>

“ሞቅ ሞቅ በየት ዞረሽ መጣሽ!” ኤርሚያስ ለገሰ   ( ከዋሽንግተን ዲሲ)

“ሞቅ ሞቅ በየት ዞረሽ መጣሽ!”
ኤርሚያስ ለገሰ 
 ( ከዋሽንግተን ዲሲ)
 መንደርደሪያ
ከብዙ ጉትጐታ በኃላ የቀድሞው ኮሙዩኒኬሽን ጽህፈት ቤት ፈርሶ በምትኩ የፕሬስ ሴክሬተሪያት ተቋቁሟል። እርምጃው ቢዘገይም ይበል የሚያስብል ነው።በዛኑ ቀን የሴክሬተሪያቱ የበላይ ሹማምንት በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት መግለጫ ሰጥተዋል። ኃላፊዎቹ ከፕሬስ አባላትም ጋር ትውውቅ አድርገዋል። ይሄም ጥሩ ጅማሮ ነው። ሆድና ጀርባ ሆነው ለቆዩት የመንግስት አካላት እና የሚዲያ ተቋማት በመርህ ላይ የተመሰረተ ግንኙነት ለመፍጠር እድል ይፈጥራል።
በሌላ በኩል የዛሬውን ክስተት እንደ አንድ የቅርብ ተመልካች ስመለከተው በርካታ ያልተመለሱ ጥያቄዎች በፊቴ ተደቀኑ። በተለይ የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ “ እርካብና መንበር” አንብቤ ስለ ጋዜጠኝነት ያላቸውን አመለካከት ከተገነዘብኩ በኃላ እርምጃው ከቀድሞው “አልሸሹም ዞር አሉ!” እንዳይሆን ከፍተኛ ስጋት አደረብኝ። የጋዜጠኝነት የወደፊቱን ወርቃማ ዘመን በእርካብና መንበር ውስጥ ተሽለኩልኬ በማለፍ መሳካቱ አጠራጠረኝ።
በመሆኑም አሮጌው እስከ ዘላለሙ እንዲሞት እና አዲሱ እንዲወለድ ወደ ኃላ ሄዶ ማስታወሱ ተገቢ መስሎ ተሰማኝ። በፕሬስ ዙሪያ ያለው ያ የጨለማ ወቅት አሁንም ሙሉ በሙሉ ያልገፈፈ በመሆኑ ወደሚቀጥለው ዘመን ከመሻገራችን በፊት እንዳይደገም መልሶ መቃኘቱ አግባብ ይሆናል። የዛሬ አስር አመት የተቋቋመው የኮሙዩኒኬሽን ጽህፈት ቤት ግልፅና ስውር ስልጣኑ ምን ነበር? አዲስ የተቋቋመው የፕሬስ ሴክሬተሪያት ምን ስልጣን አለው? ስራውን በተቀመጠለት ተልእኮ መሰረት መፈፀም ይችላል ወይ? በሴክሬተሪያቱ፣ በተቋማትና ክልሎች መካከል ምን አይነት ግንኙነት ሊኖር ይችላል? በሴክሬተሪያቱ እና በፓርቲ መካከል ያለው ተዛምዶ ወዴት ያመራል የሚለውን መዳሰሱ ያስፈልጋል።
#አንድ: የፈረሰው የኮሙዩኒኬሽን ጽህፈት ቤት ስልጣንና ኃላፊነት፣
ከዛሬ አስር አመት በፊት የማስታወቂያ ሚኒስትር ፈርሶ የኮሙዩንኬሽን ጽህፈት ቤት ሲቋቋም አላማ አድርጐ የተነሳው በኢትዮጵያ ሕዝብና መንግስት መካከል የመረጃ ድልድይ ሆኖ ማገናኘት ነበር። የጽህፈት ቤቱ ተልእኮም ከራማ እስከ አሶሳ፣ ከዛላ አንበሳ እስከ ሞያሌ ቶጐጫሌ ድረስ ያለውን የኢትዮጵያ ሕዝብ የልብ መሻት ለመንግስት ማቅረብ ነበር። በግልባጩም መንግስት የሕዝቡን ችግሮች ለመፍታት የሚያወጣቸውን የኢኮኖሚ፣ ፓለቲካዊና ማህበራዊ እቅዶችን ማስተዋወቅና ማስተቸት ነበር። ይሄ በወረቀት ላይ የሰፈረ፣ ከወረቀትም ያልተሻገረ ስልጣን እና ሀላፊነት ነበር።
የኮሙዩኒኬሽን ጽህፈት ቤት ከላይ ከተጠቀሰው በተጨማሪ በሕግና በፓርቲ የውስጥ አሰራር የተሰጠው ስልጣን በዝርዝር ለተመለከተ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ቀጥሎ ከፍተኛ ኃይልና ስልጣን የነበረው ነበር። ለምሳሌ ያህል አንድ ብንወስድ እንኳ የኮሙዩኒኬሽን ጽህፈት ቤት በሁሉም የፌዴራል መስሪያቤቶች፣ በአዲስ አበባ መስተዳድር፣ ምርጫ ቦርድ፣ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን ፣ ፓርላማ ጨምሮ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊዎች መመደብ በአዋጅ የተሰጠው ስልጣን ነበር። የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊዎቹ እና በስራቸው ያሉት ሰራተኞች (“ ኮሙዩኒኬተርስ”) ተጠሪነታቸውም ለተቋማቱ የበላይ ኃላፊ ( ሚኒስትሮችን ጨምሮ) ሳይሆን በቀጥታ ለኮሙዩኒኬሽን ጽህፈት ቤት ነበር።
የተቋማቱ የኮሙዩኒኬሽን ጽህፈት ቤት ኃላፊዎች ከመንግስታዊ ኃላፊነታቸው በተጨማሪ የፓርቲው የፓለቲካ ጉዳዮች የበላይ ኃላፊዎች በመሆናቸው ሚኒስትሩን ጨምሮ ሌሎች ባለስልጣናትን የማዘዝ ያልተፃፈ ስልጣን አላቸው። በተቋማቸው ውስጥ የሚሰሩትን ሰራተኞች እና ባለስልጣናት ፕሮፋይል በፓለቲካ አመለካከታቸው ( የኢህአዴግ አባል፣ ደጋፊ፣ መሐል ሰፋሪ፣ ተቃዋሚ) በሚል የመሰነድ ስራ እንደሚሰሩ ስለሚታወቅ በመስሪያ ቤቱ ውስጥ እጅግ ተፈሪዎች ናቸው። ሚኒስትሩም፣ ኮሚሽነሩም፣ ዋና ዴሬክተሩም፣ ዋና ስራ አስፈፃሚውም ሆነ ሌሎች ሹማምንት የኮሙዩንኬሽን ጽህፈት ቤት ኃላፊው መግለጫ እንዲሰጡ ትእዛዝ ካልሰጣቸው በስተቀር መናገር አይችሉም። ኃላፊው ደግሞ አስቀድሞ ከኮሙዩንኬሽን ጽህፈት ቤት የይለፍ ወረቀት ማግኘት አለበት።
በኮሙዩኒኬሽን ጽህፈት ቤት ውስጥ የተቋቋመው “ የፌዴራል ክልሎች ላይዘን ዴሬክቶሬት” አዲስ አበባና ድሬደዋን ጨምሮ በሁሉም ክልሎች ላይ ፍጹማዊ ስልጣን እንዲኖረው ተደርጐ የተቀረፀ ነበር። ፌዴራል ላይዘኑ የፓርቲና የመንግስት ማስፈራሪያ ኃይሉን በመጠቀም መረጃዎች ተዛብተው እንዲቀርቡ አሊያም እንዲደበቁ ያደርግ ነበር። ለአብነት ያህል በ2001 ዓ•ም• በደቡብ ክልል የተከሰተው ረሃብ ከ100 በላይ ህፃናትና እናቶች መግደሉን ክልሉ ለህዝብ ይፋ አድርጐ የድረሱልኝ ጥሪ ማስተላለፍ ቢፈልግም ከፌዴራል ኮሙዩኒኬሽን ፅህፈት ቤት በደረሰበት ማስፈራሪያ ከመግለፅ ተቆጥቧል። የክልሉ ኮሙዩኒኬሽን ኃላፊም አዲስ አበባ ተጠርቶ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቶታል።
የሆነው ሆኖ ኮሙዩኒኬሽን ጽህፈት ቤት ከጠቅላይ ሚኒስትር ቀጥሎ የመንግስት እና የፓርቲ ስልጣን እንዳለው የሚገለጠው ከላይ በተቀመጡት ምክንያቶች ነው። የምደባው መመዘኛም ለፓርቲው ታማኝነት በሚቀመጥ መስፈርት ብቻ የሆነው ለዛ ነው። በዚህ ምክንያት ጽህፈት ቤቱ ከመላው ኢትዮጵያ የመጡ ካድሬዎች ዋልጌነታቸውን የሚገልጡበት የአደባባይ የጩኸት መድረክ ሆኖ ሰንብቷል። ጽህፈት ቤቱ መንግስት እና ፓርቲ ድብልቅልቅ ብለው የጨረባ ተዝካር የሚደገስበት ነበር። ጽህፈት ቤቱ የአገርና የሕዝብ ተስፋ በማምከን የመንግስትን ስልጣን ለማርዘም መሳሪያ ሆኖ ያገለገለ ነበር።
#ሁለት:  የፕሬስ ሴክሬተሪያት ስልጣንና ኃላፊነት፣
የፕሬስ ሴክሬተሪያት ጽህፈት ቤት ኃላፊ የሆነችው ወይዘሮ ቢልለኔ ስዩም እንደገለጠችው ሴክሬተሪያቱ የተቆጠሩ ሶስት ስልጣንና ኃላፊነቶች አሉበት። በመንግስት ውሳኔዎችና አቋሞች ዙሪያ ወቅታዊ፣ ግልፅና ትክክለኛ መረጃ ማሰባሰብና ማሰራጨት። በመንግስት አሰራር ላይ የሚነሱ የሕዝብ ምላሾች፣ አስተያየትና ግብረ መልሶችን ማቀናጀት፣ መተንተንና ማሳደግ። እንዲሁም በመገናኛ ብዙሃንና በመንግስት መካከል ያለውን ግንኙነት ማጠናከር እንደሆነ ይፋ ተደርጓል። ወይዘሮዋ “ ተገቢውን መረጃ በወቅቱ ለሕዝቡ እናደርሳለን!” የሚል መሪ መፈክርም አሰምተዋል።
በሌላም በኩል ሴክሬተሪያቱ የቀድሞውን ኮሙዩንኬሽን ጽህፈት ቤት ስልጣን እና ኃላፊነት ተረክቦ እንደሚሰራ ወ/ሮ ቢልለኔ ከፕሬስ አካላት ጋር በጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት ባደረጉት ትውውቅ ላይ ይፋ አድርገዋል። ይሄ ማለት ምን ማለት ነው? አሁንም ቢሆን በየተቋማቱ የሚመደቡትና ፕሬስ ሴክሬተሪያቶች በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት በተደራጀው ሃይል ይሆናል? በየተቋማቱ የሚመደቡ ሴክሬተሪያት ተጠሪነት ለማን ነው? እስከ 300 የሚጠጋው የኮሙዩኒኬሽን ፅህፈት ቤት ሰራተኞች እና ከ400 በላይ የሚሆኑት በተቋማት ህዝብ ግንኙነት (ኮሙዩኒኬተር) የተመደቡት የኢህአዴግ ካድሬዎች እጣ ፈንታ ምን ይሆናል? ባሉበት የሚቀጥሉ ከሆነ የፓርቲ አባልነታቸውን ይዘው ነወይ በቀድሞ አመለካከታቸው የሚቀጥሉት?
ይሄ ብቻ አይደለም። በፌዴራሉ እና በክልል ሴክሬተሪያት መካከል የሚኖረው ግንኙነትም በኢህአዴግ አባል ድርጅቶች መካከል እንዳለው “ አወቅኩሽ ናቅኩሽ” ሆኖ መቀጠሉ አይቀርም። የፓርቲ አባል ያልሆነችው ( በግምት ነው) ወይዘሮ ቢልለኔ በእንዲህ አይነት የፓርቲ ውጥረት ባለበት አይደለም ለህዝቡ ለራሷም ተገቢውን መረጃ በወቅቱ ማግኘቱ ይቸግራታል። አይደለም ለእሷ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ የማይታዘዙ ክልሎች በተፈጠሩበት ሁኔታ ወቅታዊ፣ ግልፅና ትክክለኛ መረጃ ማሰባሰብና ማሰራጨት አትችልም። በዚህ ዙሪያ በርካታ ማሳያዎች ቢኖሩም ከጅምሩ ጨለምተኛ ላለመሆን በዚህ ላቁም።
ሶስት የግዮን ሆቴል እና የጠ/ ሚኒስትር ቢሮ
           ( ቧልተኛው ታሪክ ሲደገም!)
የዛሬ አስር አመት ማስታወቂያ ሚኒስትር ፈርሶ የኮሙዩኒኬሽን ጽህፈት ቤት ሲመሰረት በኢትዮጵያ የሚገኙ የፕሬስ አካላት በሙሉ ለትውውቅ እና እራት ግብዣ ግዮን ሆቴል ተጠርተው ነበር። በጥሪውም ላይ አብዛኛው የአገር ውስጥም ሆነ የውጭ ሚዲያ ወኪሎች ተገኝተው ነበር። በወቅቱ በፕሬሱ አባላት ዘንድ የነበረው አዲስ መንፈስ እና መነቃቃት በቅርበት ማየት ይቻል ነበር። እርግጥም አሳዳጅ እና ተሳዳጅ የነበረው መንግስት እና ሚዲያው አንድ ማዕድ ለመቁረስ መታደማቸው ጥሩ ስሜት ቢፈጥር የሚገርም አልነበረም። እርግጥም ከጅምሩ አንስቶ በፕሬስ አባላት ላይ የተወረወረው የመርዝ ፍላፃ በኃላም ያንን ተከትሎ የተከሰተው የዋስትና ማጣት በመንግስት እና በፕሬሱ መካከል ያለውን ቅራኔ አክርሮት ነበር።
እናም የእራት ግብዣው ከመጀመሩ በፊት የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ የነበረው አቶ በረከት ስምኦን የትውውቅ እና እንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር ለማሰማት ወደ መድረክ ወጣ። አቶ በረከት በመንግስት እና በሚዲያው መካከል የነበረውን የቀድሞውን መጥፎ ግንኙነት በተመለከተ ዘለግ ያለ ዲስኩር አሰማ። የግንኙነቱ መሻከር መፈጠር እንዳልነበረበት እና አሁን በተሃድሶ መንፈስ በአዲስ ራዕይ ለመስራት መዘጋጀቱን ተናገረ። በመጨረሻም እንዲህ አለ፣
 “ ከዚህ በኃላ ምንም ነገር ከህዝብ የሚደበቅ ነገር አይኖርም። ከአሁን በኃላ ከሁሉም የሚዲያ ተቋማት ጋር በጋራ እንሰራለን። የመንግስት ባለስልጣናትም በአዋጁ መሰረት ለፕሬስ ሰዎች መረጃ የመስጠት ግዴታቸውን ይወጣሉ። ባለስልጣናቱ ከሕግ በላይ ሆነው የሕዝብን የማወቅና መረጃ የማግኘት መብት በኃይል ተጋፍተው መረጃ ለመስጠት ፍቃደኛ ካልሆኑ ተጠያቂ ይሆናሉ” በማለት ተናገረ።
ከፕሬስ አባላት ጭብጨባው አስተጋባ። አቶ በረከት የጠቅላይ ሚኒስትሩ የቀኝ እጅ በመሆኑ ንግግሩ ወደ ተግባር እንደሚቀየር ተስፋ ተደረገ። በወቅቱ ከፍተኛ ተነባቢነት አትርፋ የነበረቸው “ አዲስ ነገር” ጋዜጣ የግዮኑን ድራማ አሞካሽታ እስከ መፃፍ ደረሰች። ጋዜጣዋ የቅዳሜው ክስተት አዲስ አሰራር ለመከተል የመፈለግና ቀና ሂደትን ለመላመድ ከፓርቲ ድንበር የተሻገረ መሆኑን አሰመረችበት። ዘላቂነቱ ላይ ጥርጣሬ እንዳላት ጨምራ ገለፀች።
የግዮኑ ግብዣ እለት ለአጫጭር ጥያቄዎች መድረኩ ክፍት ተደረገ። የመጀመሪያው ጠያቂ የአሜሪካ ድምፅ የአማርኛ ክፍል ዘጋቢ የሆነው ጋዜጠኛ እስክንድር ፍሬው ነበር። እስክንድር ምስጋና ካቀረበ በኃላ “ የኮሙዩኒኬሽን ጽህፈት ቤቱ ቋሚ የፕሬስ ኮንፍረንስ ቀን ለማድረግ እቅድ ይዟል ወይ?” በማለት ጠየቀ። አቶ በረከት በኩራት ውስጥ ሆኖ ዘወትር ሰኞ ጠዋት ጠዋት በኮሙዩኒኬሽን ቢሮ፣ በሁለት ወር አንዴ በቋሚነት ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር እንዲኖር መታቀዱን አበሰረ። አቶ በረከት ይሄን ሲናገር ኮሙዩኒኬሽን ጽህፈት ቤት አንዳችም እቅድ አላወጣም ነበር።
እነሆ! ከአስር አመት በኃላ ኮሙዩኒኬሽን ጽህፈት ቤት ፈርሶ በፕሬስ ሴክሬተሪያት ተተካ። ብፃይ በረከት ስምኦንን ኦቦ ሽመልስ አብዲሳ ተካው። ከርቀት እንደምንሰማው ከሆነ ኦቦ ሽመልስ የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ የቀኝ እጅ ናቸው። ወደ ጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የመጡትም የዶክተር አቢይን ራዕይ ለማስፈፀም እንደሆነ በመጀመሪያ ቀን ንግግራቸው ይፋ አድርገዋል። ኦቦ ሽመልስ ስለሚመሩት ፕሬስ ሴክሬተሪያት ፍላጐት ሲናገሩ ፣
   “ ከዚህ በኃላ ምንም ከህዝብ የሚደበቅ ነገር አይኖርም። ከአሁን በኃላ ከሚዲያ ተቋማት ጋር እንደ አንድ ቤተሰብ እንሰራለን” በማለት ተናገሩ። በቤተመንግስቱ የታደሙት ጋዜጠኞች አጨበጨቡ።
በዚህ የቤተመንግስቱ የፕሬስ አካላት ትውውቅ ላይ በሴክሬተሪያት ኃላፊዋ ወ/ሮ ቢልለኔ ስዩም ግብዣ ጋዜጠኞች ጥያቄ እንዲያቀርቡ ተጋበዙ። አንድ ሰው ቀድሞ እጁን አወጣ። የአሜሪካን ድምፅ አማርኛ ክፍል ዘጋቢ የሆነው ጋዜጠኛ እስክንድር ፍሬው ነበር። እስክንድር ምስጋና ካቀረበ በኃላ “ የኮሙዩኒኬሽን ጽህፈት ቤቱ ቋሚ የፕሬስ ኮንፍረንስ ቀን ለማድረግ እቅድ ይዟል ወይ?” በማለት ጠየቀ።
የትላንቱን ጊዬን የዛሬውን የቤተመንግስት ( የአስር አመት ክስተት) መገጣጠም ስመለከት አንድ ነገር ትዝ አለኝ። ክስተቱ ከዛሬ ሰላሳ አመት በፊት በኢህአፓ እና በህውሓት መካከል የተካሄደ የቃላት ጦርነት ነበር። ኢህአፓዎች የህውሓትን ኃላቀርነት እና ተቸንክሮ መቅረት የሚያመላክት ዶክመንት ይፋ ያደርጋሉ። በዚህ ሰነድ ላይ ኢህአፓዎች “ የትግራይ ነፃ አውጭ የሆነው ህውሓት ነገሮች የሚገቡት ከአስር አመት በኃላ ነው!” የሚል ፍሬ ሃሳብ የያዘ ነበር። በዚህ የተናደዱት ህውሓቶች “ ወጣ ወጣና እንደ ሸምበቆ፣ ተንከባለለ እንደ ሙቀጫ!” በሚል ዳጐስ ያለ መፅሀፍ ላይ “ ሞቅ ሞቅ በየት ዞረሽ መጣሽ!” በሚል ምእራፍ ላይ ኢህአፓን አብጠለጠሉ። መርህ አልባ የሞቅታ ፓለቲከኞች በማለት ተሳለቁባቸው። እውነታው ግን ህውሓት አስር አመት ጠብቆ ኢህአፓ የደረሰበት የአስተሳሰብ እድገት ደረጃ ኮርጆ ወሰደው። አሁንም ህብረተሰቡ ከደረሰበት የእድገት ደረጃ አስር አመት ዘግይቶ በመጀመር የቁልቁለት ጉዞውን ቀጥሎታል።
 አዲሱ የኢህአዴግ አመራር የሆነው የዶክተር አቢይ ቡድን በሚዲያ ላይ ያደረገው እውነተኛ ለውጥ ይሁን “ ሞቅ ሞቅ በየት ዞረሽ መጣሽ!” የምናየው ይሆናል። “ እርካብና መንበር” የሚለውን የዶክተር አቢይ መፅሐፍ ካነበብኩ በኃላ ዶክተሩ ስለ “ዘመናዊ ጋዜጠኝነት” ያላቸው አመለካከት እንዳስደነገጠኝ መደበቅ አልፈልግም። የልማታዊ ጋዜጠኛ ወዳጅ የሚመስሉት ዶክተር አቢይ በገፅ 119 ላይ፣
   “… የዘመናዊ ጋዜጠኝነትም ልክ እንደ ውሻው ጥቂት ስህተት አጉልቶ እንደሚያወራው ሰው ወይም የተሞላው የብርጭቆውን ክፍል ከመናገር ይልቅ ስለጐደለው አብዝቶ እንደሚያወራው ሰው ነው” ይለናል።
ቸር እንሰንብት።
ማስታወሻ: – ይሄ መጣጥፍ የፍትሕ መፅሔት ለህዝብ መቅረብ ስትጀምር በመጀመሪያው እትም የወጣች ናት። በዛን ሰሞን ኮሙዩኒኬሽን ጽህፈት ቤት ፈርሶ በምትኩ በጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮ ስር የፕሬስ ሴክሬተሪያት የተደራጀበት ነበር። በወቅቱ ፕሬስ ሴክሬተሪያቱ እና የበላይ ሀላፊ ሆና የተመደበችው እንስት ውጤታማ ትሆን ይሆን? የሚል ጥያቄ የተነሳበት ነው። ዛሬ በሴክሬተሪያቱ አካባቢ ሊካሄድ ስለታሰበው ለውጥ ሽርፍራፊ መረጃዎች እየወጡ ነው። እናም የማህበራዊ ድረገፅ ወዳጆቼ የቀድሞውን መጣጥፌን በምልሰት ውስጥ ሆናችሁ እንድታነቡት የተለጠፈ ነው
Filed in: Amharic