>

ኣስተያየት በ”ኣብራክ” ልብወለድ ድርሰት ላይ (በመርስዔ ኪዳን)

ኣስተያየት በ”ኣብራክ” ልብወለድ ድርሰት ላይ

በመርስዔ ኪዳን

ኣብራክ የተባለውን የሙሉጌታ ኣረጋዊ መጽሓፍ ኣነበብኩት። ኣገራችን ከሊቅ አስከደቂቅ በዘውጌ ብሄርተኝነት ተጠፍሮ ከዘውጉ፣ ወይ ከብሄሩ፣ ወይ ከጎሳው ኣሻግሮ ማሰብና ማለም ባልቻለበት ጊዜ ለንባብ መብቃቱ በጣም ጠቃሚ ሆኖ ኣግኝቸዋለሁ።

ኣብራክ ኣርካኒ ጫላ በተባለች ኦሮሞ ኢትዮጵያዊት አና ዋልታ ሓጎስ በተባለ ትግሬ ኢትዮጵያዊ መካከል ያለውን የፍቅር ግንኙነት ተመርኩዞ በዚህ ግዜ በኣገራችን የገነነውን የብሄርተኝነት ፖለቲካ ኣስከፊ ገጽታ ያሳየናል። ኣብራክ በኣርካኒ እና በዋልታ ዙሪያ ያሉ ቤተሰቦቻቸውን፣ ጓደኞቻቸውን፣ ዘመዶቻቸውን፣ የስራ ኣለቆቻቸውን እና ሰራተኞቻቸውን ጭምር በመጠቀም በኣገሪቷ ውስጥ ያለውን ስር የሰደደ ብሄርተኝነት እና የስርኣት ብልሹነት ፍንትው ኣድርጎ ያሳያል።

ኣብራክን ስታነብ

የዋልታ እናት ወ/ሮ ጽጌ እውነተኞቹን ለነፃነት እና ለእኩልነት የታገሉ ነገር ግን ያ የታገሉለት የነፃነት እና የእኩልነት ኣላማ በራስ ወዳዶች እና በጭፍን ካድሬዎች ተቀልብሶ ህዝብ ሲበደል አና ኣገር ስትታመስ እያዩ የሚብሰከሰኩ የህወሓት ታጋዮችን ወክላ ስትታመም ኣብረሃት ትታመማለህ፣ ስትቆጭ ኣብረሃት ትቆጫለህ፣ ስትታሰር ኣብረህ ትታሰራለህ።

የኣርከኒ ኣባት ኣቶ ጫላ ባንድ በኩል በወንድማቸው በኣቶ ታዬ ግፊት አንዲሁም በሚኖሩበት በኣምቦ ከተማ የመንግስት ባለስልጣናት ህዝቡ ላይ በሚፈጽሙት ወከባ እና በደል ወደ ኣክራሪ ኦሮሞ ብሄርተኝነት ሲጎትታቸው በሌላ በኩል ደግሞ ያሳለፉት ረጅም የስራ ልምድ እና በትምህርት ያገኙት እውቀት ላይ የልጆቻቸውና ዘመናዊ ኣስተሳሰብ ተጨምሮ ወደ ኣመክንዮ ሲጎትታቸው ኣንባቢውም ኣብረሻቸው ትዋልያለሽ።

የዋርካ ወንድም ኣቶ ክብረት እቺን ሃገር ብዙ ሺህ ወጣቶችን መስዋእት ኣድርጎ የመንግስት ስልጣንን ከተቆጣጠረው ድርጅት ውጪ ሌላ ሊመራት የማይችል የሚመስላቸው በድርጅቱ ርእዮት ተወልደው፣ በድርጅቱ ፕሮፓጋንዳ ተጠምቀው፣ በድርጅቱ ፍፁም ታማኝ ኣባልነት የጎለመሱ፣ ከድርጅቱ ውጪ ያለ ሁሉ ጠላት የሚመስላቸው የደነዘዙ የህወሓት ካድሬዎችን ወክሎ ባንድ በኩል ወንድሙንና እናቱን ሳይቀር ህዝብን ሲያንገላታ በሌላ በኩል ራሱ ለፍቶ በገነባው የድርጅት መዋቅር አስረኛ ሆኖ ሲንገላታ እያነበብክ ተበሳጭተህበት ከንደገና ታዝንለታለህ።

የዋልታና የክብረት እህት መብራት ደግሞ በድርጅቱ የፕሮፖጋንዳ ጫና አንዲሁም ድርጅቱ አያንዳንዱ ግለሰብን በሚያስገድድበት ማህበረሰባዊ ጫና በገፍ ወደኣባልነት የገቡትን ለኣለቆቻቸው ፍፁም ታዛዥና ተገዢ ለበታቾቻቸው ጨካኝ ኣለቃ፣ ለህዝብ ደግሞ ሰይጣንን አንኳ በሚያስንቅ መጠን ጭካኔ አና ጋጠወጥነት የሚያሳዩ የድል ኣጥቢያ ኣርበኛ ካድሬዎችን ወክላ በተለይ የህወሓት ካድሬዎች በትግራይ ህዝብ ላይ የሚያደርሱትን ኣስከፊ በደል ታሳይሃለች። የድርጅቱ ካድሬዎች በፕሮፓጋንዳና ግምገማ ደንዝዘው ሰብኣዊነታቸውን ኣጥተው ህዝቡን ሲያንገላቱ በገነቡት የኣፈና መዋቅር መልሰው ራሳቸው ሲንገላቱ ኣንብበህ በጣም ታዝንባቸዋለህ መልሰህ ደግሞ ታዝንላቸዋለህ።

የዋሁ እና ለጋሱ የኣርካኒ ኣጎት ኣቶ ታዬ ስርኣቱን እና የትግራይን ህዝብ ሳይለይ በትግሬ ጥላቻ ሲናውዝ። ጋዜጠኛው ሞቲ ሃሳቡን በመግለፁ ብቻ በሚጠላው ፖለቲከኛነት ተከሶ ለእስር ሲዳረግ። ሰለሞን የተባለው ሓቀኛ የህወሓት ባለስልጣን ራስ ወዳድና ጭፍን ባልደረቦቹ ህዝቡ ላይ የሚያደርሱት በደል እያሳዘነው ነገር ግን ያለውን ሁኔታ ለመቀየር ሊያደርገው የሚችለው ነገር ባለመኖሩ ተስፋ ቆርጦ ሲብከነከን፣ ከመሬታቸው ተፈናቅለው በገዛ መሬታቸው ላይ በተሰራ ቤት በዘበኝነት የተቀጠሩት የዋልታ ዘበኛ፣ ከትግራይ መጥተው በኣርካኒ አና በኦብሴ ቤት በቤት ሰራተኝነት የተቀጠሩት ሴቶች፣ የዋልታ ጓደኛ በቀለ እና ሌሎች ገፀ ባህሪያት የሚያደርጉት መስተጋብር በህዝቡ ውስጥ ያለውን የተለያየ ኣስተሳሰብ ትዳስሳለህ።

ሙሉጌታ ኣረጋዊ በኣብራክ ውስጥ በጊዜው ያለውን ነባራዊ ሁኔታ በመፅሓፉ ላይ ፍንትው ኣድርጎ ኣሳይቶና። እንደ ሀዲስ ኣለማየሁ የዛሬ ችግራችንን ዛሬ ነግሮናል። እንደ በዓሉ ግርማ በራሱ ህይወት ዙሪያ የራሱን አይታ ተርኮልናል። ነገር ግን ድርሰቱ በሀዲስ እና በበዓሉ ድርሰቶች ውስጥ የምናየው ስዕላዊነት ይጎድለዋል። በመጀምሪያው ገፆች ላይ የኣርካኒ ወላጆች ቤትን በጥሩ ስዕላዊ ኣገላልፅ የሳለልን ሲሆን ከዚያ በሁዋላ ያሉትን መችየቶች በቅጡ ኣልሳላቸውም። ከኣምቦ ከተማ በስተቀር ሌሎች ከተሞችን አንደ ግኡዝ ኣካል ስማቸውን ከመጥቀስ በስተቀር ህያው ባህሪያቸውን ኣልተረከልንም። ለምሳሌ መቀሌ በድርሰቱ ውስጥ የትርክቱ  ዋነኛ ኣካል ብትሆንም የመቀሌን ታሪክ፣ መልክኣምድር እንዲሁም የኗሪዎቿን ባህል እና ኣኗኗር በቅጡ ኣልሳለልንም። በተለይም የህዝቧን ሰው ኣፍቃሪነትና አንግዳ ኣክባሪነት ሳይተርክ ማለፉ መቀሌን ለሚያውቃት ሰው ኣይዋጥለትም። ድርሰቱ የገፀባህሪያቱን ሃሳብ በቀላልና ውብ ሁኔታ የሳለልንን ያክል መችየቱንም ኣስውቦ ቢገልፅልን ይበልጥ መሳጭ ይሆን ነበር ብዬ ኣስባለሁ።

በዚህ ሁላችንም በኣክራሪ ብሄርተኝነት ተለክፈን እርስ በራስ በምንራኮትበት ጊዜ የዚህች መፅሓፍ ለኣንባቢ መድረስ በጣም ኣስፈላጊ ነው። ኣንድ ወዳጄ የኣስቴር የፍቅር ዘፈኖች ፍቅር ለያዛቸው ሰዎች መድሃኒት ይሆን ዘንድ በየመድሃኒት ቤቱ መሽጥ ኣለበት ይለኝ ነበር አኔ ደግሞ ኣክራሪ ብሄርተኝነት የተጠናወታቸው ሰዎች ኣብራክን ኣንብበው ይፈወሱ እላለሁ።

መርስዔ ኪዳን

ከሜኔሶታ፡ ሃገረ ኣሜሪካ

mersea.kidan@gmail.com

Filed in: Amharic