>
5:13 pm - Sunday April 19, 7029

የአስተዳደር ወሰን እና የማንነት ጉዳዮች ኮሚሽን ፋይዳና ተግዳሮቶች!! (ዶ/ር ደረጀ ዘለቀ መኮንን)

አስተዳደር ወሰን እና የማንነት ጉዳዮች ኮሚሽን ፋይዳና ተግዳሮቶች!!
ክተር ደረጀ ዘለቀ መኮንን _ አዲስ አበባ የኒቨርሲቲ የህግ ተባባሪ ፕሮሰር
ሁለት አስገራሚ ትዕይንቶች
የአስተዳደር ወሰን እና የማንነት ጉዳዮች ኮሚሽን ማቋቋሚያ አዋጅ የፀደቀበትን የፓርላማ ውሎ የተከታተለ ሁለት አስገራሚ ትዕይንቶችን መገንዘብ ይችላል፡፡ ቀዳሚውና የብዙዎችን ቀልብ የያዘው፣ “የሕገመንግሥት (በግብር ስሙ ሕገ-አራዊት) ይከበር” ባዮች ሃፍረት የለሽ ማንቋረር ሲሆን፣ ሁለተኛው አስደማሚ ትዕይንት ደግሞ፣ ገዢው ፓርቲ 100% ድል ባስመዘገበበት ፓርላማ፣ ጥቂት ወንበርተኞች ለቀደመ ሃጢኣታቸው ስርየት ለማግኘት ያለመ በሚመስል ድፍረት፣ “ወክለነዋል” ለሚሉት ሕዝብ “በቁጭት”? የተናገሩበት ያልተለመደ ትዕይንት ነበር፡፡
አዋጁ ወገን ለይቶ የከረረ እንካስላንቲያ ማስነሳቱ ያልተጠበቀ ባይሆንም፣ ለህወሓት ፈቃድ ይሁንታ እየቸረ ሕጋዊነት ከማላበስ የዘለለ ሚና ኖሮት የማያውቀው ፓርላማ፣ የለውጡን ንፋስ ተከትሎ ሎሌነት በቃኝ ያለ መስሏል፡፡ በዚሁ የፓርላማ ውሎ፣ በህወሓት አድራጊ ፈጣሪነት ድቡሽት ላይ የተዋቀረው ገዳይ-ዘራፊ ሥርዓት ፍፃሜ፤ ያንኑም ተከትሎ ዕውን ሊሆን የተቃረበው “የነፃነት አደጋ” የታያቸው ህወሃታውያን  የመጨረሻውን ጩኸት ማሰማታቸው፣ ትዕይንቱን የበለጠ አስደማሚ፣ ምናልባትም “ታሪካዊ” አድርጎት አልፏል፡፡
ከነዚህ አስገራሚ ትዕይንቶች ባሻገር መሰረታዊው ጉዳይ፣ በአዋጅ የተቋቋመው ኮሚሽን በእርግጥም ሰቅዞ የያዘንን አብይ ችግር የመፍታት ፋይዳ አለውን? የሚለው ጥያቄ ነው፡፡
የአዋጁን አስፈላጊነትና ዓላማ የሚገልፀው ክፍል (preamble) “የፌደራል ሥርዓቱን በማጠናከር እየተገነባ የመጣውን የብሔር ብሔረሰብ እና ህዝብ ብዝሃነት ማጎልበት አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ” በሚል ተራ ፕሮፓጋንዳ ይጀምራል፤ እንዲህም አድርጎ “የብዝሃነት ግንባታ” የለ! ይልቁንስ፣ ከወሰን/ማንነት ጋር የተያያዙ ውዝግቦች የቅራኔ ምንጭ መሆናቸው፤ ከዚሁ ጋር ተያይዞ የሚነሱ ግጭቶችም “ከፍተኛ ለሆነ አለመረጋጋት መንስኤ መሆናቸው” የተገለጠበት ክፍል ለዕውነታው ጥቂት ቀረብ ያለ ይመስላል፡፡ በዚህ መሃል ግን፣ በዝምታ የተዘለለው አሳዛኝ ዕውነታ የሚሊዮኖች መፈናቀል፣ የሺዎች ሞትና ከፍተኛ የአገር ሃብት ውድመት እንደሆነ ልብ ይሏል፡፡
የአዋጁ ግብ፣ “በክልሎች የአስተዳደር ወሰን፣ ራስን በራስ ማስተዳደርና በማንነት ጥያቄዎች ዙሪያ በተደጋጋሚ የሚታዩ ችግሮችን አገራዊ በሆነና በማያዳግም መንገድ መፍታት” ሲሆን፣ ወደዚህ ፍፁም ደስታና ሰላም (nirvana) የሚያደርሰን ሰረገላ ደግሞ፣ “ለነዚህ ችግሮች ገለልተኛ በሆነ፣ ከፍተኛ ሞያዊ ብቃት ባለውና ሰላማዊ በሆነ መንገድ” መፍትሔ የማፈላለግ ታሪካዊ ተልዕኮ የተሰጠው ኮሚሽን ነው፡፡ በእርግጥ ኮሚሽኑ ይህንን ታላቅ ተልዕኮ ፈፅሞ ወደምንመኘው ሠላም ሊወስደን ይቻለዋል? ይህ ፈረንጆች “የሚሊዮን ዶላር ጥያቄ” የሚሉት አይነት ነው፤ በጣም ተወደደ ካልተባለ፡፡
ትርጓሜ ወይስ ምኞት?
በአዋጁ ትርጓሜ የተሰጣቸው ቃላት ሁለት ብቻ ናቸው፤ “የአስተዳደር ወሰን” እና “ኮሚሽን”፡፡
“የአስተዳደር ወሰን ማለት፣ ራስን በራስ ማስተዳደር፣ ከማንነት ጥያቄ እና ከሌሎች ተመሳሳይ ክስተቶች ጋር በተያያዘ የሚነሱ የወሰን ጉዳዮች ነው” ተብሎ ተተርጉሟል፡፡ በቅድሚያ፣ ይህ ትርጓሜ እንኳንስ ለሕግ ባለሙያ የሌላ ሙያ ባለቤት ለሆነ ተራ ዜጋ በሚታይ መልኩ ትርጉም የሌለው ተራ ንግግር ነው፡፡ በምንም መመዘኛ የአስተዳደር ወሰን “ራስን በራስ ማስተዳደር” ተብሎ ሊተረጎም አይችልም፡፡ እርግጥ ነው፣ ራስን በራስ ማስተዳደር የሚተገበርበት ስፍራ (መልክዓምድር) ያስፈልጋል፤ ነገር ግን፣ የዚህ ስፍራ ወሰን “ራስን በራስ ማስተዳዳር” ሊሰኝ አይችልም፡፡  በላቀ አመክንዮ (a fortiori) የማንነት ጥያቄም ሆነ ተያያዥ የወሰን ጉዳዮች፣ “የአስተዳደር ወሰን” ትርጓሜ ሊሆኑ የሚችሉበት አግባብ የለም፡፡ ስለዚህ፤ ሊቁ ገጣሚ በዕውቀቱ ሥዩም በአንድ ግጥሙ “ሎንዶን ከተማ አይደለም” እንዲል፣ ይህ “የአስተዳደር ወሰን” ትርጓሜ ትርጉም አይደለም እላለሁ፡፡ ዛዲያ ምንድር ነው ብሎ ለሚያጠይቅ፣ መልሴ “ምኞት” ነው የሚል ይሆናል፡፡ ለምን እንዲህ እንዳልኩም አስረዳለሁ፡፡
ህወሓት መራሹ ሥርዓት በተከለው የዘውግ ማንነት ፖለቲካ በተፈጠረ የመጤ-ሰፋሪና የባለርስት-ኗሪ ዜጎች ስንጥቃት (chasm) የተጋረጠብንን የመጠፋፋትና የመበታተን አደጋ መሻገር የአገሬው ሁሉ፣ በተለይ ደግሞ ዶ/ር አቢይ የሚመሩት የለውጥ ሃይል ታሪካዊ ፈተና፤ የመሆን-አለመሆን የህልውና ጥያቄ ሆኖ ከፊታችን ተጋርጧል፡፡ ይህንኑ ጉዳይ አስመልክቶ፣ ጠቅላይ ምኒስትሩ በአንድ ንግግራቸው፣  በዘመነ ኢሕአዴግ የተመረጠው የግዛት አወቃቀር ዘይቤ – ቋንቋን መሰረት ያደረገ የዘውግ ክልል – የሁላችን በሆነች ኢትዮጵያ እንዳስፈላጊነቱ ሊለወጥ የሚችል  ውስጣዊ “የአስተዳደር ወሰን” መሆኑን አበክረው ገልጠዋል፡፡ በዚህ እሳቤ፣ “በሕገመንግስት ይከበር” ስም ወደጥልቁ ሊወረውሩን ለሚባጁ ህወሓታውያንም ሆነ፣ ጋዜጠኛ ቴዎድሮስ ፀጋዬ በውብ አገላለፅ “ኩርማናውያን” ለሚላቸው የዘውግ ሪፐብሊክ ተስፈኞች ሊነገራቸው የሚገባ ሃቅ፣  የክልሎች ወሰን የሁላችን በሆነች ኢትዮጵያ ግዛት በነፍጥ ሥልጣን በጨበጡ ፋኖዎች ፈቃድ የተበጀ፣ እንዳስፈላጊነቱ ሊለወጥ የሚችል “የአስተዳደር ወሰን” እንጂ፣ ባዕዳን በቪዛ የሚሻገሩት፣ ባለርስቶቹም በደማቸው የሚያስከብሩት “ድንበር” አለመሆኑን ነው፡፡ ነገር ግን፣ ይህ የነጠረ እውነት፣ ቅዱስ ሃሳብ፣ ቅን ህልም፣ በጎ ምኞት . . . ብቻ እንጂ የወቅቱ የአገራችን ፖለቲካዊ እውነታ ነፀብራቅ አይደለም፡፡ ሕገመንግስቱም ይህንን “የኑፋቄ ቋንቋ” ከቶ አያውቀውም፡፡
የኢትዮጵያን የግዛት ወሰን የሚደነግገው የሕገመንግስቱ አንቀፅ 2፤ “የኢትየጵያ የግዛት ወሰን የፌደራሉን አባሎች ወሰን የሚያጠቃልል ሆኖ በዓለማቀፍ ስምምነቶች መሰረት የተወሰነ ነው” ሲል፣ ኢትየጵያዊ ዜግነት “በብሔር፣ብሔረሰብ፣ ሕዝቦች” ማንሜነት እንደተዋጠ ሁሉ፣ በአጎራባች አገራት፣ በኬክሮስ፣ ኬንትሮስ የሃሳብ መስመሮች ይገለጥ የነበር የኢትየጵያ ድንበር፣ በክልሎች ድንበር ቅጥልጣይ የመዋጡን እውነታ የሚያስረግጥ መሆኑ ግልፅ ነው፡፡ የህገመንግስቱ ቋንቋ “የክልሎች ወሰን” እንጂ፣ ባለቤት አልቦ የሆነው “የአስተዳደር ወሰን” አይደለም፤ ክልል የባለቤቶቹ “ብሔር፣ ብሔረሰብ፣ ሕዝቦች” የተስፋ አገር እንጂ፣ ከእነርሱ ባለቤትነት ተነጥሎ ሊቆም የሚችል “የአስተዳደር ወሰን” አይደለም፡፡ ከክልሎች ወሰን ጋር ተያያዥ የሆኑ የሕገመንግሥቱ አንቀጾችም ይህንኑ እውነታ የሚያስረግጡ ናቸው፤ “የክልሎችን ወሰን በሚመለከት ጥያቄ የተነሳ እንደሆነ ጉዳዩ በሚመለከታቸው ክልሎች ስምምነት ይፈፀማል” እንዲል፣ አንቀጽ 48(1)፡፡
ኮሚሽኑ ምን ፋይዳ አለው?
በአዋጁ አንቀጽ 4 እንደተመለከተው የኮሚሽኑ ዓላማ “አሳታፊ፣ ግልጽ፣ አካታችና ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ ከአስተዳደር ወሰኖች፣ ራስን በራስ ማስተዳደር እና ከማንነት ጋር የተያያዙ ግጭቶችንና መንስኤያቸውን በመተንተን የመፍትሄ ሃሳቦችን ለሕዝብ፣ ለፌደሬሽን ምክር ቤት፣ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና ለአስፈጻሚው አካል ማቅረብ ነው፡፡” ይህንን ዓላማውን ከግብ ለማድረስም፣ አስፈላጊ የሆኑ ሥልጣንና ተግባራት ተዘርዝረው ተሰጥተውታል (አንቀጽ 5)፡፡ አገሩ አገር ሆኖ ቢሆን፣ እንዲህ ያለው ታላቅ ሃላፊነት በአገሪቱ ልሂቃን፣ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት፣ በምርምር ማዕከላት፣ በሙያ ማህበራት፣ ወዘተ. የሰርክ ተግባር ሆነው በተሰሩ ምርምሮች ከሞላው አገራዊ የዕውቀት ቋት እየተመዘዘ ለመፍትሔነት የሚውል “በእጅ ያለ መላ” እንጂ፣ እንዲህ እንደዛሬው፣ በሚሊዮኖች መፈናቀልና በሺዎች ሞት ማግስት “ሰርገኛ መጣ በርበሬ ቀንጥሱ” ፈሊጥ በቆመ ኮሚሽን የሚወለድ ዘዴ ባልሆነ ነበር፡፡
ይሁን፤ ቢዘገይም ከዘለቀ ጅምሩ በጎ ነው፡፡ አስፈጻሚው አካል ለአገራዊ ችግር ዕውቀትን፣ ሙያንና ተቋምን መሰረት ያደረገ መፍትሔ የመፈለግ በጎ ፈቃድ ማሳየቱ ዘለቄታዊ አቅጣጫ ከሆነ፣ መቀመቅ ካወረደን “የሁሉን አወቅ ባለራዕይ መሪ” አድራጊ ፈጣሪነት ቁራኛ የመላቀቂያችን ምዕራፍ በመሆኑ እሰየው፣ ይበል፣ ይዝለቅ ልንለው የሚገባ እመርታ ነው፡፡ ነገር ግን፣ ይህ “የሕገመንግሥት ተጣሰ ጩኸት” የቀሰቀሰ፣ “የጦር እንገጥማለን ቀረርቶ” ያስለፈፈ ኮሚሽን መቋቋም በእርግጥም ከተራራ ለገዘፈው፣ በሞትና መፈናቀል ለታጀበው ችግር መፍትሔ፣ አሊያም አንዳች ማስታገሻ ያመጣል? ተስፋ እንዳናደርግ “ይህ ዕውን የማይሆን ህልም፣ የማይጨበጥ ተስፋ ነው” ብሎ ኩም የሚያደርገን የአዋጁ አንቀጽ 6 ነው፤ “ማንኛውም የአስተዳደር ወሰን ውሳኔ፣ ራስን በራስ ማስተዳደርና የማንነት ጥያቄ በኮሚሽኑ ተጠንቶ አግባብነት ባላቸው ህጎች መሰረት ለፌደሬሽን ምክር ቤት ቀርቦ እልባት ያገኛል” በማለት፡፡
ኮሚሽኑ ከሰለሞን በሚጠበቡ ጠቢባን ቢሞላ፣ ጠቢባኑም አለምን አጀብ የሚያሰኝ መላ ቢዘይዱ፣ ጥበቡን ተረድቶና አክብሮ፣ መላውንም መዝኖና ፍቱንነቱን አምኖ የሚተገብረው ዛሬም እንኳ “አላየሁም፣ አልሰማሁም” ከሚል ዕውነታን የመካድ አባዜ ያልተላቀቀው የፌደሬሽን ምክር ቤት ነው፡፡ ይህ ደግሞ በጎ ሕልም፣ ሰናይ ምኞት፣ ቅን ሃሳብ፣ ብርቱ ጥረት፣ ታላቅ ተስፋ . . . በዜሮ ሲባዛ እንደማለት ነው፡፡
በሰፊ ሕዝባዊ ተቃውሞ፣ በብዙ መስዋዕትነት እና ከፍተኛ ውስጣዊ ትግል ወደ ሥልጣን የመጣው የለውጥ ሃይል የተጋፈጠውን አደጋ፣ ያሳየውን ቁርጠኝነትና የወሰዳቸውን ጉልህ የለውጥ እርምጃዎች እንደሚያደንቅ ታዛቢ ይህንን አሳዛኝ የዜሮ ብዜት እውነታ ከለውጥ ሃይሉ ቅንነት ማጣት፣ ወይም ድብቅ ፖለቲካዊ ዓላማ ጋር ማገናኘት፣ ምክንያታዊም ሰብአዊም እንዳልሆነ ከልብ አምናለሁ፤ ለጊዜው የሚታየኝ፣ ለሁነቱ ተመጣጣኝ የሆነ መግለጫ “የቸገረው እርጉዝ ያገባል” የሚለው ብሂል ነው፡፡ ለገጠመን ግዙፍ ችግር አፋጣኝ ፍቱን መፍትሔ የመሻት ዕዳ “ፈቃድህ ቢሆን ከእኛ ይለፍ” የማንለው፤ አሳልፈንም ለሌላ “ሙሴ” የማንሰጠው፣ የራሳችን የኢትጵያውያን ዕዳ ነው፡፡ “ይህ ዕዳ የእኔም ዕዳ ነው” ብሎ እንደሚያምን ዜጋ፣ “የመፍትሔው ጉዳይ ያገባኛል” እላለሁ፤ ስለዚህም የተመረጠውን ”የቢቸግር” መፍትሔ ትተን እውነታውን በመጋፈጥ ዘላቂ መፍትሔ እንውለድ ስል እሞግታለሁ፡፡
ምን እናድርግ?
ልንጋፈጠው የሚገባን ዕውነታ የችግራችን ዋነኛ ምንጭ በዘውጌ ማንነት ፖለቲካ ጭንጫ ላይ የተዘራው ስመ-ፌደራላዊነት (pseudo federalism) የመሆኑ ሃቅ ሲሆን፣ የመፍትሔ ፍለጋ ጥረታችንም ይህንኑ ሃቅ አምኖ ከመቀበል የሚጀምር ሊሆን ግድ ነው፡፡ “ዜጎች” በሌሉባት ኢትዮጵያ፣ የሉዓላዊ ሥልጣን ባለቤት የሆኑ ብሔር፣ ብሔረሰብ ሕዝቦች በወደዱ ጊዜ “ናፅነት” መርጠው ጎጆ መውጣት ሕገመንግሥታዊ መብታቸው ነው፡፡ የብሔር-ብሔረሰቦች እስር ቤት ከነበረችው ኢትዮጵያ፣ ጋጥ የተፈቱ ከሃምሳ በላይ ብሔር-ብሔረሰብ-ሕዝቦች ወያኔ በፈበረከላቸው አዲስ የጋራ ቋንቋ “ወጋጎዳ” እያውካኩ ተዳብለው እንዲኖሩበት “ታስቦ” ከተቀለሰው አዲሱ ጋጥ (ደቡብ ክልል) በቀር፣ ክልሎች የተዋቀሩት ይህንኑ “የመብቶች ሁሉ መብት” ለመተግበር በሚያስችል “የዘውግ አገር” ድንበር ተከልለው የመሆኑ እውነታ ማንም የማይክደው ሃቅ ነው፡፡ ነጻ አውጪዎቹ ፋኖዎች የሚኮሩበት አንፀባራቂ ድል፣ የብሔር ብሔረሰቦች እስር ቤት የፈረሰበት የነፃነታቸው ቀን፣ የዘመነ ወያኔ ኢትዮጵያ Bastille Day ህዳር 29ም፣ የዚህ ግርምቢጥ ቋሚ መታሰቢያ መሆኑ ሊስተባበል አይችልም፡፡
በዚህ የብተና ስሌትና እሳቤ አምነው እና ተማርከው ነው ዘውጌ ብሔርተኞች ከማለዳው ሥርዓቱን አይናቸውን ሳያሹ የደገፉት፤ “እንወክለዋለን” የሚሉትን ሕዝብ በማሰር፣ በማሰቃየት፣ በመግደል፣ በተፈቀደላቸው መጠን በመዝረፍና ታማኝ የቤት ውልድ ባሪያዎች ሆነው በማገልገል የአገዛዙን እድሜ፣ የሕዝቡንም መከራ ያረዘሙት፡፡ ዛሬም ድህረ-ወያኔ ያለሃፍረት ጥብቅና የሚቆሙለት የነገ ዓለማቀፍ ድንበሯ በዛሬው የክልል ወሰን የተሰመረና፣ በአንቀፅ 39 አዋላጅነት የምትከሰት ነፃ አገራቸውን ለመረከብ በመጠባበቅ ተስፋ ሰክረው ነው፤ ለዚህም ነው እያንዳንዷ ቅንጥብጣቢ መሬት፣ ሽርፍራፊ ቀበሌና ጎጥ የይገባኛል ቱማታ፣ የጅምላ ፍጅትና መፈናቀል ምክንያት የሆነችው፡፡
 “ተራሮችን ያንቀጠቀጠው” ትውልድም ቢሆን በቅድመ-ሕገመንግሥት የመሬት ንጥቂያ እና ተራራ ዝርፊያ ቅሌት የተዘፈቀው የወደፊቷን ነጻ አገር፣ የተስፋይቱን ሪፐብሊክ በአይነ ህሊናው ሲስል ክሳቷ፣ ማነሷ ቢያስበረግገው በሂትለራዊ ሰፊ የመኖሪያ ግዛት (lebens raum) ቅርምት ሊያሰፋት፣ የተንጣለለ እርሻ መሬት ባለጠጋ፣ የሰማይ ጠቀስ አረንጓዴ ተራራ ባለቤት ሊያደርጋት አልሞ ሲባጅ መሆኑ የማይታበል ሃቅ ነው፡፡
ይህን ዕውነታ ከተቀበልን፣ በመፍትሔ ፍለጋ ጥረታችን ፖለቲካዊ አይናፋርነትን እና አድርባይነትን አውልቀን ጥለን፤ ውሱን አገራዊ ሃብትና ውድ ጊዜያችንን በዋናው የችግራችን ዕምብርት ላይ በማዋል፣ ሳይረፍድብን ቀጣይ ሕልውናችንን ለማረጋገጥ መረባረብ አይገደንም፡፡ ፈረንጅ ለከባድ ችግር ቁርጥ ያለ የድፍረት እርምጃ የመውሰድን አስፈላጊነት በሚያወሳበት ብሂሉ sometimes, it is necessary to take the bull by the horn ይላል፤ “አንዳንዴ ፊጋ በሬንም ቢሆን ቀንዱን መያዝ ግድ ነው” እንደማለት ነው፡፡ ወያኔ በአናሳ አምባገነናዊ ሕልሙ በድዱ እስኪገዛ በንግሥናው ለመሰንበት አልሞ ያነበረውን የጎሳዊ ማንነት ፓለቲካ ነቅሎ በመጣል በምትኩ የዜግነትን ፖለቲካ መትከል አይቀሬው “ቀንድ የመያዝ” እርምጃ፣ የዘለቄታው አዋጭ መንገድ መሆኑን አምኖ ለዚሁ በቁርጠኝነት መስራት አማራጭ የሌለው መውጫ መንገድ ነው፡፡ ይህን ቸል በማለት ከሳሎን የተገሸረውን ዝሆን ያላዩ መስሎ ቤት ለማሰናዳት መሞከር ዋጋ የሚያስከፍል ተላላነት፣ አሊያም ከጎሳዊ የማንነት ፖለቲካ “መለያየት ሞት ነው” የሚል የልብ እምነት ያሰረው አክሳሪ ተቸካይነት ነው፡፡
Filed in: Amharic