>
5:26 pm - Saturday September 17, 6512

ለአታላይ ስለማያመቹት የኢትዮጵያ ወሰን ፈጣሪ ወንዞችና ስለክልል የለሹ አማርኛ ተናጋሪ ጥቂት ነጥቦች (ከኤፍሬም የማነብርሐን (J.S.D.))

ለአታላይ ስለማያመቹት የኢትዮጵያ ወሰን ፈጣሪ ወንዞችና ስለክልል የለሹ አማርኛ ተናጋሪ ጥቂት ነጥቦች

 

ከኤፍሬም የማነብርሐን  (J.S.D.)

 

ባለፉት 27 ዓመታት፣ ማለትም ኢትዮጵያን ከተቆጣጠረበት 1983 ዓመት ምህረት ጀምሮ፣ ወያኔ ኢትዮጵያን በትግራይ የበላይነት ቢያንስ ለመቶ ዓመታት ለመምራት የሚያስችለውን የወሰን አከላለልና የሕዝቦቿን የዜግነት መብት ለራሱ በሚያመቸው አኳኅን ብዛት ያለው ሕዝብ ያለተወከለበትን ሕገመንግስት ነድፎ፣ በሕዝቦቿ ላይ ከፍተኛ ሰቆቃ በመፈጸም ይህንን የክፋትና የጥፋት ዓላማ ለመተግበር ላይ ታች ሲል ከረመ።

ለዚህም ዓላማ መሳካት የመጀመሪያ ዋና ኢላማ ያደረገው አገሪቱ በመጀመሪያ የተቋቋመችባቸው በዋና መሰረት በመልከዓ ምድራዊ የወንዞችን አወራርድ፣ የሕዝብን ባሕልና፣ የሕዝብን ስነልቦናዊ መስፈርቶችን ባላገናዘብ መልኩ፤ የራሱን ተስፋፊነትና፣ አማራና አማርኛ ተናጋሪውን ሕብረተሰብ በሚጎዳ አኳኃን አስልቶ፣ በማንኛውም መስፈርት ተአማኒነት በሌለው በፖለቲካ ውሳኔ ላይ የተመሠረተ የአገር ውስጥ ወሰን አከላልን በጉልበት ላለፉት 27 ዓመታት ሲተገብርና ሲያስተገብር መክረሙ ገሃድ ሐቅ ነው።  በተለይ ከጥንት ጀምሮ ኢትዮጵያን ከኛ ሌላ ማነም ሊገዛት አይገባም፣ ከአጼ ዮሐንስ አጼ ሚኒሊክ ስለነጠቁን ነው እንጂ የሚለውን በሐሰት ላይ የተመሠረተ ትርክት ለረጅም ዓመታት ሲያብላላ የሰነበተው የትግራይ ጽንፈኛ ኤሊት፣ ዕድልና በለስ ቀንቶት በሸዋ የሚኒሊክን ግቢ ሲቆጣጠር፣ የሌት ተቅን ስሌቱ ይሕንን የረጅም ዓመታት የትግራይ ኤሊትን ምኞት እንዴት እንደሚተግብረው ነበር።

ለዚህም ዓላማው በዋናነት ያነጣጠረው፣ የአማራን ወሰን እንዴት መክበብና በተቻለ መጠን ለማፈን የሚያስችል የወሰን ቅርጽ መፍጥርና፣ ከዝንተ ዓለም ጀምሮ የአማራ ቦታዎች የነበሩትን በጉልበት በመያዝና የአማራ ተወላጆችን በመግደል፣ በማሰር፣ ከአገር በማባረር፤ እዚያው የቀሩትንም እንዳይወልዱ በማምከን፣ የትግራይ ነጋዴዎችን አግባብ ባልሆነ የኢኮኖሚ ድጋፍ ፣ የአማራ ነጋዴዎችን ግን በኢኮኖሚ በማዳከም ሕዝቡ ስነልቦናው ወደ ትግራይ ኢንዲያዘነቢል በማድረግ፤ የአማራ ዘፈንና ባሕልን በማዳከምና የትግራይ ባሕልና ዘፈንን በከፍትኛ አድልዎ በማበረታት፣ ትግራይን በሕዝብ ቁጥሩና በቆዳ ሥፋቱ ከፍ ማድረግን አይነተኛ እስትራተጂው አድርጎ ላለፉት 27 ዓመታት ላይ ታች ሲል መክረሙ ሁሉም የሚያውቀው ነው።

የወያኔ መሠረታዊ ችግሩ፣ “ከኔ በላይ ብልጥ ላሳር” እንዳለው የሰፈር አውደልዳይ ሞኝ ሁሉ ነገር በገሃድ የሚታይበት መሆኑን አለመገንዘቡ ወይም “የት ይደርሳል ተወው” የሚል አባዜ ውስጥ ሁሌም የተነከረ መሆኑ ነው። በአማራው ላይ ከበባ እያደረግበት መሰንበቱ ደጋግሞ የተነገር ቢሆንም፣ የዚህ ሴራ ጥልቀት ግን በቅርቡ የቤኒ ሻንጉሉ የቀድሞ ባለሥልጣን “ወልቃይትም እኮ የቤኒ ሻንጉል ክልል ነው ተብለን ነበር” ያሉትን ላያክል ይችል ይሆናል። መቼም ወልቃይትን ለቤኒ ሻንጉል ያሏት እንኳን ገና መጀመሪያው ላይ ለኛ ካለተሳካለን አማራን አባልተን እንሄዳታለን ከሚል እኩይ መንፈስ የተነሳ ይሆናል እንጂ፣ በኋላ ጊዜውም እየቆየ፣ የትግራይም የወልቃይት ፍቅርና ይዞታ ጥልቀቱ በጨመረባቸው የሗለኞቹ ዓመታት ላይ እነዲፈጸም ያደርጉታል ብሎ ለመገመት ያስቸግራል።

ያም ሆነ ይህ፣ ግራም ነፈሰ ቀኝ፣ የቀድሞዎቹ የኢትዮጵያ መሪዎች ከጀርባው ቅንነትን በተላበሰ መርሆ የነደፉትን የአገር ውስጥ የወሰን አከላለል፣ ወያኔ ቅንነት ከጎደለውና የወያኔን ተስፋፊነት በሥራ ለመተርጎም ከቀረጸው የኢትዮጵያ የውስጥ ወሰን አከላለል በማስተያየት የወያኔን እኩይ ዓላማ በቀላሉ መመልከት ይቻላል።  ከረጅም ጊዜ ጀምሮ የተጻፉትን የታሪክ መዛግብትም ሆነ እስከ ደርግ ዘመነ መንግስት ድረስ የቅርብ ትዝታ የሆነውን የበጌምድርና ሰሜን ወሰን እንኳን ወደጎን ብንተወው፣ የወልቃይት ግዛት በምንም ተዓምር የትግራይ ሊሆን እንደማይችል የኢትዮጵያን መልከዓ ምድርና የወንዝ ድንበሮችን በማየት የቱ የማን ወሰን እንድሆነ ምመልክት አያዳግትም። የትግራይ ሕዝብ እርገጥ የትም መኖር መብቱ ነው።  ወያኔ ግን ያለ ነዋሪው በነጻ ከተሰጠ ፈቃድ ውጭ፣ በማስገደድ ወደራሱ የማድረግ ሥልጣን የለውም። ይህ ግዛት አስፋፊነት ነው።

ከላይ ጣልያን ከመረብ ምላሽ እስከ ባድመ ድረስ ከዚያ ግን ወደ ደቡብ በቀጥታ ወርዶ ተከዜን ወሰኑ በማድረግና ለም የሆነውን ምዕራብ ትግራይ ወደራሱ በመቀላቀል አሁን ለተፈጠረው የትግራይ የለም መሬት ጥማት መነሻውን ፈጠረ። ይሕም ማለት ጣልያን ከላይ መጥቶ ቅኝ ግዛት ባይተክል የአሁኑ የቤገምድር ታሪካዊ ግዛት የሆነውን ወልቃይትን የመመኝት ሀሳብ ከመጀመርያም ላይፈጠር ይችል ነበር ማለት ነው። ተከዜ በምዕራቡ ኢትዮጵያን ከኤርትራ በመለየት የኢትዮጵያና የኤርትራ ወሰን መለያ መሆኑ አሁንም ያለ ነው።  ከመረብ በላይና መረብ በታች ያለው ሕዝብ ጣሊያን ባይለየው ኖሮ ተከዜን ይዞ ትግራይን ጨምሮ በአብላጭ የትግርኛ ቋንቋ ትናጋሪ ሕዝብ ነበር። ይህም ማለት ተከዜ ተፈጥሮአዊ የትግርኛና አማርኛ ተናጋሪ መለያ ወንዝ ነበር ማለት ነው። ምናልባትም ተከዜ ባይኖር ኖሮ አማርኛና ትግርኛ የሚለው ልዩነት መጀመሪያም አይፈጠርም ነበር።

በጋርዮሽ ወይም ከዝያ በኋላ በመጡት ዘመናት አማራውና ትግራዩ ቋንቋው ለምን እንደተለያየ ከተከዜ የበለጠ የምክንያት ማስርጃ ማቅረብ ያዳገታል።  ተከዜ አንድ የሚታውቅበት መለያ አለው። የተከዜ ወንዝ የፈጠረው ገደል (gorge/canyon) በጥልቀቱ በአፍሪቃ ወደር የማይገኝለት ሲሆን፣ በዓለምም ደርጃ ቢሆን አሉ ከሚባሉት የገደል ጥልቀቶች ውስጥ የሚካተትና ባንዳንድ ቦታዎች ከሁለት ሺህ ሜትር በላይ የገደል ጥልቀት ሊፈጥር የቻለ ወንዝ ነው። በዚህም የተከዜ አስቸጋሪነት ሳብያ በዘመናቱ ተከዜን ወደደቡብ ያቋረጡት ሕዝቦች እነደፈለጉት የሚያቋርጡት ባለመሆኑ የተነሳ፣ አማሪግና ተናጋሪነት ተፈጥሮ ሕዝቡ ቀስ በቀስ ከግእዝ ተናጋሪ ከተከዜ በላይ ከቀሩት ወንድሞቻቸው እየተራራቁና የቋንቋ ልዩነት እያዳበሩ መምጣታችውን መገመት ብዙም አያስችግርም። ክረምቱ በመጣ ወንዙም በሞላ ሳቢያ ቁልቁለቱን ወርዶ ገደሉን ተሻግሮና አቀበቱን ወጥቶ መግናኘት እየቸገረ፣ አንድ ቋንቋ ይናገሩ የነበሩ ሕዝቦች ቀስ በቀስ ወደ ሁለት ቋንቋ መከፋፈላቸውን እየተራራቁ መምጣታችውን ለመገመት የኑክሌር ሳይንቲስት መሆንን አያስፈልገውም።

ተከዜ የአማራና የትግራይ ሕዝብ ዋና የስብዕናችውና የመሬት ወሰናቸው መለያ መሰረት እነደመሆኑ፣ ይህ በወንዝ ላይ የተመሰረተ መሰረታዊ፣ ተፈጥሯዊና መልክአ ምድራዊ መለያ ለሌሎቹም የኢትዮጵያ ከፍላተ ሃገራት የወሰን ማካለያ መሆኑ የኢትዮጵያን የወንዝ አወራረድ መልክዓ ምድር በማየት ብቻ መገመት ይቻላል። የኢትዮጵያን የውስጥ ወሰን ክልል የወሰኑት ቅድም አያቶቻችን እነደወያኔ የፖለቲካና የሕብረተሰብን ልበሰባዊ ስብዕና የመቀየር (social engineering) አጀንዳ አንግበው ስላልመጡ የአገሪቱን ወሰን መለየት ላይ ወያኔ ጫካ ከገባ ያጠፋዊን ጊዜ የእንቅልፍ ጊዜአቸውን አላጠፉም።  ከላይ በጌምድርን ከትግራይ (የኤርትራን ተጋሩዎች ጨምሮ) ለመለየት ተከዜን እንደተጠቀሙ ሁሉ፣ በጌምድርን ከጎጃም ለመለየት የአባይን አካሄድ ብቻ ነው የተጠቀሙት። የዘመነ መሳፍንት ንጉሶችም እንዲሁ ወንዝ ዋና የወሰን መለያ ስለነበር፣ ትግራይን ከበጌምድር፤ በጌምድርን ከጎጃም፤ ሸዋንም ከጎጃም ለመለየት ከተከዜና ከዓባይ ወንዝ ያለፈ የመለከዓ ምድር ጥናት ተመራማሪ አላስፈለጋቸውም። የወያኔ “ጠቢባን” ያለፉትን 27 ዓመታት ከናዚ ጀርመን በሚወዳደር ደረጃ፤ የዘር ማጥፋትና ማጽዳት ሥራቸውን ሲያካሂዱ፣ በዚህ ድርጊታችው ግን እግዚአብሔር በተፈጥሮ ያሰመረውን የወሰን ክልል ሊያዛቡት እነደማይችሉና ሁሌም እንደሚያጋልጣቸው ቢገነዘቡ ኖሮ፣ አሁን ላለንበት አሳዛኝ ክስተት አገሪቱን አያጋልጧትም፤ አነሱም እንዲህ በግላጭ ለሰሩት አስከፊ የዘር ማጽዳት ወንጀል አይጋለጡም ነበር። ነገር ግን “ከኛ በላይ ላሳር” የሚለው ጀብደኝነታችውን የት ያደርሱት።

የቀድሞ የኢትዮጵያ ወሰን አካላዮች በዚህ ተፈጥሮ ኢትዮጵያን በለገሰችው የወሰን ማካለል ጉዳይ በትግሬ፣ ጎንደር፣ ጎጃም፤ አና ሸዋም አላበቁም።  ጎጃምን ከወለጋ ለመለየት ዞሮ በሚጠመጠመው አባይ ወንዝ፤ ወለጋን ከኢሉአባቡር ለመለየት የባሮን ወንዝ በመጠቀም፤ ኢሉአባቡርን ከከፋ ለመለየት የጊቤን ወንዝ በመጠቀም፤ ከፋን ከገሙጎፋ ለመለየት የኦሞን ወንዝ በመጠቀም፣ ገሙጎፋን ከሲዳሞ ለመለየት የተለያዩ ሐይቆችን መለክዓ ምድር በመጠቀም፤ ሲዳሞን ከባሌ ለመለየት ገናሌን ወንዝ በመጠቅም፤ ባሌን ከሐረርጌ ለመለየት የዋቤ ሸበሌን ወንዝ በመጠቀም፤ መሃል ላይ ቁጭ ያለችው ሸዋንም ከደቡብ አዋሳኝ ክፍላት ሃገራት ለመለየት ጥርትም ባለ አኳኅን ባይሆንም አዋሽና ዋቤ ሸበሌን በመጠቀም እግዚአብሄር ለሚወዳቸው ሕዝቦቿ ያለግጭት መኖሪያ ትሆን ያስችላት ዘንድ ወንዞቿን አሳምሮ ሰርቶላት የቀድሞ አባቶቻችንም ቅንነት በተሞላው መንፈስ ለማንም አድልዎ በማይኖረው አኳኅን የወሰን ክልሎች አዘጋጅተውላት አልፈው ነበር።  

አንዳንድ የመለስ ምልምሎች የቀድሞ መሪዎች የኦሮሞን፤ የደቡብን ሕዝብ በሚጎዳ መልኩ ነው ወሰን ያካለሉት የሚል ሚዛን የማይደፋ ክርክር ያነሱ ይሆናል።  ነገር ግን ሰሞኑን የወለጋው ኦነግ የሚያሳየው ባህርይ፤ የአርሲ አክራሪዎች የሚያሳዩት ጸንፈኝነት፤ የሸዋ ኦሮሞ የመገንጠል ጥያቄ የማይዋጥላችሀው መሆኑና ከወንድም አማራ ጋር በእኩልነት አገር ለመምራት የሚያሳዩት ፈቅደኝነትና እንዲሁም አማራ አንድ ሳይሆን እግዜር ባዘጋጀለት መልክዓ ምድር ከጥንትም ጎንደር፣ ጎጃም፣ ሸዋ፣ ወሎ ሁኖ ይኖር የነበረና ይህንን እውነታ ለመቀየር የቀድሞ ወሰን አካላዮቹ በጭንቅላታችው አለማስገባታችው የሚያሳዩት ነገር ቢኖር፣ አንድን ብሔር ለይቶ ለመጥቀምም ሆነ ለመጉዳት በፍጹም ያላሰቡት ጉዳይ መሆኑን ነው። እነደወያኔ ሕብረተሰቡን ባዘጋጁለት ቅርጽ እንዲገባ የማድረግ ወንጀል (social engineering) እንዳልፈጸሙ ነው የሚያሳየው።

ሁለተኛው ዋና ዒላማ ደግሞ በተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍላተ ሀገራት ታሪክ ባስከተለው የረጅም ዘመን እንቅስቃሴ፣ በንግድ ልውውጥና፣ በከተማ አብሮ መኖር ካስከተለው ከተለያዩ ጎሳዎች የመዋለድ ዕጣ ፈንታ ሳቢያ በአንድ መግባቢያ ቋንቋ መናገር የተገደደውን አማርኛ ተናጋሪ ማኅበረ ሰብ ክልል አጣሽ በማድረግ በሄዱበት ሁሉ መጤ እንዲባሉ የሚያስችሉ ክልሎችን በመፍጠርና ባሉባቸው ከተሞች ሁሉ የመምርጥ፣ የመመረጥ፤ ሲወለዱ በሚናገሩት በአማርኛ ቋንቋ እንዳይማሩ፣ እንዳይዳኙ፤ በአጠቃላይም በአካባቢያቸውና በአገራቸው የፖለቲካ ጉዳይ ሙሉ በሙሉ እንዳይሳተፉ በማድረግ ዋነኛውን ሴራ በስራ አዋለ።  ለዚሕም ማስፈጸሚያ በሕገ መንግስቱ ውስጥ አማርኛ ተናጋሪውን በተለያየ ቦታ የሚኖረውንና ከአማራ ክልል ውጭ እስከ 14 ሚሊዮን የሚገመተውን አማርኛ ተናጋሪ የወያኔው ሕገ መንግስት ዕውቅና ነስቶት በየትም ቦታ ይህንን ሰፊ ሕዝብ ከጥቅም ውጭ አድርጎት ይገኛል።

ለዚህም እኩይ ዓላማና ሥራ ምሳሌ የሚሆኑት (1) አዲስ አበባን ሲያመቸው የፌደራል መንግስቱ ዋና ከተማ ሲያደርግ፤ የከተማው ሕዝብም በ1997 በምርጫ እንዳልመረጠው ሲያውቅ፣ የአዲስ አበባን ሕዝብ ምክር ሳይጠይቅ ፣ የኦሮሞ ዋና ከተማን ከናዝሬት/አዳማ በማንሳት ወደ አዲስ አበባ በማምጣት ኦሮሞዎች ልዩ ጥቅም መብት በከተማዋ ያላቸው መሆኑን በመንገር (በመውደቂያው ዋዜማም ይህንኑ ጥረት ሲያደርግ እንደነበረና አሻጥሩ የገባቸው የኦሮሞ የፓርላማ አባላት ቀልድህን አቁም ማለታቸው የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው)፣ አዲስ አበቤዎች በመጤነት መንፈስ እንዲታመሱ ማድረጉ፤ (2) ሐረርና ድሬደዋን አብዛኛው ነዋሪ አማርኛ ተናጋሪ ቢሆንም፣ የነዚህን ከተሞች አማርኛ ተናጋሪ ነዋሪዎችን ጥቅም በሚጎዳ አኳሗን ፍርደገምድላዊ የመምረጥና መመረጥ መለኪያዎችን በመጠቀም ከፖለቲካ ተሳትፎ ማስወገድ አለያም መሠረታዊ መብታቸውን በሚጻረር መልኩ ድምጻቸውን ጥቅም አልባ ማድረግ፣ እና (3) ናዝሬት/አዳማ፣ ደብረ ዘይት/ቢሾፍቱ፣ ጂማ፣ መቱ፣ ጎሬ፣ ወዘተ የሚኖሩ አማርኛ ተናጋሪዎችን በሚኖሩባቸው ከተሞች የፖለቲካ ተሳትፏቸውን የመምረጥ መመረጥ መብታችውን በክልል ሕገመንግስት በማገድ ከጥቅም ውጭ ማድረግ ናቸው። ይህ ለአዲስ አበቤና በተለያዩ ከትሞች በአብላጭ ቁጥር የሚኖሩ የተለያዩ ነዋሪዎች መብት በማንኛውም የሰለጥነ አገር ለከተማ ነዋሪው የሚሰጥ መሰረታዊ መብትና የሚኖርበትን አካባቢ የፖለቲካ እንድምታም እንደማንኛውም ነዋሪ በዲሞችራሲያዊ መርሆ  የሚወስንበት እንጂ ጥያቀው የአማርኛ ተናጋሪው የተስፋፊነት ፍላጎት አይደለም። የከተሜው ነዋሪ አማርኛ ከመናገሩ በቀር ከየገጠሩ የተሰባሰቡ የተለያየ ጎሳ ውጤት የሆኑ ሕዝቦች ውጤት አንጂ፣ ወያኔ ወልቃይት ላይ አንደሚያረገው የጉልበት ሰፋሪዎች ውጤት አይደለም። በከተማ የሚኖረው ሰው ከአንድ ዘር ወይም ጎሳ ነኝ የሚል ማግኝት አይቻልም በአጋጣሚ ካልተገኘ በቀር። ሁሉም የዚያች አገር የተለያዩ ጎሳዎች ውጤት ነው። እስቲ አስቡት የምዕራብ ወይም የምስራቅ ወይ የደቡብ አዲስ አበባን አይቶ የማያውቅ ሰው፣ አዲስ አበቤዎችን መጤ ናችሁ ውጡልኝ ብሎ ለመጠየቅ ሲደፍር።

በወቅቱ የአማራው ክልል ወኪልነቱን የያዙት በረከት ስሞኦንን  የመሰሉ መሪዎች ቀድሞም በወያኔ ሥራ አስፈጻሚነታቸው ሳቢያ ይህንን ጉዳይ ሊያነሱት ቀርቶ ያሰቡትም አይመስልም ነበር።  ካለፉት 10 ወራት ጀምሮ በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ፤ አቶ ለማ፣ አቶ ገዱና፤ አቶ ደመቀ መሪነት በኢትዮጵያ ውስጥ ወያኔ የገነባውን የጥላቻ ግድግዳ ገርስሶ በቦታው በኢትዮጵያውያን መግባባት ላይ የተመሰረተች አገር ለመግንባት ከፍተኛ ርብርቦሽ እየተካሄደ ይገኛል። መቼም እስካሁን ባየነው ሙሴያዊ ወሳኝነትና ሰለሞናው እውቀትን በአንድ ላይ ያላበሳቸው መሪ አግኝተናል።  የእግዚአብሔር/አላህ እርዳታ አይለያችው።

ይህንን በተለያዩ የኢትዮጵያ ቦታዎች ክጥንት አገር ግንባታ ጀምሮ በሰፈራ፣ የኢኮኖሚና ንግድ ስበት፤ አንዲሁም በአብዛኛው የጎሳዎች በአንድነት በመኖር ሳብያ በተፈጠረ መዋለድ የተዋቀረውን በቁጥሩ ቀላል ያልሆነውን የአማርኛ ተናጋሪ ሕዝብ አዲሶቹ መሪዎች እንዴት ሊያሰተዳድሩት እያሰቡ ነው?  በቅርቡ የአማራው ክልል መሪ አቶ ገዱ በአትላንታ ለተሰበሰበ የኢትዮጵያ አሜሪካዊ ዜጋ የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ በምን ዘዴ ሊፈቱት እንዳሰቡ ግልጽ ማድረጉንና በይፋ ማውጣቱን የፈሩ በሚያስመስል መልኩ መልሰውታል። አቶ ገዱ እንዳሉት እየተነጋገሩ ያሉበት ዘዴ፣ ለምሳሌ “የኦሮሞ ክልል የኔ ነው ብሎ በኦሮሞ ክልል የሚኖር አማራ . . . የኦሮሞ ክልል ነዋሪ ነው። … ከኦሮሞ ሕብረተሰብ ተለይቶ የሚታይበት ሁኔታ in principle  መኖር የለበትም።” ነገርግን በዚሁ የኦሮሞ ክልል ውስጥ አንዱን ለይቶ ሌላውን ተጠቃሚ የሚያደርግ ሁኔታ እንዳይፈጠር፣ “አማራ በብዛት በሚኖርባቸው አካባቢዎች በሁሉም ቦታ ሕጻናት በሚፈልጉት ቋንቋ የመማር መብታቸው የሚከበርበት ሁኔታ፤ እንደነዋሪ በአስተዳደሩ በቀበሌ በወረዳ ውክልና የሚያገኙበት ሁኔታ” እንዲፈጠርና በተጠናከረ መንገድ ይኸው ተግባራዊ እንዲሆን ራሱን የቻለ አደረጃጀት ለመፍጠር በየክልሎቹ ጥሩ መግባባት እንዳለ አስረድተዋል።

ይህ የሚያሳየው የአማርኛ ተናጋሪ የወደፊት ዕጣ ፈንታ ገና ያልተወሰነ መሆኑንና ገና ብዙ ውጣ ውረድ ያለው መሆኑን ነው። በተለይ አማርኛ ተናጋሪ በጣም በከፍተኛ ፐርሰንቴጅ የሚኖርባቸው አዲስ አበባ፣ አዋሳ፣ ናዝሬት፣ ደብረ ዘይት፣ ምናልባትም ሐረርና፣ ድሬደዋ የፌደራሉ አስተዳደር ውስጥ ተካለው የፌደራል ግዛት መሆን ይገባቸው አይገባቸው፤ እንዲሁም አማርኛ ባብላጭ በሚነገርባቸው በተለይ በደቡብ ያሉ አንደ ሻሸመኔ፣ ጂማ፣ አሰላ የመሰሉ ከተሞች በቻርተር ሊተዳደሩ የሚችሉበት ጥናት እየተካሄደ እንዳለ አቶ ገዱ ምንም አልጠቆሙም። ይህ ሁኔታ የአማርኛ ተናጋሪውን ልብ አሁን ድረስ ሰቅሎት የሚገኝ ሲሆን በትክክል ካልተፈታ፣ የዚህ ሕዝብ አባላት በተለይም ብዛት ያለው የውጭ አገር ነዋሪ ለጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ መንግስት ራስ ምታት የሚፈጥርበትና ምናልባትም በውጭ ያለውን ደጋፍ ሊያሳጣቸው የሚያስችል ጉዳይ መሆኑን ተገንዝበው አሰፈላጊውን ትኩረት በጉዳዩ ላይ ሊያደርጉበት እንደሚገባ በአጽንኦት ማሳሰብ ያሰፍልጋል።

አምላክ ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ይባርክ!! ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!!

ኤፍሬም የማነብርሐን

ዋሺንግቶን ፣ ዲሲ

Filed in: Amharic