>
5:13 pm - Monday April 20, 8731

እነበረከት ለሌሎች የነፈጉትን መብት ልንነፍጋቸው አይገባም!!! (መስፍን ነጋሽ)

እነበረከት ለሌሎች የነፈጉትን መብት ልንነፍጋቸው አይገባም!!!
መስፍን ነጋሽ
* በረከት ጋዜጠኞችንና ፖለቲከኞችን አድብቶ የሚከላ ሾተላይ ነበር ያም ሆኖ!!!
 
ዘመኑ ባይቀየር ኖሮ፣ የበረከት ስምኦን መታሰር ከመለስ ሞት ያላነሰ ዜና ይሆን ነበር። ልዩነቱ፥ መለስ ዕድለኛ ነው። ይኼኛው ቢያንስ ለጊዜው ዕድለ ቢስ ይመስላል።
ለብዙ ሰው፥ ቁም ነገሩ በረከት የታሰረበት ምክንያት አይደለም። መታሰሩ ራሱ፣ ለመታሰር መቻሉ ራሱ ነው ብርቁ። ሰውየው ክፉ ፖለቲካኛ ነበር። አፈናንና ሰቆቃን እንደ ጥሩ የፖለቲካ መሣሪያዎች ቆጥሮ፣ በአጠቃቀማቸው ላይ ለመራቀቅ የሞከረ ሰው አድርጌ እቆጥረዋለሁ። አፈናውን “ያራቀቀው” በመሰለው መጠን የሆነ የላቀ ተልእኮ እንዳሳካ በመቁጠር እየተደሰት ሳይኖር አልቀረም።  ይህን ሁሉ ሲያደርግም፣ አገሩንና ሕዝቡን “በቅንነት” እያገለገል እንደሆነ ለማስረዳት የሚሞክር ራሱን ጠይቆ የማያውቅ ሰው ይመስለኛል። ጋዜጠኞችንና ፖለቲከኞችን አድብቶ የሚከላ ሾተላይ ነበር። ዝርዝሩ ብዙ ነው።
እንዲያም ቢሆን፣ አሁን ስለታሰረ ከሚደሰቱት ወገን አይደለሁም። በእስሩና በክስ ሒደቱም ሰብአዊ ክብሩን የሚነካ ተግባር እንዳይፈጸምበት አጥብቆ ማሳሰብ ይገባል። ያለንበት የሽግግር ወቅት ለእውነተኛ ፍትሕና ርትእ ብዙ የተመቻቸ ባይሆንም፣ የተጠርጣሪነት መብቱ ሙሉ በሙሉ ተጠብቆለት፣ ቢያንስ በፍርድ ቤቱ አደባባይ እንደንጹሕ የመቆጠር መብቱ ሳይገፈፍ፣ አካላዊ ጥቃት እንዳይደርስበት ጥበቃ ተደርጎለት የፍርድ ሒደቱ መካሔድ ይኖርበታል። ይህ ለእርሱ ብቻ ሳይሆን ለሁሉም ተጠርጣሪዎች ሊጠበቅላቸው የሚገባ ነው። እነበረከት ለሌሎች የነፈጉትን መብት ልንነፍጋቸው አይገባም። ስሕተት በስሕተት፣ ክፋትም በክፋት አይታረምም።
Filed in: Amharic