ከተሞች ሲስፋፉ ገበሬው ከመሬቱ ተፈናቅሎ የትም ከተጣለ ልማቱ መጣብኝ እንጅ መጣልኝ ሊል አይችልም። ስለሆነም ገበሬዎች ከመሬታቸው ሲፈናቀሉ ሊያቋቁማቸውና ህይወታቸውን ሊቀይር የሚችል ተመጣጣኝና ተገቢው ካሳ ሊከፈላቸው ይገባል። እንዲሁም የሚመለከታቸው የከተማ አስተዳደሮች ቢያንስ በሚይዟቸው የጋራ መኖሪያ ቤቶች ግንባታ ፕሮግራም ውስጥ የአርሶ አደሮቹን ጉዳይ ማካተት እንዳለባቸው ማሰብ ያስፈልጋል፡፡ ከዚህም ባለፈ አርሶ አደሮቹ ወደሌሎች የኢኮኖሚ/የሥራ ዘርፎች ሊሸጋገሩ የሚችሉበትን የገንዘብና የሙያ (financial & technical) ድጋፍ መስጠትም አብሮ መታየት ያለበት ጉዳይ ነው፡፡ ሆኖም ግን፣ ይህ አካሄድ ቀደም ሲል በጋራ መኖሪያ ቤቶች ግንባታ ፕሮግራም ተመዝግበው ገንዘብ ሲቆጥቡ የቆዩና ዕጣቸውን የሚጠባበቁ የከተማ ነዋሪዎችን መብት የሚያጣብብ መሆን እንደሌለበት ሊሰመርበት ይገባል፡፡ አሁን በመገንባት ላይ ያሉ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ግንባታ ወጭ የሚሸፈነው እነዚህ ዜጎች ባዋጡት ገንዘብ መሆኑም መዘንጋት የለበትም፡፡
ህገ-ወጥ ግንባታ/ቤቶችን የማፍረስ እርምጃ፣
መንግሥት ሕግና ሥርዓትን የማስከበር ኃላፊነት እንዳለበት እሙን ነው፡፡ ይሁንና ህግና ሥርዓትን በማስከበር ረገድ አስቀድሞ የመከላከል መርህን መከተል ያስፈልጋል፡፡ ግለሰብ ዜጎች ህግና ደንብን ተላልፈው ሲገኙም፣ በተለይ አስተዳደራዊ እርምጃ ለመውሰድ፣ ነባራዊ ሁኔታዎችን ግምት ውስጥ ማስገባት ተራ የፖለቲካ ሀሁ ይመስለኛል፡፡ ከዚህ አንፃር በአዲስ አበባ ከተማ ዙሪያ በተለያዩ ጊዜያት በተለምዶ “ህገ-ወጥ” የሚባሉ ግንባታዎችን/”ሰነድ አልባ” ቤቶችን ለማፍረስ የሚወሰዱ እርምጃዎች ሊያስከትሉ የሚችሉት ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ቀውስ ግንዛቤ ውስጥ የሚገባ አይመስልም፡፡ ውሎ አድሮም ፖለቲካዊ ቀውስ ሊፈጥርና ከፍተኛ ዋጋ ሊያስከፍል እንደሚችል ሊጤን ይገባዋል፡፡
ከላይ ለመግለፅ እንደተሞከረው በአዲስ አበባ ከተማ ዙሪያ ግለሰብ ዜጎች “ህገ-ወጥ” የሚባሉ ቤቶችን ለመሥራት ቦታውን ከገበሬዎች በውድ ዋጋ እንደገዙ ይታወቃል፡፡ ጥረው ግረው ባጠራቀሙት ገንዘብ ቦታውን ከገዙም በኋላ እንደገና ያላቸውን ጥሪት አሟጥጠው ጎጆ በመቀለስ ኑሯቸውን መግፋት ይጀምራሉ፡፡ በዚህ መንገድ ለአንገታቸው ማስገቢያ ጎጆ ሲያገኙ ቀሪው ሀሳብና/ጭንቀታቸው ልጆቻቸውን ማስተማርና “ከእጅ-ወደ አፍ” የሚሉትን የዕለት ቀለብ ማሟላት ይሆናል፡፡ መቼም በዚህ ዘመን ጥሮ/ተፍጨርጭሮ በየጊዜው እያሻቀበ የሚሄደውን የኑሮ ውድነት ተቋቁሞ መኖር ምን ያህል ፈታኝ እንደሆነ መገመት ይቻላል፡፡ በዚህ አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ በጭንቀት ተወጣጥሮ የሚኖርን ቤተሰብ ቤቱን አፍርሶ ሜዳ ላይ መበተን ምን ሊባል ይችላል? እንደምግብና መጠጥ ሁሉ የመጠለያ ጉዳይ ከሰው ልጅ መሠረታዊ ፍላጎቶች የሚመደብ መሆኑ የሚታወቅ ነው፡፡ ስለሆነም መንግሥት በሚችለው መንገድ ሁሉ ዜጎችን የቤት ባለቤት ማድረግ ሲገባው በራሳቸው ጥረት/ጥሪታቸውን አሟጥጠው የሠሩትን ቤት አፍርሶ ሜዳ ላይ መበተን ከሰብኣዊ መብት ባለፈ ሞራላዊ ጥያቄዎችን ሊያስነሳ የሚችል ነው፡፡
የታከለ ኡማ ፈተና፣
የታከለ ኡማን ፈተና ለመረዳት በእሱ ጫማ ውስጥ ሆኖ ማሰብ ያስፈልጋል፡፡ ትናንት የአዲስ አበባ ከተማ ማስተር ፕላንን በመቃወም ረገድ ግንባር ቀደም ተጠቃሽ ሰው ነው፡፡ ያኔ የከተማዋን መስፋፋት የተቃወመው ከአካባቢው አርሶ አደሮች መፈናቀል ጋር በተያያዘ ነው ተብሎ ይገመታል፡፡ ከዚህም ባለፈ የወያኔ ሥርዓት በተለይ መሬትን በመቀራመት ረገድ ሲያሳየው የነበረው ከልክ ያለፈ ስግብግብነትና ይሉኝታ ቢስነት የማንንም ሰው ትዕግስት ሊፈትንና ሊያስቆጣ እንደሚችልም መረሳት የለበትም፡፡ ትናንት ግን ዛሬ አይደለም፡፡ ዛሬ የወያኔ/ኢህአዴግ አገዛዝ መልሶ ማንሰራራት በማይችልበት ሁኔታ በሽንፈት ተዘርሮ ታከለ ኡማም የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ሆኗል፡፡ ስለሆነም የአዲስ አበባን ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ችግሮች መፍታት መቻል ታከለ ኡማ እንደከንቲባና/ፖለቲከኛ የሚፈተንበት ይሆናል፡፡
ታከለ ኡማ እንደከንቲባ በአዲስ አበባ የራሱን አሻራ ትቶ ማለፍ እንደሚፈልግ መገመት ይቻላል፡፡ በተግባርም በርካታ በጎ ተግባራትን ሲያከናውን ተመልክተናል፡፡ ታከለ ኡማ ከሚያደርገው በተጨማሪ በትህትና የታጀበና ጨዋነት የተሞላበት አነጋገሩና አስተሳሰቡ ሰብዕናውን ብቻ ሳይሆን ግብሩንም ጭምር ገላጭ ነው ማለት ይቻላል። ስለሆነም አንዳንድ ወገኖች በታከለ ኡማ ዙሪያ ያላቸውን አጉል ጥርጣሬ; አሉታዊ አመለካከትና መሠረተ-ቢስ አሉባልታ እንደወረደ ለመቀበል ያስቸግራል። ታከለ ኡማ የአዲስ አበባ ከተማ ም/ከንቲባ ሆኖ የተሾመበትን አግባብ ጥያቄ ውስጥ ማስገባትም አሁን ካለንበት የሽግግር ሂደት አንፃር ጭራ ከመሰንጠቅ ያለፈ ትርጉም የለውም፡፡ ይሁንና ታከለ ኡማ በተለይ የኦሮሞን ህዝብ ጥቅም የሚያቀነቅነው የኦህዴድ/ኦዴፓ አባል መሆኑ አይዘነጋም፡፡ ዛሬ ላለበት ቦታ የበቃውም በዚሁ የአስተሳሰብና የአደረጃጀት መስመር መሆኑም እሙን ነው፡፡
እንደ አዲስ አበባ ከንቲባ፣ የአዲስ አበባ ከተማን ህዝብ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ችግሮች/ፍላጎቶች መሠረት አድርጎ መሥራት ይጠበቅበታል፡፡ ይህን ሲያደርግ፣ በተለይ ከከተማው መስፋፋት ጋር በተያያዘ፣ ምናልባትም ትናንት ሲያራምደው ከነበረው አቋም ጋር በቀጥታ ሊያጋጩት የሚቻሉ ፈታኝ ሁኔታዎች (conflict of interest) ውስጥ ሊገባ እንደሚችል ይታሰባል፡፡ ሁኔታውን ይበልጥ ፈታኝ የሚያደርገው ደግሞ፣ ትናንት እነታከለ ወደ ሥልጣን የመጡበትን አጀንዳ ነጥቀውና እነሱን አውርደው ሊፈጠፍጧቸው ያሰፈሰፉ ኃይሎች መኖራቸው ነው፡፡ ታከለ በዚህ ፈታኝ ሁኔታ ውስጥ እነዚህን የሚጋጩ ፍላጎቶች እንዴት (tactically) አስታርቆና አጣጥሞ ማለፍና ብቃቱን ማረጋገጥ እንደሚችል አብረን የምናዬው ይሆናል፡፡
እንደመንግሥት ባለሥልጣን፣ ታከለ ኡማ ህግና ሥርዓትን ማስከበር ይኖርበታል፡፡ ህግና ደንብን በሚተላለፉ ወገኖች ላይም ተገቢው ህጋዊ እርምጃ እንዲወሰድ ማድረግ ይጠበቅበታል፡፡ በዚህ ረገድ፣ በህገ-ወጥ መንገድ የተገነቡና በተለምዶ “ሰነድ አልባ” የሚባሉ ቤቶችን ማፍረስ ከህግ አንፃር ትክክለኛ እርምጃ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል፡፡ ከዜጎች መሠራታዊ መብትና ከሞራል አንፃር ግን የድሆችን ቤት አፍርሶ ቤተሰብን ሜዳ ላይ መበተን አነጋጋሪና ቁጣን ሊቀሰቅስ የሚችል ነው፡፡
ታከለ ኡማ እነዚህ ቤቶች እንዲፈርሱ በቀጥታ ትዕዛዝ ላይሰጥ ይችላል፡፡ ምናልባትም በማወቅም ይሁን ባለማወቅ የለውጥ ሂደቱን ለማደናቀፍ የሚፈልጉ ኃይሎች መሣሪያ የሆኑ ወገኖችም ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ በተለይ አሁን ባለንበት የሽግግር ጊዜ በመንግሥት የሚወሰዱ እርምጃዎች የሚኖራቸውን ፖለቲካዊ አንደምታና ሊፈጥሩ የሚችሉትን ክፍተት በሚገባ ማጤን ያስፈልጋል፡፡ ከዚህ አንፃር በህገ-ወጥ መንገድ የተገነቡ ቤቶችን ለማፍረስ ግምት ውስጥ ያለባቸው ሁኔታዎች አሉ፡፡
ሲጀመር ዜጎች በህጋዊ መንገድ የቤት መሥሪያ ቦታ የሚያገኙበት አማራጭ ቢኖር ኖሮ ገንዘባቸውን አውጥተው ህጋዊነቱ ያልተረጋገጠ ቦታ የሚገዙበት፣ በድሀ አቅማቸው የሚገነቡበትና በሥጋት (ከዛሬ-ነገ ሊፈርስ ይችላል በሚል) የሚኖሩበት ምክንያት አይኖርም፡፡ ሲቀጥል ድርጊቱ ህገ-ወጥ ነው ከተባለ፣ ግንባታ ከመካሄዱ በፊት ማስቆምና መከልከል እየተቻለ፣ የግለሰብ ዜጎች ብቻ ሳይሆን የሀገር ሀብት የፈሰሰበትን ቤት/ንብረት ማፍረስ ማንንም የሚያሳምን አይደለም፡፡ ይህም ሆኖ፣ “ላለፈ ክረምት ቤት አይሠራም” እንዲሉ ቤታቸው የፈረሰባቸውና በአዲስ አበባ ከተማ ዙሪያ ሜዳ ላይ የተበተኑ ቤተሰቦች ዕጣ-ፈንታ ምን ይሆናል?
ታከለ ኡማ የሚፈተንበት ይሆናል፡፡
Filed in: Amharic