>
8:45 am - Saturday November 26, 2022

የከባዱ እስረኛ ማስታወሻ (ሳምሶን ጌታቸው)

የከባዱ እስረኛ ማስታወሻ
ሳምሶን ጌታቸው
* ….ሳላስበው “የኢትዮጵያ አምላክ ይባርካችሁ!” አልኳቸው። በዕድሜዬም እንዲህ ብዬ አላውቅ ነበር…!
ከሌሊቱ 8:00 ላይ የእስር ቤቱ በር መቀርቀሪያ ቀቀቀቅ ቀቀቀቅ ጓ ጓ ጓ አለና ብርግድ ብሎ ተከፈተ። በሩ በጉልበት በመከፈቱ ከውስጠኛው ግድግዳ ጋር በኃይል ተጋጭቶ ተመልሶ ሊዘጋ ሲል፣ አንደኛው ወታደር በአንድ እግሩ በከስክስ ጫማው አስቆመው። ከተኛሁበት ባንኜ ተስፈነጥርኩና የሳር ፍራሼ ላይ በፓንትና ከነቴራዬ ሆኜ፣ ብርድ ልብሴን እስከ ወገቤ ድረስ እንደለበስኩ ዓይኔን አፍጥጬ በግማሽ ጎኔ ቁጭ አልኩ። የክፍሉን መብራት ሳያበሩ ሁለት ግዙፍ ወታደሮች ወደ ውስጥ ሲገቡ በውጭው መብራት ወጋገን ታዩኝ።
ልክ ድንጋይዋ ውስጥ እንደምትደበቅ ዔሊ ራሴን በብርድ ልብሱ ለመሸሸግ ሞከርኩ። የት ልሂድ። ዓይኔን ይበልጥ አፍጥጬ አጮልቄ እያየኋቸው ነው። ወደ ደረታቸው በኩል አድርገው ከወደሩት አሜሪካ ሰራሽ ጠመንጃዎቻቸው በተጨማሪ አንደኛው ትልቁን የታሸገ ውኃ አንጠልጥሏል። ሌላኛው ደግሞ ቀይ እጄታ ያለው ፒንሳና የብሎን መፍቻ ካቻቢቴ ይዟል። በነዚያ የወታደር ጫማዎቻቸው የታሰርኩበትን ክፍል አሮጌ ጣውላ ወለል እየረገጡ፣ ወደ አጠገቤ ሲራመዱ፣ በልጅነቴ በ1960 ዎቹ መጨረሻ በሰሜን ተራራዎች ለመጀመሪያ ጊዜ በቅርበት ሆኜ እንደሰማኋቸው የመድፍ ጥይቶች፣ እያንዳንዷ ርምጃዎቻቸው ልቤን ሲያርዱት ታወቀኝ። ተሸበርኩ።
“ም ም ም ም ምን ልታደርጉኝ ነው? ሃይ ላንድ ውኃ በኔ ላይ? ምን በደልዃችሁ?” ብዬ አጠገቤ መሬቱ ላይ ያስቀመጥኳትን ሱሪዬን በፍጥነት ለበስኩና ተመልሼ በብርድ ልብሱ ወገቤን ጠቀለልኩ። ቀበቶዬን አጥብቄ አሰርኩ።
“እጮኻለሁ፣ ልብ አድርጉ ኋላ። እዚችው ትገድሉኛላችሁ እንጂ አስነዋሪ ኢሰብአዊ ተግባር ስትፈፅሙብኝ ዓይኔ እያየ አልተባበራችሁም። ዶ/ር ዓብይ ይሄን ነገር አድርጉ ብሎ አይልካችሁም። ዶ/ር ዓብይ በእኔ አይጨክንም። በሰው አይጨክንም። ልቡ ሩኅሩኅ ነው። ድሮም እወደው ነበር። እኔ እኮ ተደምሬያለሁ። ሁሉም አመራሮች ያውቃሉ፣ ዓብይን እናግዘው ስል ነው የከረምኩት። ዛሬ በኔ ላይ ግፍ ብትፈፅሙ ነገ ለዓብይ ነገሬ ሁለታችሁንም አስቀጣችኋለሁ።” እያልኩ ቀባጠርኩ። የሳር ፍራሼን አፈፍ አድርጌ አነሳሁና እንደ ምሽግ ሰርቼ ወደ ግድግዳው አንድ ጥግ ተንፏቀቅኩ። ወታደሮቹ እየተያዩ፣ መልሰው ያዩኛል።
“ኧረ ኡኡ ኡ ኡ ስለ ወንድ ልጅ አምላክ ተዉኝ። ፒንሳውስ ምን ልታደርጉበት ነው? ጥፍሬን ልትነቅሉት? እባካችሁ ወንድሞቼ፣ ከኔ ማወቅ የምትፈልጉትን ሁሉ በጣም በፈቃደኝነት እነግራችኋለሁ። መቼ ጠይቃችሁኝና አልናገር አልኩ? ልፋቴ ሁሉ እኮ የአማራ ገበሬዎች ሕይወት እንዲቀየር ነው። እ እ እ የኦሮሞ ገበሬዎችንም እወዳቸዋለው። አዪዪዪ አዪዪ ኢይይይ” ሆድ ባሰኝ። አለቀስኩ።
“ኦሮምኛም እሰማለሁ እኮ አባ ኪያ፣ ማሎ ማሎ” እያልኩ ስቅስቅ ብዬ እያለቀስኩ። በየቋንቋው የተሻለ የወዳጅነት ስሜት ለመፍጠር ሞከርኩ። ዋናው ጓዳችን የሞተ ለት ነበር በሕይወቴ እንዲህ ያለ የመረረ ለቅሶ የገጠመኝ። በአስመራሪዎቹ የሰባዎቹ መጨረሻ ውጊያዎች ጊዜ እንኳ እንዲህ አልቅሼ አላውቅም ነበር። ወይኔ ሰውዬው!
ወዲያው አንደኛው ወታደር መናገር ጀመረ። “እባክዎ ጋሼ ይረጋጉ። እኛ የመጣነው እዚህኛው መደዳ ያሉ ጥቂት ክፍሎችን ብቻ ለይቶ ድንገት ኤሌክትሪክ ስለተቋረጠ ነው። በሩንም በፒንሳ፣ በመፍቻ ሰብረን የገባነው፣ ቁልፉን የያዘው ኋላፊ ከጊቢ ለስራ ወጥቶ የሬዲዮ ጥሪ ሊመልስ ስላልቻለ ነው። እናም እኛ የመጣነው ለደህንነትዎ እና ለጥንቃቄ ብለን በፍጥነት ከዚህ ክፍል አውጥተን ወደተሻለ ክፍል ልንቀይርዎ ነው። አሁን ወደምንወስድዎ ክፍል ነገ በጠዋት እንድንቀይርዎ ነበር ትዕዛዝ የተሰጠን። ግን ድንገት የመብራት መጥፋት በመከሰቱና የክፍሏን ቁልፍ የያዘው ኃላፊ ሬዲዮ አልመልስ ማለቱ ስለተገጣጠመብን ሰግተን ነው። በሉ ይፍጠኑ፣ ይነሱ። እንኩ ይኼን ውኃ ደግሞ ቅድም ተረስቶ ስላላስገባንልዎ ነው።” አሉኝ ወታደሮቹ እየተቀባበሉ። የሳር ፍራሿን ከላዬ ላይ አነሱልኝና ግራና ቀኝ ከንዴን ለቀም አድርገው ይዘው እንደ ቀላል ነገር አንጠልጥለው አቆሙኝ።
“ኦሮሞዎች ናችሁ ወይስ አማራዎች?” ፈገግ ብዬ ጠየኳቸው። ለቋንቋና ባሕላቸው በቀረበ አነጋገር ላመሠግናቸው ፈልጌ።
አንዱ ወታደር ፈርጠም ብሎ “እኛ ኢትዮጵያውያን ነን።” አለኝ። ሳላስበው “የኢትዮጵያ አምላክ ይባርካችሁ!” አልኳቸው። በዕድሜዬም እንዲህ ብዬ አላውቅ ነበር። በቀዝቃዛው የሌሊት አየር ታጅበን ከነበርኩበት ክፍል ራቅ ወዳለና መብራቱ ወዳልተቋረጠበት፣ ታጣፊ አልጋ ወደተዘጋጀበት፣ የተሻለ ስፋትና ንጽሕና ወዳለው ክፍል በክብር አዛወሩኝ።
አሁን የታሰርኩባት ክፍል በሬ ላይ ቁጭ ብዬ የጠዋት ፀሐይ እየሞኩ ነው። ባሳለፍኩት ሌሊት የገጠመኝ ድንጋጤ አሁንም አለቀቀኝም። ብቻ አለተፈጥሮዬ በአንዳንድ ጉዳዮች በሀሳብ ወደ ኋላ እየሄድኩ ይፀፅተኝ ጀምሯል። ከዚህ በፊት እንደሚያውቁት ዜማ ደጋግሞ አንድ ሐረግ በሀሳቤ ይመላለሳል። “ጊዜን ማን ይረታል?” የሚል። በሉ ነገ ፍርድ ቤት ቀራቢ ነን።
Filed in: Amharic