>

“እኔና ጎሳዬ የሰፈርንበት መሬት የግል ንብረታችን ነው!” ማለት የሀገሪቱን ሉዓላዊነት መዳፈር ነው!!! (ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ)

“እኔና ጎሳዬ የሰፈርንበት መሬት የግል ንብረታችን ነው!” ማለት የሀገሪቱን ሉዓላዊነት መዳፈር ነው!!!
ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ
ኦነጎች
አንድ ሰው ብዙ ማንነቶች አሉት። አንድ የሚያደርገን ግን ኢትዮጵያዊነት የሚባለው ማንነታችን ነው።  ማንነት እንደ እሳት ጉዳትም ጥቅምም አለው። ጥቅሙ ማቀራረቡ፥ ማዛመዱ፥ ነው። በጉዳቱ በኩል፥ ያለያየናል፤ የክልል ፖለቲካን ያመጣብን ማንነት ነው። አለያየን፤ አፋጀን፤ እያፋጀንም ነው። በቅርብ ጊዜ፥ አንድ የኦሮሞ ፖለቲከኛ፥ “ትግላችን ለማንነታችን ነው” ሲል ሰማሁት። ማንነት ያታግላል፥ ያጋድላል ማለቱ ነው። “ትግላችን ለማንነታችን ነው” ሲል “ማንነታችንን ለማስከበር ነው” ማለቱ መሰለኝ።  ማንነቱ ተዋርዶ ከሆነ፥ ማስከበር የሚጠበቅበት ነው። ሆኖም፥ “አንድ ነን፤ አንድ እንሁን” ስንል፥ አንድነት ሊታገሉት፥ ሊቃወሙትር  የሚገባ የማንነት ጠላት ነው ማለት ነው ወይ?
በአማርኛ “ማዋረድ” ማለት “አንድን ሰው ከማንነቱ በታች ዝቅ ማድረግ” ማለት ነው። “የሚገባውን የማንነት ክብር መንሣት” ማለት ነው። የሰው ልጅ ባርነትን፥ በቅኝ መገዛትን፥ በሕግ ፊት እኩል አለመታየትን እስከሞት ድረስ የሚታገላቸው ማንነቱ  ስለተነካበት ነው።  እንዲህ ከሆነ፥ ኦነጎች ጦር የመዘዙት፣ ማንነታቸውን አስከብረው በኦሮሞአዊ  ማንነታቸው ሕይወትን ለመግፋት የሚችሉት በአንዲት ኢትዮጵያ ጥግ ስር ሳይሆን፥ የሰፈሩበትን መሬት ለራሳቸው ብቻ አድርገው ሲኖሩበት እንደሆነ ቢያምኑ ነው። ለምን እንደዚህ ያምናሉ? ሕዝቦች ማንነታቸው ሳይነካባቸው በአንድ ሀገር ውስጥ በአንድነት መኖር አይችሉም ወይ? መዘየድ ከቻሉ፣ ይችላሉ። ይህ ጽሑፍ የሚደመድመው በዚያ ዘዴ ይሆናል።
ትግላችን ለማንነታችን ነው
ብንቀበለውም ባንቀበለውም፥ ብዙ ኢትዮጵያውያን፥ “ትግላችን ለማንነታችን ነው” ቢሉ፥ እንዲህ ከሚል አስተሳሰብ ላይ ለመድረስ ምክንያት አላቸው። የኢትዮጵያ አንድነት በአንድ ነገድ (በአማራ) ማንነት ላይ የተመሠረተ ስለ ሆነ፥ ሌሎች ነገዶችና ጎሳዎች በኢትዮጵያዊ አንድነት ላይ መደመር፣ የራሳቸውን ማንነት አውልቀው አንድነት የተመሠረተበትን (የአማራን) ማንነትን እንዲለብሱ እንደሚያስገድዳቸው ይሰማቸዋል። እንዲህ ከሆነ፥ አንድነት የማንነት ጠላት የሆነውን ያህል፥ ማንነት የአንድነታችን ጠላት ሊሆን ነው።
ማንነት ምንድን ነው? ማንነት ራስነት ነው። አንድ ሰው ራሱን ሳያውቅ ቢቀር፣ ከታላቅ ጭንቅ ላይ ይወድቃል። ዛሬ በጉዲፈቻ ስለሚያድጉ ልጆች አዲሱ ፍልስፍና፣ ከሥጋ ወላጆቻቸው ጋር ያላቸውን ግንኙነት እንዳይቋረጥ ማድረግ ነው። ማንነታቸውን መደበቅ፥ እንዲያውም ነፍስ እስኪያውቁ ድረስ ማቆየት ስሜታቸውን ይነካል፤ ማንነታቸውን ያናጋል ይባላል። አንድ ሰው ማን እንደሆነ የሚያውቀው ራሱ ብቻ ነው። የሱን ማንነት ሌሎቻችን የምናውቀው እሱ ነግሮን ነው። አለዚያ፥ ያልሆነውን “ነው” እያልን ማማት ይመጣል።
የማኅበረሰብ ጥናት ሊቃውንት እንደሚሉት፥ የማንነት መገለጫ ብዙ ነው፤ ዘር፥ ቋንቋ፥ ሃይማኖት፥ ቀየ (ጎጥ) ዋና ዋናዎቹ ናቸው። ከነዚህ ውስጥ ከሃይማኖት በቀር ሁሉም የማይቀሩና ከፖለቲካ አንጻር ግን ዋጋ ቢሶች ናቸው። ሃይማኖት የሌላቸው ብዙ ሰዎች አሉ። ዘር፥ ቋንቋ፥ ቀየ (ጎጥ) የሌላቸው ሰዎች ግን የሉም። ሁሉም፥ ያሉና በየኋላ-ቀር ኅብረተ ሰብ የፖለቲካ በሽታዎች ሲሆኑ እናያቸዋለን። በሽታው፣ ጤነኛውና የሠለጠነው ዓለም የዘመተበት “ዘረኝነት” የሚባለው ነው። “የኔ ዘር ያልሆነ፥ የኔን ቋንቋ ያልተናገረ፥ እንደኔ ያላመለከ፥ የቀየ ልጅ ያልሆነ ወገኔ አይደለም፤ እንዲያውም፥ ተቃዋሚ ባለጋራዬ  ነው” ይላሉ። የኢትዮጵያ መንግሥት ጎሳዎች የሰፈሩበትን ቀየ እንደ አራዊት ከልሎ ስለሰጣቸው፥ ሌላ ሰው (በገዛ አገሩ) አይድረስብን ይላሉ። ከቤቱ እያስወጡ ያባርሩታል፤ ይገድሉታል።
ክልልን የሙጥኝ የሚሉ ወገኖች “ዘራችን አንድ ነው” ብለው ያምናሉ። ግን፣ ሊሰሙት አይፈልጉም እንጂ፣ ይህን እምነታቸውን ውድቅ የሚያደርግ እውነተኛ ታሪክ አለን። አንድ ሕዝብ ሆነን በአንድ መንግሥት ሥር አብረን የኖርንበት ዘመን እጅግ ረጅም ስለሆነ፥ ደማችንን ደባልቆታል። ስለዚህ፥ ዘር ማንነታችንን የመወሰን ኀይሉ ተንኗል። የቀረው ቀፎው ብቻ ነው። ባዶውን ቀፎ ተሸክመን ነው ማር አለበት የምንለው። ዛሬ፣ ማንነታችንን የሚወስነው ስለ ዘር ያለን እምነት እንጂ፣ ራሱ ዘር አይደለም። ይህን ለማስረዳት  ወደኋላ ሄደን የታሪክ ምንጮችን መጎርጎር አያስፈልገንም። ከአማራና ከኦሮሞ ጋብቻ የተወለደ ልጅ፣ አክራሪ አማራ ወይም አክራሪ ኦሮሞ ሲሆን እያየን ነው። ክልልን የሙጥኝ ያሉ ወገኖች ለመዋለድ ዋጋ የማይሰጡት ስለዚህ ነው። ይህ እውነታ፥ “ተዋልደናል እኮ! አንድ ነን እኮ!” የሚለውን የመከራከሪያ ጭብጣችንን በግላጭ ውድቅ ያደርግብናል። መዋለድ ማንነትንን አይወስንም።
እንዴት አንድ ሆነን መኖር አንችላለን
ታዲያ እንዴት ነው ያንን የምናምንበትን ማንነታችንን እንደያዝን፥ ሳንካለል አንድ ሕዝብ ሆነን ለመኖር የምንችለው? እዚህ ላይ አንዳንድ ነጥቦች ቢነሡ ይረዳሉ፤
አንዱ፥  ማንነት ከሰፈሩበት ቀየ ጋር ያለውን ግንኙነት በሕግ ማስተካከል ነው።  አንድ ሀገር የሀገሬው ሁሉ መብት ነች። አንድ ሰው የሰፈረው በእንዲህ ያለ ቀየ ስለሆነ፥ የዚያ ቀየ ሰው መሆኑን ማንም ሊክድበት ወይም ሊያስጥለው አይችልም። “የዚያ ሰፈር ሰው ነኝ” ቢል እውነትነት ያለው መብቱ ነው። “እኔና ጎሳዬ የሰፈርንበት መሬት የግል ንብረታችን ነው” ማለት ግን ፣የሀገሪቱን ሉዓላዊነት መዳፈር ነው። አገር ጠባቂ መንግሥት ይኸንን አገር ማፍረስን ማቆም ግዴታው ነው። መሬቱ የወል እንጂ የሰፋሪዎቹ የግል ንብረት አይደለም። “እዚያ ያልተወለደ ሌላ ሰው አይስፈርበት” ማለት አይቻልም። የሰው መብት መጣስ ነው።  ከዚያም አልፎ ይሄዳል፤ ኢትዮጵያን እንዳንድ ሀገር አለመቀበል ነው።
ሁለተኛው ነጥብ፥ ጠቅላይ ሚንስትሩ ስለኢትዮጵያ የጦር ሠራዊት ማንነት የነገሩን ነው። የኢትዮጵያን የጦር ሠራዊት በጎሳ አባላት የተሰባጠረ አድርጎ ስላዋቀረው፥ “ኢትዮጵያዊነት የሚታይበት አወቃቀር” ብሎ አድንቆታል።  “ራሱን የቻለ የትግራይ፥ የአማራ፥ የኦሮሞ . . . ክልል መፍጠር ኢትዮጵያዊነት የሚታይበት አወቃቀር አይደለም” ብሎ መንቀፉ ነው። እግዚአብሔር ይባርከው። እምነቱን እንዲፈጽም ዘዴውንና ድፍረቱን ይስጠው።
ሦስተኛው ሊነሣ የሚገባው ነጥብ፣ በኢትዮጵያ ውስጥ አንድ ነገድ ብቻ ለብቻው የሚኖርበት ሰፊ ቦታ አለመኖሩ ነው። “ራሱን የቻለ የትግራይ፥ የአማራ፥ የኦሮሞ . . . ክልል መፍጠር” የሌለ ነገር መፍጠር ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ አንድ ነገድ ብቻ የሚኖርበት መንደር እንጂ ሰፈር የለም። ኢሕአዴግ ለአንድ ጎሳ በዳረገው ቦታ የሌላ ጎሳ አባላት አሉበት። ስለዚህ፥ አንድን አካባቢ ከልሎ ለትልቁ ነገድ መስጠት፣ አናሳ ሕዝቦችን በገዛ አገራቸው ባይተዋር ማድረግ ነው።  አንድ ቦታ ላይ ለመስፈር አንዱ ከሌላው የበለጠ ወይም ያነሰ መብት የለውም። በሀገር ሕግ ፊት፣ የአናሳ ጎሳ አባል የሆኑትን፣ ወይም ለትልቅ ጎሳ ከተሰጠ ክልል መጥተው አናሳ ጎሳ የሆኑትን ሰዎች የሰፈራ መብት መጣስ፥ በመንግሥት ተባባሪነትር የደካማ ሰውን ንብረት የመቀማት ያህል ይቈጠራል።
አንድን ክፍለ ሀገር በዘር ወይም በትልቁ ቋንቋ ከልሎ በዚያ ቋንቋ  የሚተዳደር ክልላዊ መንግሥት እንዲቋቋም መፍቀድ፥ መሪውንም “ፕሬዚዴንት” ማለት፥ በሕግ መከልከል አለበት።  ከተፈቀደ፥
አንደኛ፥ አንድ ሀገር  ውስጥ ሌላ ሀገር መፍጠር ነው።
ሁለተኛ፥ በዚያ ክልል የሚኖሩ የክልሉን ቋንቋ የማያውቁትን  እጅግ ብዙ ኢትዮጵያውያንን ከክልሉ አስተዳደር ጋር መገናኛ መንገድ ማሳጣት ነው።
ለዚህ ተቃውሞዬ የሚሰጠው አጭሩ መልስ፥ “በክልሉ ከኖሩ የክልሉን ቋንቋ ይማሩ” ነው። ለምንድን ነው ሰማንያ ቋንቋዎች የሚነገሩባት አገር ወስጥ፥ የጋራ ማንነትና የጋራ የሆነ ቋንቋ  እያለን፥ ክልላውያን  አስተዳደሮች የፌዴራል መንግሥት በሚሠራበት ቋንቋ የማይሠሩት? ለአንድ ሀገር አንድ ቋንቋና አንድ ባንዲራ መኖር ዓለም የሚሠራበት የአንድ አገርነት ምልክት ናቸው። አማርኛ በአራቱም ማዕዘነ ኢትዮጵያ ያለውን ሕዝብና የሀገሪቱን መንግሥት ሲያገለግል ዘመናት አልፈዋል። ትግራይ ውስጥ የተጻፉ የግዕዝ የብራና መጻሕፍት ውስጥ የሚገኙት የኅዳግ ማስታወሻዎች የተጻፉት በአማርኛ ነው። የደቡብ ጎሳዎች እርስ በርሳቸውም ሆነ ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ጋር የሚገናኙት በአማርኛ ነው። የኢትዮጵያ መንግሥት በአማርኛ መሥራት ከጀመረ ከዘመናት በኋላ፥ ለምንድን ነው ዛሬ የጥንታውያንነታችንን ምልክት ችግር ሲገጥመው መንግሥት ችላ የሚለው?
የሚያዛምዱን የጋራ ማንነት ከምላቸው ውስጥ አንዱና ዋነኛው ኢትዮጵያዊነት ነው። ለኢትዮጵያዊነት የተለያየ ትርጕም እንሰጠው ይሆናል እንጂ (የውጪ አገር ሰው ካልሆነ) ኢትዮጵያ ውስጥ በቅሎ ወይም ኢትዮጵያ ውስጥ ከበቀሉ ቤተ ሰቦች ተወልዶ፥ “ኢትዮጵያዊነት የለብኝም” ማለት አይቻልም። እኛ የተወለድነው፥ ምድር በሀገርነት ተከፋፍላ ካለቀችና፣ አባቶቻችን የኛን ድርሻ ኢትዮጵያ የሚል ስም ካወጡላት፥ መገናኛቸውን አማርኛ ካደረጉ በኋላ ነው። አንድ ኢትዮጵያዊ እሌላ አገር ሄዶ ዜግነቱን ቢለውጥ እንኳን መነሻውን ማንነት ሊፍቀው አይችልም። እርግጥ የምድሪቱን ኢትዮጵያዊነት በመካድ የራሱን ኢትዮጵያዊነት አብሮ መካድ ይችላል። ይኸ ዓይነት ክሕደት፣ ሸፍጥ (ማንነትን መደበቅ) እንጂ ክሕደት አይባልም።
ችላ ልንለው የማይገባ ምክንያት
ኢትዮጵያዊነትን የማይፈልጉ “ኢትዮጵያውያን” ችላ ልንለው የማይገባ ምክንያት አላቸው። በግላጭ ተወያይተን ካልተረታታን ቅሬታው በሽታ ሆኖ ሲያመረቃ ይኖራል። እኛ እንጀምረውና፥ እንደሰማሁት ከሆነ፥ የሚሉት፥ “አማሮች ኢትዮጵያዊነትን በአማራነት ስለለወጡት፥ ኢትዮጵያዊነትን መቀበል የራስን ማንነት ትቶ የአማራን ማንነት መቀበል ይሆናል” ነው። ኢትዮጵያዊነት አማርኛ ተናጋሪ መሆንን ያስገድዳል ማለታቸው ነው። የሚሰጣቸው መልስ አጥጋቢ መሆን አለበት። ምንድን ነው እሱ?
አንደኛ፥ ይህ ችግር የተፈጠረው ኢትዮጵያ ላይ ብቻ አይደለም። ብዙ ሕዝቦች (ነገዶች፥ ጎሳዎች) በሰፈሩበት ምድር ላይ መንግሥት ያቋቋሙ ሕዝቦችን  ሁሉ የገጠማቸው ችግር ነው።  የፈቱትም ኢትዮጵያ በሂደት በፈታችበት መንገድ ነው። አማርኛን የምንማረው የመንግሥቱን የመሥሪያ ቋንቋ ለማወቅና የመንግሥቱ ተሳታፊ ለመሆን፥ በዚያውም ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ጋር ለመግባባት እንጂ፥ የአማሮችን ቋንቋ  መማር አምሮን አይደለም።  የዓለም ሕዝብ እንግሊዝኛ የሚማረው እንግሊዞች ወይም አሜሪካውያን ለመሆን አምሮት አይደለም። አስገዳጁ ሁኔታ አስፈላጊነቱ ነው።
የመንግሥት አካል ለመሆን የራስን ማንነት በሌላ ማንነት መተካት አያስፈልግም። ኢትዮጵያዊ ለመሆን የራስን ማንነት በሌላ ማንነት መተካት አያስፈልግም ማለት ነው። ኦሮሞነትን፥ ጉራጌነትን፥ ጉሙዝነትን፥ ትግሬነትን፥ አማራነትን . . . እንደያዙ ኢትዮጵያዊ መሆን ይቻላል።  አሜሪካውያን የሆኑ ብዙ ኦሮሞዎች፥ አማራዎች፥ ጉራጌዎች አውቃለሁ። “አሜሪካውያን በመሆናችን ማንነታችን ተነካ” ሲሉ ሰምቼ አላውቅም። በቋንቋችን (በግዕዝ ሳይቀር) እናስቀድሳለን፤ በመስጊድ፥ በምኵራብ እንሰግዳለን። “የምንኖረው ፈረንጅ ባቋቋመው መንግሥት ሥር ካልሆነ ማንነታችን ይነካል” አይባልም፤ ነውር ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ ሁሉም በቋንቋው ያመልካል፤ በቋንቋው ይጽፋል። የሸሪዓ ሕግ ሳይቀር ይከበር ነበር። የማንነት ክብር የሚጠበቀው በቋንቋው መንግሥት ሲቋቋምበት ብቻ አይደለም። ፍላጎታቸው ኤምፓየር ለማቋቋም ከሆነ፥ ምድሩ ሁሉ መንግሥታት ተቋቁመውበታል።
ሁለተኛ፥ በአንድ ምድር ላይ መንግሥት ሲቋቋም፥ መገናኛ የሚሆነው ቋንቋ  የመንግሥት መሥራቾቹና የአስተማሪዎቹ  ቋንቋ ነው። የኢትዮጵያን መንግሥት ያቋቋሙት ጉሙዞች ቢሆኑ ኖሮ፥ ዛሬ የመንግሥታችን ቋንቋ ጉሙዝኛ ይሆን ነበር። ጉሙዝኛን የመንግሥት ቋንቋ ማድረግና መቀበል የራስን ማንነት መካድ አይሆንም። ፍላጎቱና ለአንድነት መጓጓት ካለ ሰማንያ ጎሳዎች ቋንቋቸውን እያዳበሩ የፌዴራሉን ቋንቋ  መማርና የአካባቢያቸውን አስተዳደር ቢያካሂዱበት አይቸግራቸውም። ሰማንያ ጎሳዎችን የሚያገናኝ ሁሉም የሚማሩት አንድ ተጨማሪ ቋንቋ ያስፈልጋል። ያ ቋንቋ አማርኛ እንዲሆን ሁኔታችን ያስገድደናል።
ይህ መልስ በቍጥራቸው ብዛት የሚተማመኑትን ኦሮሞዎች ላያረካቸው ይችላል። መመዘኛው የቍጥር ብዛት ይመስላቸዋል። እንግሊዝኛ የብዙ አገሮች መንግሥታት ቋንቋ የሆነው እዚያ አገር እንግሊዞች በብዛት ስላሉ አይደለም። በተለየም ከፍተኛ የሚባለውን ባህል (የኢትዮጵያን ሥነ ጽሑፍ) የአማሮችና የትግሬዎች ብቻ ስለሚያደርጉት፥ መከባበሪያ በመሆን ፈንታ መናናቂያ አድርገውታል። ግን ብናውቅበት፥ በዘር ከመደባለቃችን የበለጠ አንድ በሚያደርገን በባህል ተደባልቀናል። የወረስነው ሥነ ጽሑፋችንም በግዕዝና በአማርኛ ይሁን እንጂ፥ የጎሳዎች አስተዋፅኦ ነው። የሌሎቹ ቋንቋዎች ተጽዕኖ የአማርኛን ሴማዊ ቋንቋነት ከጥያቄ ላይ ጥሎታል። ተጽዕኖ ማለት፣ አማርኛ የሌሎችን ባህል በመምጠጥ ማንነቱን ለውጧል ማለት ነው።
ሌላው ነጥብ፥ አንዳንዶቻችንን “አማራ የሚባል ዘር የለም” እስክንል ያደረሰን ታሪክ ነው። ጥናቱ የሚቻል ቢሆንና ቢደረግ፥ ዛሬ “አማራ ነን” የምንል ኢትዮጵያውያን ከጥንቶቹ አማሮች የመጣንና በዘመን ብዛት አማራ የሆንነው (Amharicized) በቍጥር ብንነጻጸር ከአንድ ለዐሥር (1:10) እንደማንበልጥ እገምታለሁ። ሁላችንም የዛሬዎቹ አማሮች  ከጥንቶቹ አማሮች የመጣን አማሮች አይደለንም። ይህን ሁሉ የሚያኰራንን የጋራ ታሪክ ለአንድነታችን ማጠንከርያ በማዋል  ፈንታ፣ ቀፎ ማንነት ተሸክመን ስናባክነው እንገኛለን።
ጠቅላይ ሚንስትራችን “ችግራችንን የሚያጎላ እንጂ መፍትሔ የሚያቀርብ የለም” ይለናል። እንዲህ ከሆነ፥ እሱም ሆነ ጉዳዩን እንዲያጠና ያቋቋመው ኮሚቴ የሚመለከተው መፍትሔ ላቅርብ። ክልልን የምንፈልገው በባህላችን ለመኖር (ማንነታችንን ለማስከበር) ከሆነ፥ አንድነታችንን ሳያናጋ ልንጠቀምበት የምንችልበት ሁለት የአከፋፈል ሥርዓቶች መፍጠር ነው፥ አንዱ የባህል ክልል (cultural zones) ሌላው የአስተዳደር ክፍል (administrative regions)። የባህሉ ክልል የሚዳሰስ ድምበር አይኖረውም። ጎሳዎቹ የሚኖሩበት ሁሉ ግዛቱ ይሆናል። የቋንቋው ጥናት፥ የቋንቋው መጻሕፍት፥ ሙዚቃ፥ እስክስታ፥ የባህል ጥናት፥  ወዘተ. ባለባህሉ (ነገዱ) ካለበት ቦታ ሁሉ ይዳረሳል። ትምህርት ቤት ይከፈታል። ለዚህ ሁሉ ኀላፊነቱ የባህል ክልል የሚመርጣቸው ባለሥልጣኖች ይሆናል። የCivic Society ሥራ ስለሆነ፥ መንግሥት በምንም መንገድ አይገባበትም። የአስተዳደር ክፍል የሚመለከተው ሀገሪቱ በኢኮኖሚ የምትዳብርበትን፥ ከማእከላዊው መንግሥት ጋር ስላለው ግንኙነት ይሆናል። የሚካሄደው በፖለቲከኞች ይሆናል። በሌላ አገርም (ለምሳሌ፥ በአሜሪካ፥ በህንድ) የሚሠራበት ዘዴ ነው። አሜሪካን አገር መንግሥቱ የሚተዳደረው በእንግሊዝኛ ሆኖ ሳለ፥ ሁሉም ማኅበራዊ ኑሮውን የሚያካሂደው በቋንቋው ነው–በግሪክኛ፥ በዐረቢኛ፥ በአማርኛ፥ ወዘተ.።
ሐሳቡን መንግሥት ከተስማማበት ከግቡ ለማድረስ በሥልጣኑ ለመጠቀም መብት አለው። ኳስ ካልተመታች ድል አታስገኝም።
Filed in: Amharic