>
5:13 pm - Wednesday April 19, 8580

ይድረስ ለአቶ ጌታቸው ረዳ! (መስፍን ማሞ ተሰማ)

ይድረስ ለአቶ ጌታቸው ረዳ!

መስፍን ማሞ ተሰማ

አቶ ጌታቸው ሆይ – ዕውን የነበረከት እስር ደንቆሃል? ወይስ ነግ በኔ ታይቶህ ደብሮሃል? አዎ ባንተ ልኬት እነ በረከት በሙስናው ዝቅተኛ ወለል ላይ የሚገኙ ናቸውና የታሰሩበት ምክንያት ፖለቲካዊ ነው ብለሃል። (ይገርማል ደሞ የዝርፊያቸውንም ልክ ታውቃለህ ማለት ነው?) ለማንኛውም እስራቸው ፖለቲካዊ መሆኑን ለማን ነው የምትናገረው? ለራስህ ከሆነ ዕውነት ብለሃል። አንተና በረከት ሞክሼህ ጌታቸውና ሁላችሁ በህወሃት አቁማዳ ውስጥ ሆናችሁ ከኢኮኖሚው በባሰ በፖለቲካው የሰራችሁትን ሰቆቃ ታውቃለህና!

አዎ፤ እንኴን እኛ ዓለም በረከትን የሚያውቀው በዘር አጥፊነቱ <በናዚስት ጎብልስነቱ> ነው። ስለ በረከት <ናዚስታዊ ተግባር> (የኛን ዝርዝር ለጊዜው አቆይተን) የአውሮፓ ፓርላማን ስመ ጥር አባል ወ/ሮ አና ጎሜዝን ዋቢ እንሰጥሃለን። ክሱ ከምንጠበቀው ከፍታ ላይ እስኪወጣ <አይነኬው> በረከት <በኢኮኖሚም> ቢሆን መታሰሩ ወደናንተ መቅረባችን ነውና እኛ ደስ ብሎናል።

ደግሞምኮ መንግሥት ነኝ ብሎ ሀገር መዝረፍ የድሃ ጥሪት መግፈፍ ያስቀፈድዳል – በተዘረፈ ሀብትና ንብረት ክምችት መለኪያችሁ ወለልም ላይ ሆንክ ጣራ ላይ!! ዘንድሮ ከነጔዶችህ አይቀርላችሁም። ረስተኸው ከሆነ <እሳትና ጭድ> በሚለው የዘር ዕልቂት ፕሮፓጋንዳህ ትጠየቅበታለህ/ትጠየቁበታላችሁ! ለሁሉም ጊዜ አለው – እንዲል መፅሐፉ።

በነገራችን ላይ የሚከተለውን አባባልህን አንተና ግብራበሮችህ ተዋንያን ለነበራችሁበት ዘመነ ህወሃት የተናገርካት ስላቅ ነች ብዬ አምናለሁ። «አንድ ሰው የፖለቲካ እንቅስቃሴ የሚያደርግ ወይም የክልል ወይም የፌዴራል መንግሥትን የሚተች በመሆኑ ለእስር የሚዳረግ ከሆነ ተገቢውን ፍትህ ያገኛል ብሎ መጠበቅ የዋህነት ነው።» ጉድ ነሽ የአንኮበር ቅጠል ከማቃጠልሽ የመለብለብሽ – አሉ! አይ የድሮው ኮሙኒኬሽን ሃላፊ – የሃያ ሰባት ዓመት ስራችሁንኮ ነው በቢቢሲ አማርኛ በኩል ያወጅከው!!! ለቀባሪው አረዱት – እንዲሉ። ጉድኮ ነው ባካችሁ «አፍ ሲያመልጥ ፀጉር ሲመለጥ አይታወቅም»  ደግሞ ሰነባብቶ ተረኛው ማናችሁ ትሆኑ? መቼም ዘንድሮ ዜናው ሁሉ ለእኛ ቸር ለእናንተ መርዶ ነው!!

ፈጣሪ ኢትዮጵያንና ህዝቧን ይታደግ!

ፍትህ ፍትህን በረገጧት ሁሉ ላይ ትስፈን!

ጥር 2011 ዓ/ም (ጃንዋሪ 2019)

ሲድኒ አውስትራሊያ

Filed in: Amharic