>
7:33 am - Tuesday December 6, 2022

ኦሮሚያ አሁን ያለበት ሁኔታ ኦ.ፌ.ኮን ያሳስባል!!! (ከኦሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግሬስ የተሰጠ መግለጫ)

ኦሮሚያ አሁን ያለበት ሁኔታ ኦ.ፌ.ኮን ያሳስባል!!!
 ከኦሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግሬስ የተሰጠ መግለጫ
 በአሁኑ ጊዜ በኦሮሚያ ክልል የተለያዩ ቦታዎች በመከላከያ ሠራዊትና በተለያዩ ታጣቂ ኃይሎች መካከል እየተካሄደ ያለዉ ግጭት ሕዝቡን እያሸበረ እንደሚገኝ ከሚታየዉና ከሚሰማዉ ድርጊት ለመረዳት ችለናል፡፡ ምሳሌ መጥቀስ ቢያስፈልግ በቅርቡ በምዕራብ ጉጂ ዞን ፊንጫኣ አከባቢ በመንግስት ኃይሎች ነዉ ተብሎ በሚጠረጠር አካል በተተኮሰ ከባድ መሳሪያ የ13 ሰዎች ሕይወት ጠፍቷል፡፡ በተጨማሪም የሌሎች ክልሎች ታጣቂ ኃይሎች ወደ ኦሮሚያ ክልል ወለጋ፣ ቦረና፣ ጉጂና ሐረርጌ ዞኖች ዉስጥ በመግባት የኦሮሞን ዜጎች እየገደሉ፣ እየዘረፉና እያፈናቀሉ እንደሚገኙ የተለያዩ አካላትን ጨምሮ መንግስትም ያመነዉ ጉዳይ ነዉ፡፡ የኦሮሞ ሕዝብ በከፍተኛ መስዋዕትነት ያስመዘገበዉን ድል ለመጠበቅም ሆነ ፍሬዉን ለማጣጣም አለመቻል ብቻ ሳይሆን ወደ ሚቀጥለዉ የልማትና ዕድገት ትግል አቅጣጫ ለመሸጋገር ተደናቅፎ ለሌላ ዙር ለቅሶና ድህነት መጋለጡ በእጅጉ ይሰማናል፡፡ በተለይም በምዕራብ ኦሮሚያ ወለጋ ዞኖችና በደቡብ ኦሮሚያ በጉጂና ቦረና ዞኖች ያጋጠሙ ችግሮችና የተፈጸሙ ድርጊቶች አሁንም ሕዝባችን ሌላ መስዋዕትነት እንዲከፍል የሚጋበዝና የማህበረ ኤኮኖሚያዊ ብክነትን ሊያመጡብን የሚችሉ መሆናቸዉን እናምናለን፡፡ ከዚህ በላይ የተዘረዘሩት ችግሮች እንዳይቀጥሉና ወደባሰ ችግርም እንዳንገባ የኦሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግሬስ የሚከተሉት ዕርምጃዎች እንዲወሰዱ ጥሪ ያደርጋል፡፡
 1. መንግስትና የኦሮሞ ነፃነት ግንባር በመካከላቸዉ ያለዉን አለመግባባት በአስቸኳይ ፈትተዉ በሕዝቡ ዉስጥ ተሰራጭተዉ የሚገኙ የመከላከያ ሠራዊት አባላትንና ታጣቂ ኃይሎችን ከሕዝቡ መሀከል እንድስቡ አጥብቆ ይጠይቃል፡፡ ሁለቱ አካላት ያደረጉት ስምምነት ለሕዝብ ይፋ እንዲሆንና እንዲተገበር እናሳስባለን፡፡
 2. የፌዴራሉ መንግስት ከሌሎች ክልሎች ወደ ኦሮሚያ በመግባት ንጹኃን ዜጎችን እየገደሉ፣ እየዘረፉና እያፈናቀሉ የቆዩና ያሉትን ታጣቂዎች እንዲከላከል አጥብቀን እንጠይቃለን፡፡
3. የኢትዮጵያ ማህበረሰቦችን፣ የሃይማኖት ተቋማትን፣ ያገር ሽማግሌዎችንና አባገዳዎችን የምንጠይቀዉ በሕዝቡ መሀከል በመሰራጨት ሕዝቡን እያሸበሩ የሚገኙ ኃይላት ላይ ትኩረት አድርገዉ እንዲሰሩና ለተፈጠሩ ችግሮች የመፍትኼና የእርቅ አካል እንዲሆኑ እንጠይቃለን፡፡
 4. የፌዴራሉና የኦሮሚያ ክልል መንግስታት እንዲሁም የአገር ዉስጥና የዉጭ አገር ማህበረሰብ ሁሉ ለተፈናቀሉትና ለተዘረፉት ዜጎች ዕርዳታ በማድረግ ተመልሰዉ እንዲቋቋሙ እንዲያደርጉ በተፈናቀሉ ዜጎች ስም እንጠይቃለን፡፡
5. የኦሮሞ ሕዝብ ወጣት ለማንም ቡድን ሳይወግን ከሕዝቡ ጎን በመቆም ሙሰኞችንና መልካም አስተዳደር አጉዳዮችን እየታገሉ በብዙ መስዋዕትነት የተገኘዉን አንፃራዊ መሻሻል ማስቀጠል የሚቻልበትን ሁኔታ እንዲያመቻቹ ጥሪ እናደርጋለን፡፡
 6. የኢትዮጵያ መንግስትም ከዚህ በኋላ ሕዝብን በኃይል ለመግዛት መሞከር የዴሞክራሲ ተቃርኖ መሆኑን አዉቆና ገዥዉ ፓርቲም የአገሪቱን ችግር ብቻዉን መፍታት እንደማይችል በመገንዘብ በሥልጣን ላይ ያለን ፓርቲ ጨምሮ የሚመለከታቸዉ ዋና ዋና አካላት ሁሉ የሚሳተፉበት ብሔራዊ የአንድነት መንግስት እንዲቋቋም ደግመን እንጠይቃለን፡፡
 የኦሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግሬስ ፊንፊኔ፣ ታህሳስ 23/2011
Filed in: Amharic