>

ሕዝብ ለሕዝብ እንዋቀስ (ከይኄይስ እውነቱ)

ሕዝብ ለሕዝብ እንዋቀስ

ከይኄይስ እውነቱ

ኢትዮጵያ ውስጥ የለውጥ ሂደት እንደተጀመረ ይነገራል፡፡ በእኔ ትሁት እምነት በዐቢይ አገዛዝ እስካሁን የተደረጉት በጎ ርምጃዎች በሙሉ ቅድመ ሥርዓተ ለውጥ የሚደረጉ መንገድ የመጥረግ እንቅስቃሴዎች እንጂ ወደ መንግሥተ ሕዝብ፣ እኩልነት፣ የሕግ የበላይነት፣ ፍትሐዊ የሀብት ክፍፍል ወዘተ የሚደረጉ፤ በተሟላ ፖሊሲ፣ በሕግ፣ በተቋማት፣ በመዋቅር የተደገፉ መሠረታዊ የሥርዓት ለውጦች ምልክት አላየንም፡፡ ተደጋግሞ እንደሚገለጸውም የዐቢይ አገዛዝ ለሽግግር ጊዜውም ሆነ ከዚያ በሚዘልቅ መልኩ አገራችን ወዴት እየሄደች እንደሆነ የሚጠቁም አመላካች ፍኖተ ካርታ አላዘጋጀም፡፡

ወደ አንድ ዓመት እየተጠጋ ባለው የዐቢይ አገዛዝ የተመዘገቡ፣ ቀጣይነታቸውም መበረታታት ያለበት በቀላሉ የማይታዩ በጎ ጅምሮች ያሉትን ያህል፤ ጅምር ለውጡ እየንተገራገጨ፣ ወደኋላ የመሄድ አዝማሚያም እያሳየ፣ በአራቱም ማዕዝናት በዜጎች ሕይወት፣ አካል፣ ንብረት በተለይም በስፋት መፈናቀል የሚታየው ጥፋት ቀጥሎ አሁንም ከተሰፋው ይልቅ ሥጋቱ አይሎ ይታያል፡፡

ጅምር ለውጡን የማደናቀፍ፣ መላ አገሪቱን የማሸበር፣ ሥርዓተ አልበኝነት እንዲነግሥ ሌት ተቀን የሚሠሩ የተደራጁ አፍራሽ ኃይሎች መኖራቸው የዐቢይ አገዛዝን ከፍተኛ ፈተና ላይ ጥሎታል፡፡ እነዚህ አፍራሽ ኃይሎችን ሕዝቡ በሚገባ ዐውቋቸው፣ እንዲመጣ የሚፈልገውን ለውጥ የማስከበርና የማስቀጠል ኃላፊነት አለበት፡፡ ባልመረጠው መንግሥት፣ የመንግሥት ድርሻ ነው ብሎ እጅና እግሩን አጣጥፎ ከተቀመጠ የሚከተለውንም ውጤት ለመቀበል ተዘጋጅቷል ማለት ነው፡፡ ከዚህም አልፎ ጥቅማቸው የተነካባቸው ደናቁርትና ካድሬዎቻቸው እንደ አህያ ጆሮ በጎተቱት መንገድ እየሄደ ርስ በርሱ መጋጨቱን ከመረጠ እንደ ዜጋ መሠረታዊ መብቶቹ ተከብረው በአገሩ እኩል የሚሆንበት መንግሥተ ሕዝብ መመሥረት ቀርቶ አገርም አይኖረውም፡፡ ኢትዮጵያ የገጠማት ፈተና እንቆቅልሽ ጅምር ለውጡን እመራዋለሁ የሚለውም፤ እኔ የማልገዛት ኢትዮጵያ መጥፋት አለባት ብሎ ሕዝብን በማሸበርና አገርን በማወክ የተሠማራውም ሕወሓት/ኢሕአዴግ የሚባል ባለፉት 27 ዓመታት ሕዝብና አገርን ያጠፋ ሽብርተኛ ድርጅት አባላት ናቸው(ኢሕአዴግ አሁንም አለ ወይ ብለው የሚጠይቁ ወገኖች እንዳሉ ሆኖ)፡፡

ባለፉት 27 ዓመታት ኢትዮጵያንና ሕዝቧን ከፋፍሎ፣ ተወዳዳሪ የሌለው ዝርፊያና የመሬት ወረራ በማድረግ አገራችን ከባዕዳን ኃይሎች በከፋ መልኩ ያዋረደው ሕወሓት ሥልጣኑንና በዚህም የሚገኘውን የማይገባ የዝርፊያ ጥቅም ካጣ በኋላ መለ መሽጎ ሽብርን አከፋፋይ ሆኗል፡፡ በሥልጣን ዘመኑ የቀፈቀፋቸው ግልገል አሸባሪዎችም በቀሩት 3 ድርጅቶችና ‹አጋር› ተብዬዎቹም ውስጥ በስፋት ይገኛሉ፡፡

የዐቢይ አገዛዝ እስከነ ድክመቶቹ (ሕግን በማስከበር ረገድ÷ የቀድሞ ባህሉን ተከትሎ ብቃት የሌላቸውን በወንጀል ጭምር የሚጠረጠሩ በርካታ የድርጅት ሰዎችን በሹመት መመደቡ÷ በአንኳ አገራዊ ጉዳዮች ላይ ወሳኝነተ ባለው መልኩ አሳታፊ አለመሆኑ ወዘተ)፣ የሚመራውና ኢትዮጵያውያን ያልመረጡት ድርጅቱም እስከነ ዘርፈ ብዙ ቀውሱ አሁን ለሚታየው (በተለይም የሰላምና የፀጥታ እጦት) አገራዊ ምስቅልቅል የራሳቸው ድርሻ እንዳላቸው የማይካድ ቢሆንም፤ በእኔ እምነት (እንደ አንድ የሕዝብ ወገን) ሕዝብም የራሱ ድርሻ ያለው ይመስለኛል፡፡

ሕዝብ በጅምላ አይወቀስም ካልተባለ በስተቀር ሕዝባችን ከጊዜ ወደ ጊዜ የሚያሳያቸው አቋሞች (ማኅበራዊ ድቀቱ፣ መጨካከኑ፣ መንደርተኝነቱ/ዘረኝነቱ፣ የመንጋ አስተሳሰብ ወዘተ) ምን እንደሚፈልግና ወዴት እየሄደ እንደሆነ ሳስተውል አልፎ አልፎ የቀቢፀ ተስፋ ስሜት (frustration) ይጎበኘኛል፡፡ ‹ፈሪሃ እግዚአብሔር አለው›፣ ‹አስተዋይ› ነው እያልን በጅምላ የምንናገርለት ሕዝብ እኮ ነው የገዛ ወገኑን አትድረስብኝ እያለ የሚገለው፣ የሚያፈናቅለው፣ የሚያሳድደው፡፡ የሕዝባችን አብዛኛው አካል ወጣቱ መሆኑም ሳይዘነጋ ይኸው ሕዝብ እኮ ነው የማይገባ ትርፍ ለማግበስበስ በደሀ ወገኑ ላይ የሚጨክነው፡፡ ይኸው ሕዝብ እኮ ነው የገዛ ወገኑን በየመንግሥት መ/ቤቱ በአገልግሎት አሰጣጥ የሚያጉላላው፡፡ ይኸው ሕዝብ እኮ ነው ለሙገሳውም ለወቀሳውም ሚዛን ያጣው፡፡ ይኸው ሕዝብ እኮ ነው ለወገኑ፣ ለምድራዊውም ሆነ ለሰማያዊው መንግሥት አልመች ያለው፡፡ ይህን የምለው ራሴን ታዛቢ አድርጌ አውጥቼ አይደለም፡፡

ሕዝባችን ባገዛዞች ለዘመናት ሲደቆስ፣ አገዛዞች ደንቁረው ሲያደናቁሩት ኖረዋል፡፡ በአእምሮም በቁስም ጨርሰው አደህይተውታል፡፡ እንደ ግለሰብ፣ ቤተሰብ፣ ማኅበረሰብ፣ ኅብረተሰብ ብሎም እንደ አንድ አገር ዜጋ ለምን ሁለንተናዊ ዝቅት ውስጥ ገባን የሚለው ጥናት የሚሻና ብዙ ማብራሪያዎች ሊቀርቡበት የሚገባ ሆኖ፤ በግለሰብ ደረጃ ‹ሰው› ነን ካልን÷በአካልም ሆነ በአእምሮ የጤና እክል ከሌለብን ምንም ዓይነት ምክንያት ከተጠያቂነትና ኀላፊነት ማምለጫ አይሆነንም፡፡ ጠያቂ ኅሊና አለና፡፡ ሰው በተፈጥሮው ዐዋቂ ፍጡር ነው፡፡ አእምሮ ጠባይዕ የሚባል ነገር አለ፡፡ ክፉና በጎን፣ እውነትና ሐሰትን፣ ትክክል የሆነውን እና ትክክል ያልሆነውን የምንለይበት የተፈጥሮ ዕውቀት ማለት ነው፡፡ በትምህርት÷ በንባብ÷ በልምድ የሚጎለብት ቢሆንም ሰው ከሌሎች እንስሳት የሚለይበት አእምሮና ኅሊና የሚባሉ ነገሮች አሉ፡፡ እነዚህን ገንዘቦች ያደረግን ታላቅ ፍጡራን፤ ከዚህም አልፎ በአብዛኛው የክርስትናና እስልምና ሃይማኖቶች ተከታዮች ነን የምንል እኛ ኢትዮጵያውያን ምን ነካን? በወገናች ላይ እስከዚህ ድረስ የመጨከን ምሥጢሩ ምን ይሆን? ኢትዮጵያ ለእኛ ጠበበችን ወይ? ያላት የተፈጥሮ ሀብት እኛን ለማስተዳደር አንሶ ነው ወይ? ያለንንስ በአግባቡ ተጠቅመንበታል ወይ? ወገን ወገኑን ባይተዋር ከማድረግ አልፎ እንደ ጠላት የሚመለከተው ለምንድን ነው? በሰላም ተነጋግረን ከተደማመጥን፣ በሚያግባቡን ነገሮች ላይ ከተሰማማንና ለሁላችን እኩል የምትሆን ኢትዮጵያን የሚያመጣ ሥርዓት ካደራጀን ይሄ የእገሌ መሬት ነው፤ ይሄ አካባቢ ደግሞ የእገሌ ጎሣ/ነገድ የግል ግዛቱ ነው ስለዚህ ሌላ ኢትዮጵያዊ ማየት አንፈልግም፤ ገሚሱ ደግሞ ወረዳ÷አውራጃ÷ክፍለ ሀገር ካልሆንን እያልን እስከመቼ እንደናቆራለን? ለእኩልነት ሥርዓት አጥብቀን ከደከምን መሬቱም ሆነ ማንነቱ ወዴት ይሄዳል? ወደ ኋላ ቀር አስተሳሰብና አኗኗር ተመልሰን እስከመቼ የዓለም ኹሉ መሳቂያና መሣለቂያ እንሆናለን? በበጎ ሥራቸው የምንኮራባቸውና የምንመካባቸው የቀደሙ አባቶቻችን ፊደልን ከነሙሉ ሥነጽሑፉ፣ ሥነ ጥበብን ከኪነ ሕንፃ፣ አገርን ከነሙሉ ክብሯና ነፃነቷ ወዘተ ትተውልን ያለፉት መደበኛ ትምህርት ቤት ገብተው ስለተማሩ አይደለም፡፡ በተፈጥሮ ባገኙት እንዲሁም በሕይወት ተሞክሮ ባገኙት ልምድና ዕውቀት እንጂ፡፡

እኛ በ21ኛው መቶ ክ/ዘመን የምንገኝ ኢትዮጵያውያን እንዴት ከእንስሳት አንሰን እንገኛለን፡፡ አሁንም ‹ሰው› ነን ካልን፣ ከዛም አልፎ በእምነት እግዚአብሔር በምሳሌውና በመልኩ የፈጠረን ነን ብለን የምናምን ከሆነ፣ ከሰውነት በሚጠበቅብን የሞራል ልዕልና ላይ እንገኝ፡፡ ያ ባይቻለን እንኳ ቢያንስ የገዛ ወገናችንን አንግደል፣ አናፈናቅል፣ አንበድል፣ አንግፋ፡፡ ከምንጸየፋቸው፣ ምድሪቱም ጭምር ከተጸየፈቻቸው ሕወሓቶች አንሰን አንገኝ፡፡ ማንን እና በምን ሁኔታ መታገል እንዳለብን ለይተን ዕንወቅ፡፡ ማንም ደናቁርት እንደ አህያ ጆሮ ለምን ይጎትተናል፡፡ ቆም ብለን እናስብ/እናስተውል፡፡ አገር ስለሚያጠፉ ‹የተማሩ ደናቁርት› ብዙ ስለተባለ በዚህ አስተያየቴ የማነሳው ነጥብ አይደለም፡፡ ለአገርና ለሕዝብ በእውነት ቆመናል የምትሉ እውነተኛ ምሁራን፣ የፖለቲካ ማኅበራት፣ የሃይማኖት ተቋማት፣ የአገር ሽማግሎች፣ የማኅበረሰብ አገልግሎት ድርጅቶች ካላችሁ ለሕዝባችን ቀናውን መንገድ አመላክቱት/ምሩት፡፡ በመንግሥትነት የተሰየመውም አካል ቢያንስ ሕግንና ሥርዓትን በማስከበር አገሪቱን ያረጋጋ፡፡ ኢትዮጵያን የሚያውቁ ዋኖቻችንን ምክር ስሙ፡፡ ምክር ሠናይት ለኵሉ ዘይገብራ እንዲል መጽሐፍ፡፡

Filed in: Amharic