>
4:56 am - Friday July 1, 2022

የዴሞክራሲ ሽግግሩና የተደቀኑበት አራት ተግዳሮቶች!!! (ነዓምን ዘለቀ)

የዴሞክራሲ ሽግግሩና የተደቀኑበት አራት ተግዳሮቶች!!!
ነዓምን ዘለቀ የአርበኞች ግንቦት 7 ሥራ አስፈፃሚ አባል
ሀገራችን ኢትዮጵያ  ባለፉት ጥቂት ወራት ዉስጥ አስገራሚ በሆነ የለውጥ ሂደት ወስጥ እንደምትገኝ ለአብዛኛው ኢትዮጵያዊ  ግልጽ ነው። የኢትዮጵያ ህዝብ ለዘመናት የታገለለት ፍትህ፣ ነጻነት፣ እኩልነትና የህግ የበላይነት የሚረጋገጥበት እዉነተኛ   ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ለመመስረት የሚያስችል ጭላንጭል በመታየት ላይ ነዉ።  በአሁኑ ሰዓት በኢትዮጵያ የተፈጠረዉ ሁኔታ  ወርቃማ  መሁኑን በመገንዘብ፣  የተፈጠረዉን መልካም  እድልና አጋጣሚምም በጥበብና በትዕግስት መጠቀም ያስፈልጋል። የአሁኑን መልካም አጋጣሚ ካልተጠቀምንበት ግን፣ ዴሞክራሲያዊ ማህበረሰብ መገንባት ይቅርና  የኢትዮጵያ አንድነት ከባድ አደጋ ውስጥ ይወድቃል።
አሁን በሀገር ውስጥ ያሉ ነባራዊ ሁኔታዎች በጥቅሉ ምን ይመስላሉ? ከዚህ ሂደት ጋር ተያይዘው የሚመጡ ተግዳሮቶችና ስጋቶች ምንድን ናቸው? በምን ይገለጻሉ? የሚሉትን ጥያቄዎች በጥልቀት መፈተሽና ደረጃ በደረጃ መልስ ለመስጠት መሞክር፣ የተረጋጋና ቀጣይነት ያለዉ ዲሞክራሲያዊ ስርዓት ለማቆም በጣም አስፈላጊ ነዉ።  ከበርካታዎች መካከል ዋና ዋናዎቹን እንመልከት፣
ተግዳሮት #1 ያለፉት ሥርዓቶች ጥለውት ያለፉት ችግሮች
 የለውጡ ሂደት ከተጀመረ በኋላ፣ ከደህንነትና ከጸጥታ ጉዳዮች ጋር በተያያዙ ማእከላዊ መንግስቱን የገጠሙት ፈተናዎች፣ ያለፉት አገዛዞች ተክለው ያለፉትን የችግሮች መጠንና ጥልቀት ቁልጭ አድርገው የሚያሳዩ ናቸው ማለት ይቻላል።
እነዚህን ችግሮች ለመፍታት መንግስት ያስቀደመው ኃይልን ሳይሆን ድርድርንና ትዕግሥትን መሆኑ ጥሩ ቢሆንም፣ ነገሮች ከቁጥጥር ውጭ እንዳይወጡ ደግሞ መንግስት ህግ የማስከበር ኃላፊነቱን መወጣት አለበት፡፡ በሁለቱ መካከል ያለው ሚዛን እንዳይዛባ መጠንቀቅ ያስፈልጋል፡፡
 ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ ያለፉት ሥርዓቶች ጥለው የሄዱትን ችግሮች ለመፍታት መሟላት ከሚገባቸው  ወሳኝ የሆኑ መሰረታዊ ቅድመ ሁኔታዎች መካከል ህዝባዊ ህገ መንግስት፣ ነጻ ዲሞክራሲያዊ ተቋማት፣ ገለልተኛ የደህነትና የመከላከያ ሃይል፣ ከሙስና የጸዱ፡ ግልጽና ተጠያቂ የስርአተ መንግስት ተቋማት ዋና ዋናዎቹ ናቸው፡፡
በተጨማሪም፣ ነጻ የፍትህና የዳኝነት ስርአት፣ ነጻ የምርጫ ቦርድ፡ ነጻ ሚዲያ፣ በማንኛቸውም የኢትዮጵያ አካባቢዎች ተዘዋውረዉ ልዩ ልዩ የሃሳብ /የራዕይ አመራጮች ለማቅረብ የሚችሉ፣ በነጻነት ለማንቃት፣ ለማደረጀትና ለመንቀሳቀሰ የሚችሉ፣ ጠንካራና ውስጣዊ ዴሞክራሲያዊ አሰራርና ባህል ያዳበሩ የፓለቲካ ፓርቲዎች ወሳኝ ማገሮች ናቸው። ጠንካራና ልዩ ልዩ የመብት ጥያቄዎችንና ሀገራዊ ችግሮችን ለመቅረፍ የተደራጁና ትኩረት ሰጥተው የሚሰሩ  የሲቪክ ማህበረሰቦች (civil society organizations) አስፈላጊ ናቸው።  ተቋማት ለብቻቸው መፍትሄ ስለማይሆኑ፣ ዴሞክራሲያዊ የሆነና ስልጡን የፓለቲካ ባህል ማዳበር ስለሚያስፈልግ፣ የሰጥቶ መቀበል ፓለቲካ፣ የድርድር ፓለቲካ፣ የመደማመጥ ባህልና የመቻቻል ፓለቲካ መቀበል የግድ ይላል።
ከእነዚህ  አይነት ዴሞክራሲያዊና ዘመናዊ እሴቶች ውጭ ዕውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ስርአት ለመመስረት በጣም አዳጋች ይሆናል።  ከዚህ አኳያ ለውጡን የሚመራው የመንግስት አካል የተጀመሩ መዋቅራዊ፣ ህጋዊ ማሻሻያዎች ለማድረግ የተቋቋሙ  ኮሚሽኖችና፡ የተወሰዱ እርምጃዎች የሚበረታቱና ጥሩ ጅማሮዎች ቢሆኑም፣ እነዚህ ለዲሞክራሲያዊ ስርአት አሰፈላጊ የሆኑ እሴቶችና ተቋማት  አቅም እንዲገነቡና ዴሞክራሲያዊ ባህልና እሴቶችን እንዲያሳድጉ ደረጃ በደረጃ ብዙ ርብርብ እንዲያደርግ ይጠበቅበታል።
ተግዳሮት #2.  በስራ ላይ የሚገኘው ህገ መንግስት 
ህገ መንግስት የአንድ ዴሞክራሲያዊ ህገ መንግስት ዋና መለያ ደግሞ የዜጎች መሰረታዊ መብቶችና ነጻነቶች የተደነገጉበት፡ በዜጎችና በመንግስት መካከል ያለውን ግንኙነትና መስተጋብር በዝርዝር የተቀመጠበት ሰነድ ነው። የዴሞክራሲያዊ ህገ መንግስት ዓላማ ደግሞ፣ ‘”ስልጣን የሁለት ጎንዮች ቢለዋ ነው፤ ስልጣን ያባልጋል፣ ፍጹማዊ ስልጣን ደግሞ ፍጹም ባለጌ ያደርጋል” (“Power corrupts, Absolute power corrupts absolutely”) የሚለውን ሃሳብ ተመርኩዞ፣  ለፖለቲካ ስልጣን ገደብ ማበጀት ነው። እንዲሁም፣  የሀገርና የህዝብ እጣ ፈንታም፣ ይሄን የሚወስኑ ትላልቅ የፓለቲካና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች፣ ፓሊሲዎችና አቅጣጫዎች ለጥቂት “እናውቃለን” ለሚሉ ወይንም “እውቀቱ” ሀብት ላላቸው ሊሂቃን (Elites, Oligarchs, and Artisocrats of talent and wealth) የሚተው ሳይሆን፣ እያንዳንዱ ዜጋ  ከታች ከቀበሌ/አካባባቢ  ጀምሮ በሚመርጣቸው ተወካዮቹ ንቁ ተሳታፊና ወሳኝ መሆን አለበት የሚልም ጭምር ነው።
ህገ መንግስት የህዝብ ቅቡልነትን (legitimacy) የሚያገኘው፣  ለዜጎችና ለህዝብ በሚሰጠው መብትና ስልጣን ይጀምራል።  ዴሞክራሲያዊ ስርአት የሚመነጨው ከዚህ መሰረታዊ (foundational) ሰነድ ከሆነ፣ በኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን ሁኔታ ስንመረምር፣ ትልቁ ፈተና የሚጀምረዉ፣ ሀገራችን የምትመራበት ህገ መንግስት የማነው? ለሚለው ጥያቄ ያለው መልስ፣ ህዝቡ በህገ – መንግስቱ ላይ ያለው  የባለቤትነት መብት (ከመረቀቁ አስከ ማፅደቁ ባለው ሂዳት) አልተከበረለትም የሚል መሆኑ ነው። እንደሚታወቀው፣ አሁን ያለው ህገ መንግስት  ሁሉም ኢትዮጵያዊ ተወያይቶበት የጸደቀ ሰነድ አይደለም።  ሕወሓት ይዘውረው በነበረው አገዛዝ፣ ህገ መንግስቱ  በህዝብ ላይ የተጫነ ነው፡፡ በህዝብ ተሳትፎና ፍቃድ አልፀደቀም፡፡ ስለዚህ፣ ዴሞክራሲያዊ ስርአት ይገንባ ከተባለ፣ አሁን በስራ ላይ የሚገኘው ህገ መንግስት በህዝብ ባለቤትነት የተረቀቀና የፀደቀ ህገ – መንግስት መተካት አለበት፡፡  ጤናማ ህገ መንግስት ሊኖር የሚችለው፣ ጤናማ መሰረት ላይ ሲቆም ብቻ ነው፡፡ የአንድ ህገ መንግስት መሰረት የረቀቀበትና የፀደቀበት ሂደት ነው፡፡
ተግዳሮት #3 ዲሞክራሲያዊ ፓለቲካና የማንነት/የብሄር ፓለቲካ (democratic politics vs Identity politics)
 ህገ መንግስቱን  መሰረት ያደረገው የፌደራል መዋቅር፣  የማንነት ግጭቶችን በመቀስቀስ ከፍተኛ ችግር እያስከተለ እንደሆነ  ይታወቃል። እሁንም በየአካባቢው የሚከሰቱ  ግጭቶች መጠናቸዉን እያሰፉና ብዙ የሰው ህይወት ይገኛሉ።  እነኚህ የማንነትና “የራሴ ክልል ይገባኛል” ጥያቄዎች፣ ለብዙ ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን ዜጎች መፈናቀል፣ ሞት፣ ጉስቁልና መንስኤ መሆናቸው ብቻ ሳይሆን፣ እጅግ ሰፍተውና ተለጥጠው፣ ቀደም ሲል ዞን የነበሩ መስተዳደሮች ተጨማሪ የ ‹‹ክልል መሆን ይገባኛል›› ጥያቄ እያቀረቡ መሆናቸዉ፣ የተግዳሮቱን ስፋትና ጥልቀት በገሀድ ያሳያሉ።
የማንነት ጥያቄ በሀገሪቷ የወደፊት አቅጣጫ፣ ላይ ከፍተኛ የሆነ ጫናና ተጽእኖ እየፈጠረ ነው። ይህ አስቸጋሪ ሁኔታ እንዲንሰራፋ ያደረገዉ ደግሞ፣ ላለፉት 27 አመታት በስራ ላይ ለማዋል የተሞከረው ፌደራላዊ  አወቃቀር ነው።  ይህ አወቃቀር፣ ክልሎች እርስ በእርስ ለመዋጋት እንዲዘጋጁ እስከማድረግ አድርሷል፡፡ በብዙ ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያዊያን በየክልሉ በሁለተኛና በሶስተኛ ዜግነት፣ አልፎም ከዚያም በታች በሆነ እስከፊ በደል ውስጥ ሆነው ከማህበራዊ፣ፓለቲካዊና፣ኢኮኖሚያዊ ሕይወት የተገለሉበትና  ለከፍተኛ መድሎና በደል የተጋለጡበት ሁኔታ ተፈጥሯል። አደጋው ተዘርዝሮ አያልቅም፡፡
 ከማነንት ጋር የሚነሱ አግባብ ያላቸውን ጥያቀዎች በስርአትና በአግባቡ መልስ ማግኘት እንደሚገባቸዉ እሙን ነዉ። ኢትዮጵያዊነት ተሰርቶ ያለቀ  የደቀቀ ሃገራዊ ማንነት አይደለም። በታሪክና በአገር ግንባታ ሂደት ሳቢያ ራሳቸውን በሀገራዊ ማንነት/ኢትዮጵያዊነት ውስጥ በበቂ ማየት ያልቻሉ የቋንቋ/የባህል ማህበረስቦች፣  በጎ እሴቶቻቸው የትልቁ ሀገራዊ ማንነት  አካል እንዲሆኑ ማድረግ አንዱ የመፍትሄ መንገድ ነው። ለምሳሌ፣ የኦሮምኛ ቋንቋ አንዱ የፌደራል ቋንቋ መሆን ይገባዋል። ልዩ ልዩ ብሄራዊ በአሎች፣ ብሄራዊ ምልክቶች፣ የህንጻዎች፣ የመንገዶች ስያሜዎች እሴቶቻቸውን የሚያንጸባርቁ እንዲሆኑ በማድረግ፣ ኢትዮጵያዊነት ሰፊና አቃፊ (inclusive) መደረግ አለበት።
 ሀገራዊው ማንነት/በኢትዮጵያዊነት ከአንድ ቋንቋና ባህል (በአመዛኙ ከግእዝ ስልጣኔ፣ ቋናቋና፣ የታሪክ አሻሮዎችና ትረካዎች)  ጋር ብቻ አቆራኝቶ የሚነገረውን ትርክት መቀነስ፣ እዉነተኛ፣ ሁሉን አቃፊና፣ በህብረ-ብሄራዊነት ላይ የተገነባ ኢትዮጵያዊ/ሀገራዊ ማንነት እንዲጠናከር ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደርጋል።  ‹‹እኔም አለሁበት፣ ተወክየበታለሁ›› የሚል ስሜት እንዲፈጥር ተግባራዊ ስራ መስራት ያስፈልጋል።
ተግዳሮት #4. ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ሁኔታዎች
በሃገራችን የተንሰራፋዉ ፓለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ፣ (ሞራላዊ፣ ስነልቦናዊ ኣንዲሁም ባህላዊ ሁኔታዎች) ችግሮች ስር የሰደዱና የረጅም ጊዜ ታሪክ ያላቸዉ ቢሆኑም፣ በሕወሃት/ኢህአዴግ አምባገነናዊ አገዛዝ ዘመን ይበልጥ ተጠናክረዉ ቀጥለዋል።
በሀገሪቱ ዉስጥ አብዛኛው ህዝብ በአስከፊ ድህነት ዉስጥ ይገኛል።. የወጣቱ የህብረተስብ ክፍል ከፍተኛ የስራ አጥነት፣ በሀብታምና በድሀው ህብረተስብ  መካከል በከፍተኛ መጠን እየጨመረ የመጣው የሀብት መጠን ልዩነት፣ የኢኮኖሚ ተቋማትና እንቅስቃሴዎች የጥቂቶችን ጥቅም ለማስጠበቅና ለማስቀጠል ሲባል የተቃኙ  መሆን፣ በከፍተኛ የህዝብና የሀገር ዘረፋ ጭምር ላለፉት 27  አመታት የተንሰራፋው ቅጥ ያጣ ኢፍትሀዊ የኢኮኖሚ ቅኝትና ተጓዳኝ የተሳሳቱ ፓሊሲዎች፣ የውቅቱ የሃገሪቱ ኢኮኖሚያዊ ዉጥንቅጥ መገለጫዎች ናቸዉ። እነኝህን ሁኔታዎች ማሰተካከል ረጅም ጊዜ የሚወስድ ቢሆንም፣  የአብዛኛዉን ህዝብ  ችግር ሊቀርፉ የሚችሉ ስራዎችን በፍጥነት መጀመር  አንገብጋቢ ጉዳይ የሆነበት ጊዜ ላይ ነን።
መንግስትና ልዩ ልዩ ባለድርሻዎች ትኩረት ሰጥተው ሊሰሩባቸው የሚገባው ሌላው ጉዳይ፣ አሁን ላይ ከተጋረጡብን ኢኮኖሚያዊ  ችግሮች ባሻገር፣ የነኚህን ችግሮችን መሰረታዊ መነሻ በማጥናት ለረዥም ጊዜ የሚያገለግለን ስትራቴጂክ የኢኮኖሚ  እቅዶችን መንደፍ ላይ ነው። ህዝብን ማእከል ያደረጉና አሳታፊ የሆኑ የልማት ፓሊሲዎችንና ሂደቶችን ካልተከተልን ወደ ዲሞክራሲ የሚደረገው ጉዞ ትልቅ አደጋ ላይ ይወድቃል።
ወደ ዲሞክራሲያዊ ስርአት ሽግግር ላይ የነበሩ ሀገሮች ተመልሰው ወደ አምባገነናዊ ስርአት የኋሊት የሄዱበት አንዱና ዋነኛው ምክንያት፣ የህዝቡን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች መፍትሄ ለመስጠት ባለመቻላቸው ነው። ስለዚህ ኢኮኖሚያዊ ሁኔታዎችን ማስተካከልና፣ ለህዝቡ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ችግሮች መፍትሄ የሚሆኑ አፋጣኝ እርምጃዎች መውሰዱ ወደ ዴሞክራሲያዊ ስርአት የሚደረገውን ሂደት በእጅጉ የሚያግዝ መሆኑ መዘንጋት የለበትም።
Filed in: Amharic