>
5:18 pm - Friday June 15, 4896

የህዝብ ደምን ለአጉል የፖለቲካ ትርፍ መስዋዕት ማድረግ ማንንም አይጠቅምም!!! (አለማየሁ አንበሴ)

የህዝብ ደምን ለአጉል የፖለቲካ ትርፍ መስዋዕት ማድረግ ማንንም አይጠቅምም!!!
አለማየሁ አንበሴ
እኔ የምርጫ ማራዘም ጉዳይ በራሱ እንዲነሳ አልፈልግም!!!
የፖለቲካል ሳይንስ ምሁሩና አንጋፋው ፖለቲከኛ ፕ/ር መረራ ጉዲና ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ጋር በግላቸው የጀመሩትን የመብት ትግል ከሞላ ጎደል በአሸናፊነት እያጠናቀቁት ያሉ ይመስላል፡፡ ካለፈው ሃምሌ ወር ጀምሮ ወደ መደበኛ የማስተማር ሥራቸው መመለሳቸውን ይናገራሉ፡፡
 ያልተከፈላቸው የአንድ ዓመት ደሞዝ እንዲከፈላቸውም የትምህርት ክፍሉ ለሚመለከተው አካል መጻፉን ገልጸዋል፡፡ የተከለከሉትን የፕሮፌሰርነት ማዕረግም በቅርቡ እንደሚያገኙ እምነት አላቸው፡፡ በፖለቲካው በኩል ግን ብዙ ጥያቄዎች፣ ተግዳሮቶች ይቀራሉ፡፡ የምርጫ ቦርድ አወቃቀር፣ የምርጫ ጊዜ መራዘምና አለመራዘም፣ የለውጡ መቀጠልና መቀልበስ፣ ብሔራዊ የአንድነት መንግስት መቋቋም— እሳቸውና የፖለቲካ ድርጅታቸው
ከሚያሳስቧቸው ጉዳዮች መካከል ይጠቀሳሉ፡፡ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ፣ በእነዚህና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ ከፕ/ር መረራ ጉዲና ጋር ተከታዩን ቆይታ አድርጓል፡፡
የፖለቲካ ድርጅቶች ውይይት ተጀምሯል፡፡ ውይይቱ እንዴት እየሄደ ነው?
አሁን በውይይቱ መሃል መንገድ ላይ ደርሰናል። መለወጥ አለባቸው የሚባሉት ጉዳዮች በሰፊው እየተነሱ ነው፡፡ ነገር ግን የታሰረ ነገር የለውም። እስካሁን በጉዳዮቹ ላይ ነው መጠነኛ የሃሳብ መንሸራሸር ያለው፡፡ የምርጫ ቦርድ ጉዳይ፣ የፖለቲካ ፓርቲ ምዝገባ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ስነምግባር፣ ለፖለቲካ ፓርቲዎች የሚደረግ የገንዘብ ድጋፍ፣ የምርጫ ጊዜ ግጭት አፈታት ጉዳዮች በውይይቶቹ ተንፀባርቀዋል፡፡ ነገር ግን እስካሁን መቋጫ አላገኙም፡፡
እንደ “መድረክ” በዋናነት  ውይይት  ያስፈልገዋል ብላችሁ የተዘጋጃችሁበት ጉዳይ ምንድን ነው?
የኛ ዋና ትኩረት የምርጫና የምርጫ ጉዳይ ነው። የምርጫ ቦርድ አወቃቀር ከላይ እስከ ቀበሌ ድረስ ገለልተኛ ሊባሉ በሚችሉ ወይም በገለልተኝነታቸው በሚታመኑ ሰዎች ካልተያዘ፣ ምርጫው ምርጫ ሊሆን አይችልም፡፡ ከ1997 ምርጫ በቀር እስካሁን የተደረጉት እንኳን የምርጫ ባህሪ ሊኖራቸው የቅርጫ ይዘት እንኳ የላቸውም፡፡ አሁን እየታሰበ ያለው ነፃና ትክክለኛ ፍትሃዊ ምርጫ ነው፡፡ መንግስት እንደ ድሮው በአፉ ነፃና ፍትሃዊ ምርጫ እያለ፣ በተግባር የታጠቀ ሰራዊቱን አሰማርቶ፣ የምርጫ ዘረፋ ውስጥ ከገባ፣ አሁንም ቢሆን ታጥቦ ጭቃ ነው የሚሆነው፡፡ ስለዚህ ተስፋ የሚደረገው በሁላችንም ስምምነት ከላይ እስከ ታች ድረስ የምርጫ መዋቅሩ፣ ገለልተኛነታቸው በተረጋገጠ ሰዎች ይሞላል የሚል ነው፡፡ ይሄን ተስፋ ይዘን ነው እንግዲህ ወደ ውይይቱ የገባነው፡፡
ከዚህ ቀደም በተለይ የምርጫዎች መቃረብን ተከትሎ፣ ድርድሮችና ውይይቶች ተደርገዋል። የአሁኑ ውይይት ከዚህ ቀደም ከነበሩት በምን ይለያል?
ቢያንስ አሁን የሃገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር፣ ይሄን ነገር በቁርጠኝነት መለወጥ አለብን የሚል ቃል ገብተዋል፡፡ ፈረንጆች “walk your talk” ይላሉ፡፡ ቃል መግባት ብቻ ሳይሆን የተገባውንም ቃል በተግባር መፈፀም ወሳኝ ነው፡፡ ቀሪው የዶ/ር ዐቢይ ፈተና ይሄ ነው፡፡ ድሮ የለበጣ ቃል መግባት ነው የነበረው። በህዝብ ፊት ቃል ይገባል፤ በጎን ፓርቲዎችን ለማጥፋት ሴራ ይጠነሰሳል። ይሄ ነበር ያለፉት 27 ዓመታት የፓርቲ ፖለቲካ ልማዳችን። ኢህአዴግ እንዴት አጭበርብሮ ስልጣን ላይ እንደሚቆይ እንጂ ከተቃዋሚ ኃይሎች ጋር የሃገሪቱን ችግሮች ተወያይቶ ለመፍታት አልነበረም፣ ከዚህ በፊት ሲሰራ የነበረው። አሁን ከዚያ የወጣን ይመስላል፡፡ በተደጋጋሚም ቃል እየተገባ፣ በተግባርም እየተገለጡ ያሉ ነገሮች አሉ፡፡
ጠ/ሚኒስትሩም ወደ ስልጣን ከመጡበት ጊዜ ጀምሮ ምርጫውን ነፃና ዲሞክራሲያዊ ለማድረግ ቁርጠኝነት እንዳላቸው እየገለጹ ነው፤በተደጋጋሚም ቃል ገብተዋል፡፡ ነገር ግን አሁን በሃገሪቱ ውስጥ ከሚታየው ተጨባጭ ሁኔታ አንጻር ቃል የገቡትን ለመፈጸም ይቻላቸዋል ብለው ያስባሉ?
በዋናነት ዶ/ር ዐቢይ በተለይ ኢህአዴግ የሚባለውን ፓርቲ አጠናክረው ይዘው በቁርጠኝነት ከገፉበት የማይሳካበት ምክንያት የለም፡፡ ህዝብ ነፃ ምርጫ እንዲደረግ በፅኑ ይፈልጋል፡፡ ዋናው ጉዳይ ይሄ ነው፡፡ የህዝብ ፍላጎትን ለማሟላት በተንቀሳቀሱ ቁጥር እንቅፋቶች እየቀነሱላቸው፣ ነገሮች እየሰመሩ የማይሄዱበት ምክንያት የለም፡፡
የሕዝብን ነፃና ፍትሃዊ ምርጫ ፍላጎት ወደ ጎን መግፋት ነው በቀጣይ ሃገሪቱን ወደ ቀውስ የሚከተው እንጂ ነፃና ፍትሃዊ ምርጫ ማካሄድ አይደለም፡፡ ዞሮ ዞሮ ዶ/ር ዐቢይ ይሄን አድርገው ከተሳካላቸው አንዳንዶች እንደሚሉት፣ ነብይ የሚሆኑበት ካልተሳካላቸው ደግሞ ያው በፊት እንደነበሩት የኢትዮጵያ መሪዎች በታሪክ ሚዛን ውስጥ ዝቅተኛውን ቦታ የሚይዙበት ይሆናል ማለት ነው፡፡ ከዚህ አንፃር ነገሩን ስመለከተው፣ ዶ/ር ዐቢይ ያለፉ መሪዎችን ታሪክ ለመድገም ያለሙ ሰው ሆነው አይታዩኝም።
ከተሳካላቸው ልክ እንደ ማንዴላ የፖለቲካ ጀግና የማይሆኑበት ምክንያት የለም፡፡ የ50 ዓመታት የኢትዮጵያ ፖለቲካ ውጣ ውረድን አቅጣጫ በማስያዝ ዶ/ር ዐቢይ ሊታወሱ ይችላሉ፡፡ የታሪክ ፈተናውን ማለፍ መቻልና አለመቻላቸውን አብረን  የምናየው ይሆናል፡፡
በዚህ የለውጥ ሂደት ውስጥ ግጭቶችና መፈናቀሎች እንዲሁም የዜጎች ሞት እየተከሰተ ነው፡፡ ከሰሞኑ የሰብአዊ መብቶች ጉባኤ ባወጣው ሪፖርቱ፤ በ2 ወራት ጊዜ ውስጥ ከ250 በላይ ዜጎች በግጭት ተገድለዋል ይላል፡፡ ይሄ ለአገሪቱ መጻኢ እጣ ፈንታ ስጋት አይፈጥርም? 
ይሄ ኢትዮጵያ አሁንም በፖለቲካ ቀውስ ውስጥ መሆኗን ነው የሚያሳየው፡፡ ከቀውስ ወደ ሌላ ቀውስ እየተሸጋገረች ያለች ሃገር መሆኗን የሚያመለክት ነው፡፡ ግን የፈለገውን ያህል የገዘፈ ቀውስ ቢሆን ጉዳዩ የሚመለከታቸው ወገኖች መፍትሄ ፍለጋ ላይ መሰማራት አለባቸው፡፡ ለጠባብ የስልጣን ጥያቄ ብሎ ህዝብን አጥፍቶ ራስንም ወደ ማጥፋት፣ ክቡር የህዝብ ደምን ለአጉል የፖለቲካ ትርፍ መስዋዕት ማድረግ ማንንም አይጠቅምም፡፡ ሁሉም ወገን ከእንደዚህ ያለው ለኪሳራ የሚዳርግ የፖለቲካ ቁማር ተቆጥቦ፣ የየራሱን የመፍትሄ መዋጮዎች ቢያመጣ በአጭር ጊዜ ውስጥ የተሻለ አቅጣጫ ልንይዝ እንደምንችል ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ ስለዚህ ዋናው ገዥውን ፓርቲ ጨምሮ ሁሉም የፖለቲካ ኃይል፣ የቤት ስራውን መስራት የመቻልና ያለመቻል ጉዳይ ነው፡፡ ህዝብን ላልተፈለገ መስዋዕትነት የሚዳርገው የፖለቲካ ልሂቃኑ የቤት ስራቸውን በተገቢው መንገድ ያለመስራታቸው ነው እንጂ ህዝብ እንደ ህዝብ ወደዚህ ዓይነት ተግባር ሊገባ አይችልም፡፡
በኦነግ እና በመንግስት መካከል የተፈጠረው ውዝግብና ግጭትም ብዙ ዋጋ እያስከፈለ ነው—-
እኛም በጉዳዩ ተቸግረናል፡፡ ችግሮቹ በሰላማዊ መንገድ እንዲፈቱ፣ ሁለቱ ኃይሎች በቀና መንገድ እንዲደራደሩ፣ ተደራድረው የተስማሙባቸውን ነገሮች ደግሞ በስራ እንዲተረጉሙ በምናገኛቸው አጋጣሚዎች እየመከርን ነው የቆየነው፡፡ እንግዲህ እነሱም ወደዚህ መንገድ ይሄዳሉ የሚል ግምት አለን። ኢትዮጵያ ውስጥ በጠመንጃ ጉዳይን ለማሳካት የተደረጉ ሙከራዎች በሙሉ ውጤት አምጥተው አያውቁም፡፡ ከንጉሱ ጊዜ ጀምሮ በጠመንጃ አላማን ለማስፈፀም የተደረጉ ሙከራዎች በሙሉ የረባ ውጤት አላመጡም፡፡ ህዝብ በሚፈልገው አቅጣጫ ነገሮችን ለመፍታት መንቀሳቀሱ ነው ጠቃሚው። ሁለቱም ኃይሎች በዚህ እሳቤ መጓዝ ያለባቸውን መንገድ ተጉዘው፣ ወደ መሃል መንገድ መጥተው ችግሮችን ለመፍታት ዝግጁ መሆን አለባቸው፡፡ ህዝቡም ያንን ይፈልጋል፤ እኛም ያንን እንፈልጋለን፡፡ ስለዚህ ሁለቱም ኃይሎች በዚህ መንገድ ሰከን ብለው ነው፣ ወደ መፍትሄ መቅረብ ያለባቸው፡፡
 
ኦፌኮ ስለ መጪው ምርጫ ምን ያስባል?
በኛ በኩል መጪው ምርጫን ማንም ያሸንፍ ማን፣ ዋናው ነፃና ፍትሃዊ መሆኑ ላይ ነው፡፡ የምናተኩረው ነፃና ፍትሃዊ መሆኑ፣ ህዝብ የፈለገውን መምረጥ የመቻሉ ጉዳይ ነው እኛን የሚያሳስበን እንጂ በምርጫው የምናገኘው ውጤት አይደለም፡፡ ህዝቡን ከ50 ዓመት መከራ የማስወጣት ጉዳይ ነው ለኔ ግድ የሚለኝ እንጂ እገሌ አሸነፈ፣ እገሌ ተሸነፈ የሚለው አይደለም፡፡
ምርጫው ይራዘም አይራዘም የሚለው እያነጋገረ ነው፡፡ የእናንተ አቋም ምንድን ነው?
ምርጫው ይራዘም የሚለው ነገር እኔን ያሳስበኛል፡፡ ህዝቡ በራሱ ነፃ ፍላጎት ኢህአዴግን እንኳ ቢመርጥ እኔ ግድ የለኝም፤ ግን ምርጫ ይራዘም የሚለው ያስጨንቀኛል፡፡ ባለፉት 27 ዓመታት ግፍ ሰርቶብናል ብለን ስንቃወመው የነበረውን ኢህአዴግ፣ እንደገና በራሳችን ፍላጎትና ማመልከቻ ስልጣኑን አራዝመንለት፣ የተሻለ ሁኔታ ያመቻችልናል የሚል ህልም ውስጥ የገቡ ሰዎች አሉ፡፡
ይሄ አደጋ አለው፡፡ ኢህአዴግ ዶ/ር ዐቢይ እና ለማ አይደሉም፤ ወደ 8 ሚሊዮን አባላት ካድሬዎች አሉት፡፡ ይሄ ሁሉ እያለ ዶ/ር ዐቢይንና ለማን በማየት ብቻ እነሱ የስልጣን ጊዜያቸው ካለቀ በኋላም ያስተዳድሩን ብሎ ማመልከቻ ማስገባት ከምን የመነጨ እንደሆነ ለመገመት ያስቸግረኛል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ይህቺ ሃገር ላይ እየተፈጠረ ያለው ግጭት ትንሽ ገፋ ካለ ሩዋንዳና ሶማሊያ የማንሆንበት ሁኔታ የለም። ይልቁንስ የጋራ አጀንዳ ቀርፀን መሰረታዊ ነገር ካልሰራን እንዲሁ ያዝ ለቀቅ እየተባለ ወደ ሶማሊያና ሩዋንዳ አይነት የምንሄድበት ሁኔታ ሊፈጠር ይችላል። ያ ከሆነ ደግሞ ሁላችንም ነን የምንከስረው።
 አሁን ለምሳሌ በምዕራብ ኦሮሚያ ወለጋ ብዙ ችግር አለ፡፡ ህዝቡ እኛን ለም ዝም ትላላችሁ እያለን ነው፡፡ ከቦረና እስከ ሞያሌ፣ ጭናቅሰን… ያለው ችግር ቀላል አይደለም፡፡ በአንዳንድ አካባቢዎችም ተቃውሞዎች ጭምር እየተፈጠሩ ነው፡፡ በሁመራ ገንዳ ውሃ ላይ መከላከያና ህዝብ የተጋጨበት ሁኔታ እንዳለ ሰምተናል፡፡ እንዲህ ያሉ ነገሮች እየሰፉ ከሄዱ ማን ነው ኃላፊነቱን የሚወስደው?
ለምሳሌ የኦሮሞ ወጣቶች አመፅ የተቀጣጠለው 2006 ላይ ነበር፤ 2007 ግን ሰው ከምርጫ ብዙ ነገር ይመጣል ብሎ ስለጠበቀ እኔ እስከማውቀው ድረስ ሙሉ ትኩረቱን ምርጫው ላይ አድርጎ፣ አንድ ድንጋይ ሳይወረውር ሂደቱን እስከ መጨረሻው ሲከታተል ነበር፡፡ ሰው ሙሉ አይኑ፣ ልቡ፣ ፍላጎቱ ምርጫው ላይ ነበር፡፡ ምርጫው የሆነ ነገር ያመጣልኛል ብሎ በፅሞና ሲጠብቅ ነበር፡፡ ኢህአዴግ መቶ በመቶ አሸነፍኩ ሲል ነው እንደገና ወደ አመፅና ሌሎች ነገሮች ህዝቡ የገባው፡፡
ስለዚህ ምርጫ ራሱ የሰውን ልብና የእንቅስቃሴ አቅጣጫ ይለውጣል፡፡ የምርጫ እንቅስቃሴ በራሱ የሰውን ልብና አዕምሮ የመቆጣጠር አቅም አለው፡፡ ምርጫው በተያዘለት ጊዜ ቢካሄድ ግጭቶችን ለማስቆም በራሱ መፍትሄ ነው፡፡ ይራዘም የሚሉ ሰዎች ጉዳዩን በዚህ መልኩም ቢያዩት ጥሩ ነበር፡፡ በሌላ በኩል፤ የቀበሌና የወረዳ ተመራጮች ከህዝብ ባልተሰጣቸው ስልጣን ነው ላለፉት ስምንት ወራት በስልጣን ላይ የተቀመጡት። የአካባቢ ምርጫ መካሄድ ነበረበት። ዛሬ ህዝቡ ለውጡ እኛ ጋ አልደረሰም፣ እገሌ የተባለው ሲያስገድለን የነበረ ካድሬ፤ ዛሬም በስልጣን ላይ ነው ያለው እያለ አቤቱታ እያቀረበ ነው፡፡ ቢያንስ የአካባቢ ምርጫ ቢካሄድ ለውጡ ህዝቡ ጋ ሊደርስ ይችላል፡፡ ከዚህ ውጭ ለውጡ ህዝብ ጋ እንዲደርስ ምን የፖለቲካ ቀመር ሊኖር ይችላል? የለም፡፡
ምርጫ ቦርድን እንደ አዲስ አዋቅሮ፣ ህጎችን አፅድቆ ምርጫ ለማካሄድ ያለው ጊዜ በቂ ይመስልዎታል?
ምርጫ ቦርድን የማሻሻል ጉዳይ አንድ ዓመት ቢወስድ፣ ሌላው በአጭር ጊዜ ውስጥ መጠናቀቅ የሚችል ነው፡፡ ገዥውን ፓርቲ ጨምሮ ሁሉም ኃይሎች ተቀምጠው ከወዲሁ የምርጫውን ቀን ከቆረጡ፣ ያንን ግብ ለማሳካት የሚደረገው ሩጫ በራሱ መሪ ሊሆን ይችላል፡፡ አሁን ግን መነታረኩ ጊዜውን መግፋት ነው የሚሆነው፡፡ ከክርክሩ ወጥቶ ቀን መቁረጡ፣ ግብ አስቀምጦ ለመንቀሳቀስ ያስችላል፡፡ ሃገሪቱ ላይ ግጭት አለ ከተባለ ግጭቱን ለመፍታት ከምርጫ በላይ ምን የተሻለ ነገር አለ? ከዚህ የተሻለ ጊዜስ ይመጣል? አይመጣም፡፡ ምክንያቱም ህዝብ ምን ተስፋ ያደርጋል? ፍላጎቱ ካለ ሁሉንም ነገር ህዝብን በንቃት እያሳተፉ፣ ትኩረቱን በሙሉ ምርጫው ላይ እንዲሆን አድርጎ መስራት፣ ሃገሪቱንም ወደ ሰላማዊ እንቅስቃሴ መመለስ ይቻላል፡፡
የሚዋሃዱ ፓርቲዎችም የጊዜ ሰሌዳው ከተቀመጠላቸው ያንን ግብ ለማሳካት ጥድፊያ ውስጥ ይገባሉ፡፡ ስለዚህ ዋናው ከልብ ለመስራት መፈለግ ነው፡፡ ያለው ጊዜ ጥሩ ምርጫ ለማድረግ በቂ ይመስለኛል፡፡  እኔ የምርጫ ማራዘም ጉዳይ በራሱ እንዲነሳ አልፈልግም፡፡ ይሄን ማንሳት በራሱ አስፈላጊ አይደለም፡፡ ድሮ አራት ወር ይፈጅ የነበረውን የእጩዎች ምዝገባ በአንድ ወር መጨረስ ይቻላል፤ ድሮ በሶስትና አራት ወር የሚደረጉትን በሁለትና በአንድ ወር እንዲያልቁ ማድረግ ይቻላል። የአሰራር ለውጥ ማለት ይሄ ነው፡፡ ይሄ ከተደረገ ህገ መንግስቱም ሳይጣስ በህገ መንግስቱ በተቀመጠው ጊዜ ማድረግ ይቻላል፡፡ ህገ መንግስቱ ተጣሰ ተብሎ ሌላ ጦርነት ከሚከፈት ስልጣን ላይ ያለው መንግስት የሚወስዳቸውን እርምጃዎች በጥንቃቄ ማየት ያስፈልጋል፡፡ ይሄ አሁን ያለው ፓርላማ ብዙ ጭቅጭቅ ያለበት፣ ለውጡ እንዲመጣ ምክንያት የሆነ ነው፡፡ ታዲያ በምን ተቀባይነቱ ነው፣ ምርጫን አራዝሞ ራሱን በስልጣን ላይ ሊያቆይ የሚችለው?
በርካታ ለመመለስ የሚያስቸግሩ ነገሮችን የሚፈጥር ጉዳይ ስለሆነ፣ ምርጫውን በተቀመጠው ጊዜ ውስጥ ለማካሄድ ከወዲሁ ወስኖ መንቀሳቀሱ ተገቢ ነው፡፡ ሁላችንም በፍጥነት የሚቻለንን ብንሰራ የተሻለ ነው የሚሆነው፡፡ በፍጥነት ወደ ብሔራዊ መግባባትና እርቅ ሄደን፣ ካለንበት ችግር መውጣትም አለብን። ሌላ የተሻለ ጊዜ ይመጣል ብለን ስንጠብቅ እየበራ ያለው ቀን እንዳይመሽብን ነው የኔ ስጋት፡፡
በስልጣን ላይ ባለው መንግስትም ሆነ በኛም ላይ ቀኑ እንዳይመሽብን መጠንቀቅ ያስፈልጋል፡፡ ምርጫው ይራዘም አይራዘም የሚል ክርክር ትተን፣ ሁላችንም ስራችንን በፍጥነት መስራት አለብን፡፡ ከአሁኑ ቁጭ ብሎ ምርጫ ይራዘም ማለት ራዕይና እቅድ ማጣት ነው፤ ሃገሪቷንም ወደ ባሰ ቀውስ የሚጋብዝ ነው፡፡ እኔ እርግጠኛ ነኝ ምርጫው ቢካሄድ ከዚህ ቀደም ከነበረው የከፋ ነገር አይፈጠርም፡፡ ምናልባት አስቸጋሪ የሆኑ የተመረጡ ቦታዎች ላይ ምርጫን ማራዘም ሊኖር ይችላል፤ ነገር ግን በሁሉም ቦታ ማራዘም ተቀባይነት የለውም፡፡
 
በቅርቡ ባወጣችሁት ጋዜጣዊ መግለጫችሁ፤ ብሔራዊ የአንድነት መንግስት መቋቋም አለበት ብላችኋል፡፡ ብሔራዊ የአንድነት መንግስት ሲባል ምን ማለት ነው?
እኛ ይሄን ጉዳይ ዛሬ አይደለም ያነሳነው፤ በ1997 ምርጫ ቀውስ ወቅት ነበር፡፡ ምርጫ 2002 ላይም ይሄን ጉዳይ አንስተናል፤ ግን ተቀባይነት አላገኘም። እኛ ይሄን ስናነሳ የስልጣን ፍላጎት ተደርጎ ነው የሚታየው፡፡ ነገር ግን ይሄ ስህተት ነው፡፡ ለምሳሌ አሁን ለውጥ ተብሏል፡፡ ይሄ ለውጥ በህዝብ ተቀባይነት ባገኙ፣ ህዝብን ለማገልገል ፍላጎት ባላቸው ኃይሎች ከላይ እስከ ታች ካልተመራ ለውጡ የመቀልበስ እድሉ ሰፊ ነው፡፡ ከዚህ በፊት ከነበረው የተሻለ እውቀት ያለው አመራር ከላይ እስከ ታች  ያስፈልጋል፡፡
በብዙ ቦታ አሁን ህዝብና ነባሩ ካድሬ መግባባት አቅቶታል፡፡ ታዲያ ለዚህ ምንድን ነው መፍትሄው? በምን ተአምር ነው ማግባባት የሚቻለው? ስለዚህ በእንደዚህ አይነት ሁኔታዎች ውስጥ እውቀቱና ፍላጎቱ ያላቸውን አካላት ወደ መንግስት ስርአቱ አስገብቶ መጠቀሙ ይበጃል። ከሁሉም በላይ አሁን ያለው መንግስት፣ የማን መንግስት ነው የሚል ጥያቄ ነው ህዝብን ለለውጥ ያነሳሳው፡፡ ስለዚህ ከላይ እስከ ታች ህዝብ የኔ ነው ብሎ የሚቀበለው መንግስት በዚሁ ወቅት መኖሩ ጠቃሚ ነው፡፡ ህዝቡ የሚያምንባቸው፣ እውቀትና ችሎታ ያላቸው ኃይሎች በጋራ እየመሩኝ ነው የሚል መተማመን ውስጥ እንዲገባ፣ የብሔራዊ አንድነት መንግስት አወቃቀር አቅጣጫ ሊያዝ ይገባዋል የሚል እምነት አለን፡፡ ምርጫ ቦርድንና ስርአቱን ለማሻሻል፣ ይሄ የመንግስት ቡድን መቋቋሙ ጠቀሜታው የጎላ ነው፡፡
 አብዛኛው የኢትዮጵያ ህዝብ አምኖ የሚቀበለው የመንግስት መዋቅር በአፋጣኝ መፍጠሩ ጠቀሜታው ለሁሉም ነው፡፡ ይሄ የሽግግር መንግስት የሚባለው፣ አዲስ መንግስት መመስረትን ይፈልጋል፡፡ ይሄኛው ግን ስልጣን ላይ ያለው መንግስት ሃገር እየመራ፣ ነገር ግን መሰረቱ ይስፋ፣ ህዝባዊ ይሁን ነው ጥያቄው፡፡ እውቀትና ችሎታ ያላቸው ሰዎች በመዋቅሩ ይግቡበት የሚል ቀና ጥያቄ ነው ያቀረብነው፡፡
ምሁራንን ጨምሮ ሃገር ማገልገል የሚፈልጉ ሁሉ ይግቡበት ነው ጥያቄው፡፡ እኛ ዶ/ር ዐቢይ ይውረድ አይደለም ጥያቄያችን፡፡ ዶ/ር ዐቢይና ቡድኑ እንዳለ ሆኖ ከስር ጀምሮ ሁሉም የተሳተፉበት አስተዳደር ይፈጠር ነው ጥያቄው፡፡
 ምሁራን፣ የህዝብ ተወካዮች ወደ መንግስቱ ስርአት ይደባለቁ ነው ጥያቄው። በአዲስ እውቀት፣ በአዲስ ልምድ እንሂድ ነው ጥያቄያችን፡፡ የጋራ መንግስት ስንል ይሄን ማለታችን ነው፡፡ እየተካሄደ ያለው ለውጥ የተሳካና ከቅልበሳ ስጋት ነፃ እንዲሆን የዚህ ዓይነቱ የመንግስት አደረጃጀት ቅርፅ ጠቃሚ ነው፡፡ በሰፊው የኢትዮጵያ ህዝብ ሊደገፍ የሚችል መንግስት እንፍጠር ነው ጥያቄው፡፡
እና ዶ/ር ዐቢይም የመንግስታቸውን ማህበራዊ መሰረት ማስፋቱ ይጠቅማቸዋል፡፡ ሃገርም ትጠቀማለች፡፡ እኛ ይሄ መንግስት ሚዛን አጥቶ እንዲወድቅ አንፈልግም፡፡ ብቻውን ከቅልበሳ ስጋት ነፃ የሆነ ለውጥ ማካሄድ ይችላል በሚለው ጥርጣሬ ስላለን ነው ይሄን ሃሳብ ያቀረብነው፡፡ ሁላችንም የየራሳችንን አስተዋፅኦ ማድረግ እንዲቻል ነው ጥያቄው፡፡ ስራውን ከተለመደው የካድሬ ስራ ወደ እውቀትና ችሎታ አሰራር የመቀየር ጥያቄ ነው። ይሄን ደግሞ ብዙ ሃገሮች አድርገውታል፡፡ ግሪክን እስራኤልን መጥቀስ እንችላለን፡፡
የብሔራዊ አንድነት መንግስት ሲባል በስራ አስፈፃሚ ደረጃ ነው ወይስ ዋናውን የመንግስት አካል ፓርላማውንም ይመለከታል? ፓርላማውን የሚመለከት ከሆነስ የህገ መንግስት ጥሰት አይሆንም?
ለጊዜው በስምምነት በድርድር ልናቆያቸው የምንችላቸው ይኖራሉ፡፡ ፓርላማው ምን ይሆናል የሚለው ለምሳሌ የድርድር ነጥብ ነው የሚሆነው። ዋናው ነገር ግን የስራ አስፈፃሚውን መሰረት ማስፋቱ ነው፡፡ የኛ ጥያቄ ትኩረትም እዚህ ላይ ነው። ስራ አስፈፃሚው መመሪያዎችን እያወጣ፣ ሃገሪቱን ባቀረብነው ሃሳብ መሰረት መምራት ይቻላል፡፡ እኛ ያለው መንግስት ሙሉ ለሙሉ ይውረድ የሚል አቋም የለንም፡፡
በዚያው ልክ አሁን ያለው መንግስት ሃገሪቷን ያሸጋግራል የሚል እምነትም የለንም፡፡ የተሳካ ዲሞክራሲያዊ ለውጥ ለማምጣት ይሄ ዓይነቱ አሰራር ተመራጭ ነው፡፡
Filed in: Amharic